2018-06-11 15:58:00

ር.ቃ.ጳ. ፍራንቸስኮስ “በቅናት ላይ የተመሠረቱ የሐሰት ክሶች እንደ ገዳይ መርዝ ናቸው” ማለታቸው ተገለጸ።


Papa all' Angelus: le false accuse per invidia sono veleno mortale

ር.ቃ.ጳ. ፍራንቸስኮስ “በቅናት ላይ የተመሠረቱ የሐሰት ክሶች እንደ ገዳይ መርዝ ናቸው” ማለታቸው ተገለጸ።

ቅዱስነታቸው ይህንን የተናገሩት በትላንትናው እለት ማለትም በሰኔ 03/2010 ዓ.ም እለተ ሰንበት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን እና የሀገር ጎብኚዎች በእለቱ የአውሮፓዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ምዕመናን ዘንድ በላቲን ስርዓተ አምልኮ የቀን አቆጣጠር ደንብ መሰረት ከማርቆስ ወንጌል ከምዕራፍ 3፡20-35 ላይ ተወስዶ በተነበበው እና ከኢየሩሳሌም የመጡ ጸሐፍትም፣ “ኢየሱስን ብዔልዜቡል አድሮበታል፤ አጋንንትን የሚያወጣው በአጋንንት አለቃ ነው” በማለት ስለኢየሱስ በተናገሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ መሰርቱን ያደርገ እንደ ነበረም ለመረዳት ተችሉዋል።

የእዚህን አስተንትኖ ሙሉ ይዘት ከእዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በትላንትናው እለት ማለትም በሰኔ 03/3010 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው የቅዱስ ጴጥርስ አደባባይ በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተመርኩዘው ያደርጉትን አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው ተርጉመነዋል አብራችሁን በመሆን ዝግጅቶቻችንን በሙሉ እንድተከታተሉ ከወዲሁ እንጋብዛለን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዛሬው እለተ ሰንበት የተነበበው የቅዱስ ወንጌል ቃል (ማርቆስ 3: 20-35) ኢየሱስ የግድ የተጋፈጣቸውን ሁለት ዓይነት የተሳሳቱ ግንዛቤዎችን ያሳየናል፡ እነዚህም ጸሐፍት እና የገዛ ዘመዶቹ ስለኢየሱስ የነበራቸው የተሳሳተ ግንዛቤ ነው።

የመጀመሪያው የተሳሳተ ግንዛቤ። ጸሐፍት ቅዱሳን መጽሐፍትን በደንብ የተማሩ እና ለሕዝቡም ቅዱሳን መጽሐፍትን የማብራራት ኃላፊነት ነበረባቸው። ከእነዚህ ጸሐፍት መካከል አንዳንዶቹ የኢየሱስ ዝና በስፊው በተንሰራፋበት ከኢየሩሳሌም ወደ ገሊላ የተላኩ ሰዎች ሲሆኑ ይህንንም ያደርጉት በሕዝቡ ፊት ኢየሱስን ዋጋ ለማሳጣት በማሰብ የአሉባልታ ወሬ ለማውራት፣ ሌላውን ሰው ዋጋ ቢስ ለማደርግ፣ እውቅና ለማሳጣት ነበር የመጡት፣ የእዚህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ ደግሞ በጣም መጥፎ የሆነ ነገር ነው። ከኢየሩሳሌም ወደ ገሊላ የተላኩትም ይህንን የአሉባልታ ወሬ ለመፈጸም ነበር። እናም እነዚህ ጸሐፍት ግልጽ እና አስቃቂ የሆነ ክስ ይዘው ነበር የመጡት-- ይህንንም ለማድረግ የተጠቀሙት ዘዴ በሕዝቡ መኃል በመግባት “ኢየሱስ ብዔልዜቡል አድሮበታል፤ አጋንትን የሚያወጣው የአጋንንት አለቃ በሆነው በብዔልዜቡል አማካይነት ነው” (ማርቆስ 3፡22) በማለት ነበር። ይህም ማለት ኢየሱስ እነዚህን ተዐምራት የሚፈጽመው በአጋንንት አነሳሽነት ነው ማለት ነው፣ ይህም ማለት ደግሞ ይነስም ይብዛም “ኢየሱስ አጋንት አድሮበታል”  ማለት ነው። እንዲያውም ኢየሱስ እጅግ ብዙ የታመሙ ሰዎችን ፈውሶ ነበር፣ ነገር ግን እነሱ ኢየሱስ እነዚህን ተዐምራት የሚፈጽመው በእግዚኣብሔር መንፈስ እንደ ሆነ ማመን አይፈልጉም እንጂ ኢየሱስ ይህንን ያደርገው በእግዚኣብሔር መንፈስ ነው፣ እነርሱ ግን በአጋንት ኃይል ነው ብለው ያምኑ ነበር። ኢየሱስ ይህንን ሐሳባቸውን ሳይቀበል ጠንካራ እና ግልጽ የሆኑ ቃላቶችን በመጠቀም ምላሽ ይሰጣቸዋል፣ ምክንያቱም እነዚያ ጸሐፍቶች ሳይታወቃቸው አስከፊ ወደ ሆነ ኃጢአት ውስጥ እየገቡ በመሆናቸው የተነሳ ነው፣ በኢየሱስን እና ኢየሱስ በሚሰራቸው ተግባሮች ውስጥ ሳይቀር የሚገኘውን  የእግዚአብሔር ፍቅር በመሳደብ ላይ ነበሩ። በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚቃጣ ስድብ ኢየሱስ እንደ ሚለው “በመንፈስ ቅዱስ ላይ የስድብ ቃል የሚናገር ሁሉ ለዘላለም አይሰረይለትምምክንያቱም በኢየሱስ አማካይነት ለሚነቀሳቀሰው የእግዚኣብሔር ምሕረት ወደ ውስጥ ጥልቆ እንዳይገባ ልብን የሚዘጋ በመሆኑ የተንሳ ነው።

