2018-07-21 16:12:00

ቤተ ሰብ፣ ዓለምን ለሰው ዘር መልካም መኖሪያ እንዲሆን ለማድረግ ተጠርቷል።


ቤተ ሰብ፣ ዓለም ለሰው ዘር ሙሉ መልካም መኖሪያ እንዲሆን ለማድረግ መጠራቱ ተነገረ።

ቤተ ሰብ፣ ሰብዓዊ ክብርን እና ግብረ ገብን በመላበስ፣ ዓለም ለሰው ዘር በሙሉ መልካም መኖሪያ እንዲሆን ለማድረግ መጠራቱ ተነገረ።

ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን፣ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ፣ ቤተ ሰብ፣ ሰብዓዊ ክብርን እና ግብረ ገብን በመላበስ፣ የሚኖርበትንም ዓለም ተንከባክቦ በመያዝ፣ ለሰው ዘር በሙሉ መልካም መኖሪያ እንዲሆን ለማድረግ መጠራቱን አስታወቁ።

ብጹዕ ካርዲናል ይህን የተናገሩት ሐምሌ 19 ቀን 2010 ዓ. ም. በፈረንሳይ አገር ፋጢማ በተባለ ሥፍራ ተገኝተው፣ የኖተርዳም ኤኩፔስ በመባል ለሚታወቀው ለባለ ትዳሮች መንፈሳዊ እንቅስቃሴ አባላት መሆኑ ታውቋል።

የኖተርዳም ኤኩፐስ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ፣ በፈረንሳይ አገር በኖተርዳም ከተማ፣ በ1930 ዓ. ም. በጥቂት ባለ ትዳሮች እና መሪ ካህን በሆኑት በክቡር አባ ሄንሪ ካፋረል በሕብረት የመሠረቱት ሲሆን ዓላማውም፣ ከምስጥረ ተክሊል የሚገኘውን መንፈሳዊ ጸጋ እና በረከት በውይይት፣ በጸሎትና በትምህርት የበለጠ ለመረዳት በማለት እንደሆነ ታውቋል።     

ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን በፈረንሳይ ፋጢማ ተገኝተው፣ በሺዎች ለሚቆጠሩ የኖተርዳም ኤኩፐስ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ አባላት ባቀረቡት አስተንትኖ፣ የትዳር መንፈሳዊነት በሰው ሥነ ምህዳር ወስጥ የጠበቀ ግንኙነት እና ሕብረት እንዳለው አስረድተዋል። መኖሪያ ቤቱን የመንከባከብ ሃላፊነት ያለው ሰው፣ የጋራ መኖሪያ የሆነውን ዓለማችን የመንከባከብ እና የመጠበቅ ሃላፊነት እና አደራ ምን ማለት እንደሆነ ጠንቅቆ ያውቀዋል ብለዋል። በአንድ ትንሽ ቤተ ሰብ ውስጥ የሚኖር ሰው፣ አብሮ በመኖር፣ ዕለታዊ ሥራዎችን እና እቅዶችን፣ ከጎረቤት ጋር ሊኖር ስለሚገባው ጤናማ ግንኙነት አስፈላጊነት በሚገባ ማወቅ ያስፈልጋል ብለዋል። ስለዚህ ቤተ ሰብ በየቀኑ የሚወስዳቸው ውሳኔዎች ትክክለኛነት፣ በአካባቢው ከሚገኘው ተፈጥሮም ጋር የሚያደርገው ግንኙነት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ በሚገባ ማወቅ ያስፈልጋል ብለዋል።

የዓለም አቀፉ ማሕበረ ሰብ ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ ያከናወናቸውን ሳይንሳዊ እና ፖለቲካዊ የጥናትና የምርምር ደርጃን እንዲሁም የደረሰበትን ሥነ ምህዳራዊ ግንዛቤን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን፣ ጥናቶቹ የሚጠቁሙት እና መሠረታቸውን ያገኙት ከቅዱሳት መጽሕፍት እንደሆኑ ተናግረው፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እግዚአብሔር ሰውን ከአፈር ፈጥሮት እስትንፋስንም ሰጥቶት ሲያበቃ፣ እርሱ ራሱ ውብ አድርጎ በፈጠረው የአታክልት ሥፍራ እንዲኖር ሲያደርግ ሰውም ያንን ከእግዚአብሔር የተቀበለውን ሥፍራ ተንከባክቦ በመያዝ አርሶ አንዲበላ እና እንዲኖርበት ማዘዙን ጠቅሰው ይህ ማለት የሰው ልጅ ለሚኖርባት ምድር ሊሰጥ የሚገባው እንክብካቤ ትልቅ እንደሆነ  አስታውሰዋል።

