Social:

RSS:

የቫቲካን ሬድዮ

ከዓለም ጋር የሚወያይ የር.ሊ.ጳጳሳትና የቤተ ክርስትያን ድምጽ

ቋንቋ:
የቫቲካን ሬድዮ

መታወቂያ ገጽ / ሥርዓተ አምልኮ / የእሁድ ስብከቶች

መንፈስ ቅዱስ በየጊዜው አዳዲስ ነገሮችን የሚያመጣ ፈጣሪ የሆነ መንፈስ ነው።


በግንቦት 27/2009 ዓ.ም. በመላው ዓለ በሚገኙ ክርስቲያኖች ዘንድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ከተነሳ ከሃምሳ ቀናት ቡኃላ መንፈስ ቅዱስ በሐዋሪያት ላይ በእሳት አምሳል የወረደበት የጴንጤቆስጤ በዓል በታላቅ ድምቀት ተከብሮ መዋሉ ይታወቃል።

የዚህን ዝግጅት ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጭእን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

ይህ የጴንጤቆስጤ በዓል በርካታ ምዕመናን እና የሀገር ጎብኝዎች በተገኘቡት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በርዕስ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ መሪነት መስዋዕተ ቅዳሴ ተደርጎ እንደ ነበረም የታወቀ ሲሆን በወቅቱም ቅዱስነታቸው ባሰሙት ስብከት እንደ ገለጹት መንፈስ ቅዱስ የፋሲካ በዓል ትልቁ ስጦታ ነው ማለታቸው ተግልጹዋል። ክቡራን እና ክቡራት ታዳሚዎቻችን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በወቅቱ ያደረጉትን ስብከት ሙሉ ይዜት እንደ ሚከተለው ተርጉመነዋል እንድትከታተሉን እንጋብዛለን።

መንፈስ ቅዱስ በየጊዜው አዳዲስ ነገሮችን የሚያመጣ ፈጣሪ የሆነ መንፈስ ነው። በዛሬው ቀን በተነበቡልን ምንባባት ላይ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት የተገኙትን ሁሉት አዳዲስ ተግባራትን እናገኛለን፣ በቅድሚያም በሐዋሪያት ሥራ 21-11 ላይ እንደ ተጠቀሰው መንፈስ ቅዱስ ደቀ መዛሙርቱን አዲስ ሰው ስያደርጋቸው እናያለን በመቀጠልም በዩሐንስ ወንጌል 2019-23 ላይ እንደ ተጠቀሰው ለደቀ መዛሙርቱ አዲስ የሆነ ልብ ሲፈጥርላቸው እናያለን።

አንዲስ ሰው! “በጰንጤቆስጤ ቀን መንፈስ ቅዱስ የእሳት ነበልባሎች የሚመስሉ ምላሶች አማክይነት ከሰማይ ወረደ በእያንዳንዳቸውም ላይ ዐረፉባቸው። ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ መንፈስ ቅዱስ እንዲናገሩ በሰጣቸው ችሎታ መጠን በሌሎች ቋንቋዋች መናገር ጀመሩ” (የሐዋ. 23,4) የእግዚኣብሔር ቃል መንፈስ ቅዱስን እንዲህ በማለት ይገልጸዋልበመጀመሪያ በእያንዳንዳቸው ላይ ዐረፈባቸው ቀጥሎም ሁሉንም ወደ ኅብረት ያመጣቸዋልይላል። ለእያንዳንዱ ስጦታን ከሰጣቸው ቡኃላ ኅብረት እንዲፈጥሩ ይሰበስባቸዋል።  በሌላል አነጋገር ይህ መንፈስ በልዩነት ውስጥ ኅብረት ሲፈጥር ይታያል፣ በዚህም መልኩ የተለያየ ነገር ግን ኅብረት ያለው አዲስ ነገር ይመሰርታል፣ ይህም ዓለማቀፋዊ ቤተ ክርስቲያን ብለን የምንጠራው ነው። በቅድሚያ ፈጣሪ እና ድንገተኛ በሆነ መንገድ ልዩነትን ፈጠረ፣ ከዚያም ሁሉንም በአንድነት በመሰብሰብ ኅብረትን ፈጠረየእርሱ መኖር እና እንቅስቃሴ ማድረግ የተለያዩ መንፈሶችን ኅብረት እንዲፈጥሩ ያደርጋል በተጨማሪም እያንድአንዱ የተለያየ እንዲሆን ያደርጋል። ይህንንም የሚያደርገው እውነተኛ ኅብረትን በሚያረጋግጥ መልኩ እና በእግዚኣብሔር ፍቃድ ላይ ተመስርቶ አንድ የሚያደርግ ኅብረት ሳይሆን በልዩነት ወስጥ ኅብረትን ይፈጥራል።

