Social:

RSS:

የቫቲካን ሬድዮ

ከዓለም ጋር የሚወያይ የር.ሊ.ጳጳሳትና የቤተ ክርስትያን ድምጽ

ቋንቋ:

ቤተ ክርስትያን \ ኢትዮጵያ

የሕዳር 10 ሰንበት የቃለ እግዚኣብሔር አስተንትኖ በክቡር አባ ግርማቸው ተስፋዬ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ካህን

የሕዳር 10 ሰንበት የቃለ እግዚኣብሔር አስተንትኖ በክቡር አባ ግርማቸው ተስፋዬ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ካህን - RV

18/11/2017 15:00

የሕዳር 10 ሰንበት ዘአስተምሕሮ 1ኛ

የቃለ እግዚኣብሔር አስተንትኖ በክቡር አባ ግርማቸው ተስፋዬ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ካህን

የእለቱ ምንባባት

1.ሮሜ፡   5፡ 10-21

2. 1ዮሐ  2፡1-17

3.ሐዋ.ሥ 22 1-11

4. ማቴ 6፡5-15

ቅዱስ ሐዋሪያው ጳውሎስ ወደ ሮሜ ሰዎች፡   5፡ 10-21።

የእግዚአብሔር ጠላቶች ሳለን በልጁ ሞት ከእርሱ ጋር ከታረቅን፣ ዕርቅን ካገኘን በኋላ፣ በሕይወቱማ መዳናችን እንዴት የላቀ አይሆንም! ይህ ብቻ አይደለም። ነገር ግን አሁን ዕርቅን ባገኘንበት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእግዚአብሔር ደግሞ ሐሤት እናደርጋለን።

የዚህን አስተንትኖ ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

ሞት በአዳም፣ ሕይወት በክርስቶስ

ስለዚህ ኀጢአት በአንድ ሰው በኩል ወደ ዓለም እንደ ገባ ሁሉ፣ ሞትም በኀጢአት በኩል ገብቶአል፤ በዚሁ መንገድ ሞት ወደ ሰዎች ሁሉ መጣ፤ ምክንያቱም ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል፤ ሕግ ከመሰጠቱ በፊት ኀጢአት በዓለም ላይ ነበር፤ ነገር ግን ሕግ በሌለበት ኀጢአት አይቈጠርም። ይሁን እንጂ ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ ድረስ ባሉት፣ እንደ አዳም ሕግን በመጣስ ኀጢአት ባልሠሩት ላይ እንኳ ሞት ነገሠ፤ አዳም ይመጣ ዘንድ ላለው አምሳሉ ነበረ።

ነገር ግን ስጦታው እንደ በደሉ መጠን አይደለም፤ በአንድ ሰው መተላለፍ ብዙዎቹ ከሞቱ፣ የእግዚአብሔር ጸጋና በአንዱ ሰው፣ ይኸውም በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የመጣው ስጦታ ለብዙዎች እንዴት አብልጦ ይትረፈረፍ! 

ደግሞም የእግዚአብሔር ስጦታ እንደ አንዱ ሰው የኀጢአት ውጤት አይደለም፤ ምክንያቱም ፍርዱ የአንድን ሰው ኀጢአት ተከትሎ ኵነኔን አመጣ፤ ስጦታው ግን አያሌ መተላለፍን ተከትሎ ጽድቅን አመጣ። 17በአንድ ሰው መተላለፍ ምክንያት ሞት በዚህ ሰው በኩል የነገሠ ከሆነ፣ የእግዚአብሔርን የተትረፈረፈ ጸጋና የጽድቅ ስጦታ የተቀበሉት፣ በአንዱ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እንዴት አብልጠው በሕይወት አይነግሡ!

