Social:

RSS:

የቫቲካን ሬድዮ

ከዓለም ጋር የሚወያይ የር.ሊ.ጳጳሳትና የቤተ ክርስትያን ድምጽ

ቋንቋ:

ቤተ ክርስትያን \ ኢትዮጵያ

የመጋቢት 30/2010 ዓ.ም. አስተንትኖ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ካህን በሆኑት በክቡር አባ ግርማቸው ተስፋዬ

የመጋቢት 30/2010 ዓ.ም. ሰንበት ዘትንሳሄ አስተንትኖ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ካህን በሆኑት በክቡር አባ ግርማቸው ተስፋዬ - AP

06/04/2018 16:10

የመጋቢት 30/2010 ዓ.ም. ሰንበት ዘትንሳሄ ቃለ እግዚኣብሔር እና አስትንትኖ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ካህን በሆኑት በክቡር አባ ግርማቸው ተስፋዬ

 

የእለቱ ምንባባት

1ቆሮ. 15፡20-48, 1ጴጥ 1፡1-12

ሐዋ.ሥ. 2፡22-36,

የዩሐንስ ወንጌል 20፡1-18

የእዚህን ዝግጅት ሙሉ ይዘት ከእዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

ኢየሱስ ከሞት ተነሣ

በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን፣ በማለዳ ገና ጨለማ ሳለ፣ መግደላዊት ማርያም ወደ መቃብሩ ሄደች፤ ድንጋዩም ከመቃብሩ መግቢያ ተንከባሎ አየች። ስለዚህም ወደ ስምዖን ጴጥሮስና ኢየሱስ ይወደው ወደ ነበረው ሌላው ደቀ መዝሙር እየሮጠች መጥታ፣ “ጌታን ከመቃብር አውጥተው ወስደውታል፤ የት እንዳኖሩትም አናውቅም” አለቻቸው።

“ከዚያም ጴጥሮስና ሌላው ደቀ መዝሙር ወጥተው ወደ መቃብሩ ሄዱ። ሁለቱም ይሮጡ ነበር፤ ሌላው ደቀ መዝሙርም ጴጥሮስን ቀድሞት ከመቃብሩ ደረሰ። ጐንበስ ብሎ ሲመለከት ከተልባ እግር የተሠራውን ከፈን በዚያው እንዳለ አየ፤ ወደ መቃብሩ ግን አልገባም። ይከተለው የነበረው ስምዖን ጴጥሮስ ደረሰና ወደ መቃብሩ ገባ፤ እርሱም ከተልባ እግር የተሠራውን ከፈን አየ፤ እንዲሁም በኢየሱስ ራስ ላይ ተጠምጥሞ የነበረውን ጨርቅ አየ፤ ይህም ጨርቅ ከከፈኑ ተለይቶ እንደ ተጠቀለለ ነበር። ከዚያም አስቀድሞ ከመቃብሩ የደረሰው ሌላው ደቀ መዝሙር ወደ ውስጥ ገባ፤ አይቶም አመነ፤ ይኸውም ኢየሱስ ከሙታን መነሣት እንዳለበት ገና ከመጽሐፍ ስላልተረዱ ነበር።

ኢየሱስ ለመግደላዊት ማርያም ታየ

ከዚያም በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሰው ወደ የቤታቸው ሄዱ፤ ማርያም ግን ከመቃብሩ ውጭ ቆማ ታለቅስ ነበር፤ እያለቀሰችም መቃብሩን ለማየት ጐንበስ አለች። የኢየሱስ ሥጋ በነበረበት ቦታ፣ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት መላእክት አንዱ በራስጌ ሌላው በግርጌ ተቀምጠው አየች።

እነርሱም፣ “አንቺ ሴት፤ ለምን ታለቅሻለሽ?” ብለው ጠየቋት። እርሷም፣ “ጌታዬን ወስደውታል፤ የት እንዳኖሩትም አላውቅም” አለች። ይህን ብላ ዘወር ስትል ኢየሱስ በዚያው ቆሞ አየች፤ ኢየሱስ መሆኑን ግን አላወቀችም።እርሱም፣ “አንቺ ሴት፤ ለምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ ትፈልጊአለሽ?”አላት።