ይህ እንዳይከሰት ከፈለግን ሁለት መደበኛ የሆኑ ፈተናዎችን ማስወገድ ይኖርብናል። የመጀመሪያው ፈተና አንድነትን ያለ ልዩነት ለመፍጠር መሞከር ነው። ይህ የሚከሰተው ለመለያየት ስንሞክር፣ አንድ ወገንን በመደገፍ አንድ ጎራ ስንፈጥር፣ ግትር የሆነ ሐሳብ ስናራምድ እና እኔ ብቻ ነኝ ትክክል ብለን ስናስብ፣ በራሳችን ሐሳብ ውስጥ ብቻ ተቆልፈን ወይም ተዘግተን ስንኖር፣ ነገሮችን በራሳችን አመለካከት ላይ ብቻ ተመስርተን ሥንሰራ፣ በተጨማሪም እኛ ከሌሎች የተሻልን ነን ብለን ስናስብበአጠቃላይ እውነት ሁሉ እኛ ጋር ብቻ ነው የሚገኝው ብለን ስናስብየሚከሰት ጉዳይ ነው። ይህ በሚፈጠርበት ወቅት ከአጠቃላይ ጉዳይ ይልቅ ክፋይ የሆነውን ብቻ እንመርጣለን ማለት ነው፣ በዚህ አግባብ የምንሄድ ከሆንን የቤተ ክርስቲያን አባል ሳንሆን የአንድ ቡድን አባል እንሆናለን ማለት ነው። ስለዚህ በአንዱ በመንፈስ ቅዱስ እንደ ተዋጁ ወንድም እና እህት ሳንሆን፣ አንድን ቡድን ብቻ በንቃት የምንደግፍ ሆነን እንገኛለን ማለት ነው። በቅድሚያ በኢየሱስ ጎራ ሳንሰለፍ የግራ ወይም የቀኝ ክንፍ ደጋፊ ክርስቲያኖች እንሆናለን ማለት ነው።  የዚህም ውጤት ያለ ኅብረት ልዩነት መፍጠር ይሆናል ማለት ነው።

የዚህ ተቃራኒ የሆነው ፈተና ደግሞ ኅብረትን ያለ ልዩነት ለመፍጠር መሞከር ነው። በዚህ ረገድ ሁሉም ሰው ሁሉንም ነገር በአንድነት እና ወጥ በሆነ መልኩ ማከናውን አለበት፣ ስለ ሁሉም ነገር ተመሳሳይ የሆነ አስተሳሰብ ሊኖር ይገባል የሚል ሐሳብ የሚያንሸራሽር ሲሆን ይህም ኅብረት አንድነትን መፍጠር ነው የሚለውን ያሰማል። በዚህም ረገድ ኅብረት ማለት ወጥ ወይም ተመሳሳይ የሆነ ነገር መፍጠር የሚለውን ሐሳብ በማስረጽ የሌሎችን ነጻነት ይጋፋል። ነገር ግን ሐዋሪያው ጳውሎስየእግዚኣብሔር መንፈስ በሚገኝበት ስፍራ ሁሉ ነጻነት አለ” (2ቆሮ 317) ይለናል።

ስለዚህም ለመንፈስ ቅዱስ የምናቀርብለት ጸሎት የየግላችንን ምርጫ ወደ ጎን በመተው፣ የእርሱ የሆነችውን ቤተ ክርስቲያንን እንድንወዳት እና እንድንቀበላት፣ የእኛንም ቤተ ክርስቲያን ተመሳሳይ በሆነ መልኩ እንድንወድ እና እንድንቀበል የኅብረትን ጸጋ ይሰጠን ዘንድ ነው። በሁሉም ዘንድ ኅብረት እንዳይፈጠር ብጥብጥን የሚፈጥር እንክርዳድ እና የቅናት መርዝ የሚዘረዋውን ሐሜት አስወግደን የቤተ ክርስቲያን ወንድም እና እህት ማለት ኅብረት ያላቸው ወንድም እና እህት ማለት መሆኑን እንድንረዳ ኃልፊነት መውሰድ ይኖርብናል። በተጨማሪም ቤተ ክርስቲያን እናታችን እና ቤታችን እንደ ሆነች፣ ለሁሉ ክፍት የሆነች እና ሁሉም ከመንፈስ ቅዱስ የሚመነጨውን ደስታ የሚቋደሱባት እንደ ሆነች የሚሰማው ልብ ይሰጠን ዘንድ ልንለምነው ይገባል።

