Social:

RSS:

የቫቲካን ሬድዮ

ከዓለም ጋር የሚወያይ የር.ሊ.ጳጳሳትና የቤተ ክርስትያን ድምጽ

ቋንቋ:

ቤተ ክርስትያን \ ኢትዮጵያ

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ካቶሊካውያን ዘኢትዮጵያ የ2010 ዓ.ም የዓብይ ጾም መልእክት

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ካቶሊካውያን ዘኢትዮጵያ የ2010 ዓ.ም የዓብይ ጾም መልእክት - RV

10/02/2018 17:06

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ  ሊቀ ጳጳሳት ካቶሊካውያን  ዘኢትዮጵያ የ2010 ዓ.የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዐብይ ጾም መግቢያ በማስመልከት ለመላው ምዕመናን ያስተላለፉት መልዕክት፡፡

 

በስመ አብ ወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

 

የተወደዳችሁ ብፁዓን ጳጳሳት

ካህናት ገዳማዊያን /ያት

የተወደዳችሁ ወንድሞቼና እህቶቼ እንዲሁም  በጐ ፍቃድ ያላችሁ ሁላችሁ የጌታ ሠላም ከእናንተ ጋር ይሁን፡፡

ከሁሉም በማስቀደም እንኳን ለ2010 ዓ.ም የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዐብይ ጾም  ዕድሜና ጊዜ ሰጥቶን ይህንን ዕለት እንድናይ ላደረገን ቸሩ አምላካችን ክብርና ምስጋና  ይሁን፡፡  

ጾም በሁሉም እምነቶች  ትልቅ መንፈሳዊ ዋጋ ይሰጠዋል፡፡ እኛ ክርስቲያኖች ስለምን እንጾማለን? ጥቅሙ ዓላማው ምንድነው? ብለን ስንጠይቅ፤ የምንጾመው ለተለያየ ምክንያት ነው፡፡ ይሄውም  ሰዎች የእግዚአብሔርን ቸርነት፣ ምህረትንና ደግነት ይቀምሱ ዘንድ፤ የበለጠ ወደ እርሱ ይቀርቡ ዘንድ ሰይጣንን ማሸነፍ ይችሉ ዘንድ፤ ሰላም እንዲወርድ እግዚአብሔር ክፉን እንዲያርቅ ከአደጋ እንዲጠብቅ፣   የእግዚአብሔርን ምሪት  ለማግኘት በመሳሰሉት እንጾማለን፡፡

ጾም ለእግዚአብሔርና፡  የእግዚአብሔር ለሆኑ ነገሮች ሁሉ  ቦታ የመስጠት ጊዜ ነው፡፡ ራስን በእግዚአብሔር ትፅዛዛት የማነጽ፣ እውነተኛ የመለወጥ ጊዜ ነው፡፡  ነገር ግን የጠራችሁ እግዚአብሔር ቅዱስ እንደሆነ እናንተም በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፣ እኔ ቅዱስ ስለሆንኩ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ተፅፎአል፡፡ /1ጴጥ1፡15/ ጾም ለተፈጠርንበት ዓላማ ያቆመናል፡፡  የተፈጠርነው  ደግሞ የፈጠረን እግዚአብሔርን  እንድናውቀው እንድንወደው ትእዛዙን እንድንፈፅም ይህንን አድርገን መንግስተ ሰማይ እንድንገባ ነው፡፡

ቤተክርስቲያን ለሕዝቦች የድህነት መንገድ ለማዘጋጀት፡ ፆምን ታውጃለች ክርስቲያኖች ራሳቸውን ለእግዚአብሔር የበለጠ ያስገዙ ዘንድ  በትህትና ይመላለሱ ዘንድ፤ ፀጋን ያገኙ ዘንድ  ጊዜን መድባ ፆምን እንድንጾም ታዘናለች፡፡ የቤተክርስቲያን ጉዞ የአንድነት ጉዞ የጋራ ጉዞ ነውና በዚህ የጋራ ክርስቲያናዊ ጉዞ የተለያዩ የፆም ጊዜያት ቤተክርስቲያን ወስና ሰጥታናለች፡፡ ከእነዚህም አንዱ ክርስቲያኖች ሁሉ በየዓመቱ በጉጉት የምንጠብቀው የዐብይ ጾም ነው፡፡ ይህን ልዩ የጸጋ ጊዜ፡  ወደ እግዚአብሔር የመቅረብ ጊዜ እያንዳንዳችን  ዕድሉ እንዳያመልጠን መትጋት ይኖርብናል፡፡

