2017-11-25 14:33:00

ኀዳር 17 ዘቅድስት /ዘአስተምሕሮ 2ኛ/ ቃለ እግዚኣብሔር አስተንትኖ በኩብ አባ ግራማቸው ተስፋዬ


ኀዳር 17 ዘቅድስት /ዘአስተምሕሮ 2/

አስተንትኖ በኩቡር አባ ግራማቸው ተስፋዬ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ካህን

የእለቱ ምንባባት

  1. 112-29
  2. 1ጴጥ 113-20
  3. የሐ.. 19 21-40 
  4. የዩሐንስ ወንጌል  516-27

የዚህን አስትንትኖ ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተቫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

ቆላ 1፡12-29

በቅዱሳን ርስት በብርሃን ተካፋዮች ለመሆን ያበቃንን አብን እንድታመሰግኑ ነው። እርሱ ከጨለማ አገዛዝ ታደገን፤ ወደሚወደው ልጁ መንግሥትም አሻገረን፤ 14በእርሱም መዋጀትን በደሙ አግኝተናል፤ ይህም የኀጢአት ይቅርታ ነው።

ክርስቶስ ከሁሉ በላይ

እርሱ የማይታየው አምላክ አምሳል ነው፤ ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው፤ ሁሉ ነገር በእርሱ ተፈጥሮአል፤ በሰማይና በምድር ያሉ፣ የሚታዩና የማይታዩ፣ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ኀይላት፣ ገዦች ቢሆኑ ወይም ባለ ሥልጣናት፣ ሁሉም ነገር በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል። እርሱ ከሁሉ በፊት ነው፤ ሁሉም ነገር በአንድ ላይ ተያይዞ የጸናው በእርሱ ነው። እርሱ አካሉ የሆነችው የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው፤ በሁሉ ነገር የበላይነት ይኖረው ዘንድ እርሱ የመጀመሪያ፣ ከሙታን መካከልም በኵር ነው። እግዚአብሔርም ሙላቱ ሁሉ በእርሱ ይሆን ዘንድ ወዶአልና፤ በመስቀሉ ላይ በፈሰሰው ደሙ ሰላምን በማድረግ በምድርም ሆነ በሰማይ ያለውን ነገር ሁሉ በእርሱ በኩል ከራሱ ጋር አስታረቀ።

ከክፉ ባሕርያችሁ የተነሣ ቀድሞ ከእግዚአብሔር የተለያችሁ በአሳባችሁም ጠላቶች ነበራችሁ። አሁን ግን ነውርና ነቀፋ የሌለባችሁ ቅዱሳን አድርጎ በእርሱ ፊት ሊያቀርባችሁ፣ በክርስቶስ ሥጋ በሞቱ በኩል አስታረቃችሁ፤ ይህም የሚሆነው በእምነታችሁ ተመሥርታችሁና ተደላድላችሁ በመቆም ከሰማችሁት የወንጌል ተስፋ ሳትናወጡ ጸንታችሁ ብትኖሩ ነው። እናንተ የሰማችሁትና ከሰማይ በታች ላለ ፍጥረት ሁሉ የተሰበከውም ወንጌል ይኸው ነው፤ እኔም ጳውሎስ ለዚህ ወንጌል አገልጋይ ሆንሁ።

ጳውሎስ ስለ ቤተ ክርስቲያን ያሳየው ትጋት

ስለ እናንተ በተቀበልሁት መከራ አሁንም ደስ ይለኛል፤ ክርስቶስ ስለ አካሉ ስለ ቤተ ክርስቲያን ከተቀበለው መከራ የጐደለውን በሥጋዬ አሟላለሁ። የእግዚአብሔርን ቃል በሙላት እንዳቀርብላችሁ ከእግዚአብሔር በተሰጠኝ ዐደራ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ሆኛለሁ፤ ይህም ቃል ከዘመናትና ከትውልዶች ተሰውሮ ምስጢር ሆኖ ቈይቶ ነበር፤ አሁን ግን ለቅዱሳኑ ተገልጦአል። ለእነርሱም እግዚአብሔር የዚህ ምስጢር ክብር ባለጠግነት በአሕዛብ መካከል ምን ያህል እንደሆነ ለማሳወቅ መረጠ፤ እርሱም የክብር ተስፋ የሆነው በእናንተ ውስጥ ያለው ክርስቶስ ነው።

