Social:

RSS:

የቫቲካን ሬድዮ

ከዓለም ጋር የሚወያይ የር.ሊ.ጳጳሳትና የቤተ ክርስትያን ድምጽ

ቋንቋ:

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ \ አጠቃላይ ትምህርተ ክርስቶስና የመልአከ እግዚአብሔር ጉባኤ አስተምህሮ

በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ካልሆነ የጌታ ምስክሮች ለመሆን ኣይቻልም! ር.ሊ.ጳ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ - AFP

15/12/2017 15:20

"ከሳምንቱም በፊተኛው ቀን መግደላዊት ማርያም ገና ጨለማ ሳለ ማለዳ ወደ መቃብር መጣች ድንጋዩም ከመቃብሩ ተፈንቅሎ አየች። … ያም ቀን እርሱም ከሳምንቱ ፊተኛው በመሸ ጊዜ፥ ደቀ መዛሙርቱ ተሰብስበው በነበሩበት፥ አይሁድን ስለ ፈሩ ደጆቹ ተዘግተው ሳሉ፥ ኢየሱስ መጣ፤ በመካከላቸውም ቆሞ። ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው። ይህንም ብሎ እጆቹንም ጎኑንም አሳያቸው። ደቀ መዛሙርቱም ጌታን ባዩ ጊዜ ደስ አላቸው። ኢየሱስም ዳግመኛ። ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ አብ እንደ ላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ አላቸው። ይህንም ብሎ እፍ አለባቸውና። መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ። ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል አላቸው።" (ዮሓ 20 1፣19-23)

የተከበራችሁ ወንድሞችና እኅቶች! እንደምን ኣደራችሁ! ስለቅዳሴ የጀመርነውን ትምህርት በመቀጠል በዛሬው ዕለት ‘ለመሆኑ ለምንድር እሁድ ዕለት ለማስቀደስ የምንሄደው!` የሚለውን ጥያቄ እንቃኛለን፣ ኣዲሱ የካቶሊካዊት ቤተክርስትያን ትምህርተ ክርስቶስ ቊ.2177 ላይ ‘በጌታ ቀን የሚከናወነው የእሁድ ክብረ በዓል እና መሥዋዕተ ቅዳሴ የቤተ ክርስትያን ሕይወት እምብርት ነው` ይላል፣ እኛ ክርስትያኖች እሁድ ዕለት ወደ ቅዳሴ የምንሄድበት ዋና ምክንያት ከሙታን ተለይቶ የተነሣውን ጌታ ለማግኘት በበለጠም እርሱ እንዲያገኘን ልንፈቅድለት እንዲሁም ቃሉን ለመስማትና በማእዱ ለመሳተፍ ብሎም በዓለማችን የምሥጢራዊ ሰውነቱ ኣባሎች በመሆን ቤተክርስትያን እንሆናለን፣

የኢየሱስ ሓዋርያት ከመጀመርያ ግዜ ኣንስተው ይህንን ተረድተው በሳምንቱ ኣንድ ግዜ ማለት ዕብራውያን የሳምንተ መጀመርያ ቀን ሮማውያን ደግሞ የፀሓይ ቀን ብለው በሚጠሩት ቀን የቊርባን ግኑኝነት ያደርጉ ነበር! ምክንያቱም እላይ ሲነበብ እንደሰማነው ጌታ ኢየሱስ በዛው ዕለት ከሙታን ተለይቶ በመነሳቱና ከሓዋርያት ጋር ተገናኝቶ መነጋገሩና መመገቡ ብሎም መንፈስ ቅዱስ የሰጣቸው ዕለት ስለሆነ ነው (ማቴ28.1 ማር 16.9.14 ሉቃ 24.1.13 ዮሓ 20,1.19)፣  ታላቁ ርደተ መንፈስ ቅዱስም ማለት በዕለተ ጰራቅሊጦስ የተፈጸመው መንፈስ ቅድስ እንደ እሳት ልሳን በእመቤታችን ድንግል ማርያምና ሓዋርያት የወረደበት ዕለትም ማለት ከኢየሱስ ትንሣኤ በሃምሰኛው ቀን የተፈጸመውም በዕለተ ሰንበት ነበር፣ ስለዚህ እሁድ ማለትም ዕለተ ሰንበት ለእኛ ቅድስት ዕለት ናት! የምትቀደሰውም ያ ጌታ ኢየሱስ በመካከላችን ሕያው ሆኖ ለእኛ የሚሰጥበት ምሥጢረ ጥቀ ቅዱስ ቊርባን በማቅረብ ነው፣ እሁድ ዕለትን የክርስትያን ታላቅ ዕለት የሚያደርገው መሥዋዕተ ቅዳሴ ነው፣ ስለዚህ ይህ ከጌታ ጋር የመገናኘት ፍጻሜ የሌለበት እሁድ ለክርስትያኖች ምን እሁድ ሊሆን ይችላል፣

