2018-02-10 16:53:00

የየካቲት 4/2010 ዓ.ም. ሰንበት ዘ ቅበላ ምንባባት እና አስተንትኖ በክቡር አባ ግርማቸው ተስፋዬ


የየካቲት 4/2010 .. የቅበላ እለተ ሰንበት ምንባባት እና አስተንትኖ በክቡር አባ ግርማቸው ተስፋዬ

 

የእለቱ ምንባባት

ዕብ13፡7-16

የእግዚአብሔርን ቃል የነገሯችሁን መሪዎቻችሁን ዐስቡ፤ የኑሮአቸውን ፍሬ ተመልከቱ፤ በእምነታቸውም ምሰሉአቸው። ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንት፣ ዛሬም ለዘላለምም ያው ነው። በልዩ ልዩ ዐይነት እንግዳ ትምህርቶች አትወሰዱ፤ ልባችን የሚጸናው በጸጋ እንጂ የምግብ ሥርዐት በመጠበቅ አይደለም፤ ይህንን ሥርዐት የሚጠብቁት እንኳ በዚህ አልተጠቀሙም። በድንኳኒቱም የሚያገለግሉ ከዚያ ሊበሉ መብት ያላገኙበት መሠዊያ አለን።

ሊቀ ካህናቱ ስለ ኀጢአት ስርየት የሚሆነውን የእንስሳት ደም ይዞ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ይገባል፤ የእንስሳቱ ሥጋ ግን ከሰፈር ውጭ ይቃጠላል። እንዲሁም ኢየሱስ በራሱ ደም አማካይነት ሕዝቡን ሊቀድስ ከከተማው በር ውጭ መከራን ተቀበለ። ስለዚህ እኛም እርሱ የተሸከመውን ውርደት ተሸክመን ከሰፈር ውጭ ወደ እርሱ እንውጣ። ምክንያቱም በዚህ ቋሚ ከተማ የለንም፤ ነገር ግን ወደ ፊት የምትመጣዋን ከተማ እንጠብቃለን።

ስለዚህ ዘወትር የምስጋናን መሥዋዕት ይኸውም ለስሙ የሚመስክሩ የከንፈሮችን ፍሬ በኢየሱስ አማካይነት ለእግዚአብሔር እናቅርብ። ደግሞም መልካም ማድረግንና ያላችሁንም ከሌሎች ጋር መካፈልን አትርሱ፤ እግዚአብሔር ደስ የሚሰኘው እንደዚህ ባለው መሥዋዕት ነውና።

የእዚህን ዝግጅት ሙሉ ይዘት ከእዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

 

ያዕ 4፡6-17

ነገር ግን ጸጋን አብዝቶ ይሰጠናል፤ መጽሐፍም፣“እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል” ያለው ስለዚህ ነው። እንግዲህ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አስገዙ፤ ዲያብሎስን ተቃወሙት፤ ከእናንተም ይሸሻል። ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ፤ እርሱም ወደ እናንተ ይቀርባል። እናንተ ኀጢአተኞች እጃችሁን አንጹ፤ እናንተ በሁለት ሐሳብ የምትዋልሉ ልባችሁን አጥሩ። ተጨነቁ፤ እዘኑ፤ አልቅሱም። ሳቃችሁ ወደ ኀዘን፣ ደስታችሁም ወደ ትካዜ ይለወጥ። በጌታ ፊት ራሳችሁን አዋርዱ፣ እርሱም ከፍ ከፍ ያደርጋችኋል።

ወንድሞች ሆይ፤ እርስ በርሳችሁ አትወነጃጀሉ፤ ወንድሙን የሚወነጅልና በወንድሙም ላይ የሚፈርድ በሕግ ላይ ክፉ ይናገራል፤ በሕግም ላይ ይፈርዳል። በሕግ ላይ ብትፈርድ ፈራጅ እንጂ ሕግን አድራጊ አይደለህም። ሕግን የሚሰጥና የሚፈርድ አንድ ብቻ ነው፤ እርሱም ሊያድንና ሊያጠፋ የሚችል ነው፤ ነገር ግን በባልንጀራህ ላይ የምትፈርድ አንተ ማን ነህ?

