2018-02-08 09:12:00

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአብይ ጾም ወቅት በሙሉ ልባችን ወደ ጌታ ፊት መቅረብ እንደሚያስፈልግ አሳሰቡ።


ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአብይ ጾም ወቅት በሙሉ ልባችን ወደ ጌታ ፊት መቅረብ እንደሚያስፈልግ አሳሰቡ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የዘንድሮን የአብይ ጾም በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክታቸው፣ እንደ እባብ አሳሳች የሆኑ ሐሰተኛ ነቢያት ወደ ተሳሳተ መንገድ ይወስዱናል። የእግዚአብሔርን ሕዝብ በማታለል፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ የሚገኘውን እውነተኛ ደስታን በጊዜያዊ ደስታ በመለወጥ፣ በመጨረሻም ብዙዎችን ለብቸኝነት ሕይወት በመዳረግ ወደ ባርነት ቀንበር ይጎትታሉ ብለዋል። ቅዱስነታቸው ይህን ካሉ በኋላ በማቴዎስ ወንጌል የተጻፈውን፣ የሚከተለውን ጥቅስ አስታውሰዋል። ከዓመፃም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች (የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 24 ቁ. 12) ብዙ ወጣቶች፣ የተሳሳተ መንገድ በሚከተሉ አታላዮች በመጠቃት፣ ራሳቸውን የሚጎዱ አደንዛዥ ዕጾችን ይወስዳሉ፣ መተማመንና ዘላቂነት የሌለውን የወዳጅነት ሕይወት ይኖራሉ፣ ውድ የሆነውን ሰብዓዊ ክብራቸውን ያጣሉ፣ ነጻነታቸውን ይገፈፋሉ፣ ፍቅርንም ይነጠቃሉ ብለዋል።

የዚህን ዝግጅት ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ።

በሐሰተኛ ነቢያት እንደምንጠቃ ከተገነዘብን፣ በዚህ በአብይ የጾም ጊዜ እያንዳንዳችን ራሳችንን መጠየቅ ያለብን ጥያቄ ቢኖር፣ ፍቅራችን እየቀዘቀዘ መምጣቱን የምናውቀው እንዴት ነው? የሚል ይሆናል ብለዋል። የለጋስነትና የቸርነት ልብ የሚጠፋው ስግብግነት ሲመጣ ነው። ሕይወታችን ያለ እግዚአብሔር ሲቀር፣ ከቃሉ እና ከምስጢራት በመራቅ የራሳችንን የምቾት መንገድ መከተል ስንጀምር ነው። ይህ በሚሆንበት ጊዜ ፍቅራችን እና ልባችን መቀዝቀዙን ፍጥረታት ራሳቸው በዝምታ ይመሰክራሉ፣ መሬትም ፍሬ መስጠቷን ታቆማለች፣ ባሕርም በስደተኞች ሬሳ ይደፈርሳል፣ የሰውን ነፍስ የሚገድል፣ ንብረትን የሚያወድም የጦር መሣሪያ ከሰማይ ይዘንባል።

ስለዚህ ይህ ሁሉ ሲሆን ምን እናደጋለን? ብለው ላቀረቡት ጥያቄ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልስ ሲሰጡ፣ የአቢይ ጾም ጊዜ የጸሎት ጊዜ፣ የተራቡትን፣ የተጠሙትን፣ ታረዙትን  የምንረዳበት ጊዜ እንዲሆን ቤተ ክርስትያን ታስተምረናለች ብለዋል። እነዚህ በሙሉ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን አስፈላጊዎች ናቸው። ጸሎት ሐሰትንና ራስን ማታለልን በማስወገድ ከእግዚአብሔር ዘንድ መጽናናትን እንድናገኝ ይረዳናል። የተቸገረን መርዳት ከስግብግብነት እንድንወጣ ያግዘናል፣ ሌሎችን እንደ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንድንመለከት ያግዘናል። ደሃን መርዳት ደግሞ የሕይወት አካሄድ ምን መምሰል እንዳለበት ይነግረናል። መጾም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በመኖር ከአመጽ እንድንርቅ ያግዘናል። ረሃባችንን ሊያስታግስ ከሌሎች በርካታ ችግሮች ሊያወጣን የሚችል እግዚአብሔር ብቻ እንደሆነ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስገንዝበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማከልም የቸርነትና የርህራሄ ልባችን ሊመነምን ወይም ሙሉ በሙሉ ሊጠፋ ይችላል። ነገር ግን የእግዚአብሔር ቸርነት አያልቅም። ይህን ካሉ በኋላ የካቲት 30 እና መጋቢት 1 ቀን 2010 ዓ. ም. “24 ሰዓት ለጌታ እንስጥ” በሚለው ዝግጅት እንድንካፈል አደራ ብለዋል። የቅዱስ ቁርባን እና የኑዛዜን ምስጢራት በመካፈል፣ የእግዚአብሔርን ቃል በጽሞና እንድናዳምጥ የሚያደርገንን፣ በቅዱስ ስጋው የሚመግበንን፣ ልባችን በእምነት፣ በተስፋና በፍቅር እንዲበረታ የሚያደርገንን የኢየሱስ ክርስቶስን የአብይ ጾም አዲስ ብርሃን መቀበል ያስፈልጋል ብለዋል።        








All the contents on this site are copyrighted ©.