2018-02-01 13:46:00

ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በቻይና ያለች ቤተክርስቲያን ለሁለት የተከፈለች ሳትሆን አንድ መሆኗን ገለጹ።


ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በቻይና ያለች ቤተክርስቲያን ለሁለት የተከፈለች ሳትሆን የሁለት ወገን ምዕመናን ያሉባት መሆኗን ገለጹ።

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ የሆኑት ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በቻይና በሁለት የምዕመናን ወገን መካከል እርቅን ለማውረድ ጥረት በማድረግ ላይ ያለች ቤተክርስቲያን እንጂ ለሁለት የተከፈለች አለመሆኗን ገለጹ።

ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በንግግራቸው በቅድስት መንበርና በሕዝባዊት ሪፑብሊክ ቻይና መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሳደግ እና መላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በቻይና በሚገኙ ምዕመናኖችዋ መካከል እርቅን በማውረድ ወደ አንድነት እንዲደርሱ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ እንዳለች ገልጸዋል። ከዚህ ባሻገር በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና በቅዱስ ሐዋርያው ጴጥሮስ የቅርብ ተከታዮች ሐዋርያዊ መዋቅሮች መካከል ምንም ዓይነት የሃሳብ ልዩነት አለመታየቱን አስረድተው ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በማከልም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከሌሎች ረዳቶቻቸው ጋር በመሆን በቅድስት መንበር እና በሕዝባዊት ሪፑብሊክ ቻይና የመንግሥት ባለስልጣናት ጋር ቀጥታ ግንኙነት በማድረግ ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የዚህን ዝግጅት ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ።

በቅድስት መንበር እና በሕዝባዊት ሪፑብሊክ ቻይና መንግሥት መካከል የተደረጉት የእስካሁን የጋራ ውይይቶች ለእስካሁኑ የቤተክርስቲያን ባሕል ታማኝ ከመሆንም በላይ ግልጽና ገንቢ እንደሆኑ ያስረዱት ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ ከዚህ በፊት የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክት 16ኛ፣ በ1999 ዓ ም ለቻይና ካቶሊካዊ ምዕመናን በላኩት ደብዳቤ እንደገለጹት፣ ሊገኝ የሚችል ማንኛውም ዓይነት መፍትሄ ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በቀጠለው ዘላቂ ክርክር ሊመነምን አይገባም ያሉትን አስታውሰው አሁንም ቢሆን በዚያች አገር የሚገኙ ካቶሊካዊያን ምዕመናን ተገቢ የሆነ ሐዋርያዊ አገልግሎት እንዲያገኙ፣ እምነታቸውንም እንደ ባሕላቸው መሰረት መለማመድ የሚችሉበትን መንገድ ማመቻቸት ያስፈልጋል ብለዋል።

በቻይና የቤተክርስትያን ሕይወት ቀላል አይደለም ያሉት ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን የሚነሱትን ችግሮች በሙሉ በአንድ ጊዜ ለማቃለል ያዳግታል ብለዋል። ቅድስት መንበር በዚያች አገር የጳጳስ ምርጫን ማካሄድ አንዱ አንገብጋቢ ጉዳይ ሲሆን ይህን ለማከናወን ቅድስት መንበር ከሁሉ አስቀድሞ ከመንግሥታት ጋር ያላት ግንኙነት ወሳኝነት አለው ብለዋል። በዚህ መሠረት ከሕዝባዊት ሪፑብሊክ ቻይና ጋር የተጀመረ ግንኙነት እጅግ አዝጋሚ ቢሆንም ብዙ በርካታ አዳዲስ እና ድንገተኛ ክስተቶች መታየታቸው አይቀርም። ለችግሮች ትክክለኛ  መፍትሄ ሊገኝ ይችላል ብሎ በእርግጠኝነት መናገር የሚችል ማንም የለም። በሕዝቦች መካከል በሁለቱም ወገኖች የቆየ ቁስል ስላለ እስኪፈወስ ድረስ ጊዜንና ትዕግስትን ይጠይቃል። ይህ እስከሚሆን ድረስ ተጨማሪ ድካምና ስቃይ ሊኖር ይችላል። ወደ ጳጳስ ሹመት ደረጃ ከተደረሰ በኋላ ሕዝቡ በህብረት አብሮ መኖርን ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ግንኙነት እንዳይኖር የሚያግድ ምንም ዓይነት ምክንያት ሊኖር አይችልም ብለዋል ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን።

