2018-03-30 18:21:00

የቅድመ ሲኖዶስ ስብሰባ ወጣት ተወካዮቶች “ሐቀኛ፣ ደስተኛ እና ሁሉን ወጣት የምታሳትፍ ቤተ ክርስቲያን ታስፈልገናለች!” ብለዋል።


የቅድመ ሲኖዶስ ስብሰባ ወጣት ተወካዮቶች “ሐቀኛ፣ ደስተኛ እና ሁሉን ወጣት የምታሳትፍ ቤተ ክርስቲያን ታስፈልገናለች!” ብለዋል።

በሮም የተሰበሰቡት የዓለም ወጣት ተወካዮቶች ሐቀኛ፣ ደስተኛ እና ሁሉን ወጣት የምታሳትፍ ቤተ ክርስቲያን ማየት እንደሚፈልጉ ገለጹ።

በመጭው ጥቅምት ወር 2011 ዓ. ም. በሮም ለሚካሄደው የካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጠቅላላ መደበኛ ሲኖዶስ ዝግጅት ለማድረግ፣ በሮም ከመጋቢት 10 ቀን እስከ መጋቢት 15 ቀን 2010 ዓ. ም. ድረስ የተሰበሰቡት ዓለም አቀፍ የወጣት ተወካዮች፣ በስብሰባቸው ማጠቃለያ ላይ ባቀረቡት ሃሳብ ደስተኛ፣ ሐቀኛና ሁሉን አሳታፊ ቤተ ክርስቲያንን ማየት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል። የቅድመ ሲኖዶሱ ዝግጅት ስብሰባን በአካል ተገኝተው ከተካፈሉ ከ300 ወጣቶች በተጨማሪ ሌሎች 15,000 ወጣቶች በተለያዩ አገሮች ሆነው ስብሰባውን በማሕበራዊ  ሚዲዎች በኩል ተከታትለዋል። የወጣቶቹ ስብሰባ ዋና ዓላማ በሁኑ ወቅት በመላው የዓለም ወጣቶች ዘንድ የሚነሱ ጥያቄዎች እና የሚቀርቡ አስተያየቶች ግልጽ ውይይት ተደርጎባቸው በሚቀጥለው ዓመት፣ በጥቅምት ወር ላይ በሮም በሚደረገው የካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጠቅላላ መደበኛ ሲኖዶስ ላይ ይቀርባል። ወጣቶቹ ከስብሰባቸው በኋላ የውይይታቸውን ጠቅላላ ፍሬ ሃሳብ የያዘ ሰነድ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት አቅርበዋል።

ወጣቶቹ ከሁሉ አስቀድሞ ሃሳባቸውን፣ አስተያየታቸውንና የተለያዩ ወቅታዊ ጥያቄዎቻቸውን በግልጽ አውጥተው እንዲወያዩባቸው ከመላዋ ቤተ ክርስቲያን የተሰጣቸው ዕድል እጅግ ደስ እንዳሰኛቸው ገልጸዋል። በስብስባቸው ማጠቃለያ ላይ ባቀረቡት ሃሳብ እንደገለጹት፣ ቤተ ክርስቲያን ወጣቶች ለሚጫወቱት ሚና እና መንፈሳዊ ጉዞ ትኩረትን በመስጠት፣ የምታስተምረውን በተግባር የምታሳይ ሕያው ምስክር እንድትሆን ጠይቀዋል። በተጨማሪም እውነተኛ፣ ግልጽ፣ ደስተኛ፣ ተደራሽነት ያላት እና ሁሉን አሳታፊ ቤተ ክርስቲያንን ማየት እንፈልጋለን ብለዋል።