ነገር ግን ይህ ክፍል ለሁላችን ጠቃሚ የሆነ ማስጠንቀቂያ አቅፎ ይዟል። በእርግጥ አንድ መልካም የሆነ ሰው ለሰዎች መልካም ሥራ በሚያከናውንበት ወቅት በከፍተኛ ቅንዓት የተነሳ የሐሰት ክስ ሊቀርበት ይችል ይሆናል። እዚህ ጋር አስቀድሞ ነገሮችን በማጠንጠን፣ አንዱ የሌላውን መልካም ስም ለማጥፋት የሚሞክር ገዳይ የሆነ መርዝ አለ። እግዚአብሔር ከዚህ ዓይነቱ አስፈሪ ፈተና ውስጥ ያውጣን! እኛም ህሊናችንን በጥንቃቄ ከመረመርን  ይህ መጥፎ ተክል በውስጣችን እያቆጠቆጠ እንዳለ እንገነዘባለን፣ በውስጣችን አድጎ መጥፎ የሆኑ ውጤቶችን ከማስከተሉ እና ሊዱኑ የማይችሉ መጥፎ የሆኑ ውጤቶችን ከማስከሰቱ በፊት በቶሎ በምስጢረ ንስሐ አማካይነት  ከእዚህ መንጻት ይኖርብናል። በጣም ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል፣ ምክንያቱም የእዚህ ዓይነቱ ባሕሪይ ቤተሰብን፣ ጓደኝነትን፣ ማኅበርን በመጨረሻም አጠቃላይ ማኅበረሰቡን ሊያፈራርስ  የሚችል ተግባር ነው።

የዛሬው ቅድስ ወንጌል ኢየሱስን በተመለከተ የነበረውን ሁለተኛ የተሳሳተ ግንዛቤ ያሳየናል፣ ይህም ዘመዶቹ ለኢየሱስ የነበራቸው ግንዛቤ ነው። ኢየሱስ የጀመረው አዲሱ የሕይወት ጉዞ በተመለከቱበት ወቅት እርሱ ያበደ ስለመሰላቸው ተጨንቀው ነበር። በእርግጥ ለሰዎች በተለይም ለታመሙና ኃጢአተኛ ለነበሩ ሰዎች ሳይቀር በጣም ብዙ ጊዜ ከመስጠቱ የተነሳ ምግብ ለመብላት እንኳ እስከ ማይችልበት ደረጃ ድረስ ደርሶ ነበር። እውነት ነው ኢየሱስ እንዲህ ነበር፡ ቅድሚያ ለሕዝቦቹ ይስጣል፣ ሕዝቡን ያገለግላል፣ ሕዝቡን ይረዳል፣ ሕዝቡን ያስተምራል፣ ሕዝቡን ይፈውሳል። ምግብ የሚበላበት ሰዓት እንኳን አልነበረውም። በእዚህም የተነሳ ዘመዶቹ ኢየሱስን ቤቱ ወደ ሚገኝበት ወደ ናዝሬት ይዘውት ለመሄድ ይወስናሉ። ዘመዶቹ ኢየሱስ ወደ ሚገኝበት ስፍራ ከደረሱ በኃላ ሰው ልከውበት አስጠሩት። “በዙሪያው የተቀመጡ ብዙ ሰዎችም፣እነሆ፤ እናትህና ወንድሞችህ ውጭ ይፈልጉሃልአሉት (ማርቆስ 3፡32)። እርሱም መልሶ፣ “እናቴ ማን ናት ወንድሞቼስ እነማን ናቸው?” በማለት መለሰላቸው። በዙሪያው ወደ ተቀመጡትም በመመልከት፣ እንዲህ አለ፤ “እናቴና ወንድሞቼ እነዚህ ናቸውየእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ እርሱ ወንድሜ፣ እኅቴ፣ እናቴም ነውና” (ማርቆስ 3፡33-35) በማለት ይመልስላቸዋል። ኢየሱስ አዲስ ቤተሰብ አቋቋመ፣ በተፈጥሮአዊ ትስስር ላይ ብቻ የተመሠረተ ቤተሰብ ሳይሆን ነገር ግን በእሱ ላይ ባለን እምነት፣ በሚቀበለን ፍቅሩ፣ እኛን በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት አንድ ያደርገናል። የኢየሱስን ቃል የተቀበሉ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆችና እርስ በእርሳቸው ወንድማማቾች ይሆናሉ። የኢየሱስን ቃል መቀበላችን በመካከላችን የወንድማማችነት መንፈስ እንዲኖር ያደርጋል፣ የኢየሱስ ቤተሰቦች እንድንሆንም ያደርገናል። ስለሌሎች መጥፎ ነገር መናገር፣ የሌሎችን ዝና ማበላሸት የሰይጣን ቤተሰቦች እንድንሆን ያደርገናል።

