2018-02-16 09:12:00

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ከእግዚአብሔር ቃል የሚገኘውን ሃብት መጋራት የምዕመናን መንፈሳዊ መብት እንደሆነ አስገነዘቡ።


ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ከእግዚአብሔር ቃል የሚገኘውን ሃብት መጋራት የምዕመናን መንፈሳዊ መብት እንደሆነ አስገነዘቡ።

ቅዱስነታቸው ይህን ያስገነዘቡት በተለመደው የዘወትር ረብዕ ለምዕመናን በሚያሰሙት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምሮ ወቅት እንደሆነ ታውቋል። በዕለቱ የተነበበውን የወንጌል ክፍል በማስታወስ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ማዳመጥና በሙላት መቀበል የምዕመናን መንፈሳዊ መብት እንደሆነ አስረድተዋል። መስዋዕተ ቅዳሴን የሚካፈል እያንዳንዱ ምዕመን በዕለቱ የሚነበበውን የእግዚአብሔር ቃል በሙላት ተቀብሎ የማንበብ፣ የመረዳትና በስብከትም ወቅት የሚቀርቡ የማብራሪያ አስተንትኖችን የመክታተል ሙሉ መብት አለው ብለዋል። ቀጥሎም በዕለቱ በተነበበው የወንንጌል ቃል ላይ ስብከት ከተደረገ በኋላ፣ አጭር የጸጥታ ጊዜን በመውሰድ ማስተንተን ያስፈልጋል ብለዋል።

በመቀጠልም በመስዋዕት ቅዳሴ መካከል በሚደገመው እና የጋራ ጸሎት በሆነው የሐዋርያት ጸሎተ ሐይማኖት በመሳተፍ በዕለቱ በተነበበው የእግዚአብሔር ቃል ላይ ምዕመናን ያላቸውን እምነት በጋራ ምላሽ ይሰጣሉ። ቅዱስነታቸው ይህን ሲያስረዱ እምነት ከመስማት ጋር ምን ያህል ግንኙት እንዳለው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እምነት የሚመጣው ከመስማት ነው ያለውን መልዕክት አስታውሰዋል። በተነበበው የእግዚአብሔር ቃል ማመን ወደ ቅዱስ ምስጢራት ስለሚመራን የሐዋርያት የእምነት ጸሎት በቅዱስ ቃል እና በቅዱስ ቁርባን ስርዓት መካከል የጠበቀ ግንኙት እንዲኖር ያደርጋል ብለዋል።

በምስዋዕተ ቅዳሴ መካከል ከምናቀርበው የሐዋርያት ጸሎተ ሐይማኖት ቀጥሎ ከምዕመናን በኩል የሚቀርበው ጠቅላላ ጸሎት ነው። የምዕመናን ጠቅላላ ጸሎት የተባለበትን ምክያት ቅዱስነታቸው ሲያስረዱ፣ የመላዋ ቤተ ክርስትያን እና የዓለምን ጥያቄ ስለሚያጠቃልል ነው ካሉ በኋላ የምዕመናን ጸሎት፣ ምዕመናን በጥምቀት የተቀበሉትን ክህነታዊ የእግዚ አብሔር ሕዝብ ጥሪን ያስታውሳል ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ኢየሱስ ክርስቶስ በተናገረው ቃል ላይ በማስተንተን፣ ለእኔ ብትታዘዙ፣ ቃሌንም ብትሰሙ፣ የምትጠይቁትን ሁሉ ታገኛላችሁ። ቅዱስነታቸው ይህን የማናደርግበት እና የምንጠይቀውን የማናገኝበት ዋናው ምክንያት እምነታችን በጣም የተወሰነ በመሆኑ ነው ብለዋል። በመስዎዕተ ቅዳሴ ወቅት ወደ እግዚአብሔር ዘንድ በጋራ በምናቀርበው ጸሎት ላይ እምነት እንዲኖረን፣ ጸሎታችን በሙሉ እምነት የተደገፈ እንዲሆን አሳስበዋል። በመስዋዕተ ቅዳሴ ሰዓት ከምዕመናን የሚያቀርቡት ጸሎቶች የግል ፍላጎቶችን ወይም ጥያቄዎችን የሚያንጸባርቁ ሳይሆን የመላው ዓለም ምዕመናን ፍላጎትን፣ ምኞትንና ጥያቄን   የሚወክል መሆን ያስፈልጋል ብለዋል። በመጨረሻም ቅዱስነታቸው የትናንቱን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምሮአቸውን ሲያጠቃልሉ፣ የምዕመናን ጠቅላላ ጸሎት፣ በመስዋዕት ቅዳሴ ወቅት ለሚነበበው የወንጌል መልዕክት ማጠቃለያ በመሆኑ፣ በዚህም ምዕመናን እግዚአብሔር ለልጆቹ የሚያደርገውን ጥበቃንና ፍቅር በሕብረት ሆነው የሚያስተውሉበት ነው ብለዋል።             








All the contents on this site are copyrighted ©.