ስለ ነገ መመካት

እናንተ “ዛሬ ወይም ነገ ወደዚህች ወይም ወደዚያች ከተማ እንሄዳለን፤ በእርሷም አንድ ዓመት እንቈያለን፤ እንነግዳለን፤ እናተርፋለንም” የምትሉ እንግዲህ ስሙ። ነገ የሚሆነውን እንኳ አታውቁም። ሕይወታችሁ ምንድን ናት? ለጥቂት ጊዜ ታይቶ ኋላ እንደሚጠፋ እንፋሎት ናችሁ። ይልቁንም፣ “የጌታ ፈቃድ ቢሆን እንኖራለን፤ ይህን ወይም ያንን እናደርጋለን” ማለት ይገባችኋል። አሁን ግን በትዕቢታችሁ ትመካላችሁ፤ እንዲህ ያለው ትምክህት ሁሉ ክፉ ነው። እንግዲህ መልካም የሆነውን ነገር ማድረግ እንዳለበት እያወቀ የማያደርግ ሰው ኀጢአት ያደርጋል።

 

የሐዋ. ሥራ 25፡13-27

ፊስጦስ ከንጉሥ አግሪጳ ምክር ጠየቀ

ከጥቂት ቀንም በኋላ፣ ንጉሥ አግሪጳና በርኒቄ ፊስጦስን እጅ ሊነሡ ወደ ቂሳርያ ወረዱ፤ በዚያም ብዙ ቀን ተቀመጡ፤ ፊስጦስም የጳውሎስን ጒዳይ አንሥቶ ለንጉሡ እንዲህ አለው፤ “ፊልክስ በእስር ቤት የተወው አንድ ሰው እዚህ አለ፤ ወደ ኢየሩሳሌም በሄድሁ ጊዜ፣ የካህናት አለቆችና የአይሁድ ሽማግሌዎች እንድፈርድበት ከሰውት ነበር።

“እኔም፣ ተከሳሽ በከሳሾቹ ፊት ቆሞ ለተከሰሰበት ነገር መልስ ለመስጠት ዕድል ሳያገኝ፣ አሳልፎ መስጠት የሮማውያን ልማድ እንዳልሆነ ነገርኋቸው። ስለዚህ ከሳሾቹ ከእኔ ጋር ወደዚህ በመጡ ጊዜ፣ ጒዳዩን ሳላጓትት በማግስቱ ችሎት ተቀምጬ ያን ሰው እንዲያቀርቡት አዘዝሁ። ከሳሾቹም ተነሥተው በመቆም ሲናገሩ፣ እኔ ያሰብሁትን ያህል ከባድ ክስ አላቀረ ቡበትም፤ ይልቁን ስለ ገዛ ሃይማኖታቸውና ሞቶ ስለ ነበረው፣ ጳውሎስ ግን ሕያው ነው ስለሚለው ሰው፣ ስለ ኢየሱስ ይከራከሩት ነበር። እኔም ይህን ነገር እንዴት እንደምፈታው ግራ ስለገባኝ፣ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ ስለ ዚሁ ጒዳይ እንዲፋረድ ፈቃደኝነቱን ጠየቅሁት። ነገር ግን ጳውሎስ ጒዳዩ በንጉሠ ነገሥቱ እንዲታይለት ይግባኝ ባለ ጊዜ፣ እኔም ወደ ቄሳር እስከምልከው ድረስ እስር ቤት እንዲይ አዘዝሁ።”