የወጣቶችን ጠቅላላ ሪፖርት የያዘው ሰነድ በሦስት አበይት ሃሳቦች ላይ የተመሠረተ ሲሆን የመጀመሪያው በዛሬው ዓለም ውስጥ የወጣቶች ተግዳሮቶችና ተስፋ ሰጭ እድሎች፣ በሁለተኛ ደረጃ እምነታቸውን በተመለከተ  ጥሪያቸውን ጥበብና ማስተዋል በታከለበት መንገድ በመታገዝ ትክክለኛ ውሳኔ እንዲያደርጉ፣ በሦስተኛ ደርጃ ቤተ ክርስቲያን በበኩሏ ለወጣቶች የምታቀርበውን ሐዋርያዊ እና ማሕበራዊ እገዛዎች የተመለከቱ እንደሆነ ታውቋል። ከወጣቶች የቀርቡት ሃሳቦች ወጣቶች የሚገኙበትን መንፈሳዊ እና ማሕበራዊ ሁኔታ ቤተ ክርስቲያን በሚገባ በመገንዘብ ወደ ፊት ለወጣቶች ማበርከት ያለባት ድጋፍ ምን መምሰል እንዳለበት ሃሳብ በመስጠት  የሲኖዶሱ ብጹዓን ጳጳሳት ለሚያደርጉት ውይይት እገዛ ይሆናል ተብሏል።

ወጣቶቹ ስለ ማንነት ጥያቄ አንስተው በተወያዩበት ርዕስ ላይ እንደገለጹት፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የአንድ ቤተ ሰብ ወገን እንደመሆናችን፣ የሚሰጠን ትኩረት እገዛ፣ በያለንበት መንፈሳዊም ሆነ ማሕበራዊ የኑሮ ደረጃ ላይ ብርታትን በመስጠት የሚያነቃቃ፣ እውነተኛ ተደራሽነት ያለውና፣ ኑሮአቸውን ለማሻሻል የሚያስችል መሆን አለበት ብለዋል። እምነት እንደ ግል ጉዳይ ቢታይም የቤተ ክርስቲያን ተደራሽነት ለግለ ሰቦች ብቻ ሳይሆን በቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ማሕበራት ተደራጅተው የሚጓዙ በርካታ እንቅስቃሴዎች ስለሚገኙ አስፈላጊው ትኩረት እንዲሰጣቸው አሳስበዋል። ወጣቶች በብዙ አካሄዳቸው የሚሳሳቱ ቢሆኑም ቤተ ክርስቲያን ይቅር ባይ በመሆን ከስሕተት መንገድ የምትመልስ መሆን እንዳለባት አሳስበዋል።

ወጣቶቹ በውይይታቸው መካከል አንስተው ከተወያዩባቸው ርዕሶች መካከል፣ የወጣቶች ስነ ጾታዊ ግንኙነት እውቀት፣ በጎጂ ሱሶች መጠመድ፣ በጋብቻ መካከል የሚፈጠሩ ችግሮች፣ የቤተሰብ መለያየት፣ ማሕበራዊ ሕይወት የሚያጋጥሙት ቀውሶች፣ የተደራጁ ወንጀሎች፣ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ አመጽ፣ ሙስና፣ የሠራተኛን ጉልበት መበዝበዝ፣ በሴቶች ላይ የሚደርስ ጾታዊ ጥቃት፣ የአካባቢ ጥበቃ እና ቤተ ክርስቲያን አሳታፊ፣ ይቅር ባይና ርህሩህ ስለ መሆን የሚሉ ይገኙባቸዋል። የወደ ፊት ሕይወታቸው በፍርሃት የተዋጠ፣ በራስ መተማመን የጠፋበትና ተስፋ የመቆረጥ አዝማሚያ ያለበት ቢሆንም በቤተ ክርስቲያን ማሕበራዊ አስተምሕሮ በመመራት፣ የተሻለ ዓለምን በጋራ ለመገንባት የሚያስችል ዕድል ማግኘት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል። ሰላም የነገሠበት፣ ለፍጥረታት ደሕንነት ዋስትናን የሚሰጥ፣ ዘላቂ የኤኮኖሚ እድገት ያለበትን ዓለም ማየት እንደሚፈልጉ ገጸዋል። ጦርነት እና አመጽ ባሉባቸው አገሮች ውስጥ ለሚገኙ ወጣቶች፣ ሰላም የሚወርድበትን፣ የአስተዳደር ብልሹነት የሚያበቃበትን፣ በአየር ለውጥ ምክንያት የሚደርሱትን አደጋዎች ለማስወግድ በርትቶ መሥራትን፣ የማሕበራዊ ኑሮ አለመመጣጠን መቀነስን፣ በጸጥታ ማስከበር ሥራም ከሕብረተ ሰቡ ጋር በሕብረት በመሥራት ተስፋን የሚሰጡ የሰላም ጥረቶችን ማድረግ እንደሚፈልጉ ገጸዋል።