ከእንግዲህ በአንድ ሰው መተላለፍ የተነሣ ኵነኔ በሁሉ ሰው ላይ እንደ መጣ፣ እንዲሁም በአንዱ የጽድቅ ሥራ ለሰው ሁሉ ሕይወትን የሚሰጥ ጽድቅ ተገኘ። በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኀጢአተኞች እንደሆኑ፣ በአንዱ ሰው መታዘዝ ደግሞ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ።

ሕግ በመምጣቱ መተላለፍ በዛ፤ ነገር ግን ኀጢአት በበዛበት ጸጋ አብልጦ የተትረፈረፈ ሆነ፤ ይህም የሆነው ኀጢአት በሞት እንደ ነገሠ ሁሉ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ደግሞ የዘላለም ሕይወት ይገኝ ዘንድ ጸጋ በጽድቅ እንዲነግሥ ነው።

 

1 ዩሐንስ 21-17

ልጆቼ ሆይ፤ ይህን የምጽፍላችሁ ኀጢአት እንዳትሠሩ ነው፤ ነገር ግን ማንም ኀጢአት ቢሠራ፣ በአብ ዘንድ ጠበቃ አለን፤ እርሱም ጻድቁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱም የኀጢአታችን ማስተስረያ ነው፤ ይኸውም። ለዓለም ሁሉ ኀጢአት እንጂ ለእኛ ብቻ አይደለም። ትእዛዛቱን ብንፈጽም እርሱን ማወቃችንን በዚህ ርግጠኞች እንሆናለን። “እርሱን ዐውቃለሁ” እያለ ትእዛዙን የማይፈጽም ግን ሐሰተኛ ነው፤ እውነትም በእርሱ ውስጥ የለም። ነገር ግን ማንም ቃሉን ቢጠብቅ፣ በእውነት የእግዚአብሔር ፍቅር በእርሱ ፍጹም ሆኖአል። በእርሱ መሆናችንን የምናውቀው በዚህ ነው፤ ማንም በእርሱ እኖራለሁ የሚል፣ ኢየሱስ እንደ ተመላለሰ ሊመላለስ ይገባዋል።

ወዳጆች ሆይ፤ የምጽፍላችሁ፣ ከመጀመሪያ የነበራችሁን የቈየውን ትእዛዝ እንጂ አዲስ ትእዛዝ አይደለም፤ የቈየው ትእዛዝ የሰማችሁት ቃል ነው። በሌላ በኩል የምጽፍላችሁ ጨለማው ዕያለፈና እውነተኛው ብርሃን እየበራ ስለ ሆነ፣ በእርሱም፣ በእናንተም ዘንድ እውነት የሆነውን አዲስ ትእዛዝ ነው። በብርሃን አለሁ የሚል፣ ወንድሙን ግን የሚጠላ አሁንም በጨለማ ውስጥ አለ። ወንድሙን የሚወድ በብርሃን ይኖራል፤ በእርሱም ዘንድ የመሰናከያ ምክንያት የለውም። ነገር ግን ወንድሙን የሚጠላ በጨለማ ውስጥ ነው፤ በጨለማ ይመላለሳል፤ ጨለማው ስላሳወረውም የት እንደሚሄድ አያውቅም።

