2017-12-09 14:33:00

የታህሣሥ 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ዘአስተምሕሮ 4ኛ ሰንበት አስተንትኖ እና ቃለ እግዚኣብሔር በክቡር አባ ግርማቸው ተስፋዬ


የታህሣሥ 1 ቀን 2010 .. የሰንበት ዘመፃጕዕ ወይም ዘአስተምሕሮ 4 ሰንበት የቃለ እግዚኣብሔር አስተንትኖ እና ምንባባት በኩብር አባ ግርማቸው ተስፋዬ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ካህን

 

የእለቱ ምንባባት

  1. 1ኛ ቆሮ 2፡1-16

  2. 1ኛ ዩሐንስ 5:1-5

  3. የዩሐንስ ወንጌል 9፡1-41

የዚህን አስተንትኖ ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

 

1ኛ ቆሮ 2፡1-16

ወንድሞች ሆይ፤ ወደ እናንተ በመጣሁ ጊዜ፣ የእግዚአብሔርን ምስጢር በረቀቀ የንግግር ችሎታ ወይም በላቀ ጥበብ ልገልጥላችሁ አልመጣሁም። በመካከላችሁ ሳለሁ ኢየሱስ ክርስቶስን ያውም የተሰቀለውን፣ እርሱን ብቻ እንጂ ሌላ እንዳላውቅ ወስኜ ነበርና። ወደ እናንተ የመጣሁት በድካምና በፍርሀት፣ እንዲሁም በብዙ መንቀጥቀጥ ነበር። 4ቃሌም ስብከቴም የመንፈስን ኀይል በመግለጥ እንጂ፣ በሚያባ ባል የጥበብ ቃል አልነበረም፤ ይኸውም እምነታችሁ በእግዚአብሔር ኀይል እንጂ በሰው ጥበብ ላይ እንዳይመሠረት ነው።

ከመንፈስ የተገኘ ጥበብ

በበሰሉ ሰዎች መካከል ግን ጥበብን እንናገራለን፤ ይሁን እንጂ የዚችን ዓለም ጥበብ ወይም የሚጠፉትን የዚችን ዓለም ገዦች ጥበብ አይደለም። ነገር ግን ተሰውሮ የነበረውን የእግዚአብሔርን ምስጢር ጥበብ ነው፤ ይህም ጥበብ እግዚአብሔር ከዘመናት በፊት ለክብራችን አስቀድሞ የወሰነው ነው። ከዚህ ዓለም ገዦች አንዳቸውም ይህን ጥበብ አልተረዱትም፤ ቢረዱትማ ኖሮ የክብርን ጌታ ባልሰቀሉት ነበር። ይሁን እንጂ፣ እንደ ተጻፈው፣

“ዐይን ያላየውን፣

ጆሮ ያልሰማውን፣

የሰውም ልብ ያላሰበውን፣

እግዚአብሔር ለሚወዱት አዘጋጅቶአል፤”

እግዚአብሔር ግን ይህን በመንፈሱ አማካይነት ለእኛ ገልጦልናል።

መንፈስም የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር እንኳ ሳይቀር ሁሉን ይመረምራል። በውስጡ ካለው ከራሱ መንፈስ በስተቀር ከሰው መካከል የአንድን ሰው ሐሳብ የሚያውቅ ማን አለ? እንደዚሁም ከእግዚአብሔር መንፈስ በስተቀር፣ የእግዚአብሔርን ሐሳብ የሚያውቅ ማንም የለም። ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ፣ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንምና፤ ይህም እግዚአብሔር በነጻ የሰጠንን እናውቅ ዘንድ ነው። እኛ የምንናገረው ይህን ነው፤ ከሰው ጥበብ በተማር ነው ቃል ሳይሆን፣ ከመንፈስ በተማር ነው ቃል እንናገራለን፤ መንፈሳዊ እውነትንም የምንገልጸው በመንፈሳዊ ቃል ነው። መንፈሳዊ ያልሆነ ሰው ከእግዚአብሔር መንፈስ የሆነውን ነገር ሊቀበል አይችልም፤ ምክንያቱም እንዲህ ያለው ነገር ለእርሱ ሞኝነት ነው፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ፣ ሊረዳው አይችልም። 15መንፈሳዊ ሰው ግን ሁሉንም ነገር ይመረምራል፤ ራሱ ግን በማንም አይመረመርም።

“ያስተምረው ዘንድ፣

የጌታን ልብ ማን ዐወቀው?”