ኣንዳንድ ማሕበረ ክርስትያኖች በየሳምንቱ እሁድ ዕለት መሥዋዕተ ቅዳሴ ሊያገኙ ኣይችሉም፣ ችግሩ ጉልህ ቢሆንም እነዚሁ ማሕበረ ክርስትያኖች በዚሁ ቅዱስ ዕለት እሁድ ዕለት የጌታን ቃል በመስማትና ለቅዱስ ቊርባን ያላቸውን ፍላጐት ሕያው በማድረግ በጌታ ስም በጸሎት መሰብሰብ ኣለባቸው፣

ኣንዳንድ በዓለማውነት የተሸነፉ ማሕበረክርስትያኖች ደግሞ በቅዱስ ቊርባን ያሸብረቀች እሁድ ክርስትያናዌ ትርጓሜን የረሱ ኣሉ፣ ይህ ኣስከፊ ሓጢኣት ነው፣ እንዲህ ባለ ኣከባቢ የዕለተ ሰንበት ታላቅነት እንዲሁም ዋነኛ ትርጉምዋ የጌታ ቀን የደስታ ቀን የማሕበረክርስትያን ቀን የኣጋርነት ቀን የስጋዊና መንፈሳዊ ዕረፍት ቀን መሆኑን ማስታወስ ያስፈልጋል (ኣዲስ የካቶሊካዊት ቤተክርስትያን ትምህርተ ክርስቶስ ከቊ. 2177-2188 ተመልከት)። በእነዚህ ዕሴቶች በየእሁዱ የሚያስተምረን ቅዱስ ቊርባን ነው፣ ለዚህም ነው ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ በቤተክርስትያን ሥርዓተኣምልኮ ሰነድ ቊ 106 ‘መነሻውን ከክርስቶስ ዕለት ትንሣኤ የወሰደ ሓዋርያዊ ትውፊትን መሠረት በማድረግ ቤተክርስትያን ፋሲካዊ ምሥጢርን በየሳምንቱ ክብረ በዓል ታደርጋለች፣ ከዚህም የተነሣ ይህ ቀን የጌታ ቀን ወይም እሁድ የሚል ስም ወጥቶለታል፣ . ስለዚህ ይህ ቀን በእውነት የደስታን የዕረፍት ጊዜ እንዲሆን ምእመናንን ማስተማር ያስፈልጋል’ ይላል፣

በሰንበት ከሥራ ዕረፍት ማድረግ በመጀመርያ የክርስትና ዘመናት የተለመደ ኣልነበረም በክርስትና ታሪክ የተፈጠረ ነው፣ በቅዱስ መጽሓፋዊ ባህል ዕብራውያን ቅዳሜ ዕለት ዕረፍት ያደርጉ ነበር በሮማውያን ማሕበረሰብ ግን በሳምንት ኣንድ ቀን ከሥራ ዕረፍት ማድረግ የግድ ነበር፣ በቅዱስ ቊርባን ኰትኲቶ እንደ ነጻ ልጆች እንጂ እንደባሮች ሳይሆን እሁድ ዕለትን እንደዓለም ኣቀፍ የዕረፍት ቀን እንዲሆን ትርጉም የሰጠው ክርስትያናዊ ትርጓሜ ነው፣