ልጆች ሆይ፤ ኀጢአታችሁ ስለ ስሙ ተሰርዮላችኋልና፣ እጽፍላችኋለሁ።

አባቶች ሆይ፤ ከመጀመሪያ ያለውን እርሱን ዐውቃችሁታልና፣ እጽፍላችኋለሁ።

ጐበዛዝት ሆይ፤ ክፉውን አሸንፋችኋልና፣ እጽፍላችኋለሁ።

ልጆች ሆይ፤ አብን ዐውቃችሁታልና፣ እጽፍላችኋለሁ።

አባቶች ሆይ፤ ከመጀመሪያ ያለውን እርሱን ዐውቃችሁታልና፣ እጽፍላችኋለሁ።

ጐበዛዝት ሆይ፤ ብርቱዎች ስለ ሆናችሁ፣ የእግዚአብሔር ቃል በእናንተ ስለሚኖር፣ ክፉውንም ስላሸነፋችሁ፣ ጽፍላችኋለሁ።

ዓለምን አትውደዱ

ዓለምን ወይም በዓለም ያለውን ማናቸውንም ነገር አትውደዱ፤ ማንም ዓለምን ቢወድ፣ የአብ ፍቅር በእርሱ ዘንድ የለም፤ ምክንያቱም በዓለም ያለው ሁሉ፦ የሥጋ ምኞት፣ የዐይን አምሮትና የኑሮ ትምክሕት ከዓለም እንጂ ከአብ የሚመጣ አይደለም። ዓለምና ምኞቱ ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽም ግን ለዘላለም ይኖራል።

የማቴዎስ ወንጌል 65-15

ስትጸልዩ እንደ ግብዞች አትሁኑ፤ እነርሱ ለሰዎች ለመታየት ሲሉ በየምኵራቡና በየመንገዱ ማእዘን ላይ ቆመው መጸለይ ይወዳሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፤ ሙሉ ዋጋቸውን ተቀብለዋል። አንተ ግን ስትጸልይ ወደ ክፍልህ ግባ፤ በሩንም ዘግተህ በስውር ወዳለው አባትህ ጸልይ፤ በስውር የተደረገውን የሚያይ አባትህም ዋጋህን ይከፍልሃል። ስትጸልዩ፣ ከንቱ ቃላት በመደጋገም ጸሎታቸው የሚሰማላቸው እንደሚመስላቸው አሕዛብ ነገራችሁን አታስረዝሙ። እነርሱን አትምሰሏቸው፤ አባታችሁ ከመለመናችሁ በፊት ምን እንደሚያስፈልጋችሁ ያውቃልና።

 “እናንተ ግን እንዲህ ብላችሁ ጸልዩ፤

“ ‘በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፤

ስምህ ይቀደስ፤

መንግሥትህ ትምጣ፤

ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች፣

እንዲሁ በምድር ትሁን።

የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን።

እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል፣

በደላችንን ይቅር በለን።

 ወደ ፈተናም አታግባን

ከክፉው አድነን እንጂ፣

መንግሥት፣ ኃይል፣ ክብርም፣

ለዘለዓለሙ ያንተ ነውና፤ አሜን። 

እናንተ የበደሏችሁን ይቅር ብትሉ የሰማዩ አባታችሁ ደግሞ እናንተን ይቅር ይላችኋል። ነገር ግን የሰዎችን ኀጢአት ይቅር የማትሉ ከሆነ፣ አባታችሁም ኀጢአታችሁን ይቅር አይልላችሁም።

 

የቃለ እግዚኣብሔር አስተንትኖ በክቡር አባ ግርማቸው ተስፋዬ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ካህን

በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የተወደአችሁ የእግዝአብሔር ቤተሰቦች የእግዚብሔር ጸጋና በረከት ሞልቶልን ዛሬም በጤናና በሰላም ወደ እርሱ ቤት በመመጣተ የቃሉ ተካፋይ እንድንሆን ስላደደረገን የእግዚአብሔር ሥም ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የተመሰገነ ይሁን፡፡ በመጀመሪያው መልእክት ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በጌታችን በእየሱስ ክርስቶስ ሞት አማካኝነት ከእግዝአብሔር ጋር መታረቃችንን ያበሥራል፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው እግዚአብሔር አምላካችን አንድያ ልጁን ወደዚህ ወደ ምድር ከመላኩ በፊት አያሌ አበይትና ንዑሳን ነቢያትን በመላክ ልጆቹን ከኃጢያት ባርነት ሊያወጣቸው ሞክሯል የሆነ ሆኖ በስተመጨረሻ አንድያ ልጁን በመላክ ከእርሱ ጋር የተቋረጠው ግንኙነታትን እንዲቀናል ከእርሱ ጋር ያለን  ሕብረታችን እንደገና እንዲታደስ አድርጓል፡፡ ሰው አብዛኛውን ጊዜ ከደካማ ባሕሪው የተነሣ ይህ በጌ.እ.ክ. አማካኝነት የታደሰው ሕብረታችንና ግንኙነታችን ይደፈርሳል ስለዚህ እያንዳዳችን ይህ ግንኙነት በምንሰራው ክፋትና በምናስበው የተሳሳተ ሃሳብ ቢቋረጥም ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ራሱ በሰራውና ለኃጢያታችንም ማስተስረያ እንዲሆን ባዘጋጃልን በምሥጢረ ንስሃ አማካኝነት ልናድሰው እንደገና ግንኙነታችንን እንድንቀጥል በአዲስ መንፈስ መልሰን ልንገነባው ይገባል፡፡ ማንም ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ግንኙነት የበለጠ እየጠነከረ እንዲሄድ በእግዝአብሔር ጸጋና በእምነታችን በየጊዜው እያደግን መሄድ ይገባናል፡፡ በእግዚአብሔር ጸጋና በእምነታችን እያደግን ስንሄድ ልባችን ሁልጊዜ በደስታ ይሞላል፡፡ በደሰታ የተሞላ ልብ ደግሞ ሁልጊዜ እግዚአብሔርንና ሰውን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ይሠራል፡፡

