2015-11-20 18:49:00

ለሰዎች ቅርብ ሆኖ ማገልገል ሰዎችን የማግለል ባህልን ያሸንፋል! ር.ሊ.ጳ


ቅ.አ.ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ትናንትና ረፋድ ላይ የጤና አገልግሎት ሠራተኞች ጳጳሳዊ ምክር ቤት “የጤና/የመዳን እና እንግዳ የመቀበል ባህል በሰው ልጆችና በዓለማችን አገልግሎት” በሚል ርእስ ሰላሳኛውን ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ወይም ስብሰባ ላይ እየተሳተፉ ያሉትን ከአምስት መቶ አምሳ በላይ ለሚሆኑ በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት “አንዱ ለሌላው የሚያደርገው ቅርበት የዜግነት የማኅበረሰብ እና ሃይማኖታዊ ልዩነቶችን በመሻገር መልካም ሰብአዊ ግኑኝነትን ይፈጥራል” ሲሉ ባለንበት ዘመን ስለሚታየው ትርፍ የማይገኝለትን ሰው የማግለል ባህልን አውግዘዋል፣

ቅዱስነታቸው ባቀረቡት ንግግር የዛሬ ሃያ ዓመት ቅዱስ ዮሓንስ ጳውሎስ ዳግማዊ “ኢቫንጀልዩም ቪተ” የሕይወት ወንጌል የኢየሱስ መልእክት አንኳር ነው በሚል ርእስ በጻፉት ሓዋርያዊ መልእክት በመመርኰዝ የመዳንና የአገልግሎት ባህል በዚሁ ሓዋርያዊ መልእክት በሰፊው ተገልጦ እንደሚገኝ ይህም ለሰው ልጅ ሕይወት መሰጠት ያለበትን አክብሮት እንግዳና የተቸገረው ሰውን በመቀበልና ችግሩን ተረድቶ ርኅራኄ ማሳየት የምሕረት ሥራ ማዘውተር በመንፈስም ይሁን በሥጋ ለሚሰቃዩ ለመርዳት ብቁ መምርያ ነው፣ ይህም የዘር የሃይማኖትና ማኅበረሰባዊ መዋቅሮች የሚፈጥሩዋቸውን መሰናክሎች ተሻግሮ ቅርበትን በተግባር በመግለጥ እውን እንደሚሆን የገለጡ ቅዱስነታቸው በቅርቡ ለመጀመር በዝግጅት ላይ የምንገኘው የኢዮቤልዩ የምሕረት ዓመትም ለዚሁ ይረዳናል ብለዋል፣ በተለይ ደግሞ የስብሰባው ተሳታፊዎች በጤና አገልግሎት የሚሰሩ ስለሆነ በዚሁ የምሕረት ኢዮቤልዩ ዓመት ለሕመምተኞች ኃጢአታቸው ይፍ የሆኑ ሰዎች በተለያዩ መናፍስት ለተለከፉ ለተገለሉ ለድሆችና ለእንግዶች እንደኢየሱስ ክርስቶስ ልዩ ትኵረት በመስጠት ቅርበታቸውን በተግባር ማሳየት እንዳለባቸው አሳስበዋል፣ “በሚያስገርም ሁኔታም በዘመናችን ባለው ጥቅም የማይገኝበትን አግልለው ጣለው በሚለው ባህል ሳቢያ እነኚህ እላይ የጠቀስናቸው ብቻቸውን ተጥለው ይገኛሉ፣ ይገርማል አይቆጠሩም ዋጋም አይሰጣቸውም፣ ይህ ምን ማለት ይሆን ብለው ይጠይቃሉና የዚህ ዓይነት ተግባርና ባህል የኢየሱስ አይደለም ክርስትያናዊም አይደለም፣ ስለዚህ እባካችሁ ይህ እኔ የምጠይቃችሁ ቅርበት እውን መሆን አለበት እንዲያው ለጊዜው ወይንም በሰው እንድትታይ የሚደረግ ሳይሆን ከልብ የመነጨ የፍቅር መግለጫ መሆን አለበት፣ በመካከላችን ያሉትን ሁሉን ልዩነቶች ተሻግራችሁ ጠላቴን እንደ ወንድሜ እቀበለዋለሁ እስከ ማለት መድረስ አለባችሁ፣ የመልካሙ ሳምራዊ ምሳሌ ትምህርት ይሁናችሁ ምሳሌውን ተከተሉት፣ ዘመናችን መርዞት ያለው የመጣል ባህልና ያሉንን ፍላጐቶች ለሟሟላት የመጣር በሽታን እናስወግድ፣ ይህ በሽታ በማኅበረሰባዊና ምጣኔ ሃብታዊ ኑሮአችን የሚያስችግርና መወገድ ያለበት መሆኑን እንዲህ ሲሉ ገልጠዋል፣ “በተለይ በሃብታም አገሮች ሰፍኖ ያለው ባህል ነው፣ ይህም የተከፈለ ይከፈል መልኬና አካሌ ሁሌ ወጣት መስሎ እንዲታይ ፍጹም ቅርጽ እንዲኖረኝ በሚል ሰበብ እነኚህን የማያሟላውንና እንደሸክም ሆኖ የሚሰማን መጣል ማስወገድ ነው፣ ይህ ደግሞ መጥፎ ነገር ነው፣ በጤናንና ተፈጥሮን መከባከብ መካከል ኃይለኛ መተሳሰር አለ፣ ቅርበት ስንል ለሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን የጋር ቤታችን ለሆነችው ተፈጥሮንም ቀረብ ብለን በድሆችና በተገለሉ ሰዎች እሪ ስለምትል ማዳመጥ ያስፈልጋል፣ የአከባቢ መለዋወጥ ሁኔታና አንዳንድ መድኃኒት የማይገኝላቸው በሽታዎች ሁኔታ የጋራ ቤታችንን በሚገባ ካለመንከባከብና ኃላፊነታችንን በሚገባ ካለመወጣት የመጣ ነው ብየ አምናለሁ፣ ስለዚህ በሥራችሁም ይሁን በዚሁ ሳቢያ እየተሰቃዩ ያሉና እናንተ አገልግሎት በምትሰጥዋቸው ሰዎች ሁሌ ይህንን ልብ እንድትሉት አደራ ሲሉ ንግግራቸውን ደምድመዋል፣








All the contents on this site are copyrighted ©.