Social:

RSS:

የቫቲካን ሬድዮ

ከዓለም ጋር የሚወያይ የር.ሊ.ጳጳሳትና የቤተ ክርስትያን ድምጽ

ቋንቋ:
የቫቲካን ሬድዮ

መታወቂያ ገጽ / ቤተ ክርስትያን / ኢትዮጵያ

የኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ትንሳኤ የመልካም ነገር ሁሉ ተስፋ ነው።


የተወደዳችሁ ታዳሚዎቻችን ይህ ዝግጅት የሚደርሳችሁ ከቫቲካን ሬዲዮ የአማርኛ ቋንቋ አገልግሎት ነው። ከዚህ ቀጥሎ “የኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ትንሳኤ የመልካም ነገር ሁሉ ተስፋ ነው” በሚል ርዕስ ወደ ተዘጋጀው መልዕክት እናመራለን ቆይታችሁን ከእኛ ጋር በማድረግ እንድትከታተሉ በትሕትና እንጋብዛችኋለን።

የዚህን አስተምህሮ ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ።

የእግዚአብሔር አብ ፍቅር ለእኛ የተገለጠበት አንደኛው መንገድ እኛን ለማዳን እና ራሱን ከእኛ ጋር ሊያኖር በመፍቀዱ ነው። ይህም የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስጋን በመልበስ በእኛ እና በእግዚአብሔር መከከል ያለውን መለኮታዊ ግንኙነት እውን በማድረጉ ነው። ቀጥሎም የእግዚአብሔር ፍቅር የታየበት ሌላው መንገድ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን የእኛን ኃጢአት እንዲሸከም፣ ምሕረትንም እንዲያስገኝልን በመስቀል ላይ ተሰቅሎ እንዲሞት በማድረጉ ነው። የእግዚአብሔር ኃይል የሞትን ሥልጣን አሸንፎ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በሦስተኛው ቀን ከሞት አስነሳው። በዚህም የእግዚአብሔርን ፍቅር ብቻ ሳይሆን፣ ሞት በሕይወት ላይ ስልጣን እንደሌለው እንመለከታለን።

ሐዋርያው ጳውሎስ ኢየሱስ በመሞቱ ያስገኛቸውን ፍሬዎች እንዲህ በማለት ይገልጻቸዋል፥ የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት እውነተኛ ፍርድን፣ እርቅን፣ ነጻነትን ቅድስናን ከሞት ወደ ሕይወት መሸጋገርንና በሞት ላይ ድልን ያጎናጸፈ ሞት ነው ይላል። የኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ትንሳኤ ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከሐዘን ወደ ደስታ፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከጥል ወደ እርቅ፣ ከመለያየት ወደ መቀራረብ፣ ከጭቆና ወደ ፍትሕና ነጻነት፣ ከጥላቻ ወደ ፍቅር፣ ከጦርነት ወደ ሰላም ለመሸጋገር ተስፋ የምናደርግበት መንገድ ነው። ተስፋችንም ከንቱ እንዳልሆነ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በትንሳኤው አረጋግጦልናል። ስለዚህ ይህን ተስፋ መቁረጥ የለብንም። የቤተክርስቲያናችን ትምህርተ ክርስቶስ በቁጥር 2091 ላይ እንደሚለው፥ ተስፋ መቁርጥ የእግዚአብሔርን በጎነት ጽድቁንም የሚጻረር ነው፤ ምክንያቱም ጌታ ለገባቸው ኪዳኖች ለምሕረቱም የታመነ ነውና። ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ዕብራውያን በላከው መልዕክቱ በምዕራፍ 10 ቁጥር 23 ላይ “የተስፋን ቃል የሰጠን ታማኝ ስለሆነ፥ አሁን አምነን የምንመሰክረውን ተስፋ ሳናወላውል አጥብቀን እንያዝ” ይላል።