ወጣቶች ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር ስላላቸው ግንኙነት በተመለከተ፣ የዘመኑ ቴክኖሎጂ በአንዳንድ ወጣቶች መካከል ያለውን ግንኙነት መጨመር የበኩሉን እገዛ እንዳደረገ እና በማድረግ ላይ እንዳለ የሚታመን ቢሆንም ፊት ለፊት ሊሆን የሚገባውን ግንኙነት በማደናቀፉና ሌላው ቀርቶ ከእግዚብሔርም ጋር ያለውን ግንኙነት በመቀነስ በሕይወታቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖዎችን እያስከተለ መሆኑን ጠቅሰዋል። በተለይም በማሕበራዊ ሚዲያዎች በኩል በመሰራጨት ሰብዓዊ ክብርን የሚያሳጡ ወሲባዊ ምስሎች ወጣቶች ስለ ጾታዊ ግንኙነት በሚገባ ሊያውቁ የሚገባቸውን እውነት በመሰወር ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ እየመራቸው እንደሆነ ገልጸዋል። የዓለም ወጣቶች ማሕበራዊ ሚዲያዎችን በስፋት በመጠቀም ከዕድሜ እኩያዎች ጋር የሚያደርጉት ግንኙነት ከፍተኛ ነው ብለዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የማሕበራዊ ሚዲያን በሚጠቀሙ እና በማይጠቀሙ ወጣቶች መካከል ከፍተኛ የባሕርይ እና የአመለካከት ልዩነት እንደሚታይ በመረጋገጡ ይህ ደግሞ ወዳልተጠበቀ አቅጣጫ እንዳያመራ የማሕበራዊ ሚዲያን አጠቃቀን በተመለከተ ግንዛቤን መስጠት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

የስብሰባው ተሳታፊ ወጣቶች ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ለማወቅ ከፍተኛ ምኞት እንዳላቸው ተናግረው ይህን እውን ለማድረግ እምነታቸውን በእውነትና በተግባር የሚመሰክሩ፣ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያላቸውን ግንኙነትና ፍቅር በግልጽ በማሳየት፣ ሌሎችንም ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ የሚያመጡና የሚያንጹ ምዕመናንን ማየት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል። ይህን የመሰለ ምስክርነት ወጣቶችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት በሚገባ ለማወቅ ያግዛል ብለው ቅዱሳት መጽሐፍትን ዘወትር ማንበብ ተጨማሪ እገዛ ይሆናል ብለዋል።

በርካታ ወጣቶች እምነትን የግል እንጂ የጋራ እሴት እንዳልሆነ ሲያስቡ ሌሎች ደግሞ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ  ከሌሎች ምእመናን ጋር በመሆን እምነትን ማሳደግ እንዲችሉ ቤተ ክርስቲያን እንድታግዛቸው ጠይቀዋል። በሌላው የዓለማችን ክፍሎች፣ በተለይም በአፍሪቃ፣ በደቡብ አሜሪካ እና በእስያ እምነትን እንደጋራ መንፈሳዊ እሴት በመውሰድ፣ በተለያዩ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ተደራጅተው በቤተ ክርስቲያናቸው ውስጥ የተለያዩ አገልግሎቶችን እየሰጡ መሆናቸውን ገልጸዋል። ወጣቶቹ በስብሰባቸው ማጠቃለያ ሰነድ ላይ እንደገለጹት በብዙ የዓለማችን ክፍሎች የወጣቱ እምነት ከመዳከሙ የተነሳ ከቤተ ክርስቲያን በመራቅ ላይ ይገኛሉ ብለው  ከቤተክርስቲያን የሚርቁበትን ምክንያት ለይቶ ማወቅ ለወጣቶች መንፈሳዊ ሕይወትና ለእምነታቸው አስፈላጊ እንደሆነ ጠቅሰው ወጣቶች ከቤተክርስቲያን የሚርቁበት ዋናው ምክንያት አድልዎ፣ ተደማጭነትን ማጣት እና ሐሜት ናቸው።