በሕይወታችን ክርስቶስ የሌለ እንደሆነ በዕለታዊ ድካም ችግሮች እንዲሁም የበሚመጣው ግዜ ፍራቻ ስር እንወድቃለን። በዕለተ እሁድ ከጌታ የምናደርገው ግኑኝነት የዛሬውን ዕለት በብርታት እንድንኖርና የሚመጣውን በተስፋ ለማጋፈጥ ያስችለናል፣ ስለዚህም ነው እኛ ክርስትያን በቅዱስ ቁርባን ሥርዓት ጌታን ለማግኘት ወደ ቤተርስትያን እንሄዳለን፣

ከሙታን ተለይቶ ከተነሣና ዘለዓለም ሕያው ከሆነው ኢየሱስ ጋር በቅዱስ ቊርባን መገናኘት ያ መጨረሻ የሌለው ዘለዓለማዊ እሁድ ድካምም ይሁን ስቃይ ሓዘንም ይሁን እንባ የማይኖርበት ነገር ግን በሙላት ለዘለዓለም ከጌታ ጋር የመኖር እሁድ መቅድም ነው፣ ስለዚሁ የብፅዕና ዕረፍት የእሁድ ቅዳሴ በየሳምንቱ እየተጓዘ በሰማይ ያለ ኣባታችን እጆች እንድናኖር ያስተምረናል፣

ምናልባት ዋናው ነገር በጥሩ መኖር ጓደኛን ማፍቀር ነው እንጂ በቅዳሴ መሳተፍ ኣያስፈልግም ብለው ለሚናገሩ ምን ማለት ይቻላል! ኢየሱስ በዮሓንስ ወንጌል 13.35 ‘እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፥ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ።’ እንዳለው ሁሉ የክርስትና የሕይወት ሚዛን በፍቅር እንደሆነ የማይካድ እውነት ነው፣ ነገር ግን የሚያስፈልገንን ጉልበት ለማግኘት እሁድ እሁድ ከማይደርቀው የቅዱስ ቊርባን ምንጭ መመገብ ያስፈልገናል፣ ወደ መሥዋዕተ ቅዳሴ የምንሄደው ለእግዚኣብሔር የሆነ ነገር ለመስጠት ሳይሆን የሚያስፈልገንን ነገር ከእርሱ ለማግኘት ነው የምንሄደው፣ በሮማሚው ኣራተኛ ኣኰቴተ ቊርባን ማለት የምስጋና ጸሎት ላይ እንደሚያመልክተው ‘ኣንተ የእኛ ምስጋና ኣያስፈልግህም ነገር ግን ያንተ የፍቅር ስጦታ እንድናመስግንህ ጥሪ ያቀርብልናል፣ የምስጋና ውዳሴዎቻችን ታላቅነትህ ላይ ምንም ኣይጨምሩም ነገር ግን የሚያድነን ጸጋ ያስገኙናል’ ሲል ጸሎት ያሳርጋል፣

እመጨረሻ ላይ እሁድ ለምን እናስቀድሳለን! ለሚለው ጥያቄ የቤተክርስትያን ትእዛዝ ስለሆነ ብሎ መመለስ ብቻው ኣይበቃም፣ ይህ ትእዛዝ ዕሴቱን ይዞ ወደፊት ለመራመድ ይረዳናል ነገር ግን ይህ ብቻ በቂ ኣይደለም፣ በሕይወታችንና በመካከላችን ሕያው ሆኖ በሚኖረው በጌታ ኢየሱስ ጸጋ ብቻ ትእዛዛቱን ለማክበርና ታማኝ የእርሱ ምስክር ለመሆን ስለምንችል እኛ ክርስትያኖች የግድ በእሁድ ቅዳሴ መሳተፍ ኣለብን። እግዚብሔር ይስጥልኝ፣

15/12/2017 15:20