እኛም እያንዳንዱን ሰው በክርስቶስ ፍጹም አድርገን ማቅረብ እንችል ዘንድ፣ ሰውን ሁሉ በጥበብ ሁሉ እየመከርንና እያስተማርን እርሱን እንሰብካለን፤ እኔም በብርታት በውስጤ በሚሠራው በእርሱ ኀይል ሁሉ እየታገልሁ ለዚህ ዐላማ እጥራለሁ።

1ጴጥሮስ 1:13-21

በቅድስና መኖር

ስለዚህ ልባችሁን አዘጋጁ፤ ራሳችሁንም ግዙ፤ ተስፋችሁን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ ለእናንተ በሚሰጠው ጸጋ ላይ ሙሉ በሙሉ አድርጉ። ታዛዦች ልጆች እንደመሆናችሁ መጠን ቀድሞ ባለማወቅ ትኖሩበት የነበረውን ክፉ ምኞት አትከተሉ። ነገር ግን የጠራችሁ እርሱ ቅዱስ እንደሆነ እናንተም በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፤ ምክንያቱም “እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” ተብሎ ተጽፎአል።

ለሰው ሳያደላ በእያንዳንዱ ላይ እንደ የሥራው የሚፈርደውን አባት ብላችሁ የምትጠሩት ከሆነ፣ በዚህ ምድር በእንግድነት ስትኖሩ በፍርሀት ኑሩ። ከቀድሞ አባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከንቱ ከሆነ ሕይወት የተዋጃችሁት በሚጠፋ ነገር፣ በብር ወይም በወርቅ እንዳልሆነ ታውቃላችሁ፤ ነገር ግን እናንተ የተዋጃችሁት ነውርና እንከን እንደሌለበት በግ ደም፣ በክርስቶስ ክቡር ደም ነው። እርሱ አስቀድሞ የታወቀው ዓለም ከመፈጠሩ በፊት ሲሆን አሁን ግን በመጨረሻው ዘመን ስለ እናንተ ተገለጠ።

 

የዩሐንስ ወንጌል 5:16-27

እንደዚሁም ሰዎች መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማይ ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ በሰዎች ፊት ይብራ።

የሕግ ፍጻሜ

 “ሕግንና የነቢያትን ቃል ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ለመፈጸም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም። እውነት እላችኋለሁ፤ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ ሕግ ሁሉ ይፈጸማል እንጂ ከሕግ አንዲት ፊደል ወይም አንዲት ነጥብ እንኳ አትሻርም። ስለዚህ ማንም ከእነዚህ ትእዛዛት አነስተኛዪቱን እንኳን ቢተላለፍ፣ ሌሎችንም እንዲተላለፉ ቢያስተምር በመንግሥተ ሰማይ ታናሽ ተብሎ ይጠራል፤ ነገር ግን እነዚህን ትእዛዛት እየፈጸመ ሌሎችም እንዲፈጽሙ የሚያስተምር በመንግሥተ ሰማይ ታላቅ ይባላል። ጽድቃችሁ ከፈሪሳውያንና ከኦሪት ሕግ መምህራን ጽድቅ ልቆ ካልተገኘ መንግሥተ ሰማይ መግባት አትችሉም።

ነፍስ መግደል አይገባም

“ለቀደሙት ሰዎች፣ ‘አትግደል፤ የገደለ ይፈረድበታል’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል፤ እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ወንድሙን ያለ አግባብ የሚቈጣ ይፈረድበታል፤ ማንም ወንድሙን ‘ጅል’ የሚል በሸንጎ ፊት ይጠየቅበታል፤ ‘ደደብ’ የሚለው ደግሞ የገሃነመ እሳት ፍርድ ይጠብቀዋል።

