2018-01-19 11:39:00

ር.ሊ.ጳ ልማዳዊ ከሆነው የሃይማኖት አካሄድ ተላቅቀን የኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ምስክሮች መሆን እንደሚያስፈልግ አሳሰቡ።


 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ልማዳዊ ብቻ ከሆነው የሃይማኖት አካሄድ ተላቅቀን የኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ምስክሮች መሆን እንደሚያስፈልግ አሳሰቡ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ፣ ዓለም አቀፍ የስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ቀን ምክንያት በማድረግ ካሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ በኋላ፣ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ሆነው ከሚጠባበቋቸው በርካታ ምእመናንና ሀገር ጎብኚዎች ጋር በመሆን የእሁዱን የእኩለ ቀን ጸሎታቸውን አቅርበዋል። ከጸሎቸው በኋላ፣ ምዕመናን የኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ምስክሮች መሆን እንደሚያስፈልግ አሳስበውል።

የእዚህን ዜና ሙሉ ይዘት ከእዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጭእን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

በኢየሱስ ክርቶስ ላይ  መቆም ለዕለታዊ ሕይወታችን መመሪያ እንደሚሆነን፣ ለእምነታችን ብርታትን የሚሰጥ፣ ተስፋ የሚሆነንና መንፈሳዊ ሃይላትን የሚሰጥ እንደሆነ ገልጸው በዕለቱ የተነበበውን የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል  በማስታወስ፣ አጥማቂው ዮሐንስ፣ ለሁለቱ ደቀ መዛሙርት፣ ለእንድርያስና ለስምኦን ጴጥሮስ፣ “እነሆ የእግዚአብሔር በግ” ባላቸው ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን እንደተከተሉት፣ ኢየሱስን ከመከተልም በላይ ወደ ሚኖርበት ሥፍራ ድረስ መምጣት እንደቻሉ የሚያስረዳው የወንጌል ክፍል፣ ኢየሱስ ክርስቶስን ማግኘት ብቻውን በቂ እንዳልሆነ፣ አልፎ ተርፎም የሚገኝበትን ስፍራ ማግኘት ያስፈልጋል ብለዋል። የደቀ መዝሙሮቹ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚኖርበትን ስፍራ ለማወቅ በመፈለግ፣ ጌታ ሆይ የት ነው የምትኖረው፣ በማለት ያቀረቡት ጥያቄ ጥልቅ የሆነ መንፈሳዊ ትርጉም ያለው እንደሆነ ሲገልጹ፣ ደቀ መዝሙሮቹ መምህራቸው የሚኖርበትን ስፍራ መጠየቃቸው በእርሱ መማረካቸውን፣ በየዕለቱ ወደ እርሱ እየመጡ አብረውት በመዋል፣ እርሱ የሚናገራቸውን ለማዳመጥ፣ እንዲያውም ቢቻል ከእርሱ ጋር ለመኖር ሁሉ ፍላጎት እንደነበራቸው የሚገልጽ ነው ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ኢየሱስን መፈለግ፣ ኢየሱስን ማግኘትና ኢየሱስን መከተል እውነተኛ የእርሱ ደቀ መዝሙር የመሆን ምሳሌ እንደሆነ ገልጸው፣ ኢየሱስን መፈለግ ማለት ከእግዚአብሔር ዘንድ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የተሰጠንን እውነተኛ ደስታን፣ ፍቅርንና ሙሉ ሕይወትን ማግኘት የምንችልበት መንገድ እንደሆነ አስረድተዋል።      

ብዙ የሕይወት ልምዶች ይኖሩን ይሆናል፣ ብዙ ነገሮችንም አከናውነን ይሆናል፣ ከብዙ ሰዎች ጋርም እንተዋወቅ ይሆናል። ከሁሉም በላይ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የምናደርገው ግንኙነት፣ ከእርሱ ጋር የምናደርገው ወዳጅነት ለሕይወታችን የተሟላ ትርጉም ሊሰጥ እንደሚችልና ለእቅዶቻችንም መልካም ፍሬን ሊያስገኝ ይችላል ብለዋል።

የእምነት ጉዞአችን፣ ብቻችን የምንወጣው እንዳልሆነ በማስረዳት ቅዱስነታቸው፣ በየዕለቱ የሚደግፈንና የሚመራን፣ አለኝታ የሚሆነንን ማግኘት እንዳለብን፣ እርሱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ሊሆነን ይገባል ብለዋል። ስለዚህም ኢየሱስ ክርስቶስን ካገኘን በኋላ እርሱ የሚገኝበትንና የሚኖርበታን ቦታ ማወቅ ያስፈልጋል ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማከልም ከምስጢራት የምናገኛቸው ጸጋዎች፣ ዕለታዊ ጸሎቶቻችንና አስተንትኖአችን ለእምነት ጉዞአችን መሠረታዊ እንደሆኑ አስረድተዋል።

የዓለም ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ቀን መልዕክታቸውን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በሮቻችንን የሚያንኳኳ እያንዳንዱ ስደተኛ፣ ወደ ልባችን እና ወደ ሕይወታችን ውስጥ ለመግባት የሚፈልገውን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመቀበል የምንችልበትን ዕድል ይፈጥርልናል ብለዋል። ስደተኞች በሚሄዱባቸው አገሮች  ሊደረግላቸው የሚገባውን አቀባበል የጠቆሙት ቅዱስነታቸው፣ ጦርነትን፣ ስቃይን፣ መከራንና ጭቆናን በመሸሽ የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ለሚሰደዱትን የሚሄዱባቸው አገሮች ድንበሮቻቸውን ክፍት በማድረግ መልካም አቀባበልን እንዲያደርጉላቸው፣ ወደ አገሮቹ ከደረሱ በኋላም ዓለም አቀፍ የሰብ ዓዊ መብት ያረጋገጠላቸው መብቶች ተከብሮላቸው፣ ለኑሮአቸው የሚያስፈልገውን ቁሳዊም ሆነ ስነልቦናዊ ድጋፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግ፣ የሚሰደዱት ሰዎች የተሻለ ሕይወት ዋስትናን ማግኘት ያለበት በተሰደዱበት አገር ብቻ ሳይሆን በትውልድ አገራቸውም የተስተካከለ ሕይወት የመኖር መብት፣ ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት እንዲረጋገጥላቸው ያስፈልጋል። ቀጥሎም ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች በሚስተናገዱበት አገር ማሕበራዊ ሕይወታቸው የተስተካከለ እንዲሆን ለማሕበራዊ ሕይወት ራሳቸውን ማዘጋጀት፣ የሚኖሩበትን አገር ሕዝብ ባሕልና ቋንቋን ማወቅ ሁለቱንም ወገኖች ይበልጥ እንዲተዋወቁ ያደርጋቸዋል ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን እና ሃገር ጎብኚዎች ባሰሙት ንግግራቸው ወደ ላቲን አሜርካ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት በማስታወስ፣ በጸሎት እንዲያስታውሷቸው አደራ ብለዋል።

 








All the contents on this site are copyrighted ©.