አሁን ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ወደ ተገኘው ሁለተኛው አዲስ ነገር እንሻገር፣ ይህም አዲስ ልብ የሚለው ነው። ከሙታን የተነሳው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶ በመጀመሪያ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በተገናኘበት ወቅትመንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ፣ እናንተ የሰዎችን ኃጢአት ይቅር ብትሉ ይቅር ይባልላቸዋል፣ እናንተ የሰዎችን ኃጢአት ይቅር ባትሉ ግን ይቅር አይባልላቸውም” (ዩሐ. 2022,23) ብሎዋቸው ነበር። ኢየሱስ  ደቀ መዛሙርቱ እርሱን በመከራው ጊዜ በመካዳቸው እና ብቻውን ጥለውት በመሄዳቸው የተነሳ አላወገዘም፣ ነገር ግን የይቅርታን መንፈስ ሰጣቸው።  መንፈስ ቅዱስ ከሙታን የተነሳው ጌታ የመጀመሪያ ስጦታ ነው፣ ይህም በቀዳሚነት የተሰጠው ኃጢአን ለማስተሰረይ ነው። እዚህ ላይ የቤተ ክርስቲያንን አጀማመር እናያለን፣ ሁላችንንም አንድ ላይ አጣብቆ የሚይዝ ማጣበቂያ እንዳለ እንገነዘባለን፣ ይህም ይቅርታ ማድረግ ነው። ይቅርታ ማድረግ ልባችን ነጻ እንዲሆን በማድረግ ነገሮችን በአዲስ መልክ እንድንጀምር ያስችለናል። ይቅርታ ተስፋን ያጎናጽፋል፣ ይቅር መባባል ባይኖር ኖሮ ቤተ ክርስቲያን አትመሠረትም ነበር። የይቅርት መነፍስ በኅብረት አማክይነት ለሁሉም ነገር መፍትሄ ይፈልጋል፣ በተለያዩ መንገዶችን በችኮላ የሚደረጉ ውሳኔዎችን፣ በሮቻችንን ለሌሎች መዝጋት፣ ሌሎችን የመተቸት እነዚህን እና እነዚህ የመሳሰሉ መንገዶችን እንድናሰውግድ ይረዳናል። በምትኩም መንፈስ ቅዱስ ይቅር የማለት እና ይቅርታን መቀበል የሚሉትን ሁለት ዓይነት የይቅርታ መንገዶችን እንድንከተል ይረዳናል፣ ይህም መለኮታዊ ፍቅር ባልንጀራችንን እንድንወድ ይረዳናል ይህም ፍቅርአንድ ነገር መሠራት እንዳለበት ወይም መሠራት እንደ ሌለበት፣ መለወጥ እንዳለበት ወይም መለወጥ እንደ ሌለበት መወሰን የሚያስችለን ብቸኛው መመዘኛሊሆን ይገባል። ራሳችንን በይቅርታ አድሰን እና ራሳችንን በራሳችን በማረም ከቤተ ክርስቲያን ጋር ያለን ግንኙነት ያማረ ይሆን ዘንድ የሚረዳን ጸጋ እንዲሰጠን እንጠይቅ። ከዚህም ቡኃላ ብቻ ነው ሌሎችን በፍቅር ማረም የምንችለው።

እኛ መንፈስ ቅዱስን በኃጢአታችን ምክንያት በአመድ ብናዳፍነውም ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በቤተ ክርስቲያን እና በልባችን ውስጥ የሚቀጣጠል የፍቅር እሳት ሆኖ ይቀጥላል። እንዲህ ብለን እንጠይቀውበልባችን እና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የምትኖር፣ የምትመራን እና በልዩነቶች እንድናምን የምታደርግ የእግዚኣብሔር እና የጌታ መንፈስ ሆይ ! እንደ ውሃ ለሕይወታችን ታስፈልገናልህ። እንደ አዲስ በእኛ ለይ ውረድ፣ ኅብረትን መፍጠር አስተምረን፣ ልባችንን አድስ፣ አንተ እንደ ምትወደን መውደድ እንድንችል፣ አንተ ይቀር እንደ ምትለን ይቅር ማለት እንድንችል አስተምረን። አሜን!”

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ቀደም ሲል የታደማችሁት ርዕሰ ሊቃነ ጳጵእሳት ፍራንቸስኮ በግንቦት 27/2009 ዓ.ም. በመላው ዓለም በሚገኙ ክርስቲያኖች ዘንድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ከተነሳ ከሃምሳ ቀናት ቡኃላ መንፈስ ቅዱስ በሐዋሪያት ላይ በእሳት አምሳል የወረደበት የጴርቅሊጦስ በዓል በታላቅ ድምቀት በተከበረበት ወቅት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ መስዋዕተ ቅዳሴን ላይ ያሰሙትን ስብከት ሙሉ ይዘት ነበር አብራችሁን በመሆን ስለተከታተላችሁን ከልብ እናመስግናለን።