ቅዱስ ሐዋርያፀወ ጳውሎስ በዚህ ለሮሜ ሰዎች በፃፈው መልእክት ኃጢያት በአዳምና በሔዋን አለመታዘዝ ምክንያት ወደ ሰው ዘር እንደገባ ይናገራል፡፡ /ዘፍ. 2፡15-17 3፡1-3/ አዳም የሰው ልጆች ሁሉ በኩር ሆኖ ሳለ እርሱ በሰራው ኃጢያት ምክንያት ሁሉም የሰው ዘር ተበከሉ ኃጢያትንም ሠሩ እንደ አዳምም ኃጢያተኞች ሆኑ፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የአዲስ ኪዳን በኩር በመሆን ከሰው ልጆች ሁሉ የአዳምን ኃጢያት በማጥፋት በሞቱም ሠይጣንንና ክፋቱን ሞትንም ድል በመንሣት እርሱን ለሚከተሉ ሁሉ የመልካምነትና የጽድቅ ምሳሌ ሆነ፡፡              

በአንዱ አዳም ምክንያት ሞት ወደ ሰው ልጆች እንደመጣ እንዲሁ በአንዱ በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ደግሞ ሕይወት መጣ፡፡ በአዳም በኩል ሞት በሰው ልጆች ላይ ሥልጣን እንዳገኘ በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በኩል ደግሞ የሕይወትን ሥልጣን አገኘ፡፡ ሮሜ፡ 8፡1-12 እንዲህ ይላል በክርስቶስ እየሱስ ያሉት አሁን  ኩነኔ የለባቸውም ምክንያቱም የሕይወት መንፈስ ሕግ በክርስቶስ እየሱስ ከኃጢያትና ከሞት ሕግ ነፃ አውጥቶአችዋልና፡፡

ብርሃን በጨለማ ላይ ከእንደሚሰለጥን እንዲሁ የእግዚብሔር ጸጋ በኃጢያት ላይ ይሰለጥናልና ሁላችንም በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ያገኘነውን ጸጋ ይዘን ወደፊት ልንጓዝ ይገባል፡፡ ምክንያቱም የትኛውንም ዓይነት ኃጢያት ለመቋቋም ኃይልና ብርታት  ይኖረናልና ነው፡፡ ኃጢያት ሁልጊዜም ወደ ሞት ይመራል ጸጋ ደግሞ በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ወደ ዘለዓለም ሕይወት ይመራል፡፡

