2018-01-09 09:53:00

ካርዲናል ኦናየካን፣ በናይጀሪያ ማብቂያ የሌለው አመጽ እንደሚካሄድ ተናገሩ።


ካርዲናል ኦናየካን፣ በናይጀሪያ ማብቂያ የሌለው አመጽ እንደሚካሄድ ተናገሩ።

ጠንካራ መንግሥት ካለመኖሩ የተነሳ የእምነት ተቋማትን ጨምሮ በሁሉም የሃገሪቱ ክፍሎች አመጽ እየተስፋፋ መሄዱንና የሕዝቡም ተስፋ መጨለሙን ካርዲናል ኦናየካን ገለጹ።

በናይጀሪያ የሕዝቡ ሕይወት አደጋ ላይ የወደቀው ቦኮ ሃራም የተባለ አማጺ ቡድን በሚያደርሰው ጥቃት ብቻ ሳይሆን ሕዝቡ እርስ በርስ በሚያነሳው ብጥብጥ የበርካታ ሰዎች ሕይወት እየጠፋ እንደሆነ ካርዲናሉ ገልጸዋል። በቅርቡ ፉላኒ በተባሉ ዘላን ማሕበረሰብ፣ መንግሥት ባወጣው ሕግ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ለመግለጽ በተቀሰቀሰው አመጽ 20 ሰዎች መሞታቸው ታውቋል። ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በመካከለኛው ናይጀሪያ በኑወ በተባለ ግዛት፣ በሙስሊሙና በእርሻ በሚተዳደሩ ክርስቲያኖች መካከል በተቀሰቀሰው ግጭት ከ300 በላይ ሰዎች መሞታቸው ታውቋል። ባለፈው ረቡዕ በሰሜን ናይጀሪያ፣ ቦሮ ግዛት ዉስጥ በአንድ መስጊድ ላይ በተፈጸመ ጥቃት ቢያንስ 10 ሰዎች መሞታቸው ታውቋል። በደቡባዊ ምስራቅ ናይጀሪያም በአንድ ቤተክርስቲያን ላይ በተከፈተው ተኩስ 16 ሰዎች መገደላቸው ታውቋል።

በኢጉሪያኪ ግዛት ከአንድ ገዳም ታግተው የተወሰዱትን ስድስት ደናግል ለማስለቀቅ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቢማጸኑም ደናግሉ እስካሁን አልተለቀቁም። በሌሎችም የሃገሪቱ ክፍሎች በሚታዩ የጸጥታ መጓደል ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ማደጉን የተገነዘቡት የአቡጃው ሊቀ ጳጳስ፣ ካርዲናል ጆን ኦናየካን፣ የናይጀሪያን መንግሥት ኮንነዋል። ካርዲናሉ እንዳሉት የናይጀሪያ ሕዝብ መንግሥት መላ ቢያገኝ በማለት ጥያቄ ቢያቀርብም መንግሥት በቂ ምላሽ መስጠት አልቻለም ብለዋል። ሕዝቡ ያቀረበው ጥያቄ በሌሎች መንግሥታት በኩል መልስ የሚሰጥበት ከሆነ የናይጀሪያ መንግሥት መልስ የማይሰጥበት ምክንያት አይታየኝም ብለው ጥያቄውም እጅግ አንገብጋቢና በተለይም የመኖር ዋስትናንና የሕዝቡን ጸጥታ የማስከበር ጥያቄ ነው ካሉ በኋላ የናይጀሪያ መንግሥት ይህን የሕዝብ ጥያቄ መመለስ ካልቻለ የአስተዳደር ብቃት ማነስና ሃላፊነትን ለመውሰድ ካለመፈለግ ነው ብለዋል።

በናይጀሪያ አመጸኞች በየቦታው ጥቃት እያደረሱ ነው። በጎሳዎች መካከል የሚነሱ ግጭቶች ወይም ሃብት መቀራመትን ተከትሎ የሚነሱ ግጭቶች ናቸው ያሉት ካርዲናል ኦናየካን፣ የእነዚህ ጥቃቶች ሰለባ የሚሆነው ንጹሐን ክርስቲያን ወይም ሙስሊሙ ሕዝብ ነው ብለዋል። በሰሜናዊው የሃገሪቱ ክፍል የሚኖሩ ሕዝቦች ዘላን ሲሆኑ የደቡቡ ክፍል ሕዝብ በእርሻ የሚተዳደር በመሆኑ፣ ዘላኑ ሕዝብ ወደ ደቡብ ለም አካባቢዎች በሚጓዝበት ጊዜ ገበሬዎች ማሳቸውን ለመከላከል በሚያደርጉት ወቅት ግጭቶች ሊከሰቱ ይችላል ብለዋል። ምንም እንኳን ዘላኑ የእስልምና እምነት ተከታይ፣ በእርሻ የሚተዳደሩት ደግሞ የክርስትና እምነት ተከታዮች  ቢሆኑም ግጭቱ በሃይማኖቶች መካከል የሚደረግ እንዳልሆነ አስረድተዋል።

ታግተው ስለቆዩ ደናግል ጉዳይ ሲያስረዱ ካርዲናል ኦናየካን፣ ከአጋቾቹ ጋር ድርድር በመካሄድ ላይ እንዳለ ተናግረው የገንዘብ ክፍያ ጥያቄ ቀርቦ እንደነበር ነገር ግን ለተመሳሳይ ክስተቶች በሙሉ የገንዘብ ቤዛ ከፍሎ መጨረስ የማይቻል ስለሆነ ገንዘብ መክፈሉ የቤተክርስቲያናቸው ፍላጎት አይደለም ብለው ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለስልጣናት ጋር ድርድሩ ቀጥሏል ብለዋል። በሌላ ወገንም ከመላው ምዕመናን ጋር ሆነን በጸሎት መበርታት ይኖርብናል ብለዋል።     

          








All the contents on this site are copyrighted ©.