 “ስለዚህ መባህን በመሠዊያው ላይ ለእግዚአብሔር በምታቀርብበት ጊዜ ወንድምህ የተቀየመብህ ነገር መኖሩ ትዝ ቢልህ፣ መባህን በዚያው በመሠዊያው ፊት ተወው፤ በመጀመሪያ ሄደህ ከወንድምህ ጋር ተስማማ፤ ከዚያም ተመልሰህ መባህን ለእግዚአብሔር አቅርብ።

“የከሰሰህ ባላጋራህ እንዳያስፈርድብህ፣ ዳኛውም ለአሳሪ አሳልፎ እንዳይሰጥህ፣ በወህኒም እንዳትጣል፣ በመንገድ ላይ ሳለህ ከባላጋራህ ጋር ፈጥነህ ተስማማ። እውነት እልሃለሁ፤ ካስፈረደብህ ግን የመጨረሻዋን ሳንቲም እስክትከፍል ድረስ ከዚያ አትወጣም።

 

 

ኀዳር 17 ዘቅድስት /ዘአስተምሕሮ 2/

አስተንትኖ በክቡር አባ ግርማቸው ተስፋዬ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ካህን

 

በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ዛሬም እንደ ሌላው ጊዜ ሁሉ የእግዚብሔር ጥበቃና ሥጦታ በዝቶልን በቤቱ ተገኝተን የቃሉ ተካፋዬች አድርጐናልና የበረከቱ ተካፋዬች አድርጐናልና የእግዚአብሐሄ ሥም ከዘላዓለም እስከ ዘለዓለም የተመሰገን ይሁን፡፡

በዛሬው የመጀመሪያ መልእክት ቅዱስ ሕዋርያው ጳውሎስ ለቆላስያስ ሰዎች ሲፅፍ እግዚብሔርን የምናመሰግንበት ብዙ ነገሮች አሉ ይላል ቆላ 1፡3 እውነት ነው እያንዳንዳችን እግዚአብሔርን የምናመሰግንበት በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡ በመጀመሪያ ሰው አድርጐ ስለፈጠረን ከዛም በክርስቲያን ማኀበር ውስጥ እንድንገባና በብርሃን መንግሥት ውስጥ ሃዘንና ስቃይ ረሃብና ጥማት በሌለበት መንግሥት ውስጥ ከቅዱሳን ጋር ርስት እንድንካፈል ስላደረገን እግዚአብሔርን እናመሰግናለን ቆላ 1፡12፡፡

በሁለተኛ ደረጃ እግዚአብሔር በአንድያ ልጁ አማካኝነት ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሞት ወደ ሕይወት ካለመኖር ወደ መኖር ከእስራት ወደ ነፃነት ከኃጢያት ባርነት ወደ ቅድስና ጐደና እንድንገባና በእርሱም አማካኝነት ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንድንገባና የመንግሥት ሰማይ እጩዎች ስላደረገን እግዚብሔርን እጅግ አድርገን እናመሰግነዋልን፡፡ 

