2018-02-10 11:31:00

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ኢራቅን ለመጎብኘት ዝግጁ ቢሆኑም ጊዜው አሁን እንዳልሆነ ተገለጸ።


ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ኢራቅን ለመጎብኘት ዝግጁ ቢሆኑም ጊዜው አሁን እንዳልሆነ ተገለጸ።

የኢራቅ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን ፓትሪያርክ አቡነ ሉዊስ ራፋኤል ሳኮ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ኢራቅ ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ ዝግጁ ቢሆኑም ለጊዜው ሁኔታዎች በኢራቅ ምቹ አለመሆናቸውን ገልጸዋል።

የዚህን ዝግጅት ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ።

ፓትሪያርክ ሉዊስ ራፋኤል ኢራቅ ያለችበትን ሁኔታ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅርብ እንደሚከታተሉ አስረድተዋል። ፓትሪያርክ ሉዊስ ራፋኤል ከቫቲካን ጉብኝታቸው መልስ ባደረጉት ንግግር፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ኢራቅን ለአንድ ቀን እንኳን ጎብኝተው መስዋዕተ ቅዳሴን ለማሳረግ፣ ከሌሎች አብያተ ክርስትያናት ጋር የሕብረት ጸሎት ለማድረግ፣ ከሃይማኖት መሪዎችና ከመንግሥት ባለስልጣናት ጋር ሰላምታን ለመለዋወጥ በማለት የግብዣ ጥሪ ቢቀርብላቸውም በፖለቲካ አለመረጋጋትና በጸጥታ ችግር ምክንያት ጊዜው የተመቻቸ ሆኖ አልተገኘም ብለዋል።

ፓትሪያርኩ በኢራቅ ጦርነትን ሲያካሂድ የቆየው የእስላማዊ መንግሥት ታጣቂ ሃይል ስለተሸነፈ ሕዝቡ ወደ መኖሪያ ሠፈሩ መመለስ ይፈልጋል ብለው በማከልም የተሻለ የጸጥታ ሁኔታ እየታየ በመሆኑ በኢራቅ ሕዝብ መካከል እርቅንና መረጋጋትን ለማምጣት በርትቶ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።

አክራሪነት እና ሽብርተኝነት የክፋት፣ የአመጽን የጦርነት መንገድ በመሆናቸው ምንም የወደፊት መልካም ዕድል የላቸውም ያሉት ፓትሪያርክ ሉዊስ ራፋኤል በኢራቅ አሁንም ችግሮች ቢኖሩም እንደምንሻገራቸው ተስፋ አለ ብለዋል። ከኒኒቨ እና ከሞሱል መኖሪያቸውን ለቅቆ ከተሰደዱት ከ20 ሺህ ቤተ ሰብ መካከል 7 ሺህ ቤተሰብ ብቻ ወደ ቤታቸው የተመለሱ ሲሆን የተቀሩት ደግሞ መኖሪያ ቤታቸው ክፉኛ ስለተጎዳ መመለስ አልቻሉም ብለዋል። በኢራቅ የክርስቲያን ማሕበረሰብ የሆኑት ከቤተክርስቲያን በኩል ዕርዳታ ካልደረሳቸው በቀር ከሌላ ቦታ ዕርዳታ ማግኘት አይቻልም ብለዋል። መንግሥትም ቢሆን በእርዳታ አሰጣጡ ላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ለሺአ፣ ለሱኒት እና ለኩርዶች ነው ብለዋል።

ፓትሪያርክ ሉዊስ ራፋኤል አንስተው ከተወያዩባቸው ርዕሶች መካከል አንዱ የእምነት ነጻነትን በተመለከተ ሲሆን ይህን አስመልክተው ሲናገሩ እምነትን በነጻነት ማካሄድ የሚቻልበት ጊዜ እስከሚደርስ መጠበቅ ያስፈልጋል ብለው በማከልም ክርስትናንም ሆነ የእስልምናን እምነት ሕዝቡ በግድ እንዲቀበል ማድረግ አይቻልም ብለዋል። ከምዕራቡ ለጋሽ ሀገሮች የምናገኘውን እርዳት የሐይማኖት ልዩነት ሳናደርግ ለእያንዳንዱ እርዳታ ፈላጊ ክፍል እናዳርሳለን ብለው ከምዕራቡ ዓለም ክርስቲያኖች በኩል የሞራል፣ የመንፈሳዊ እና ቁሳዊ እገዛ ያስፈልገናል ብለዋል። ኢራቅን መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ቤተ ክርስትያን የበኩልዋን አስተዋጾን ማበርከት እንድትችል ከሌሎች ዕርዳታ ሰጭ ድርጅቶች መታገዝ ይኖርባታል። ፓትሪያርክ ሉዊስ ራፋኤል ሳኮ በኢራቅ የሚገኙ ካቶሊካዊ ምዕመናን ቁጥር ከ 1.5 ሚሊዮን ወደ ግማሽ ሚሊዮን መውረዱንም ተናግረዋል።

የምዕራቡ ዓለም ድጋፍ ያስፈልገናል ያሉት ፓትሪያርክ አቡነ ሉዊስ ራፋኤል ሳኮ፣ በኢራቅ ክርስቲያኖች ሲሰቃዩ እና ለሰማዕትነት ሲበቁ የምዕራቡ ዓለም ክርስቲያኖች እምነታቸውን መለስ ብለው መመልከት ይኖርባቸዋል ብለዋል። ለእምነቱ ሲል ራሱን ለሞት የሚዳርግ ማነው በማለት ጥያቄ አቅርበው፣ የምዕራቡ ዓለም ክርስትያኖች ድምጻቸውን የተነፈጉትን የምሥራቁ ዓለም ክርስትያኖች በመወከል ድምጻቸውን ማሰማት ያስፈልጋል ብለው የዓለም አቀፉ ማሕበረ ሰብም ድምጹን ቢያሰማ ለኢራቅ ሕዝብ ትልቅ እገዛ እንደሚሆን ሲር ለተባለ የቤተ ክርስቲያን የዜና አገልግሎት ገልጸዋል።                   

 








All the contents on this site are copyrighted ©.