አግሪጳም ፊስጦስን፣ “እኔም እኮ ይህ ሰው ሲናገር መስማት እፈልግ ነበር” አለው።

እርሱም፣ “እንግዲያውስ ነገ ትሰማዋለህ” አለው።

ጳውሎስ በንጉሥ አግሪጳ ፊት

በማግስቱም አግሪጳና በርኒቄ በታላቅ ክብር መጥተው፣ ከከፍተኛ መኰንኖችና ከከተማዪቱ ታላላቅ ሰዎች ጋር ወደ መሰብሰቢያው አዳራሽ ገቡ፤ በፊስጦስም ትእዛዝ ጳውሎስ እንዲቀርብ ተደረገ። በዚህ ጊዜ ፊስጦስ እንዲህ አለ፤ “ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፤ እንዲሁም እዚህ አብራችሁን ያላችሁ ሁሉ፤ ይህን ሰው ታዩታላችሁ? በኢየሩሳሌምና እዚህ በቂሳርያም የሚኖሩ አይሁድ ሁሉ፣ ይህ ሰው ከእንግዲህ በሕይወት መኖር አይገባውም በማለት እየጮኹ ለመኑ። እኔም ለሞት የሚያበቃ አንዳች ነገር አለ ማድረጉን ተረዳሁ፤ ሆኖም ወደ ንጉሠ ነገሥቱ ይግባኝ በማለቱ ወደ ሮም ልልከው ወሰንሁ። ነገር ግን ስለ እርሱ ወደ ጌታዬ የምጽፈው የተረጋገጠ ነገር አላገኘሁም፤ ስለዚህም ከተመረመረ በኋላ የምጽፈውን ነገር ለማግኘት ሁላችሁም ፊት በተለይ ደግሞ ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፤ በአንተ ፊት አቀረብሁት፤ ይኸውም አንድ እስረኛ ወደ በላይ ሲላክ የተከሰሰበትን ምክንያት አለመግለጽ ትክክል ስላልመሰለኝ ነው።”

 

 ዬሐ 310-24.

ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “አንተ የእስራኤል መምህር ሆነህ ሳለ እነዚህን ነገሮች አታውቅምን? እውነት እልሃለሁ፤ የምናውቀውን እንናገራለን፤ ያየነውንም እንመሰክራለን፤ እናንተ ግን ምስክርነታችንን አትቀበሉም። ስለ ምድራዊው ነገር ነግሬአችሁ ያላመናችሁ፣ ስለ ሰማያዊው ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ? ከሰማይ ከወረደው ከሰው ልጅ በቀር፣ ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም።ሙሴ በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ፣ የሰው ልጅም እንዲሁ ሊሰቀል ይገባዋል፤ይኸውም በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው ነው።

“በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአልና፤ እግዚአብሔር ልጁን ወደ ዓለም የላከው በዓለም ለመፍረድ ሳይሆን፣ ዓለምን በእርሱ ለማዳን ነው። በእርሱ የሚያምን ሁሉ አይፈረድበትም፤ በእርሱ የማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ፣ አሁኑኑ ተፈርዶበታል። ፍርዱም ይህ ነው፤ ብርሃን ወደ ዓለም መጣ፤ ሰዎች ግን ሥራቸው ክፉ ስለ ነበረ፣ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ወደዱ፤ ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላል፤ አድራጎቱም እንዳይገለጥበት ወደ ብርሃን አይመጣም። በእውነት የሚመላለስ ግን ሥራው በእግዚአብሔር የተሠራ መሆኑ በግልጽ ይታይ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል።”

መጥምቁ ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ መሰከረ

ከዚህ በኋላ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ይሁዳ አገር ሄዱ፤ እዚያም ከእነርሱ ጋር ጥቂት ተቀመጠ፤ አጠመቀም።

በዚህ ጊዜ ዮሐንስም በሳሌም አቅራቢያ ሄኖን በተባለ ስፍራ ብዙ ውሃ ስለ ነበረ፣ ያጠምቅ ነበር፤ ሰዎችም ለመጠመቅ ይመጡ ነበር። ይህም የሆነው ዮሐንስ ከመታሰሩ በፊት ነበር።

 

 

አስተንትኖ በክቡር አባ ግርማቸው ተስፋዬ

በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም መልካም ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ ዛሬ እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት አቆጣጠር ዘቅበላ የተሰኘውን ሰንበት እናከብራለን፡፡

ዛሬም እንደ ወትሮው ሁሉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቀደም ሲሉ በተነበቡት ንባባት አማካኝነት እያንዳንዳችንን ይጐበኘናል፡፡ ያስተምረናል፡፡

በመጀመሪያው ንባብ ቅዱስ ሕዋርያዋ ጳውሎስ ለዕብራዊያን በጻፈው መልእክቱ  እንዲህ ይላል “የእግዚአብሔርን ቃል ያስተማሯችሁን የቀድሞ አባቶቻችሁን አስቡ የኑሮአቸውንም ፍሮ እየተመለከታችሁ በእምነታችሁ ምሰሉዋቸው” ይላል

