2018-03-23 15:44:00

ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮ በስብከታቸው “እግዚኣብሔር ልክ እንደ እናት እና አባታችን ይወደናል” ማለታቸው ተገለጸ።


ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በትላናትናው እለት ማለትም በመጋቢት 13/2010 ዓ.ም. በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ካህናት፣ ደናግላን እና ምዕመናን በተገኙበት ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት እንደ ገለጹት ወደ ምጢረ ንስሐ መሄድ ማለት የቆሸሸውን ልብሳችንን ለማሳጠብ ወደ አንድ የልብስ ንጽህና ጣቢያ እንደ ምንሄድ ዓይነት ከቆሸሸው ሕይወታችን ለመንጻት ሳይሆን በእግዚኣብሔር በሞገስ የተሞላ የፍቅር እቅፍ ውስጥ ለመግባት ነው ማለታቸው ተገለጸ።

እግዚኣብሔር ታማኝ በመሆኑ የተነሳ እኛን በፍጹም ሊረሳን አይችልም በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ይህም በደስታ እንድንፈነድቅ ያደርገናል ካሉ በኃላ ወደ ሕማማት ሳምንት እየቀረብን ባለንበት በአሁኑ ወቅት ቤተ ክርስቲያን ታማኝ በሆነው በእግዚኣብሔር ፍቅር ላይ እንድናሰላስል ትጋብዘናለች ብለዋል። በእለቱ በቀዳሚነት ከኦሪት ዘፍጥረ 17:3-9 ላይ ተወስዶ በተነበበው የመጀመሪያ ምንባብ ላይ በተጠቀሰው እና “እግዚኣብሔር ለአብራሃም የገባውን ቃል ኪዳን ሁል ጊዜም ቢሆን ያስታውሳል” የሚለውን በማስታወስ ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ምንም እንኳን እኛ በኃጢኣት እና በጣዖት ተተብትበን የምንኖር ቢሆንም ቅሉ ነገር ግን ይህ እግዚኣብሔር ለአብርሃም የገባው ቃል ኪዳን በዘመናችን ታሪክ ውስጥ ተጠብቆ ይኖራል ብለዋል።

እግዚኣብሔር ለእኛ ያለው ፍቅር አንድ እናት እና አንድ አባት ለልጆቻቸው የሚያሳዩት ዓይነት ፍቅር መሆኑን በመገልጽ ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው በእርግጥ ጌታ ለእኛ እጅግ ጥልቅ የሆነ ፍቅር እንዳለው እና የገባልንን ቃል ኪዳን በፍጹም እንደ ማይረሳ ቅዱነታቸው ጨምረው ገልጸዋል።  ይህንን በተመለከተ የሚከተለውን በለዋል . . .

“እግዚኣብሔር ለእኛ ያለው ፍቅር ልክ አንድ እናት ለልጇ እንዳላት ዓይነት ፍቅር ነው። እግዚኣብሔር እኛን በፍጹም አይረሳንም። በፍጹም! ሊረሳንም በፍጹም አይችልም፣ ለገባልን ቃል ኪዳን ታማኝ ነው። እኛ ስለራሳችን ‘የእኔ ሕይወት በጣም መጥፎ የሆነ ሕይወት ነው. . .እኔ በእዚህ ዓይነት ችግር ውስጥ እገኛለሁ፣ እኔ ኃጢኣተኛ የሆንኩ ሰው ነኝ’. . .ወዘተ ልንል እንችል ይሆናል። እርሱ ግን ስለ አንተ ወይም ስለ አንቺ በፍጹም አይረሳም ምክንያቱም እርሱ ለአንተ ወይም ለአንቺ ያለው ፍቅር ልክ አንድ አባት እና እናት እንዳልቸው ዓይነት ውስጣዊ ፍቅር ለእኛ ስላለው ነው”።

ሰለእዚህም እግዚኣብሔር ለቃሉ ያለው ታማኘነት እኛ ደስተኞች እንድንሆን ያደርገናል በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ልክ እንደ አብራሃም እኛም በእዚህ ተስፋ ምክንያት በደስታ እንፈነድቃለን ያሉት ቅዱስነትቸው እያንዳንዳችን ታማኝ አለመሆናችንን በሚገባ ብናውቅም እግዚኣብሔር ግን ለቃሉ ሁሌም ታማኝ ነው ብለዋል። በእዚህ ረገድ ይህንን በሚገባ ለመረዳት በሉቃስ ወንጌል 23፡39-43 ላይ የተጠቀሰውን ኢየሱስ በተሰቀለበት ወቅት ከእርሱ ጋር ተሰቅለው የነበሩ ከሁለቱ ወንጀለኞች መካከል አንዱ “ጌታ ሆይ በመነግሥትህ አስታውሰኝ” ያለውን ሰው ታሪክ ማስታወስ እንደ ሚገባ ቅዱስነታቸው ገለጸው ይህንን በተመለከተ ደግሞ የሚከተለውን በለዋል . . .

“እግዚኣብሔር በመሆኑ የተነሳ ራሱን ሊክድ፣ እኛንም ሊክደን አይችልም፣ እግዚኣብሔር ፍቅሩን መካድ በፍጹም አይችልም፣ እግዚኣብሔር ሕዝቡን መካድ በፍጹም አይችልም፣ በአጠቃላይ ሊከደን አይችልም ምክንያቱም ለእኛ ከፍተኛ የሆነ ፍቅር ስላለው ነው። ይህም የእግዚኣብሔርን ታማኝነት ያሳያል። እኛ ወደ ምስጢረ ንስሐ በምንቀርብበት ወቅት ሁሉ እባካችሁን ልክ ወደ አንድ የልብስ ንጽሕና መስጫ ጣቢያ በመሄድ የቆሸሸውን ልብሳችንን እንደ ማሳጠብ አድርጋችሁ እንዳትመለከቱ። በፍጹም። ወደ ምስጥረ ንስሐ የምንሄድበት ዋነኛው ምክንያት የእዚህን ለቃሉ ታማኝ የሆነውን እና ሁል ጊዜ ቆሞ የሚጠብቀንን የእግዚኣብሔር ፍቅር ለመቀበል ነው።

በእለቱ ከዩሐንስ ወንጌል 8፡51-59 ላይ ተወስዶ በተነበበው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ “አይሁዳዊያን የኢየሱስን ትንሳኤ እውነታ ለማደምዘዝ በማስብ ድንጋይ አንስተው ኢየሱስን ሊወግሩት እንደ ፈለጉ በሚገልጸው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ ተመርኩዘው እና የእለቱ ስብከታቸው ማጠቃለያ ይሆን ዘንድ በማሰብ የሚከተለውን ብለዋል “እርሱ ታማኝ ነው፣ እርሱ ያውቀኛል፣ እርሱ ይወደኛል። በፍጹም ብቻዬን አይተወኝም። እጄን ይዞ ያሻግረኛል። ታዲያ ምን ማድረግ ይኖርብኛል? በተስፋ ተሞልቼ መፈንደቅ ይኖርብኛል። በተስፋ ፈንድቁ ምክንያቱም እግዚኣብሔር እንደ እናት እና አባት ሆኖ ስለ ሚወድህ ነው” ካሉ በኃላ ለእለቱ ያዘጋጁትን ስብከት አጠናቀዋል።

 








All the contents on this site are copyrighted ©.