2018-02-01 12:38:00

መልካም እረኛ የኢየሱስን ምሳሌ የሚከተል መሆን አለበት።


መልካም እረኛ፣ የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ከሕዝቡ ጋር የሚሆን፣ ሕዝቡን የሚያዳምጥ፣ ለሕዝቡም የሚራራ መሆን እንዳለበት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አሳሰቡ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት ማክሰኞ በቅድስት ማርታ በሚገኘው ጸሎት ቤታቸው ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ለተገኙት ካህናት ደናግልና ምዕመናን ባሰሙት ቃለ ምዕዳን፣ ሐዋርያዊ እረኞች የኢየሱስን ፈለግ በመከተል ለምዕመናኑ የሚጨነቁ እና የሚራሩ መሆን ያስፈልጋል ብለዋል።

የዚህን ዜና ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ።

ቅዱስነታቸው ይህን የተናገሩት በላቲን ስርዓት መሰሠረት ለዕለቱ ከተዘጋጀው ከሐዋርያው ቅዱስ ማርቆስ ወንጌል ምዕ 5 ከቁጥር 21 እስከ 31 የተጻፈውን መሠረት በማድረግ ባሰሙት ቃለ ምዕዳን ሲሆን፣ መልካም እረኛ ከምዕመናን ጋር በመሆን፣ እነርሱን የሚያዳምጥ፣ ለእነርሱ የሚራራ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

ሐዋርያዊ እረኛ ከሕዝቡ ጋር በመጓዝ ስለ እነርሱ የሚያስብ መሆን ያስፈልጋል ብለዋል። ሐዋርያው ማርቆስ በወንጌሉ እንደሚያስገነዝበን ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱን በሚከተለው ሕዝብ ታጅቦ በሚጓዝበት ጊዜ እግዚአብሔርም ለሕዝቡ የገባላቸውን አደራ በተግባር እንዲታይ ያደርጋል ብለዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ የግል መሥሪያ ቤት ወይም ቢሮ በመክፈት የሥራ ቀንና ሰዓት ማስታወቂያን በመለጠፍ  ሕዝቡ ወደ እርሱ የሚመጡበትን ጊዜን አልወሰነም። የመግቢያ ዋጋ ወይም የአገልግሎት ክፍያ፣ የገንዘብ መጠን አላስቀመጠም።  ሕመምተኞችን ተቀብሎ ሕክምናን የሚሰጥበትን ቀን አልወሰነላቸውም። ኢየሱስ ፈጽሞ ይህን አላደረገም ያሉት ቅዱስነታቸው ይልቅስ እርሱ ያደረገው ወደ ሕዝቡ መሄድን ነው የወደደው። ወደ ሕዝቡ ውስጥ መግባትን ነው የመረጠው ብለዋል።

ይህ ነው ኢየሱስ የሚሰጠን የአንድ እውነተኛ ሐዋርያዊ እረኛ ምሳሌ ካሉ በኋላ ይህን በማስመልከት ቅዱስነታቸው በምዕመናኑ መካከል ሆነው ሲያገለግሉ፣ ላይ ታች ሲሉ በመዋላቸው ድካም የሚሰማቸው እውነተኛ ሐዋርያዊ እረኞች መኖራቸውንም አስታውሰዋል።

ለሕዝቡ በመራራት፣ ችግራቸውን መጋራት፣ ችግራቸውን አብሮ መጋፈጥ የኢየሱስ ክርስስቶስ ቀዳሚ ሥራው ነበር። ወንጌል እንደሚለው ኢየሱስ ወደ ሕዝቡ ዘንድ ከመምጣትም አልፎ ሳይጸየፍ ወደ እያንዳንዱ በመጠጋት በእጁ ይነካቸው ነበር፣ ጸጋውንም ያካፍላቸው ነበር። ይህ ነው የእውነተኛ ሐዋርያዊ እረኛ ተግባር በማለት አስረድተዋል።

ሐዋርያዊ እረኛ ለክህነት አገልግሎት የሚያበቃውን ቅዱስ ምስጢር ሲቀበል በዘይት ይቀባል። እውነተኛ ዘይት ለሕዝቡ እንዲራራ፣ በሕዝቡ መካከል እንዲሆን የሚያደርግ ውስጣዊ ዘይት ነው። ከሕዝቡ ጋር መሆንን የማይፈልግ ሐዋርያዊ እረኛ ችግር አለበት። ምናልባትም ከሐዋርያዊ እረኝነት ይልቅ የእርሻ ባለቤት መሆን ይሻለዋል ብለዋል። አንድ እረኛ ለመንጋው የማይራራ እና የማይጨነቅ ከሆነ መንጋውን ዘወትር በአርጩሜ ይገርፋል፣ ያሰቃያል። ይህ እረኛ ርህራሔ ይጎድለዋል፣ መልካም እረኛ ሊሆን አይችልም ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በማከልም መልካም እረኛ በቀኑ መጨረሻ ላይ ይደክመዋል፣ የሚደክመውም መልካምን ሲሰራ ስለዋለ ነው። ይህን በማደረጉ በንጋውም የእግዚ አብሄርን አለኝታነት ይገነዘባል።

ሐዋርያዊ እረኞች ከሕዝባቸው ጋር አብረው እንዲሆኑ፣ ብሶታቸውን እንዲሰሙ፣ ችግሮቻቸውን አብረው ለማቃለል የሚያስችላቸው ጸጋ እንዲበዛላቸ ለአገልጋዮቻችን መጸለይ ይስፈልጋል ብለዋል።

 

       

 








All the contents on this site are copyrighted ©.