2018-01-15 09:57:00

የጥር 06/2010 ዓ.ም. እለተ ሰንበት ምንባባት እና አስተንትኖ በክቡር አባ ግርማቸው ተስፋዬ


የጥር 06/2010 .. እለተ ሰንበት ምንባባት እና አስተንትኖ

የቅዱስ ቤተሰብ በዓል

እኛ ብርቱዎች የሆን፣ የደካሞችን ጒድለት መሸከም እንጂ ራሳችንን ማስደሰት የለብንም። እያንዳንዳችን ባልን ጀራችንን ለማነጽ፣ እርሱንም ለመጥቀም ደስ የሚያሰኘውን ነገር ማድረግ ይገባናል፤ክርስቶስ ራሱን ደስ አላሰኘምና፤ ነገር ግን፣ “አንተን የሰደቡበት ስድብ በእኔ ላይ ደረሰብኝ” ተብሎ እንደ ተጻፈው ሆነበት። በጽናትና ቅዱሳት መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ እንዲኖረን፣ ቀደም ብሎ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአልና።

የእዚህን ዝግጅት ሙሉ ይዘት ከእዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

ብርታትንና መጽናናትን የሚሰጥ አምላክ፣ ክርስቶስ ኢየሱስን ስትከተሉ፣ በመካከላችሁ የአንድነትን መንፈስ ይስጣችሁ፤ ይኸውም በአንድ ልብና በአንድ አፍ ሆናችሁ፣ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክና አባት ታከብሩ ዘንድ ነው። እንግዲህ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሆን ዘንድ ክርስቶስ እንደተቀበላችሁ፣ እርስ በርሳችሁ ተቀባበሉ። ለአባቶች የተሰጠውን የተስፋ ቃል ያጸና ዘንድ ለእግዚአብሔር እውነት ሲል ክርስቶስ የአይሁድ አገልጋይ እንደሆነ እነግራችኋለሁና፤ እንዲሁም አሕዛብ እግዚአብሔርን ስለ ምሕረቱ ያመሰግኑት ዘንድ ነው፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፤ “ስለዚህ በአሕዛብ መካከል አመሰግንሃለሁ፤ ለስምህም እዘምራለሁ።”ደግሞም፣

“አሕዛብ ሆይ፤ ከሕዝቡ ጋር ደስ ይበላችሁ” ይላል። እንደ ገናም፣ “አሕዛብም ሁላችሁ ጌታን አመስግኑ፤ ሕዝቦች ሁሉ ወድሱት” ይላል። ኢሳይያስም እንዲሁ፣ “በሕዝቦች ሁሉ ላይ የሚነግሠው፣ የእሴይ ሥር ይመጣል፤ በእርሱም አሕዛብ ተስፋ ያደርጋሉ” ይላል። በእርሱ በመታመናችሁ የተስፋ አምላክ ደስታንና ሰላምን ሁሉ ይሙላባችሁ፤ ይኸውም በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ተስፋ ተትረፍርፎ እንዲፈስላችሁ ነው።

 

1ዩሐንስ 414-21

አብ ልጁን የዓለም አዳኝ ይሆን ዘንድ እንደላከው ዐይተናል፤ እንመሰክራለንም። ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ አምኖ በሚመሰክር ሁሉ፣ እግዚአብሔር በእርሱ ይኖራል፤ እርሱም በእግዚአብሔር ይኖራል። ስለዚህም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር እናውቃለን፤ በፍቅሩም እናምናለን።