በሁለተኛው መልእክት ቅዱስ ሐዋርያው ዬሐንስ በአንደኛ መልእክቱ ምዕራፍ 2፡ 1-17 ኃጢያታችንን ሁል ጊዜ ለእግዚብሔር መናዘዝ እንደሚያስፈልግ ይናገራል፡፡ በምንሰራቸው ኃጢያቶች አማካኝነት በውስጣችን ያለው ጸጋ እየደበዘዘ ሊሄድ ይችላል፡፡ በመቀጠልም ያለ አንዳች ንስሃ ኃጢያት መሥራታችንን ብንቀጥል በውስጣችን ያለው ጸጋ ሙሉ በሙሉ ሊጠፋ ይችላል በዚህ አኳሃን በቀላሉ የሰይጣን ሥራ ተባባሪዎች እንሆናለን ይህ ደግሞ ወደ ዘለዓለማዊ ሞት ይመራናል ስለዚህ ማንኛውም ሰው ምሥጢረ ንስሃን በተወሰነ ጊዜ መግባት ግድ ነው ምክንያቱም ሰዎች ነንና በየዕለቱ በማሰብ በማናገር በማድረግ የተለያዩ እግዚብሔርንና ሰውን የሚያሳዝኑ ድርጊቶችን እናደርጋለንና ነው፡፡ ንስሃን አዘውትሮ በመግባት ለእግዚአብሔር ሕግ በመገዛት መኖር ማለት በብርሃን ውስጥ መኖር ማለት ነው፡፡ በብርሃን ውስጥ የሚመላለስ ሰው ደግሞ ጌታችን እየሱስ ራሱ ብርሃን ነውና እርሱን ያገኘዋል ከእርሱም ጋር አብሮ በብርሃን ይጓዛል፡፡ በኃጢያት የሚጓዝና ከኃጢያቱ ጋር አብሮ የሚኖር ሰው በጨለማ ውስጥ ይጓዛል በጨለማ ውስጥ የሚጓዝ ደግሞ ሊገናኝ የሚችለው የክፋትና የጨለማ አባት የሆነውን ዲያብሎስን ነው፡፡  ለእግዚአብሔር የሚታዘዝ ሰው እግዚአብሔር ራሱ ወደ እርሱ ይሄዳል ከእርሱም ጋር  ይሆናል በእርሱም ውስጥ ይኖራል ስለዚህ ሕይወቱ በሙሉ የተባረከ የተቀደሰ ይሆናል፡፡

ቅዱስ ሐዋርያው ዮሐንስ አዲስ ትዕዛዝን ይሰጠናል ይኸውም ትዕዛዝ የፍቅር ትዕዛዝ ነው   “በብርሃን አለሁ የሚል ግን ወንድሙን የሚጠላ አሁንም በጨለማ ውስጥ አለ” ይላል፡፡

በጨለማ ውስጥ የሚጓዝ ወዴት እንደሚሄደ አያውቀም በመንገዱ ላይ ጉድጓድ ቢኖር እንኳን በጨለማ ውስጥ ሊመለከተው አይችልምና በጉድጓድ ውስጥ ይወድቃል፡፡ በተመሣሣይ ሙልኩ ወንድሙን የሚጠላ እግኢብሔርን እወዳለሁ ለማለት አይችልም ምክንያቱም በጨለማ  ውስጥ ሆኖ ከእግዚአብሔር የሚፈነጥቀውን ብርሃን መመልከት አይችልምና ነው፡፡ 1ዮሐ 2፡11 ወንድሙን የሚጠላ በጨለማ ውስጥ ነው በጨለማ ይመላለሳል ጨለማው ስላሳወረውም የት እንደሚሄድ አያውቅም ኃጢያት የጨለማ መገለጫ ነው ስለሆነም በኃጢያት ውስጥ የሚኖር ሰው ሕይወቱ የጨለመ ነው ሕይወቱ የጨለመ ሰው ደግሞ የራሱንም ሆነ የሌሎችን ሕይወት ሊያስተካክል ወይንም ሊመራ አይችልም ማንንም ሰው ብርሃን ወደሆነው ወደ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ሊያመለክት አይችልም፡፡               

