2018-02-01 12:59:00

የቨነዙዌላ ብጹዓን ጳጳሳት የሕዝባቸው ሰብዓዊ ክብር እንዲጠበቅ አሳሰቡ።


የቨንዙዌላ ብጹዓን ጳጳሳት የሕዝባቸው ሰብዓዊ ክብር እንዲጠበቅ አሳሰቡ።

የቨነዙዌላ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት፣ ሞንሲኞር አዙዋየ፣ በቨንዙዌላ የአንድ ፓርቲ ሥርዓት የሚከተል  ወታደራዊው ገዢ መንግሥት፣ ኤኮኖሚውን በመቆጣጠር፣ ሙስናን በማስፋፋትና ሕዝቡ ላይ እያደረሰ ያለውን የጭቆና ሥርዓት ዘላቂ በማድረግ ሕዝብን ለማሰቃየት ይፈልጋል ብለዋል።

የቨነዙዌላ ጳጳሳት ጉባኤ ከረጅም ጊዜ አንስቶ ሕዝቡ በረሃብ አለንጋ እየተገረፈ መሆኑን፣ በተመጣጣኝ ምግብ እጥረት የሕጻናትና የአዛውንት የጤና መታወኩን፣ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ወጣቶችና ጎልማሶች አገራቸውን ለቀው መሰደዳቸውን፣ በሰብዓዊ መብት ጥሰትና በዴሞክራሲ እጦታ አገራቸው የወደቀችበትን አስከፊ ችግሮችን ለዓለም ሲያሰማ መቆየቱ የሚታወስ ነው።

የዚህን ዜና ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ።

ሞንሲኞር አዙዋየ በዛሬው በግለጫቸው፣ ሕዝባቸው ላይ የተደቀነውን ረሃብና የጤናን ችግር ለማቃለል፣ ሕዝቡን ተሳታፊ የሚያደርግ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል መንገድ እንዲመቻች ለመንግሥታቸው አፋጣኝ ጥሪ እናቀርባለን ብለዋል። በማያያዝም በመንግሥትና በተቃዋሚዎች መከከል የሚደረገው የድርድር ሂደት የሕዝቡን ስቃይ የተመለከተና ያገናዘበ መሆን አለበት እንጂ ፓርቲዎች ለራሳቸው ምቾት የሚወያዩበት መሆን የለበትም ብለዋል።  ሞንሲኞር አዙዋየ በማከልም ዓላማችን ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ሕይወት መከላከል እንጂ በመንግሥት ወይም በተቃዋሚው ጎራ ለመቆም አይደለም ብለዋል። ይህን አቋማችንን ከርጅም ጊዜ ጀምሮ ለሁለቱም ወገኖች ግልጽ አድርገናል ብለዋል።

ቨነዙዌላ ያለችበት ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ነው ያሉት የቨነዙዌላ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት ሞንሲኞር አዙዋየ፣ በሃገሪቱ ከፍተኛ የምግብና የመድሐኒት እጥረት፣ ለእርሻ የሚውሉ የምርት ግብዓቶች እጥረትና ምርትን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የማጓጓዝ ከፍተኛ ችግር አለ ብለዋል። ብዙ የምርት ዓይነቶች ገበያ ላይ የሉም፣ ቢኖሩም ዋጋቸው የሚደረስ አይደለም ብለዋል። ለሠራተኛው የሚከፈል ወርሃዊ ደሞዝ አጥጋቢ የዕለት እንጀራን ለመግዛት የሚያስችል አይደለም ብለው ይህም በሕዝቡ መካከል ጭንቀት ፈጥሯል ብለዋል። 

ሞንሲኞር አዙዋየ በንግግራቸው በየዕለት ከመንግሥት በኩል አዳዲስ መግለጫዎች እንደሚወጡና እነዚህ   መግለጫዎችም ሕዝቡ ያለበትን ሁኔታ ያላገናዘቡ፣ ነገር ግን የመንግሥትንና የባለሥልጣናትን ዕድሜ ለማራዘም የታለሙ እንደሆነ ገልጸው፣ በዴሞክራሲ እጦት የተነሳ ሀገራቸው በከባድ ችግር ውስጥ በመውደቁ ለአስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ ልመና ተዳርጓል ብለዋል። ቤተ ክርስቲያናቸውም ሕዝባቸውን በሚጠቅሙ በማንኛውም የውይይት ሂደት ለመሳተፍ ዝግጁ መሆንዋን ሲር ለተባለ ለቤተክርስቲያን የዜና ማሰራጫ ገልጸዋል።          








All the contents on this site are copyrighted ©.