የእግዚአብሔርን ቃል ያስተማሩን ማናቸው? ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በምድር ላይ ቅን በነበሩ ሰዎች አማካኝነት በነ ሙሴ በነ አሮን እንዲሁም ከዛም በኃላ በተለያዩ ነቢያት አማካኝነት ሕዝቡን ያስተምር ነበር፡፡

ነገር ግን ይህ ሁሉ ትምህርትና ተግሳጽ የሰውን ልብ ሙሉ በሙሉ ሊገዛው ባለመቻሉ በስተመጨረሻ አምላክ ራሱ ሰው በመሆን አስተማረ ከሱም በኃላ እንዲያስተምሩ ሐዋርያቶችን አዘጋጀ በዓለምም ሁሉ እየተዘዋወሩ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እንዲያጠምቁ ላካቸው፡፡

ዛሬ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ እነዚህን አስተማሪዎች አስቡ የደረሱበትንም ቦታ በማሰብ የሚላችሁን ስሙ መንገዳቸውንም ተከተሉ በእምነታችሁም ምሰሉአቸው ይለናል፡፡

እነዚህ የቀድሞ አባቶቻችን ለእግዚአብሔር ፍጹም ታዛዦች ነበሩ ከሁሉ በፊት ቅድሚያ ለአምላካቸው ለፈጣሪያቸው ይሰጡ ነበር በመሆኑም እግዚአብሔርን አከበሩ እርሱም አከበራቸው፡፡

እግዚአበሔር ስለ እነርሱ መሰከረ “እኔ የአብርሃም፣የይስሐቅ፣ የያዕቆብ የሕያዋን አምላክ ነኝ አለ፡፡

ስለዚህ እነዚህ አባቶቸችን የደረሱበትን ቦታ በማሰብ እናንተም በእምነታችሁ የእነርሱን አብነት ተከተሉ ይለናል፡፡ እነርሱ እግዚአበሔር ባመላከታቸው መንገድ ስለተጓዙ እምነታቸውን ጠብቀው ስለኖሩ ስማቸው በሰማይም ሆነ በምድር ሕያው ሆኖ ይኖራል፡፡ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ለዚህ ነው እነርሱን ምሰሉ የሚለን እኛም እንደነሱ በሰማይም ሆነ በምድር ሕያው ሆነን እንድንኖር ነው፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እነዚህ አባቶች ከመፈጠራቸው በፊት ነበር ዛሬም ከኛ ጋር አለ ወደፊትም ይኖራል፡፡ በዕብራውያን መልእክት ቁ8 ላይ ሲነበብ እንደሰማነው “ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ዘለዓለም ያው ነው ይለናል፡፡

እንግዲህ ይህ ጥንትም የነበረ ዛሬም ያለ አምላክ እምነታችን ጠንካራ እንዲሆን  በሰው አምሳል ተፈጥሮ አስተማረን፡፡ የእርሱንም ትምህርት ይዘው እንዲቀጥሉ ሐዋርያቶችን ወደ ዓለም ሁሉ ላከ የእነርሱንም ትምህርትና እምነት እንድንከተል እኛንም በጸጋው ሞላን፡፡

ታዲያ ዛሬ እኛ ይህንን ትምሕርት፣ የእነዚህን ቅዱሳኖች አብነት በመከተል ላይ እንገኛለን ወይስ ደግሞ በራሳችን ስሜትና ፍላጎት ብቻ በመመራት በዓለም ላይ እየተቅበዘበዝን እንገኛለን? ልባችን በእግዚአበሔር ላይ ካልፀና በምንም መልኩ የተረጋጋ ሕይወት ሊኖረን አይችልም እውነተኛ ውስጣዊና ውጫዊ ሰላምሊኖረን አይችልም  “በዚሁ ተመሳሳይ መልዕክት ቁ.9 ላይ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ምን ይላል “ ልዩ ልዩ ዓይነት በሆነ እንግዳ ትምህርት አትወሰዱ ልባችሁ በጸጋ ቢፀና መልካም ነው ይለናል፡፡