እኛ ግን የክርስቶስ ልብ አለን።

 

1ዩሐ5፡1-5

በእግዚአብሔር ልጅ ማመን

ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ የሚያምን ሁሉ ከእግዚአብሔር ተወልዶአል፤ አባትንም የሚወድ ሁሉ ልጁንም እንደዚሁ ይወዳል። እግዚአብሔርን ስንወድና ትእዛዛቱን ስንፈጽም የእግዚአብሔርን ልጆች እንደ ምንወድ በዚህ እናውቃለን፤

እግዚአብሔርን መውደድ ትእዛዛቱን መፈጸም ነውና። ትእዛዛቱም ከባድ አይደሉም፤ ምክንያቱም ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋል። ዓለምን የሚያሸንፈውም እምነታችን ነው። ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ከሚያምን በስተቀር ዓለምን የሚያሸንፍ ማነው?

 

የዩሐንስ ወንጌል 9፡1-41

ኢየሱስ ዐይነ ስውር ሆኖ የተወለደውን ሰው ፈወሰ

በመንገድ ሲያልፍም ከተወለደ ጀምሮ ዐይነ ስውር የሆነ ሰው አየ። ደቀ መዛሙርቱም፣ “ረቢ፤ ይህ ሰው ዐይነ ስውር ሆኖ እንዲወለድ ኀጢአት የሠራ ማን ነው? እርሱ ራሱ ወይስ ወላጆቹ?” ብለው ጠየቁት።

ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እርሱ ወይም ወላጆቹ ኀጢአት አልሠሩም፤ ይህ የሆነው ግን የእግዚአብሔር ሥራ በእርሱ ሕይወት እንዲገለጥ ነው። ቀን ሳለ፣ የላከኝን ሥራ መሥራት አለብን፤ ማንም ሊሠራ የማይችልበት ሌሊት ይመጣል፤ በዓለም ሳለሁ የዓለም ብርሃን እኔ ነኝ።”

ይህን ካለ በኋላ፣ በምድር ላይ እንትፍ ብሎ በምራቁ ጭቃ አበጀ፤ የሰውየውንም ዐይን ቀባና፣ “ሄደህ በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብ” አለው፤ ሰሊሆም ማለት ‘የተላከ’ ማለት ነው። ሰውየውም ሄዶ ታጠበ፤ እያየም ተመልሶ መጣ።

ጎረቤቶቹና ከዚህ ቀደም ብሎ ሲለምን ያዩት ሰዎች፣ “ይህ ሰው ተቀምጦ ሲለምን የነበረው አይደለምን?” አሉ። አንዳንዶቹም፣ “በርግጥ እርሱ ነው” አሉ። ሌሎችም፣ “ይመስለዋል እንጂ እርሱ አይደለም” አሉ። እርሱ ግን፣ “እኔው ነኝ” አለ። እነርሱም፣ “ታዲያ ዐይኖችህ እንዴት ተከፈቱ?” ሲሉ ጠየቁት። እርሱም፣ “ኢየሱስ የሚሉት ሰው ጭቃ አድርጎ ዐይኔን ቀባኝ፤ ወደ ሰሊሆም ሄጄ እንድታጠብም ነገረኝ፤ ሄጄ ታጠብሁ፤ ማየትም ቻልሁ” ሲል መለሰ። እነርሱም፣ “ታዲያ፣ ያ ሰው የት አለ?” አሉት። እርሱም፣ “እኔ አላውቅም” አለ።

ፈሪሳውያን ሰውየው እንዴት እንደ ተፈወሰ ማጣራት ቀጠሉ

እነርሱም ዐይነ ስውር የነበረውን ሰው ወደ ፈሪሳውያን ወሰዱት። ኢየሱስ ጭቃ የሠራበት፣ የሰውየውንም ዐይን የከፈተበት ቀን ሰንበት ነበር። ስለዚህ ፈሪሳውያንም እንዴት ማየት እንደ ቻለ ጠየቁት። ሰውየውም፣ “እርሱ ዐይኔን ጭቃ ቀባኝ፤ እኔም ታጠብሁ፤ ይኸው አያለሁ” አላቸው።