እርሷም የአትክልቱ ቦታ ጠባቂ መስሎአት፣ “ጌታዬ፤ አንተ ወስደኸው ከሆነ፣ እባክህ እንድወስደው፣ የት እንዳኖርኸው ንገረኝ” አለችው። ኢየሱስም፣ “ማርያም” አላት። እርሷም፣ ወደ እርሱ ዘወር ብላ በአራማይክ ቋንቋ፣ “ረቡኒ” አለችው፤ ትርጒሙም “መምህር ሆይ” ማለት ነው። ኢየሱስም፣ “ገና ወደ አብ ስላላረግሁ፣ አትንኪኝ፤ ይልቁንስ ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ፣ ‘ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ፣ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዐርጋለሁ’ ብሎአል ብለሽ ንገሪአቸው” አላት። መግደላዊት ማርያምም፣ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጥታ፣ “ጌታን እኮ አየሁት!” አለች፤ እርሱ ያላትንም ነገረቻቸው።

 

የመጋቢት 30/2010 .. ሰንበት ዘትንሳሄ አስትንትኖ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ካህን በሆኑት በክቡር አባ ግርማቸው ተስፋዬ

 

በክርስቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም መልካም ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ እንኳን ለበዓለ ትንሣኤው በሰላምና በጤና አደረሳችሁ፡፡-  - ዛሬ እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት አቆጣጠር መሠረት የእምነታችን መሠረት የሆነውን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ከሞት መነሣት በታላቅ ድምቀት እናከብራለን። ይህንንም ዕውነታ እንደናይና እንድንመሠክር ዕድሜን ጤናን ሰላምን የሰጠን እግዚአብሔር ኣምላክ ሥሙ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የተመሰገነ ይሁን!!

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በቆሮንጦስ መልእክቱ ሞት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ይዞ ሊያስቀረው ኣለመቻሉንና ይህ ደግሞ ለእኛም ከሞት በኃላ ተነስተን የክብሩ ተካፋዬች እንደምንሆን የሚያበስረንና ትልቅ መንፈሳዊ ስንቅ ሰንቀን ወደፊት እንድንጓዝ የሚያደርገን የተስፋ ቃል መሆኑን ያስረዳናል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ደምስሷል፣ መቃብር ፈንቅሎ በመነሳቱ ምክንያት ሞትን ድል ነስቷል፤ ስለዚህም ሞት በእኛ ላይ ምንም ዓይነት ሥልጣን የለውም።

የሞት መውጊያ የሆነ ኃጢያት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል፣ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደም ተደመስሷል፣ ራሱም ሞትም ቢሆን በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ ድል ተነስቷል፡፡ ስለዚህ ሞት ምን ጊዜም ቢሆን አያስፈራንም፡፡ በኣዳም ኃጢኣት ምክንያት የሰው ልጆች ሁሉ የኣዳምን ኃጢኣት ተላብሰው ቢወለዱም በዚሁ ኃጢኣት በኩል ሞት የሰው ልጆች ዕጣ ፈንታ ቢሆንም ዛሬ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ ኣማካኝነት ኃጢኣታችን ሁሉ ተደመሰሰ ከዘለዓለማዊ ሞት ወደ ዘለዓለማዊ ሕይወት ተሸጋገርን። በኣሮጌው ኣዳም ምክንያት ኃጢኣትና ሞት ወደ እኛ ቢጠጉም ዛሬ በኣዲሱ ኣዳም ምክንያት ደግሞ ከእኛ ርቀዋል። 

ዛሬ እኛ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ አዲስ ሕይወት አግኝተናል፡፡  ኃጢያታችን ሁሉ ተደምስሷልና፣ ሞት የሚባል ቃል ሊያስፈራን አይችልም፣ እንደውም በአንፃሩ ሞት የአዲሱ ዘለዓለማዊ ሕይወት መጀመሪያ  ነውና ይበልጥ ደስተኞች ሊያደርገን ይገባል፡፡ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች በፃፈው መልዕክት ምዕራፍ 6፡6 ላይ እንደሚለው ዛሬ የኃጢኣታችን ሥጋ ይሻር ዘንድ ኣሮጌው ሰውነታችን ከክርስቶስ ጋር ኣብሮ ተሰቅሎኣል ከክርስቶስ ጋር ኣብሮ ተቀብሯል ስለዚህም ዛሬ በእርሱ ደም የታጠብን ሁሉ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ በኩል ኣዲስ ፍጥረት ሆነናል ኣዲስ መንፈሳዊ ኃይል ተሞልተናል።