ይህንን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረውን ሐዋርያቶችና አባቶች በደማቸው የመሰከሩለትን በአንድ ዓለት ላይ የተመሰረተን እምነት ቅድስት ቤተክርስቲያን ዘወትር ለልጆቿ ታስተምራለች፡፡ ይሕ እምነታችን እንዳያድግ ብሎም ፍሬ እንዳያፈራ በመንገዳችን ላይ ብዙ መሰናክል ይኖራል፡፡

ቅዱስ ሐዋርያው ያዕቆብ ሰይጣን እምነታችን ጽኑ እንዳይሆን በብዙ መልኩ ይፈትነናል ይላል፡፡

እኛም እግዚአብሔርን በተከፈለ ልብ የምንቀርብና በተከፈለ ልብ የምንታዘዝ ከሆነ በሰይጣን ፈተናዎች በቀላሉ እንታለላለን በፈተናውም እንወድቃለን፡፡ 

እነዚህ አባቶቻችን እንዳስተማሩን በትሕትና በሙሉ ልብ ወደ እግዚአብሔር ከቀረብን እምነታችንም ደጸና ከሆነ በጸጋው ይሞላናል፡፡ ጸጋውም በእግዚአብሔር መንገድ ውስጥ እንድንመላለስ ያደርገናል፡፡  የሰይጣንን ሥራ እንድንክድና በእምነታቸንም ጠንክረን እንድንቆም ያግዘናል  ፡፡

ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ እንዲህ ይለናል “መዝ. 51 ትሑት የሆነውንና ለንሰሐ የተዘጋጀውን ልብ እግዚአብሔር አይንቅም” ይላል፡፡

ወንጌላዊው ዩሐንስም በወንጌሉ እንደሚያስተምረን በእግዘአብሔር ያመነ፣ የእርሱንም መንገድ የተከተለ፣ ፈቃዱንም የፈጸመ ለዘለዓለም እንደሚኖር፤ ይነግረናል

ይህንን ያልፈፀመ ግን በተቃራኒው እግዚአብሔር የሰጠውን ጸጋ ወደ ጐን በመተው በራሱ ፈቃድ ከዘለዓለማዊ ሕይወት ራሱን እንዳገለለ ይናገራል፡፡ 

ከእግዚአብሔር ጋር የሚጓዝ ሰው በብርሃን ውስጥ እንደሚጓዝ ይናገራል በብርሃን ውስጥ የሚጓዝ መሰናክል ቢያጋጥመው እንኳ ይህ ብርሃን ስለሚመራው ወደ ጉድጓድ አይወድቅም፡፡  በብርሃን ውስጥ የማይመላለስ ሰው  ብርሃንን የሚፈራ ሰው ነው የሚፈራበትም ምክንያት ውስጡ በኃጢአት ጨለማ ስለተዋጠ ነው ወደ ብርሃን ቢወጣ ስራው የሚታወቅበት ስለሚመስለው ነው፡፡ በዚሁ በዮሐንስ ወንጌል 3፥20 ላይ እንዲህ ይላል ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላል አድራጎቱም እንዳይጋለጥበት ወደ ብርሃን አይመጣም ይላል፡፡   እኛም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠንን እውነተኛ እምነት በጽናት ይዘን ዘወትር በብርሃን ውስጥ መጓዝ እንድንችል ራሳችንን የምንመረምርበት ወቅት ነው፡፡ ስለ ሰው ፍቅር ብሎ ራሱን አሳልፎ የሰጠውን ክርስቶስን በማሰብ   እኛም  ለሌሎች ያለንን የምናካፍልበት ወቅት ነው፡፡ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ ተሳታፊ ለመሆን ራሳችንን በጾም ጸሎት የምንዘጋጅበት ወቅት ነው፡፡ ይህንን የምናደርግ ከሆንን በእርግጥም በብርሃን ውስጥ እየተመላለስን እንገኛለን ማለት ነው ካልሆነም ደግሞ ንስሃ በመግባት ራሳችንን ከጨለማ ወደ ብርሃን እንድናወጣና የብርሃን ጉዞ እንድንጀምር ያስፈልጋል ለዚህም ዘወትር አብራን የምትጓዝ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ታግዘን ጾማችንንም ከእግዚአብሔር ልዩ ጸጋና በረከት የምናገኝበት መንፈሳዊ ሕይወታችንን የምናድስበት ይሁንልን ፡፡

 

 








All the contents on this site are copyrighted ©.