ከፈሪሳውያንም አንዳንዶቹ፣ “ይህ ሰው ሰንበትን ስለማያከብር፣ ከእግዚአብሔር አይደለም” አሉ። ሌሎች ግን፣ “ኀጢአተኛ፣ እንዲህ ያሉትን ታምራዊ ምልክቶች እንዴት ሊያደርግ ይችላል?” አሉ። በመካከላቸውም አለመስማማት ተፈጠረ።

ስለዚህ፣ ዐይነ ስውር ወደ ነበረው ሰው ተመልሰው፣ “ዐይንህን ስለ ከፈተው ሰው፣ እንግዲህ አንተ ምን ትላለህ?” አሉት። ሰውየውም፣ “እርሱ ነቢይ ነው” አለ።

አይሁድ ወደ ወላጆቹ ልከው እስኪያስ ጠሯቸው ድረስ፣ ሰውየው ዐይነ ስውር እንደ ነበረና እንዳየ አላመኑም ነበር። እነርሱም፣ “ዐይነ ስውር ሆኖ ተወልዶአል የምትሉት ልጃችሁ ይህ ነውን? ታዲያ አሁን እንዴት ሊያይ ቻለ?” አሏቸው።

ወላጆቹም እንዲህ ሲሉ መለሱ፤ “ልጃችን መሆኑንና ዐይነ ስውር ሆኖ መወለዱን እናውቃለን፤ አሁን ግን እንዴት ማየት እንደቻለና ዐይኖቹን ማን እንደ ከፈተለት እኛ አናውቅም። ሙሉ ሰው ስለ ሆነ፣ ስለ ራሱ መናገር ይችላልና እርሱን ጠይቁት።” ኢየሱስን፣ ክርስቶስ ነው ብሎ የመሰከረ ሁሉ ከምኲራብ እንዲባረር አይሁድ አስቀድመው ወስነው ስለ ነበር፣ ወላጆቹ ይህን ያሉት አይሁድን ፈርተው ነው። 23ስለዚህ ወላጆቹ፣ “ሙሉ ሰው ስለ ሆነ እርሱን ጠይቁት” አሉ።

ዐይነ ስውር የነበረውንም ሰው ዳግመኛ ጠርተው፣ “አንተ ሰው፤ እግዚአብሔርን አክብር፤ይህ ሰው ኀጢአተኛ መሆኑን እኛ እናውቃለን” አሉት።

እርሱም፣ “ኀጢአተኛ መሆኑን እኔ አላውቅም፤ ነገር ግን ዐይነ ስውር እንደ ነበርሁ፤ አሁን ግን እንደማይ ይህን አንድ ነገር ዐውቃለሁ” አለ።

እነርሱም፣ “ምን አደረገልህ? እንዴትስ ዐይንህን ከፈተ?” ብለው ጠየቁት። እርሱም፣ “አስቀድሜ ነገርኋችሁ፤ አላዳመጣችሁኝም፤ ለምን እንደ ገና መስማት ፈለጋችሁ? እናንተም ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ ልትሆኑ ትሻላችሁ?” አለ።

ከዚህ በኋላ በእርሱ ላይ የስድብ ናዳ በማውረድ እንዲህ አሉት፤ “የዚህ ሰው ደቀ መዝሙር አንተ ነህ፤ እኛስ የሙሴ ደቀ መዛሙርት ነን! 29እግዚአብሔር ሙሴን እንደ ተናገረው እናውቃለን፤ ይህ ሰው ግን ከየት እንደ መጣ እንኳ አናውቅም።”

ሰውየውም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እናንተ ከየት እንደ መጣ አለማወቃችሁ የሚያስደንቅ ነው፤ ይሁን እንጂ እርሱ ዐይኖቼን ከፈተልኝ። እግዚአብሔር የሚሰማው፣ የሚፈራውንና ፈቃዱን የሚያደርገውን እንጂ፣ ኀጢአተኞችን እንደማይሰማ እናውቃለን፤ ዐይነ ስውር ሆኖ የተወለደን ሰው ዐይን የከፈተ አለ ሲባል፣ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ማንም ሰምቶ አያውቅም። ይህ ሰው ከእግዚአብሔር ባይሆን ኖሮ ይህን ማድረግ ባልቻለ ነበር።”