እግዚአብሔር ፍቅር ነው፤ በፍቅር የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል፤ እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል። በዚህም ዓለም እርሱን እንመስላለንና። በፍርድ ቀን ድፍረት ይኖረን ዘንድ፣ ፍቅር በዚህ ዐይነት በመካከላችን ፍጹም ሆኖአል፤ በፍቅር ፍርሀት የለም፤ ፍጹም ፍቅር ግን ፍርሀትን አውጥቶ ይጥላል፤ ፍርሀት ከቅጣት ጋር የተያያዘ ነውና። የሚፈራም ሰው ፍቅሩ ፍጹም አይደለም። እርሱ አስቀድሞ ወዶናልና እኛ እንወደዋለን። ማንም፣ “እግዚአብሔርን እወደዋለሁ” እያለ ወንድሙን ቢጠላ፣ እርሱ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን መውደድ አይችልምና። እርሱም “እግዚአብሔርን የሚወድ ሁሉ ወንድሙን መውደድ ይገባዋል” የሚለውን ይህን ትእዛዝ ሰጥቶናል።

 

ሐዋ.. 1332-43

“እኛም እግዚአብሔር ለአባቶች ቃል የገባውን የምሥራች ቃል ለእናንተ እንሰብካለን፤ ኢየሱስንም ከሙታን በማስነሣቱ ለእነርሱ የገባውን ቃል ለእኛ ለልጆቻቸው ፈጽሞአል፤ ይኸውም በሁለተኛው መዝሙር እንዲህ ተብሎ ተጽፎአል፤“ ‘አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወለድሁህ።’ 

ደግሞም፣ እርሱ እንዳልበሰበሰና እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው ለማረጋገጥ እንዲህ ብሎአል፤  ‘የተቀደሰውንና የታመነውን፣ የዳዊትን በረከት እሰጣችኋለሁ።’ ስለዚህ በሌላም ስፍራ፣“ ‘ቅዱስህ መበስበስን እንዲያይ አትፈቅድም’ ይላል።

“ዳዊት በራሱ ዘመን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ካገለገለ በኋላ አንቀላፍቶአል፤ ከአባቶቹም ጋር ተቀብሮ ሥጋው በስብሶአል። እግዚአብሔር ከሙታን ያስነሣው እርሱ ግን መበስበስን አላየም። እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ የኀጢአት ይቅርታ የሚገኘው በኢየሱስ በኩል መሆኑ እንደ ተሰበከላችሁ ዕወቁ፤ በእርሱ የሚያምን ሁሉ በሙሴ ሕግ በኩል ማግኘት ያልተቻለውን ጽድቅ ያገኛል። ስለዚህ ነቢያት እንዲህ ብለው የተናገሩት እንዳይደርስባችሁ ተጠንቀቁ፤ “ ‘እናንት ፌዘኞች፤ ተመልከቱ፤ ተደነቁ፤ ጥፉም፤ ማንም ቢነግራችሁ፣ የማታምኑትን ሥራ፣ እኔ በዘመናችሁ እሠራለሁና።’ ”ጳውሎስና በርናባስ ከምኵራብ ሲወጡ፣ ሰዎቹ ስለ ዚሁ ነገር በሚቀጥለው ሰንበት እንዲነግሯቸው ለመኗቸው። ጉባኤው ከተበተነ በኋላም፣ ብዙ አይሁድና ወደ ይሁዲ ሃይማኖት ገብተው በመንፈሳዊ ነገር የበረቱ ሰዎች፣ ጳውሎስንና በርናባስን ተከተሏቸው፤ እነርሱም አነጋገሯቸው፤ በእግዚአብሔርም ጸጋ ጸንተው እንዲኖሩ መከሯቸው።

 

ማቴ.219-23

ሄሮድስ ከሞተ በኋላ የጌታ መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ተገልጦ፣ “ተነሣ፤ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ እስራኤል ምድር ተመለስ፤ ሕፃኑን ለመግደል የሚሹት ሞተዋልና” አለው። ዮሴፍም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን በመያዝ ወደ እስራኤል ምድር ተመለሰ፤ 22ነገር ግን አርኬላዎስ በአባቱ በሄሮድስ ቦታ በይሁዳ መንገሡን በሰማ ጊዜ ወደዚያ መሄድ ፈራ። ጌታ በሕልም ስላስጠነቀቀው፣ ወደ ገሊላ አውራጃ ሄደ፤ ናዝሬት ወደምትባል ከተማም ሄዶ መኖር ጀመረ። በዚህም በነቢያት፣ “ናዝራዊ ይባላል” ተብሎ የተነገረው ትንቢት ተፈጸመ።