ስለዚህ ሁላችንም ከሠይጣን መንገደ ከሆነው ከጨለማ ራሳችንን ልንጠብቅ ይገባል፡፡ ቅዱስ ሐዋርያው ዮሐንስ ልጆች ሆይ አባቶች ሆይ የእግዚአብሔር ቃል የክርስቶስ ወንጌል ነውና ኃጢያአትን የምናሸንፍበት የመንፈስ ሰይፍ ነውና እርሱን ይዘን በብርሃን እንመላለስ ይላል፡፡ ኤፌሶን 6፡17 የመዳንን ራስ ቁር አድርጉ የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ በስተመጨረሻም ቅዱስ ሐዋርያው ዮሐንስ የዓለምን ነገር እንዳንወድ የእርሱም ተገዢ እንዳንሆን ይመክረናል፡፡ ምክንያቱም ዓለምን የሚወድ የዓለም ተገዢ የሆነ ሰው እግዝአብሔርን ሊወድ አይችልም የእርሱም ተገዢ ሊሆን አይችልምና ይለናል፡፡ በዓለም ያለው ሁሉ የሥጋ ምኞት የዓይን አምሮትና የኑሮ ትምክህት ከዓለም እንጂ ከአብ የሚመጣ አይደለም ይላል ዓለምና ምኞቱ ያልፋሉ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽም ግን ለዘለዓለም ደኖራል ይላል /1 ዮሐ 2፡15-17/

በሐዋርያት ሥራም 22፡1-11 የቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስን የምሥክርነት ቃል እንመለከታለን፡፡ እርሱ ለሕዝቡ እንዴት የጌታችን እየሱስ ክርስቶስ መንገድ ይከተሉ የነበሩትንና በእርሱ ያመኑትን ይቀጣ ያሳድድ እንደነበርና አሁን ግን ጌታችን እየሱስ ራሱ በደማስቆ እንደተናገረውና ከዛም በኋላ የእርሱ ደቀመዝሙር እንደሆነ ይናገራል፡፡ 

ሳውል ጌ.እ.ክ ከተናገረው በኋላ ሙሉ በሙሉ ተቀየረ ምክንያቱም ያሳድደው የነበረው ራሱ እየሱስ መሆኑን ሲረዳ ጌታዬ ሆይ ምን እንዳደረግ ትፈልጋለህ በማለት ጠየቀ ሙሉ በሙሉ የአእምሮና የፈቃድ ለውጥን አደረገ፡፡  ዛሬም በእኛ ሕይወት ተመሳሳይ ነገር ሊኖር ይገባል፡፡ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስን በሙላት ልንረዳና ድምጹን ልንሰማ ይገባል፡ በዚህ ጊዜ ብቻ ልክ እንደ ሕዋርያው ጳውሎስ የአእምሮና የፈቃድ ለውጥ በማምጣት ሙሉ በሙሉ የእርሱ ተገዢዎች እንሆናለን ፈቃዳችንን ሁሉ ለእርሱ ተገዢ እናደርጋለን፡፡ በዚህ መልኩ ከእርሱና ከእርሱ ከሚመነጨው መንፈስ ቅዱስ ጋር ለመጓዝ እንችላለን፡፡

በዚህ በዛሬው በማቴዎስ ወንጌል 6፡5-15 ጌታችን እየሱስ ክርስሃቶስ ስለ ጸሎት ምንነትና ምን ብለን መጸለይ እንዳለብን ያስተምረናል፡፡ እኛ በተለምዶ ስንጸልይ ምንም ቅድመ ዝግጅት ሳይኖረን ልክ ቤተክርስቲያን እንደደረስን አማትበን ጸሎታችንን እንጀምራለን ነገር ግን ይህ ትክክለኛ አካሄድ አይደለም ጸሎት ከእግዚብሔር ጋር መነጋገር ከእርሲ ጋር መወያየት እንደመሆኑ መጠን ትንሽ የልብና የአእምሮ መረጋጋት ካደረግን በኋላ ጸሎት ማድረጉ ተገቢ ነው፡፡