ከአዳም በወረስነው ኃጢያትና ከእርሱም በኋላ በኛ ውስጥ ባለ የኃጢያት ዝንባሌ አማካኝነት የእግዚብሔር ወገን አልነበርንም አሁን ግን በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት አዲስ ሕዝብ ቅዱስ ሕዝብ ለእግዚብሔር የተለየ ሕዝብ ስላደረገን እግዚአብሔርን እናመሰግናለን ቅዱስ ሐዋርያው ጴጥሮስ በመልእክቱ እንዲህ ይላል እናንተ ግን ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሃን የጠራችሁን የግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ እንድታውጅ የተመረጠ ትውልድ የንጉሥ ካህናት ቅዱስ ሕዝብ እግዚአብሔር ለራሱ የላያችሁ ሕዝብ ናችሁ፡፡ ቀድሞ የእርሱ ወገን አልነበራችሁም አሁን ግን የእግዚአብሔር ሕዝብ ሆናችኋል ቀድሞ ምሕረትን አላገኛችሁም ነበር አሁን ግን ምሕረትን እግኝታችኋል ጴጥ 2፡9፡፡  እግዚአብሔርን የምናመሰግንበት ሌላኛው ምክንያት ደግሞ በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢያታችን ታጥበን ሙሉ በሙሉ ከሰይጣን የባርነት ቀንበር ተላቀን የእርሱ የጸጋው ተካፋዬች በመሆናችን ነው፡፡ እንግዲህ እግዚአብሔርን የምናመሰግንበት ሌሎች አያሌ ምክንያቶች አሉ እያንዳዳችንም የየራሳችን የሆነ ምክንያትም ይኖርናል፡፡ ስለዚህ ስለ ማያልቀው ሥጦታው ስላደረገልንም ሆነ ስላላደረገልን ነገር የእግዚአብሔር ሥም የተመሰገነ ይሁን፡፡

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ለማይታየው እግዚአብሔር እውነተኛ ምሳለ ነው ይላል ስለዚህ እኛ በመልካም ሥራችን ምክንያት የጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ሰምተን እምነን ተቀብለን በእርሱ ጸጋ እየተመላለስን ስንኖር ከዚሁ የእግዚአብሔር አብ መገለጫ ከሆነው ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ጋር ልብ ለልብ እንገናኛለን ይህም ማለት በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በኩል ከእግዚአብሔር አብ ጋር እንገናኛለን፡፡  የዮሐንስ ወንጌል 1፡18 ላይ እንዲህ ይላል ከቶውንም እግዚአብሔርን ያየ ማንም የለም ነገር ግን በአብ እቅፍ ያለው አንድያ ልጁ የሆነው አምላክ እርሱን ገለጠው ፡፡

እንዲሁም በዮሐንስ ወንጌል 1፡9 ጀምሮ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ለፊሊጶስ ሲያስረዳው እንዲህ ይላል እኔን ያየ አብን አይቷል፡፡ እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በአኔ እንዳለ አታምንምን? የምነግራችሁ ቃል ከራሴ አይደለም ነግር ግን ሥራውን የሚሰራው በእኔ ያለው አብ ነው እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ ስነግራችሁ እመኑኝ ስለዚህ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስን በመመልከት የእግዚብሔርን ባህሪ መመልከት እንችላለን እንዲሁ ደግሞ የኛ ባህሪ ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስና እርሱ ካስተማረን ትምሕርት ጋር ከተዛመደ እንዲሁ እኛም ከእግዚአብሔር አብ ጋር ዝምድና ወይንም የቀረበ ግንኘነት ይኖረናል ማለት ነው በጌታችን እየሱስ ክርስቶስን አብን ተመልከተናል ማለት ነው፡፡ በኦሪት ዘፍጥረት 1፡27 እግዝአብሔር ሰውን በአምሳሉ እንደፈጠረው እናያለን እንግዲህ አንድያ ልጁን ጌታችን እየሱስ ክርስቶስንም ዓለምን እንዲያድን ወደዚህ ምድር የላከው የእርሱን የአባቱን ባህሪ የአባቱን ፍቅር የአባቱን መሃሪነትና ይቅር ባይነት በአምሳሉ ለፈጠራቸው ልጆቹ በሙላት እንዲገልፅ ነው፡1 በሮሜ 8፡29 እንደምናገኘው ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የአብ አንድያ ልጅ የበኩር ልጅ በመሆኑ የአብ የሆነውን ነገር ሁሉ የመወረስ መብት አለው እኛም በሮሜ 8፡17 ላይ እንደምናገኘው በአካሄዳችንና በኑሮአችን ጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ከመሰልን ከአርሱ ጋር አብረን ወራሾች እንሆለን፡፡   