እነርሱም፣ “ሁለንተናህ በኀጢአት ተነክሮ የተወለድህ፣ አንተ እኛን ለማስተማር እንዴት ትደፍራለህ?” ሲሉ መለሱለት፤ አባረሩትም።

መንፈሳዊ ዕውርነት

ኢየሱስም ሰውየውን እንዳባረሩት ሰማ፤ ባገኘውም ጊዜ፣ “በሰው ልጅ ታምታምናለ ህን?” አለው። ሰውየውም፣ “ጌታዬ፤ አምንበት ዘንድ እርሱ ማን ነው?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም፣ “አይተኸዋል፤ አሁንም ከአንተ ጋር የሚነጋገረው እርሱ ነው” አለው። ሰውየውም፣ “ጌታ ሆይ፤ አምናለሁ” አለ፤ ሰገደለትም። ኢየሱስም፣ “ዕውሮች እንዲያዩ፣ የሚያዩም እንዲታወሩ፣ ለፍርድ ወደዚህ ዓለም መጥቻለሁ” አለ። ከእርሱ ጋር ከነበሩት ፈሪሳውያን አንዳንዶቹ ይህን ሰምተው፣ “ምን ማለትህ ነው? ታዲያ እኛም ዕውሮች መሆናችን ነው?” አሉት። ኢየሱስም፣ “ዕውሮችስ ብትሆኑ ኀጢአት ባልሆነባችሁ ነበር፤ አሁን ግን እናያለን ስለምትሉ፣ ኀጢአታችሁ እንዳለ ይኖራል” አላቸው።

 

የታህሣሥ 1 ቀን 2010 .. የሰንበት ዘመፃጕዕ ወይም ዘአስተምሕሮ 4 ሰንበት የቃለ እግዚኣብሔር አስተንትኖ እና ምንባባት በኩብር አባ ግርማቸው ተስፋዬ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ካህን

 

በክርሰቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ ዛሬ እንደ ቤተክርስቲያናችን አቆጣጠር ዘመፃጕዕ ወይም ዘአስተምሕሮ 4ኛ ሰንበትን እናከብራለን ፡፡

በዚህም ዕለት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በተነበቡት ንባባት አማካኝነት ለእያንዳንዳችን የሚሆን የሕይወት ስንቅ ይሰጠናል የሕይወት ምግብ ይመግበናል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል እንደ ወትሮው ዛሬም ወደ እያንዳንዳችን ይሠርፃል ፤ እኛም ወደኛ የመጣውን ቃል ሰሚዎች ብቻ ሳንሆን በተግባር እንድናውለው ያስፈልጋል፡፡

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያ መልእክቱ ከጌታችን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበለውን አምነቱን ለእነዝህ ለቆሮንጦስ ሰዎች በሙሉ እምነት ይሰብክላቸው እንደ ነበር ይናገራል፡፡ ስለዚህ ዛሬ በአጭሩ ንጉሥ የሆነ ክርስቶስ እምነታችንን በተግባር አንድናውለው ይጠየቀናል፡፡

እነዚህ የቆሮንቶስ ሰዎች ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም  ሆነ ስለ ክርስትና እምነት ምንም የሚያውቁት ነገር አልነበረም ነገር ግን እርሱ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በሚናገረው ቃል ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ሥራውን ይሰራ ነበር፡፡

ይህ መንፈስ ቅዱስ ነው የሰዎቹን ልብ እያቀሰቀሰ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲያምኑና እንዲጠመቁ ሆነ፡፡

ሰው በእግዚአብሔር መንፈስ ካልተመራ በስተቀር የእግዚአብሔር ቃል ወደ እርሱም ቢመጣ እንኳን ምን እንደሆነ ሊረዳሙ አይችልም፡፡

እግዚአብሔር ወልድ ወደ ምድር ሲመጣ የእግዚአብሔር አብ ምሥጢር መሙላት በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ተገልጧል፡፡

ይህ የቅዱስ ስላሴ ሦስተኛ አካል እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ዛሬም በቤታችን፣በእያንዳንዳችን ውስጥ አድሮ የእግዚአብሔርን ቃል እንድንረዳና በቃሉም መሠረት እንድንኖር ያግዘናል፡፡

በእግዚአብሔር መንፈስ የምንመራ ከሆንን የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ በውስጣችን ያድራል፡፡  የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ደግሞ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በገላ. 5፡22 እንደገለፀው ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግስት፣ ቸርነት፣በጐነት፣ እምነት፣ የዋህነተ፣ ራስን መግዛት ናቸው ይላል፡፡