ጸሎት በምናደርግበት ጊዜ ልክ እንደ አይሁድ መሪዎች ለታይታና ጸሎት አደረጉ ለመባል ብቻ ከሆነ ምንም ዓይነት ዋጋ አይኖረውም እግዚአብሔር እያንዳዳችን ምን እንደሚያስፈልገን አስቀድሞ ያውቃለ ስለዚህ እግዝአብሔር ከእኛ የሚፈልገው በንጹህ ልብና በሙሉ እምነት ወደ እርሲ መጸለይ እንዳለብን ብቻ ነው፡፡ በኤፌሶን 3፡20 ላይ እግዚአብሔር ከምንለምነውና ከምናሳበው በላይ እጀግ አብልጦ አሳቢና ሁሉንም ማድረግ የሚቻል መሆኑን ይናገራል፡፡ እንግዲህ ይህን የመሰለ አምላክን በመለመን ከእርሲ ጋር ለመነጋገር ተገቢ ዝግጅት ያስፈልጋል፡፡

ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን ጸሎት በመናደርግበት ግዜ እርሲ ሁሉን የሚችል አምላክ በመሆኑ ስለ ሥጦታው ሁሉ እርሲን በማመስገን መጀመር እንዳለብን ይነግረናል፡፡ መዝሙር 34፡1 እንዲህ ይላል እግዚአብሔርን ሁል ጊዜ እባርከዋለው ምሥጋናውም ዘወትር ከአፌ አይለይም

አብዛኛውን ጊዜ ጸሎት ለመጸለይ ስናስብ አስቀድመን የምናስበው እኛ ስለምንለምነው እና በኑሮአችን ስለሚያስፈልገን ነግር እንጂ ስለ እግዚአብሔር ታላቅነትና ቸርነት ብዙም አናስብም፡፡ ነገር ግን ይህንን አመለካከታችንን ልብ ልንለው ይገባል፡፡          

ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ወደ እዚህ ምድር ሲመጣ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እዚህ ምድር መቷል፡፡ ለዚህ ነው ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለችና ንስሃ ግቡ በወንጌሉም እመኑ በሎ የሰበከው ማርቆስ 1፡15፡፡ የእግዚአብሔር መንግሥት በሙላት እንዲሰራፋ ደግሞ የእኛ ትብብር ያስፈልጋል የእኛ እውነተኛ ጸሎት ያስፈልጋል፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃድ ይህ ነው፡፡ እግዚአብሔር ሁሌም የዕለት እንጀራችንን ይሰጠናል ለዚህም ምሳሌ ይሆነን ዘንድ ፀሐይን ዝናምን መመልከት እንችላለን አሁንም ሠርተን ለማግኘት የእኛ ትብብር ግድ ነው፡፡  

ጸሎት በምንጸልይበት ጊዜ የማንም የይቅርታ ባለዕዳዎች መሆን የለብንም ልባችን ንጹህ ከሆነ እግኢብሔር ሁለም ፀሎታችንን ይሰማል፡፡

ወደ ፈተና አታግባን ብለን ስንጸለይ በየትኛውም ዓይነት በሰይጣን ፈተና እንዳንወድቅ ጠብቀን ማለታችን ነው ሰይጣን በሕይወታችን ውስጥ ቦታ ከሰጠነው መንፈሳዊ ሕይወታችንን በመስረቅ ከእግዚአብሔር መንግሥት ያወጣናል ስለዚህ አሁንም ተግተን መጸለይ ያስፈልገናል፡፡ ጸሎት ሰይጣንንና የእርሱን ሥራ ለማስወገድ ዓይነተኛ መሣሪያ ነው፡፡ ዘወትር በጸሎታችንም መጨረሻ ለእግዚብሔር ምሥጋናና ክብር መስጠታችንን መርሳት የለብንም መንግሥት ኃይል ክብር ለዘላዓለም ለይተ ይሁን አሜን፡፡ 

 

 

18/11/2017 15:00