2018-01-29 08:39:00

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የኢጣሊያ ቀይ መስቀል ማሕበር አባላት ተቀብለው ንግግር ማድረጋቸው ተገለጸ


ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ ስድስተኛ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ  የተገኙትን የኢጣሊያ ቀይ መስቀል ማሕበር አባላት ተቀብለው ንግግር ማድረጋቸው ታወቋል።

የኢጣሊያ ቀይ መስቀል ማሕበር ፕሬዚዳንት ላደረጉልኝ ንግግር ምስጋናዬን እያቀረብኩ የማሕበሩ አባላትን በሙሉ እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት፣ የቀይ መስቀል ማህበር በመላው ኢጣሊያ ከሚያበረክተው አገልግሎት ባሻገር በመላው ዓለም ዘላቂ የሆነ የማቴሪያል ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

በኢጣሊያ የቀይ መስቀል ማሕበር አገልግሎትና ሥራን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በኢጣሊያ በተለያዩ ጊዜያት የተከሰቱትን የመሬት መናወጥንና ሌሎችንም አደጋዎች ለመቋቋም ማሕበሩ ከሕዝቡ ጎን በመሆን ላበረከተው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ማሕበሩ ለረጅም ዓመታት ላበረከታቸው እና እያበረከተ ለሚገኘው ከባሕር ላይ ስደተኞችን የመታደጉን አገልግሎት የጠቀሱት ቅዱስነታቸው፣ የስደተኞችን ሕይወት ለማዳን የምታደርጉት ጥረት የሚያስመሰግን እንደሆነ ጠቅሰው የእያንዳንዱን ስደተኛ እጅ በመያዝ ከሞት አፋፍ ላይ ሕይወቱን የማትረፍ ሂደት ትልቅ ትርጉም ያለው ሲሆን እንደሚከተለው ቢተረጎም የተሻለ ይመስለኛል “እጅህን በመያዝ ከባሕር ውስጥ በማውጣት ሕይወትህን ማትረፍ ብቻ ሳይሆን የወደ ፊት ሕይወት ዕጣ ፈንታህን በልቤ ውስጥ አደርገዋለሁ።” ስለዚህ ለስደተኞች የምታሳዩት አለኝታነት ለዓለማችን አስፈላጊ አገልግሎት ነው ብለዋል።

በሉቃስ ወንጌል ምዕ. 10 ከቁ. 25-37 የተጻፈውን የደጉ ሳምራዊ ታሪክ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተልዕኮ በፍቅር የታገዘ፣ ሌሎችን ለማገልገል ራስን በነጻ ማቅረብ ስለሆነ ትልቅ መንፈሳዊ ትርጉም ያለው ነው።

የማህበራችሁ ቀዳሚና መሠረታዊ ደንብም ለሰው ልጅ ሕይወት ክብርን መስጠት ነው፣ ከደረሰበት ስቃይም ነጻ ማውጣት ነው። የሳምራዊው ምሳሌም ይህን ያመለክታል። ሌሎችን አገልግሎት ማለት ራስን ዝቅ በማድረግ፣ ሰዎችን ከደረሰባቸው ማንኛውም ዓይነት አደጋና ስቃይ ነጻ ማውጣት መቻል ነው ብለዋል። በዓለማችን እርዳታ ሳያገኙ ተደብቀው ወይም ከዓይን እይታ ተሰውረው ያሉ ሕጻናት፣ አረጋዊያንና ሴቶችን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ የቀይ መስቀል ማሕበሩ በዓለም ደረጃ በሰዎች መካከል ልዩነት ሳያደርግ፣ ሰዎች ከወደቁበት አደጋ ለማውጣት ለሚያደረገው ጥረት ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

በመጨረሻም የፍቅርና የሰላም ጌታ የሆነው መንፈስ ቅዱስ ለሌሎች መልካም ለማድረግ የምንችልበትን ጥበብ እንዲያስተምር ተማጽነው ለቀይ መስቀል ማሕበር አባላት በሙሉ ቡራኬን ሰጥተው፣ የማሕበሩ አባላትም በበኩላቸው በጸሎታቸው እንዲያስታውሷቸው አደራ ብለዋል።           








All the contents on this site are copyrighted ©.