ኢየሱስ የሰጠው መልስ ለእናቱና ለቤተሰቡ አክብሮት እንደ ሌለው የሚያሳይ መልስ ግን አይደለም። ይልቁንም በተለይም ለማሪያም እጅግ የላቀ እውቅና የሰጠ መልስ ነው፣ ምክንያቱም እሷ ፍጹም የሆነች የእግዚአብሔር ደቀ-መዝሙር በመሆን ሁሉንም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመፈጸም የታዘዘች እናት ነበረች። የመንፈስ ቅዱስ ሥራ በእርሷዋና በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ እንዲሁም ዓለምን ወደ አዲስ ሕይወት እንደ ሚለውጥ በመገንዘብ ሁልጊዜ ከኢየሱስ ጋር ኅብረት ፈጥርን መኖር እንድንችል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም በአማላጅነቷ ትርዳን።

የእግዚኣብሔር መልኣከ ማርያምን አበሰራት ከሚለው ጸሎት በመቀጠል ቅዱስነታቸው በሰኔ 03/2010 ዓ.ም ለዓለም ያስተላላፉት ሳምንታዊ መልእክት. . .

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ ቀደም ሲል ያስነበብናችሁን በእለቱ በተነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ መሰረቱን ያደርገ አስተንትኖ ካደርጉ በኃላ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ ለእመቤታችን ለቅድስት ደንግል ማሪያም ከሚቀርቡ የመማጸኛ ጸሎቶች ውስጥ አንዱ የሆነው፣ ጥንታዊ መሠርት የያዘና የጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ሰው መሆን በማስታወስ የሚደገመው የእግዚኣብሔር መልኣከ ማርያምን እንዳበሰራት እና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሰለመሆኑ በሚዘክረው የገብርኤል ብሥራት ጸሎት ከምዕመናን ጋር በመቀባበል ከደገሙ በኃላ ለዓለም ባስተላለፉት ሳምንታዊ መልእክት ቅዱስነታቸው እንደ ገለጹት በቅርብ ጊዜ ውስጥ በአሜሪካ እና በሰሜን ኮሪያ መካከል በሲንጋፖር የሚደርገው ውይይት ገንቢ በሆነ መልኩ እንደ ሚደረግ እና በኮሪያ ልሳነ -ምድር ዘላቂ በሆነ መልኩ ሰላም የሚያረጋግጥ ውይይት እንዲሆን ምኞታቸው እንደ ሆነ ቅዱስነታቸው በሳምንታዊ መልእክታቸው ገልጸው ይህ ውይይት የተሳክ ይሆን ዘንድ ሁላችንም ጸሎታችንን ለእመቤታችን ለቅድስት ማሪያም ልናቀርብ ይገባል ካሉ በኃላ እንደ ተለመደው መልካም እለተ ሰንበት ለሁላችሁም እንዲሆን እመኛለሁ ብለው “እባካችሁን ለእኔ ጸሎት ማድረግ እንዳትረሱ” ካሉ በኃላ ሐዋሪያዊ ቡራኬያቸውን ሰጥተው መሰናበታቸውን ለመረዳት ተችሉዋል።

 

 








All the contents on this site are copyrighted ©.