 

በኢትዮጲያ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ካህን ክቡር አባ ግርማቸው ተስፋዬ ያደርጉት አጭር አስተንትኖ

 

በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም መልካም ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ ዛሬ እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት አቆጣጠር ዘናዝሬት የተሰኘውን ሰንበትን እናከብራለን ፡፡ በዚሁ ሰንበት ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ ሰዎች በኩል አድርጐ ለእኛም መልእክቱን ያስተላልፍልናል፡፡

እርሱም እንደሚለን በምድር ላይ በምኖርበት ጊዜ ስለራሳችን ብቻ ሣይሆን ስለሌሎችም ማሠብ መጨነቅ እንደሚያስፈልግ ይነግረናል፡፡ “ብርቱ የሆኑ ሰዎች የደካሞችን ወድቀት መሸከም አንዳለባቸው ያሳስባል፡፡”

ይህ ማለት ለምሳሌ አንድ ሰው ቶሎ የሚቆጣ ከሆነ፣ በመስከር ቤተሰቡንና ጐረቤቱን የሚበጠብጥ ከሆነ፣ ሰውን ሁሉ የሚሳደብና የሚያስቀይም ከሆን በቃ ይህ ሰው ፀባዮ ነውና ተውት እንዳሻው ያድርግ ማለት ሣይሆን ያንን ሠው ከዚህ አስነዋሪ ሥራው እንዲመለስ በተደጋጋሚ በፍቅርና በትሕትና መርዳት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ነው የደካሞችን ሸክም መሸከም ማለት  ካለበት አስከፈ ሁኔታ ወይንም ባሕሪ እንዲላቀቅ ማገዝ መርዳት ማለት ነው፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ከነ ውድቀታችን፣ ከነደካማነታችን ተቀብሎናል በኃላ ግን  ከውድቀታችን አነሣን ተመልሰን  እንዳንወድቅም በምን አቅጣጫ መጓዝ እንዳለብን መንገዱን በፍቅርና በትሕትና አስተማረን፡፡

ይህም ሆኖ በድካማችን ብዛት ብንወድቅም የምንመለስበትን መንገድ ምሥጢረ ንሰሀን አበጀልን፡፡

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በዚሁ መልዕክቱ በመቀጠል ክርስቲያኖች አንድ ልብ አንድ ሐሳብ ሆነው እግዚአብሔርን እንደሚያመሰግኑ ይመክራል

ምክንያቱም ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በኖረበት ዘመን አይሁዳውያን እኛ ከመጀመሪያው ጀምሮ እግዚአብሔርን እናውቃለን በማለት አረማውያንንና ከአረማውያን ወገን የሆኑትን ክርስቲያኖችን ሁሉ ይንቁ ነበር፡፡

በዚህ በተከፋፈለ ልብ ግን እግዚአብሔርን ማመስገን እንደማይቻል ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ይናገራል ለዚህ ነው  ክርስቲያኖች በአንድ ልብ በአንድ ሐሳብ እግዚአብሔርን ያመስግኑ የሚለው፡፡  በክርስቲያን ማኀበረሰብ ውስጥ መከፋፈልና መለያየት ካለ ይህ መንፈስ ከእግዚአብሔር የመጣ መንፈስ አይደለም ምክንያቱም የእግዚአብሔር መንፈስ ሁሌም የአንድነትና የመተባበር የመረዳዳትና የመከባበር መንፈስ ነው ፡፡

ዛሬም ምንአልባት ይህ ክስተት በኛ በክርስቲያኖች መካከል ሊኖር ይችላል፡፡  ሀብታሞች፣ ድሆችን, የተማሩት ያልተማሩትን, ጤነኞች በሽተኞችን ለመቀበል የሚቸገሩበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል፡፡