ስለዚህ የእግዚአብሔር መንፈስ በውስጣችን እንዲያድር እንደ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በሙሉ እምነት ራሳችንን ክፍት እናድርግለት፡፡

ቅዱስ መንፈስ በውስጣችን ሲያድር ሁሉንም ነገር በሙለት ይገልፅልናል እኛም ልክ እንደ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ” በመካከላችሁ ሳለው ከእየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ ነገር እንዳላውቅ ቆርጬ ነበር፡፡”  ብሎ እንደተናገረው እኛም ይህ መንፈስ በውስጣችን ሲያድር አካሄዳችን፣ አስተሳሰባችን፣ እንቅስቀሴያችን ሁሉ በእግዚአብሔር መንፈስ የተመራ ይሆንልናል ፡፡

ቅዱስ ሐዋርያው ዩሐንስ በመልዕክቱ የዓለምን ፈተና ሁሉ ለማሸነፍ የእግዚአብሔርንም ትዕዛዝ ለመጠበቅ ከእግዚአብሔር መንፈስ መወለድ እንደሚያስፈልግ ይናገራል፡፡

ይህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኒቆዲሞስ ለሚባል የሙሴ ሕግ መምህር የተናገረው ቃሉ ነው “እውነት እውነት እልሃለው ሰው ከውኃና ከመንፈስ ላልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም” ዬሐ.3፡5

ቅዱስ ሐዋርያው ዩሐንስ በመቀጠል እግዚአብሔርን መውደድና ባልንጀራን መውደድ አንድ መሆናቸውን ይናገራል፡፡  እግዚአብሔርንና ባልንጀራን መውደድ ማለት በአጭሩ ከራስ ወዳድነት ሥሜት ነፃ መሆን ማለት ነው ለራሴ ብቻ ከሚለው ሐሳብ ወጥተን ለሌሎችም ማሠብ መቻል ማለት ነው ለራሴ ብቻ ከሚለው ሐሳብ ወጥተን ሌሎችም እኔ የሚያስፈልገኝ ነገር ሁሉ እንደሚያስፈልጋችው መገንዘብ ማለት ነው ፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔርን ወዳለው የሚል ሠው ባልንጀራዬን እወዳለው የሚል ሠው ከራስ ወዳድነት ስሜት የተላቀቀ ሊሆን ይገባዋል፡፡

ሌሎችን በምንችለው አቅማችን ስንረዳ በእርግጥም እግዚአብሔርን በፍጹም ኃይላችን፣ በፍጹም ልባችን እንደምንወድ እናረጋግጣለን ማለት ነው፡፡

የዮሐንስ ወንጌልም ስለ አንድ እውር ሆኖ ስለተወለደ ሰው ይናገራል፡፡  ይህ ሰው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳዘዘው በሙሉ እምነት ሄዶ በሰሊሆም መጠመቂየ ታጠበ ተፈወሰም፡፡

ከዛም በኃላ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሰከረ “እግዚአብሔርን የሚፈራ ፈቃዱንም የሚያደርግ ቢኖር ያንን እግዚአብሔርን ይሰማዋል አለ”

እኛም ዛሬ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚሰጠን ቃል፣ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በእምነት ከተጓዝን እግዚአብሔር በእርግጥም ጸሎታችንን ይሰማል፣ ሕሳባችንን ሁሉ ይሞላልናል፡፡  ስለዚህ ዘወትር በእግዚአብሔር መንፈስ ለመመላለስ አንደ እርሱ ፈቃድ ለመመላለስ ጥረት እናድርግ፡፡

መጽሐፈ ምሳሌ 15፡29 “እግዚአብሔር ከኃጥአን ይርቃል የፃድቃንን ጽሎት ግን ይሰማል” ይላል  እኛም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንደንመላለስ፣ ጸሎታችንን፣ እንዲሰማንና ሐሳባችንን እንዲሞላልን የጽድቅን ጉዞ እንጀምር  ኃጢአትንና የኃጢአትን ዝንባሌ ሁሉ ልክ በሰሊሆም መጠመቂየ ታጥቦ እንደተፈወሰው  በምስጢ ንስሃ ታጥበን እንፈወስ፡፡ ለዚህም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የክርስቲያኖች ረዳት የሆነች ከልጇ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን ፀጋና በረከት ታማልደን የሰማነውን በልባችን ያሳድርልን፡፡

 








All the contents on this site are copyrighted ©.