ክርስቲያኖች የእግዚአብሔር ሕያው ምስክሮች ቢሆኑም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ በጣም እየተዳከመ መጥቷል። የወጣቶች እምነት ዋና መለያው ቶሎ ብለው በፍቅርና በደስታ መማረካቸው ነው። ቤተ ክርስቲያን ስህተቶችዋን በማመን ለስሕተቶቸዋም ይቅርታን የምትጠይቅ መሆን አለባት። ወጣቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚሳተፉበት የሥራ ድርሻ እንዲሰጣቸው፣ በተለይ ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚያበረክቱት አገልግሎት እውቅናን ማግኘት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።  

እኛ ወጣቶች ጥሪያቸውንን፣ ጥበብና ማስተዋል በተሞላበት መንገድ ለይተን ለማወቅ ጥረት በምናደርግበት ወቅት የወንጌልን መልእክት በተግባር እየኖሩ የሕይወት ምስክርነት የሚሰጡ ምእመናንን ማየት እንፈልጋለን። በዓለም ዙሪያ ቤተ ክርስቲያንን በታማኝነት እያገለገሉ፣ ጽድቅንና ቅድስናን ዘወትር በመፈለግ፣ በሌሎች ላይ ለመፍረድ ሳይቸኩሉ ነገር ግን ሌሎችን በመምከር፣ በማነጽና በመርዳት፣ የወጣቶችንም ጥያቄ በማዳመጥ፣ መሪ መሆን የሚችሉ ሰዎችን እገዛ እንፈልጋለን።    

ቤተ ክርስቲያን በሕጻናት ላይ ላደረሰችው ጾታዊ ጥቃቶች፣ በሃብትና በንብረት አያያዝ ላይ በፈጸመችው ስሕተት ተጸጽታ ይቅርታን መጠየቅ ይኖርባታል። ዘመናዊ የብዙሃን መገናኛ አጠቃቀምን በትክክል በማወቅ፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለሚነሱ አከራካሪ ርዕሶች ለምሳሌ ስለ ግብረ ሰዶማዊነት፣ ስለ ስነ ጾታ እና ሌሎችንም ርዕሶች ለምእመናን ግልጽ አድርጋ ማስረዳት መቻል አለባት። ለወጣቶች ሃላፊነትን በመስጠት ውሳኔ ሰጭ እንዲሆኑ ማዘጋጀት ያስፈልጋል።

ቤተ ክርስቲያን ሰዎች በብዛት በሚገኙባቸው በስፖርት ማዘወተሪያ ቦታዎች፣ በመዝናኛ ፓርኮች፣ ማሕበራዊና ባሕላዊ በዓላት በሚከበሩባቸው ሥፍራዎች በመገኘት ምስክርነትን መስጠት ያስፈልጋል። በመዝናኛ ስፍራዎች ብቻ ሳይሆን፣ በሆስፒታሎች፣ በሕጻናት ማሳደጊያዎች፣ በጦርነት በተጠቁ ሥፍራዎች፣ በማረሚያ ቤቶች፣ የተለያዩ ችግሮች ባሉባቸው ስፍራዎች በመገኘት የወንጌልን መልካም ዜና ማብሰር ያስፈልጋል። ይንን አገልግሎት ፍሬያማ ለማድረግ በስፍራው በአካል በመገኘት ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎችንም መጠቀም ያስፈልጋል።

 

 








All the contents on this site are copyrighted ©.