ይህ ግን የክርስቶስ ወዳጅ ነኘ በሚል ሰው የክርስቶስ ተከታይ ነኝ በሚል  ሰው ሊንፀባረቅ አይገባም፡፡  ምክንያቱም ዓላማችን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብ, በፍጹም ሐሳብ በፍጹም ኃይል መውደድና ባልእንጀራችንን እንደራሳችን አድርገን መውደድ ነውና፡፡

ቅዱስ ሐዋርያው ዮሐንስ በመልዕክቱ “ እግዚአብሔር ፍቅር ነው ” ይላል ስለዚህ ይህን ፍቅር የሆነን አምላክ የምናፈቅረው በፍርሃትና በመርበድበድ ሳይሆን በፍቅር ብቻ ሊሆን ይገባል፡፡

እግዘአብሔርን ይቀጣናል ወደ ገሃነም ይከተናል በሚል ሐሳብ የምንቀርበው ከሆነ የምናመልከው ከሆነ ይህ ስሕተት ነው፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ሁሌም ፍቅር የሆነ ፍቅርን የሚሰጥ ፍቅርን የሚያበረታታና ስለ ልጆቹ ፍቅር ብሎ ሕይወቱን በመስቀል ላይ ሰቶ ያዳነን አምላክ ነው ፡፡

በዚሁ  በዮሐንስ መልዕክት 4፣18 ላይ “በፍቅር ፍርሃት የለም ፍጹም ፍቅር ግን ፍርሃትን አውጥቶ ይጥላል፣ ፍርሃት ከቅጣት ጋር የተያያዘ ነውና፡፡ የሚፈራም ሰው ፍቅሩ ፍጹም አይደለም” ይላል፡፡

ስለዚህ እግዚአብሔርን በፍጹም ፍቅር እንጂ በፍርሃት መንፈስ ልናፈቅረው አይገባም፡፡ ባለ እንጀራችንንም እንዲሁ ንጹህ በሆነ ፍቅር እንጂ ብድር ስለሚመልስ መሆን የለበትም፡፡ ሉቃስ 14፣13 እንዲህ ይላል ግብዣ ባዘጋጀህ ጊዜ ድሆችን አካለ ስንኩሎችን ሽባዎችንና ዓይነስውሮችን ጥራ ትባረካለህም እነዚህ ብድር ሊመልሱልህ ስለማይችሉ በጻድቃን ትንሣኤ እግዚአብሔር ራሱ ብድራትህን ይመልስልሃል፡፡

የማቴዎስ ወንጌል 2፡19-23 ላይም እግዚአብሔርን የሚወድና በእርሱ ፈቃድ የሚመላለስ ሰው እግዚአብሔር በመንገዱ ሁሉ እንደሚረዳው፣ እንደሚመራው፣  እንደሚያግዘው፣ ያስተምረናል፡፡

የፃድቁ የቅዱስ ዬሴፍ ሕይወት የሚያመላክተን ይህንኑ ነው ገና ከጅምሩ እመቤታችን ድንግል ማርያምን በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ከፀነሰችበት ጊዜ አንስቶ እግዚአብሔር ምን ማድረግ እንዳለበት ይነግረው ነበር በሕልሙ ይገልፅለት ነበር፡፡  እርሱም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድይመላለስ ነበር፡፡

ወደ ግብፅ እናቱንና ሕፃኑን ይዞ እንዲሄድ እንደነገረው አሁን ደግሞ ከግብፅ ወደ እስራኤል እንዲመለስ ነገረው፡፡

እኛም  በሕይወታችን ለእግዚአብሔር ታማኞች ታዛዦች ከሆንን እርሱን ከልባችን በማፍቀር በእርሱ እቅድ የምንመላለስ ከሆንን እሱ ሁሌም ከእኛ ጋር ይሆናል በለመለመው መስክም ይመራናል፡፡ ለዚህም ደግሞ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የብዙሃን እናት የሆነች ከልጇ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  ይህን የማያልቀውን ፀጋና በረከትን ታማልደን፡፡  

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 








All the contents on this site are copyrighted ©.