ይህ የዐብይ ጾም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አገልግሎት ከመጀመሩ በፊት ለዝግጅት ይረዳው ዘንድ ከጥምቀቱ በኋላ ወደ በረሀ ሄዶ በጸሎት የተጋበት የሠይጣንን ፊተና ያሸነፈበት ተግባር ነው፡፡ ይህንን በማሰብ እኛም ካቶሊካውያን ይህንን ጾም በታላቅ መንፈሳዊ ተጋድሎ እንጾማለን፡፡ ቤተክርስቲያን በምታዘን መልኩ ከተከለከሉ ምግቦች እንቆጠባለን፡፡ የምህረትና የደግነት ተግባራት በመፈፀም የበለጠ ወደ እግዚአብሔር በመቅረብ በመጸለይ የተቸገረውን በመደገፍ መልካም የሆነውን ነገር ሁሉ በማድረግ እንፈፅመዋለን፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ  ክርስቶስ ስለጾም መመሪያ ሲሰጠን #ስትጾሙ መጾማችሁን ሰው እንዲያውቅ አይሁን በምሥጢር የጾማችሁን ዋጋ ፀጋን የሚሰጣችሁ እግዚአብሔር ይወቅ እንጂ; (ማቴ.6፡16)፡፡ ፀጋ በረከትን የሚሰጥ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡  የጾም ዓላማ ከእግዚአብሔር ጋር እንድንቀራረብ ነው እንጂ ማህበራዊ ገፅታችንን የምንገነባበት አይደለም፡፡ ጾም ተለምዶአዊ ተግባር ብቻ ሲሆን መንፈሳዊ ክብር ፀጋ ያጣና ባህላዊ ተግባር ይሆናል፡፡ ሁሉም ስለሚጾም እኛም  ከሰው ላለመለየት ብንጾም ሰዎች በመጾማችን ሊያከብሩን ይችሉ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ወደ እግዚአብሔር የማያደርሰን ጾም ትርጉም የለውም፡፡ ለሰዎች እይታ  የምንጾመው ጾም ትዕቢትን ያሸክመናል፡፡ እግዚአብሔር የጠራን በቅድስና እንድንኖር ነው እንጂ በርኩሰት እንድንኖር አይደለም፡፡

/1ኛ ተሰ. 4፡7/፡፡

ነቢዩ ኢሳያስ በምዕራፍ 58  የጾምን ትክክለኛ ትርጉም ከእግዚአብሔር የተቀበለውን መመሪያ  በግልፅ ቋንቋ ያስቀምጥልናል፡፡ 

“እኔ የምደሰትበት ጾም የጭቆና ሠንሠለትና የፍትህ መጓደል ቀንበር ታላሉ ዘንድ፣

ቀንበሩን ሰብራችሁ የተጨቆኑትን ነፃ ታወጡ ዘንድ አይደለምን?  

ምግባችሁ ከተራበ ሰው ጋር እንድትካፈሉ፣

ማደሪያ የሌለውን ድሃ በቤታችሁ እንድትቀበሉ፣

የተራቆተን እንድታለብሱ፣

ከቅርብ ዘመዶቻችሁም እራሳችሁን እንዳትደብቁ አይደለምን?

 ይህንን ብታደርጉ ብርሃናችሁ እንደ ንጋት ብርሃን ይበራል፡፡

 ፈውሳችሁም በፍጥነት ይመጣል; (ኢሳ 58፡-6-9) ይለናል፡፡

ስንጾም ሁልጊዜ ይህንን መመሪያ ከልብ ልናጤነው ይገባል፡፡ ወንድሞቼና እህቶቼ  የጾማችን ዋና ዓላማ በመመሪያው የተቀመጡትን የሰውን መብትና ክብር የመጠበቅ ፍትህንና ሰላምን የማስፈን ነው፡፡ ራስን የመግዛት በተጋድሎ የመመላለስ ሌሎችን የማሰብ የመደገፍ የመጸለይ ነው፡፡ እነዚህን ፈፅመን ደግሞ መልካም ክርስቲያኖች ፈጣሪያችን የምናከብር ለፈጣሪያችን የምንታዘዝ እርሱ የፈጠረውን ፍጥረት ሁሉ የምንከባከብ እንድንሆንና ፅድቅን መላበስ ችለን የእግዚአብሔር ሰዎች እንድንሆን ነው፡፡

 

 በመጨረሻ በዚህ የጾም ወቅት ለሀገራችን ኢትዮጵያና  ለሕዝቦቿ ሰላም እንጸልይ፡- ከልብ በእውነት በመነጨ ስሜት  ከተጋረጠበን  የእርስ በርስ ጥላቻ፣ ሙስናና አድልዎ እግዚአብሔር ራሱ እንዲከላከልላት፣ ኃላፊነት ያለባቸው ሰዎች ሁሉ  የእግዚአብሔር ጥበብ አድሮባቸው ፍትህን እንዲፈፅሙ እውነተኛ የሕዝብ የጋራ ጥቅም  የሚያመጣ  ትክክለኛ ውሳኔ እንዲወስኑ፤ እኛም እንደ እምነታችን ነብዩ ኢሳያስ እንዳስተማረን ቅድሚያ ከራሳችን እንጀምር፡፡ በጾምና በጸሎት እንትጋ  እውነተኛ ጾም እንድንጾም እግዚአብሔር ይርዳን፡፡

እግዚአብሔር አገራችንን ኢትዮጵያ ይባርክ!!

 

10/02/2018 17:06