የእግዚአብሔር ፈቃድ ሲፈጸም፣ በቻይና ስለ ሕጋዊ ጳጳስና ሕጋዊ ያልሆነ ጳጳስ፣ ስደት ላይ ያለች ቤተክርስቲያንና ብሔራዊ ቤተክርስቲያን ብለን የምናወራበት ጊዜ አክትሞ ወንድሞች እርስ በርስ የሚተባበሩበት፣ የጋራ ቋንቋ የሚናገሩበት ጊዜ ይመጣል። ይህ ደረጃ ሳይደረስ እንዴት ተብሎ በቻይና ምድር ላይ ወንጌልን ማብሰር፣ የእግዚአብሔርን አጽናኝነት መመስከር ይቻላል? ይቅርታን ለማድረግ ካልተዘጋጁ፣ ሌሎች የግል ፍላጎቶችን ለማስጠበቅ ከተነሱ ይህ የወንጌል ዓላማ ሊሆን አይችልም ብለዋል።

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ የሆኑት ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ንግግራቸውን በመቀጠል፣ ያለፈው ስቃይ ተረስቶ፣ በእግዚአብሔር ዕርዳታ ሕዝቦች በሰላምና በፍቅር አብረው መኖር ወደሚችሉበት ጊዜ ላይ ለመድረስ ረጅም ጊዜንና በርካታ መንፈሳዊ የሰው ሃይልን ማፍራት ያስፈልጋል ብለዋል። መላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ያለፈውን ይሁን የአሁኑን የቻይና ካቶሊካዊ ምዕመናን ስቃይ በቀላሉ የምትረሳው አይሆንም። ምክንያቱም የምዕመናኑ ስቃይ የመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ትልቅ ሃብት ነውና።

ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በማከልም፣ መላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ከቻይና ካቶሊካዊ ምዕመናን ጎን እንደሆነች አረጋግጠው፣ በጸሎት ብቻ ሳይሆን ሕብረትን ለማምጣት በሚያደርጉት ጥረት ሁሉ የማያቁርጥ ድጋፍ ታደርጋለች ብለዋል። ስለዚህ ማንም በወንድሙ ላይ በክፋት ተነሳስቶ እንዳይፈርድ፣ ያለፈውን በደል ምክንያት በማድረግ ሌላ በደልን እንዳይቀሰቅስ፣ ይልቅስ የእያንዳንዱ ምዕመን ሰብዓዊ ድክመት እንዳለ ሆኖ ወደፊት አድጋ በምትታይ ቤተክርስቲያን ላይ ተስፋ ማድረግ ይኖርበታል ብለዋል።

በቅድስት መንበር እና በሕዝባዊት ሪፑብሊክ ቻይና መካከል እየተካሄደ ያለውን የጋራ ውይይት ያስታወሱት ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ የጋራ ውይይቱ በሁለቱ መካከል አንድነትን እንጂ ልዩነትን የሚፈጥር መሆን እንደሌለበት፣ የየራሳችንን አቋም መግለጽ ትክክልና ሕጋዊ መብት ቢሆንም ከዚያ ባለፈ የግል አመለካከትን ብቻ የሚያንጸባርቅ ሳይሆን በቻይና የበርካታ ምዕመናንን ጥቅም ያገናዘበ መሆን አለበት ብለዋል። ስለዚህም ቅድስት መንበር እዉነትን ለማግኘት በምታደርገው ጥረት መካከል በምዕመናን ላይ ከቻይና ውጭ ይሁን ከውስጥ የሚደረጉ ሕጋዊ ተፅእኖዎችን እንደምትመለከት ገልጸዋል። እግዚአብሔር በቻይና ውስጥ ለምትገኝ ቤተ ክርስቲያን ያለውን ዕቅድ ለማወቅ ትሕትናና የእምነት መንፈስ እንዲኖር ያስፈልጋል ብለዋል። ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በንግግራቸው ማጠቃለያ፣ ሕብረታችንን የሚያደናቅፉ፣ የወደ ፊት መልካም ተስፋን የሚወስዱብን ጠቦች እንዳይቀሰቀሱ ከሁለቱም ወገኖች የበለጠ ጥንቃቄንና መልካም ዕርምጃ መወሰድ አለበት ብለዋል።                     








All the contents on this site are copyrighted ©.