ይህ በመሆኑ የሰው ልጅ በፍጥረት ላይ የበላይነት እንደሌለው፣ የእግዚአብሔር አምሳያነት ያለው ቢሆንም ከፍጥረታት መካከል አንዱ እና ምድራዊ ሕይወቱን ለማቆየት በፍጥረታት ላይ እንደሚመካ ገልጸው ሰው የአንድ ሕብርተ ሰብ አባል ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ፍጥረታት ጋር ያማያቋርጥ ግንኙነት እንዳለው ተናግረዋል። በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ፣     የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን በማከልም ከሁሉም በላይ የሰው ልጆች ከእግዚአብሔር ፍጥረታት መካከል፣ የእርሱም ልጆች በመሆናቸው እኩል ሰብዓዊ ክብር እንዳላቸው ይገነዘባሉ ብለዋል። ስለዚህ አንዱ የሌላውን ክብር ማሳነስ ወይም እንዱ ሌላውን ለማጥፋት መነሳሳት የተወገዘ ነው ብለዋል። እያንዳንዱ ሰብዓዊ ፍጥረት ብቸኛ እንዳልሆነ ነገር ግን በቤተ ሰብዓዊ እና በማህበራዊ ግንኙነት የተሳሰረ፣ እኩል ክብር ያለው እና የጋራ ጥቅም ተቋዳሽ እንደሆነ በጋራ እንዲኖር ተብሎ የተፈጠረ እንደሆነ ገልጸዋል።

የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ካርዲናል ታርክሰን፣ ስለ ስለ ሰው ሥነ ምህዳር ትክክለኛ ምንነት ሲያስረዱ፣ መታየት ያለበት የሰው ልጅ ከአካባቢው ጋር የሚያደርገው ግንኙነት ብቻ ሳይሆን፣ በእርግጥም የእግዚአብሔር ፍጥረት መሆኑን የሚያረጋግጥበት ጥሩነት፣ ጨዋነት፣ ፍትሃዊነት፣ ፍቅር፣ ወንድማዊነት፣ ሕብረት እና ርህራሄ ነው ብለዋል። ቤተ ሰብ፣ መልካም እሴቶች በግልጽ የሚታይበት የሕብረተ ሰብ ክፍል እንደሆነ ተናግረው፣ የዘመናችን ቤተ ሰብ የተደቀነበትን መጠነ ሰፊ ችግሮችን አስታውሰው ከእነዚህም መካከል በጣም ዝቅተኛ የወር ገቢ፣ ሥራ ማጣት፣ በተለይም ራስን ለማስተዳደር ካለመቻል የተነሳ በሚያደርጉት አደገኛ ስደት ወቅት የሚያጋጥማቸው የብዝበዛ እና የባርነት ሕይወትን አስታውሰዋል። በዚህ አጋጣሚ በዓለም ዙሪያ የተከሰተውን የአየር ለውጥ ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን በርካታ ቤተ ሰብ በመጠጥ ውሃ እጥረት፣ በምግብ ማነስ፣ በመጠለያ እጦት የሚጎስቆሉ መኖራቸውን ተናግረዋል።

እነዚህ ችግሮች ከሁላችን እይታ የተሰወሩ እንዳልሆነ ተናግረው፣ ይህን ችግር ለማቃለል ታዲያ ቤተ ሰብም የራሱን አስተዋጾ ማበርከት ይኖርበታል ያሉት ካርዲናል ታርክሰን ቤተ ሰብ አላስፈላጊ ብክነቶችን ወይም ወጪዎችን በመቀነስ እገዛ ለሚያስፈልገው ለሌላው ቤተ ሰብ የቸርነት እጁን መዘርጋት ይችላል ብለዋል። በተጨማሪም ቤተ ሰብ ቀጥታ ተሳትፎን በማከል አንዳንድ ጠቃሚ የፈጠራ ሃሳቦችን እና ሥራዎችን በድፍረት ማበርከት ይችላል ብለዋል።

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን በመጨረሻም መልካም ቤተ ሰብ ለችግር ሳይበገር፣ በመካከሉ ያሉትን መልካም እሴቶችን እና ስጦዎችን በማስተባበር፣ ክብራቸውን ከሚቀንሱ፣ ከእድገታቸው ወደ ኋላ የሚጎትቱትን እንቅፋቶችን ለማስወገድ በሕብረት መስራት እንደሚያስፈልግ አሳስበው ከ አንድ ቤተ ሰብ የሚመነጨው የሰብዓዊ ክብር እቅድ ወደ ሌሎች የዓለማችን ክፍሎችም ሊዳረስ ይችላል ብለዋል።

 

 








All the contents on this site are copyrighted ©.