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በመቀጠል እንዲህ ይላል ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የቤተክርስቲያን ራስ ነው ቆላ፡1፡18 ሁላችንም እንደምናውቀው ራስ ከሰውነት ክፍል ሁሉ ወሳኝ የሆነውን ክፍል የሚጫወት ነው፡፡  ምናልባት ሰው ዓይኑ ቢጠፋ ጆሮውን እግሩን እጁን በሆነ ምክንያት ቢያጣ በሕይወት ሊኖር ይችላል ነገር ግን ራሱን ቢመታ ወይንም ቢቆረጥ በምንም ዓይነት በህይወት ለመቆየት አይችልም፡፡ እንግዲህ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የመሰረታት የቤተክርስቲያን ራስ ነው ብለን ከተናገርን በሌላ አነጋገር ያለጌታችን እየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ የክርስትና ህይወት እንደሌለ እንረዳለን፡፡ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር አብ መገለጫ እንደሆነ እና በርሱም አማካኝነት እግዚአብሔር አብን እንደምንመለከት ሁሉ እንዲሁም እኛ የጌታችን እየሱስ ክርስቶስ መገለጫ እንድንሆንና ሰዎች በእኛ በኩል ጌታችን እየሱስ ክርስቶስን እንዲመለከቱ እርሱን እንዲገናኙ በእርሱም ውስጥ እንዲመላለሱ መንገድ ወይም ምክንያት እንድንሆንላቸው ይገባል፡፡ የእግዝአብሔር ዋናው ዓላማ በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት በሰማይም ሆነ በምድር ያሉትን ነገሮች ሁሉ ከእርሱ ጋር ማስታረቅ ነው፡፡ ስለዚህ በጌታችን በየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ አማካኝነት በክርስቶስ የምናምን ሁሉ የኃጢያታችንን ይቅርታ ስላገኘን ከእግዚአብሔር ጋር ታርቀናል፡፡ በግዚአብሔርና በእኛ መካከል  በኃጢያታችን ምክንያት ተቋርጦ የነበረው ግንኙነታችን ታድሷል፡፡ ሮሜ 5፡ 9-11 እንዲህ ይላል አሁን በደሙ ከፀደቅን ይልቁንማ በሱ በኩል ከእግዚአብሔር ቁጣ አንዴት አንድንም በኃጢያታችን ምክንያት የእግዚአብሔር ጠላቶች ሳለን በልጁ ሞት ከርሱ ጋር ታርቀን እርቅን ካገኘን በኋላ በሕወቱማ ማዳናችን እንዴት የላቀ አይሆንም፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ነገር ግን አሁን እርቅን ባገኘንበት በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በኩል በእግዚአብሔር ደግሞ ሃሴት እናደርጋለን፡፡ በጌችን እየሱስ ክርስቶስ ያገኘነውን እርቅ ይዘን ወደ ፊት በመጓዝ ከእግዚአብሔር ጋር አንድ ቤተሰብ እንሆናለን  ፡፡ ይህ ያገኘነው የእርቅ ፀጋ ካልጠበቅነው መልሰን ልናጣው እንችላለን ምክንያቱም ሴይጣን በተለያየ ጊዜ በተለያየ ሁኔታ ይህን በጌታችን በእየሱስ ክርስቶስ ደም የተገነባውን መልካምና የፍቅር ጉዞ ለማደፍረስ ዘወትር በዙሪያችን እንዳለ እንድናውቅና ይህ ፀጋ ከኛ እንዳይወሰድብን በክርስቶስ ፀጋ እና በእርሱ ውስጥ እንድንመላለስ ያስፈልጋል፡፡ ዘወትር በመልካም ሥራችን መንፈሳዊነታችንን በማነጽና ለእግዚአብሔር ትዕዛዝ ሁሉ ፍጹም ተገዢ በመሆን እውነተኛ የክርስቶስ ወዳጆች መሆናችንን ልናስመሰክር ያስፈልጋል፡፡ ይህን በምናደርግበት ጊዜ መንገዱ ሁሉ አልጋ በአልጋ ላይሆን ይችላል ምክንያቱም ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ይህን የእግዚአብሔር እቅድና የመጣበትን ዓላማ ማለትም የእግዚአብሔርን መንግሥት በምድር ላይ ለመመስረት ሲታገል የተለያዩ ስቃዮችን ብሎም እስከ ሞት እንዳደረሰው እናውቃለን፡፡ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስም ሆነ ሌሎች ሐዋርያቶች ተመሳሳይ እንግልትና ስቃይ እንደደረሰባቸው እናውቃለን ዛሬም ታዲያ ለእኛም ተመሳሳይ ነገር ሊገጥመን ይችላል፡፡ እዚህ ላይ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የጻፈውን ደብዳቤ መመልከት መልካም ነው፡፡ 2 ጢሞ. 3፡12 የእየሱስ ክርስቶስ ተከታዬች ሆነው በመንፈሳዊ ሕይወት ለመኖር የሚፈልጉ ሁሉ ስደት ይገጥማቸዋል ይህ ማለት የግድ ከአገር ወደ ሌላ አገር መሳደድ ሳይሆን ይችላል ያልቁንም ሰው ከወንድሙ ከእህቱ ከአባቱ ከእናቱ ከቤተክርስቲያን በመራቅ መስደድ ሊሆን ይችላል፡፡ ከእግዚብሔር ቤት በመራቅ መሰደድ ሊሆን ይችላል፡፡ ምሥጢራትን ከመሳተፍ መሰደድ ሊሆን ይችላል፡፡ በቤተክርስቲያን ውስጥ አገልግሎት ከመስጠት መሰደድ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ የትኛውንም ዓይነት ስደት ተቋቁመን እስከ መጨረሻ በእምነታትን በመጽናት እንድንኖር ያስፈልጋል፡፡