እኛ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠንን ህይወት ጠብቀን በመኖራችን ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ብለን በክርስቶስ ስቃይ መሳተፋችን በመጨረሻ የክርስቶስ ክብር ተካፋዬች ያደርገናል፡፡ የቆሮንጦስ ሰዎች ሰው ሞቶ ብስባሽ ከሆነ በኃላ እንዴት ይነሣል ይላሉ? ጌታችን ኢየሱስ ክርስትስ ይህንን ኣስተሳሰብ በቃሉም በተግባሩም ሽሮታል፡፡

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ትንሿ የስንዴ ፍሬ እንኳን እዲሰ ፍሬን እንድትሰጥ መሞት እንደሚገባት ይናገራል፡፡ በትንሿ የስንዴ ዘር የዚህን ዓይነት ምሥጢር ካለ በእኛማ እንዴት የበለጠው ኣይሆንም እያለ ያስተምራቸዋል፡፡ ከስንዴ ዘር ይልቅ  አዲስ ያቆጠቀጠው የስንዴው ተክል የከበረ እንደሆነ ሁሉ እኛም በኃጢያት ምክንያት ከሞተው ከአሮጌው ሰውነታችን ይልቅ ዛሬ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ያገኘነው አዲሱ ሕይወት እጅግ የከበረው ነው፡፡ ይህንን አዲሱን አካል፣ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደም የከበረውን አካል ጠብቀን መኖር ከቻልን በእርግጠኝነት የክብሩ ተካፋዬች እንሆናለን፡፡

ቅዱስ ሐዋርያ ጴጥሮስ በልዕክቱ እግዚአብሄር መረጠን፣ እግዚአብሔር ቀደሰን፣ ይህ የመረጠንና የቀደሰን መንፈቅ ቅዱስ በእግዚአብሄር ፊት ደግሞ ነቀፋ የሌለብን ቅዱሳኖች ሆነን እንድንገኘ ይረዳናል ይላል፡፡ ቅዱሳን ሆነን እንድንገኝ ደግሞ ቅዱስ ሕዋርያው ጳውሎስ በዕብራውያን መልእክቱ እንደፃፈው “በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስዋትነት ማለትም በደሙ ተረጭተን ነፅተናል” ይላል፡፡ዕብ 9፡13-14

ይህንን ከእድፋችን የነፃንበትን፣ ከኃጢኣታችን የታጠብንበትን፣ ከኃጢያት ባርነት ነፃ የወጣንበትንና ከስይጣን ሰንሰለት የተፈታንበትን ዕለት  ዛሬ እናከብራለን፡፡ እግዘአብሔር አብ መረጠን፣ እግዚአብሔር ወልድ በደሙ ዋጀን፣ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ደግሞ ቀደሰን፡፡ ይህንንም ቅድስና ይዘን ስንጓዝ የክርስቶስ ጸጋና ሰላም ይበዛልናል፡፡  ይህም ማለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለኛ ብሎ የሞተበትም ዓላማ ተሳክቷል የሰይጣን ዓላማና መቅበዝበዝ ግን ከንቱ ሆኗል ማለት ነው፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት እንደሚነሳ ለደቀመዛሙርቱ ብዙ ጊዜ ገልጾላቸው ነበር፡፡ሐዋርያቶቹ  ይህንን ባያስተውሉና ባይረዱም ጌታችን ኢየስስ ክርስቶስ ግን ከሞት ተነስቶ አዲሰ ሕይወት እንደሰጣቸው ሁሉ ለእኛም ለእያንዳንዳችን በዚህ ዕለት አዲሰ ፍጥረት የምንሆንበትን ፀጋ ይሰጠናል።

የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት መነሳት በኦሪት መፃህፍትም በብዙ ቦታዎች ተጠቅሷል ለምሳሌም ያህል ትንቢተ ኢሳ. 53፡10-12. “ነፍሱን ስለ ኃጢያት መስዋዕት ካደረገ በኃላ በአዲስ ሕይወት ይነሳል፡ ይላል” ትንቢተ ሆሴዕ. 6፡1-2 “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በ3ኛው ቀንም ከሞት ያስነሣናል በደሙ ይፈውሰናል፣ ከህመማችንም ይጠግነናል በፊቱም በሕይወት እንኖራለን ይላል” መዝ. 16፡10 ቅዱስ ዳዊት “ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትተወውም” ይላል፡፡

ይህ ሁሉ ትንቢት ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት መነሳት በኦሪት መጽሐፍ ተፅፎ እያለ ሐዋርያቶቹም ሆኑ የሙሴ ሕግ መምህራን ሊረዱት ኣልቻሉም አንደውም በእርሱ ከሞት መነሳት ግራ ተጋብተው ነበር፡፡ ለዚህ ነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  «መስማትን ትሰማላችሁ ግን አታስተውሉም፣ ማየትንስ ታያላችሁ ግን አትመለከቱም እያለ የሚነግረን። ያም ሆነ ይህ ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተናገረው መቃብሩን ፈነቃቅሎ ሞትን ድል ነስቶ ከሞት ተነስቷል፡፡

ይህንን ቃል ነው ወንጌላዊው ዬሐንስ በወንጌሉ የሚያስነብበን፡፡  ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል ነሥቶ ተነስቷል የሚለን፡፡ የእግዚአብሔር ሥም የተመሰገነ ይሁን በእርሱ ሞት እኛም የዘለዓለምን ክብር ተቀዳጅተናል፡፡

የትንሳኤ ምስጥር ሙሉ በሙሉ የክርስትናን ሕይወት የሚያለመልም ሰዎች ሁሉ በዕምነታቸው ጸንተው እንዲቆሙ የሚያደርግ ምድራዊ ሕይወታቸውን በትክክለኛ ግብረገባዊነት እንዲኖሩ የሚያደርግ ዘለዓላማዊ ተስፋን ሰንቀው እንደ እውነተኛ የክርስቶስ ወንድሞችና የእግዚአብሔር ልጆች ሆነው እንዲኖሩ የሚያደርግ  ወደተጠራንበት ወደቅድስና ሕይወት ለመድረስ መንገድ የሚመራ የእግዚአብሔርን ቃል ለማዳመጥና ብሎም ወደ ተግባር ለመቀየር ታላቅ መንፈሳዊ ኃይል የሚያላብስ በደከምን ጊዜ የሚያበረታ ባዘንን ጊዜ የሚያፅናና በወድቅን ጊዜ የሚያነሳ ተስፋ በሌለበት ተስፋን የሚሰጥ በተጣላን ጊዜ የሚያስታርቅ ታላቅ  የእግዚአብሔር ስጦታና ምሥጢር ነው።

ሰለዚህ በዚህ በዓላችን እግዚአብሔር ለተቸገሩት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ አንዲሰጣቸው ሰላም በጎደለበት ሰላምን ፍቅር በጎደለበት ፍቅርን ጥል ባለበት እርቅን እንዲያወድልን ለዓለማችን ለኣሃጉራችን ለኣገራችን ሰላምና መቻቻልን እንዲሰጠን እንለምነዋለን።

በዓላችንን የደስታ፣ የፍቅር፣ የሰላም የመተሳሰብ ያደርግልን፡ ይህ ከበዓለ ትንሣኤው የምናገኘው በረከትና ጸጋ በዚህ በምድር ላይ በምናደርገው የክርስትና ጉዞ የበለጠ ጠንካሮችና ትሑቶች እንዲሁም ታዛዦች እንዲያደርገን የዘውትር ኣጽናኛችንና ኣጋዢኣችን የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የዘውትር ኣማላጅነቷና ጥበቃዋ ከሁላችን ጋር ይሁንልን።

የሰማነውን በልባች ያሳድርልን፡፡

 

 

06/04/2018 16:10