በዚህ አጋጣሚ የእስራኤልን ሕዝብ ታሪክ በአጭሩ መመልከት መልካም ይሆናል። የእስራኤል ሕዝብ በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ እና የተመረጠ ሕዝብ ነበር። ስለዚህ ይህ ሕዝብ በሰላም በደስታና በፍቅር የሚኖሩበትን እና የሚተዳደሩበትን ሕግ እግዚአብሔር አዘጋጅቶ በሙሴ በኩል ሰጣቸው። ነገር ግን የእስራኤል ሕዝብ ሕግን አፍርሰው ወይም የሕግ የበላይነትን ሳያከብሩ ቀርተው በመካከላቸው አንዱ ሌላውን መበደል፣ ንብረቱን መዝረፍ፣ ነጻነቱን መግፈፍ፣ ባሪያ አድርጎ ለአገልግሎት መሸጥ እና ሌሎችም አስከፊ የኑሮ ገጽታዎች እየተበራከቱ በመምጣታቸው፣ እግዚአብሔርም ይህ ሕዝብ ምን ያህል አመጸኛ እንደሆነና አሳባቸውም ዘወትር በክፋት የተሞላ እንደሆነ ተገነዘበ። ስለዚህ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ዓለም በመላክ የአዲሱን ሕግ መምጣት ተስፋ አበሰረ። ኢየሱስ ክርስቶስ ያወጀው የአዲስ ኪዳን ሕግ የእስራኤል ሕዝብ ከተጨቆኑበት ነጻ በመውጣት የሰላም፣ የዕረፍት፣ የእኩልነት እና የነጻነት ሕይወት እንዲኖሩ አስቻላቸው። ነቢዩ ኢሳይያስም በትንቢቱ ሲናገር በምዕራፍ 2 ላይ፥ “በጨለማ ይኖር የነበረ ሕዝብ እነሆ ታላቅ ብርሃን አየ”።

የተወደዳችሁ የዚህ መልዕክት ተካፋይ የሆናችሁ በሙሉ፣ ከእስራኤል ሕዝብ ታሪክ እንደምንረዳው በእግዚአብሔር ፊት ሁላችንም በደለኞች ነን። ሕጉን ያቃለልን እና ያፈረስን፣ ትዕዛዛቱንም የናቅን ኃጢአተኞች ነን። ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ በትንሳኤው፣ በሞት ላይ ድልን እንደተቀዳጀ፣ በኃጢአት ምክንያት ወደ ዘለዓለማዊ ሞት ከተጣልንበት በምሕረቱ ወደ ዘለዓለማዊ ሕይወት ለመሸጋገር እንደቻልን እናምናለን።

በአንዳንድ የዓለማችን ክፍሎች፣ በሕዝቦች ዘንድ እንደ መልካም ሲቆጠር የቆየው ባሕል ለምሳሌ መከባበር፣ መተሳሰብ፣ መረዳዳት፣ መወያየት እና መደማመጥ ቀንሶ እናያለን። ከማኅበራዊ ጥቅም ይልቅ የግል ጥቅምን ማስቀደም፣ ፍትሕን ማጓደል፣ ነጻነትን መንፈግ፣ በስልጣን መመካት እና ወገናዊነት በጉልህ እየታየ መጥቷል። የዚህ ክፉ ተግባር ውጤቱ በሕዝቦች መካከል ቁጣንና አለመራአጋጋትን፣ ራስ ወዳድነትን፣ ጥላቻንና ጦርነትን በመቀስቀስ ለሕይወት መጥፋት እና ለንብረት መውደም ምክንያት ሊሆን ይችላል። ሰዎች በሰዎች ላይ የሚፈጽሙት በደል ሳያበቃ በተፈጥሮ ላይም የሚያሳዩት የግድ የለሽነት አቋም ተመልሶ በሰው ሕይወት እና በመላ ተፈጥሮ ላይ አደጋን እያስከተለ መሆኑ ይስተዋላል።

ቢሆንም ኢየሱስ ክርስቶስ በትንሳኤው የሞትን ኃይል በማሸነፍ የመልካም ነገር ሁሉ የመጀመሪያ ምሳሌ ሆነ። ዛሬ ቀኑ ቢጨልምብን፣ ስቃይ ቢበረታ፣ ሐዘን ቢገባን፣ ማንኛውም ዓይነት ክፋት እና በደል በሕይወታችን ቢደርስብን ሁሉም ለጊዜው እንጂ በመልካም እንደሚተካ ተስፋ የምናደርገው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ባሳየን የትንሳው ብርሃን ነው። ይህን ተስፋ በትዕግስት የምንጠብቅበትን እምነት እግዚአብሔር በቸርነቱ ለሁላችንም አብዝቶ ይስጠን፤ አሜን።

በአቶ ዩሐንስ መኮንን የተዘጋጀ።