በሁለተኛው ንባብ ቅዱስ ሐዋርያው ዼጥሮስ እንደሚያስረዳን ልባችንን በማዘጋጀት ራሳችንንም በመግዛት ቀድሞ ከእኛ ጋር ይኖር የነበረውን የክፋትና የኃጢያት ዝንባሌን በማሳወገድ በኑሮአችን በአነጋገራችን በአካሄዳችን ሁሉ ቅዱሳኖች እንድንሆን ያሰፈልጋል፡፡ እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ 1 ጲጥ 1፡16፡፡

በሐዋርያት ሥራም 19፡21-40 ያለው የሚያስረዳን ያህንኑ ነው፡፡  ሰው የእግዚአብሔርን ዕቅድ በተግባር ለመኖርና መልካም አብነትን ለመስጠተ መልካም ሥራን ለመሥራት ሲነሳሳ ዘወትር ሰይጣን ይህንን መለካም ሥራ ለማደናቀፍ የተለያዩ ብልሃቶትን ይጠቀማል ለዚህም ነው በኤፌሶን ላይ በጳውሎስና በእርሱ ደቀመዛምርቱ ላይ በማመፅ ሑከት የተነሳው በዛሬው ወንጌልም በዬሐንስ 5፡16-27 ተመሳሳይ ነገር እንመለከታለን፡፡ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በሰንበት ቀን በሽተኞችን በመፈወሱ በሰይጣን አስር ውስጥ ገብተው ለሚሰቃዩት ሕይወትን በመስጠቱ በኃጢያት ሰንሰለት ታሰረው ለሚሰቃዩት ሁሉ ከሞተ ወደ ሕይወት የሚሸጋገሩበትን መሥመር በመዘርጋቱ እየሱስን አሳደዱት ሊገድሉትም ፈለጉ፡፡ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ግን እግዚአብሔር አብ ይህንን የእርሱን ሥራ እንዲሰራ ልኮታልና የእርሱን የደህንነት ሥራ ከግብ እንዲያደርስ ልኮታለና እንዲህ አለ አባቴ እስከ አሁን እይሠራ ነወ እኔም ደግመ አሠራለው አላቸው ዮሐ 5፡17፡፡ እግኢበሐር መሥራቱን ቢያቆም ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ መሥራቱን ቢያቆም ዓለም ሁሉ በሠይጣን ክፋትና ተንኮል ስለምትታመስ እስከ አሁንም ባጠፋን ነበር፡፡ ምክንያቱም ሰው የሚኖረው የሚንቀሳቀሰው እግዚአብሔር በሚሰጠው እስትንፋስና እርሱ ለኑሮአችን በሚያመቻቸው ነገር ነው፡ ሐዋ. ሥራ 17፡28 ላይ እንዲህ ይላል የምንኖረውና የምንንቀሳቀሰው ያለነውም በእርሱ ነውና ፡፡

ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ አባቱ እንደሚሠራው እርሱም እንዲሁ የእግዚአብሔርን ሥራ ይሠራልና አብ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድም እንዲሁ ያደርጋልና እኔና አባቴ አንድ ነን አላቸው፡፡ ዬሐ. 5፡19

በዚህ አነጋገሩ እጅግ በጣም ተቆጡ ሊገድሉትም ፈለጉ ምክንያቱም ይህ የእርሱ አነጋገር ከእግዚአብሔር አብ ጋር ራሱን በማስተካከሉ እንደ ትልቅ ስድብና ድፍረት ስለሚቆጠር ከሕጋቸውም አንፃር የሞት ፍርድ ስለሚያስጥ ነው፡፡ ኦሪት ዘሌዋውያን 24፡16 የእግዚአብሔር ሥም የሚሳደብ ማንኛውም ሰው ይገደል ማኀበሩም ተሰብሰበው ይውገሩት ይላል፡፡

ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ይናገር የነበረው ግን እውነትን ነበር እርሱ እውነተኛ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ መሆኑን በሥራው አሳይቷቸው ነበር እነርሱ ግን ሊቀበሉት አልወደዱም እርሱ ግን በመቀጠል እንዲህ አለ እውነት እላችኋለው ቃሌን የሚሰማ በላከኝም የሚያምን የዘለዓለም ሕይወት አለው ከሞት ወደ ሕይወት ተሻጋገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም ዮሐ 5፡24፡፡

እንግዲህ ዛሬም እኛ በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በማመናችንና እርሱን በመቀበላችን የዘለዓለም ሕይወት ይኖረናል ምክንያቱም በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት የዘለዓለምን ሕይወት በመውረስ በእግዚአብሔር ቤት እንኖራለንና ነው፡፡ እዚህ ላይ በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ እናምናለን ስንል እርሱ የሰጠንን ትዕዛዝ ሁሉ በመፈፀምና መልካም ሥራን በመሥራት እምነታችን ሙሉ መሆኑን እንድናረግጥ ያስፈልጋል ያዕቆብ 2፡17 እንዲሁ ሥራ የሌለው እምነት በራሱ የሞተ ነው ይላልና፡፡   

ስለዚህ እምነታች ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ እንዲሄድና የሰማይ አባታችን ቅዱስ እንደሆነ እኛም ወደ ቅድስና ለመድረስ በውስጣችን ያለውን ቅዱስ ያልሆነውን ነገር ሁሉ እናስወግድ ቅዱስ የሆነውን ነገር ወደ ውስጣችን እናስገባና በቅድስና ጐዳና እንመላለስ፡ ለዚህም በሥጋዋ ድንግል በነፍሷ ቅድስት የሆነች በእግዚአብሔር ፊት ዘወትር ጠበቃ ሆና የምትቆምልን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም  ከልጇ ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ይህንን ጸጋና በረከት ታማልደን፡፡     

 








All the contents on this site are copyrighted ©.