2017-11-16 11:35:00

"ባልንጀራዬ ማነው"? በአባ ዳንኤል አሰፋ (ከካፑቺን ፍራንቸስካዊ የምርመርና የጽሞና ማእከል)


ባልንጀራዬ ማነው?

አባ ዳንኤል አሰፋ  (ከካፑቺን ፍራንቸስካዊ የምርመርና የጽሞና ማእከል)

 

ጥበቡ መጻሕፍትን ያገላብጣል። ከመመሰጡም ብዛት ኅሊና ወደ እርሱ መቅረብዋንም አላስተዋለም ነበር። “እንደምን አረፈድክ?” ስትለው ነው ሰው አጠገቡ መኖሩን የተገነዘበው። በታላቅ ፈገግታ “እንደምን አረፈድሽ፣ ኅሊና?” አለ። ከተቀመጠበት ተነሥቶም ወንበር አቀረበላትና ውይይታቸውን ጀመሩ፤

“ዛሬ ደግሞ ምን እያጠናህ ነው? ምንድነው እንዲህ የመሰጠህ?” አለች ኅሊና።

“ይኼ የደጉ ሳምራዊ ምሳሌ ነው ትኩረቴን የሳበው፤” አለ ጥበቡ።

“ድንቅ ነው፤ ታዲያ ምን አዲስ ነገር ተማርክ?”

“ግራ ስለገባኝ ነገር ብነግርሽ አይሻልም?”

“ምንድነው ግራ ያጋባህ?”

“ሲጀመር ‘ባልንጀራ የሚለው ቃል አልገባኝም።

“እሱማ፤  እንጀራን አብሮ የሚቆርስ፣ አብሮ አደግ፣ ወዳጅ፣ ማለትም አይደል?”

“ታዲያ ጥያቄው፣ ሊወደኝ የሚገባው ሌላ አይሁዳዊ ነው ለማለት ይሆን?” አለ ጥበቡ።

“አዎን እንደዛ ማለቱ ይመስላል፤ ነገር ግን የክርስቶስ ፍቅር ሌላም ገጽታ ይጨምራል።”

“ምን ማለትሽ ነው? እስቲ አብራሪው።”

“ይኸውልህ፣ ከኢየሱስ ጋር ይነጋገር የነበረው የሕግ መምህር፣ ሲጀመር ዓላማው ስለዘላለም ሕይወት መንገድ ማወቅም ሆነ ስለ ባልንጀራ መረዳትም አልነበረም። ዓላማው ወጥመድ መዘርጋት ሲሆን፣ የተገፋፋውም በትዕቢት ነው። ወዳጁን መምረጥና መወሰን ፈለገ። በሱ መለኪያ ሮማዊ፣ ግሪካዊ ወይም ሳምራዊ ወዳጁ ሊሆን አይችልም። ኢየሱስ ግን ለዚህ ጥያቄ ቀጥተኛ መልስ አልሰጠም። ‘ሰዎችን በዘር በቀለም ሳትለይ ለወዳጅነት ምረጥ’ አላለውም። ይልቁንም አንድ ምሳሌ ተረከ። በምሳሌውም፣ አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ሲሄድ በወንበዴዎች ተደበድቦ ለሞት እንዳጣጣረና አንድ ሳምራዊ ሰው እንዴት እንደረዳው ይናገራል። ቁስሉን አክሞ፣ ከወደቀበትም አንስቶት ወደ ማረፍያ ቦታ ይወስደዋል። የወደቀውን ሰው ከሳምራዊው በፊት አንድ ካህንና አንድ ሌዋዊ አይተውት ነበር። ነገር ግን አልደረሱለትም። ወደ ሰውየው ከመቅረብ ይልቅ መራቅን መረጡ። ባልንጀራ አልሆኑለትም።

“መቼም ይህ ምሳሌ የሕግ መምሕሩን ሳይረብሸው አልቀረም፣ አይደል? አለ ጥበቡ።

“እንዴታ፣ በጣም ይረብሸዋል እንጂ! ለሱ እኮ አንድ ሳምራዊ የመልካም ሥራ አርአያ መሆን አይችልም! ባይሆን፣ ሳምራዊው ከደብዳቢዎቹ መሃል ቢሆን የሚጠበቅ ነገር ነው ብሎ ሳያስብ ይቀራል?” 

“ታዲያ ኢየሱስ ባልንጀራ ለሌላው የሚደርስና የሚያዝን ነው ማለቱ ነዋ?”።

“ትክክል ብለሃል፤ ባልንጀራህ የአንተ ማኅበር፣ ሃይማኖት፣ ብሔር አባል መሆን አይጠበቅበትም። ለዚህ ለወደቀው ሰው ያዘነለት ሳምራዊ ዘመዱ አልነበረም። ሳምራዊው የረዳበት የተደበቀ ምክንያትም አልነበረውም፤ ልርዳውና በኋላ እሱም ይጠቅመኛል አላለም። ርኅራኄ ብቻ ነው የገፋፋው።” አለች ኅሊና። ስትቀጥልም፣ “በዛሬ ዘመን ስለተከሰተ ነገር ላጫውትህ” አለችው።

“አንዲት ነጭ ወጣት ተማሪ ነች የነገረችኝ። ለእረፍት ወደ አንድ ሩቅ አገር ትሄዳለች። እዚያም ያገሯ ሰዎች ይጠብቋታል። የሚቀበሏት ሰዎች ጥቁሮች እንዳሉና ሰው እንደማያከብሩና አደገኛም እንደሆኑ ነግረዋታል። በፍጹም በመኪናቸው ውስጥ እንዳትገቢም ተብላለች። ያጋጣሚ ነገር ሆነና አድራሻ ትሳሳትና የወሰደችው የከተማው ባቡር ወዳልሆነ ቦታ ወሰዳት። ተሳፋሪዎችም እየወጡ እርሷ ብቻዋን ቀረች። ወደ ሹፌሩ ተጠጋች፤ ጥቁር መሆኑን ስታውቅ ደነገጠች። ስትፈራ ስትቸር ትክክለኛውንም አድራሻ በወረቀት ላይ ጽፋ አሳየችው። ካሁን ካሁን ገላምጦ ዞር በይ ይለኛል ስትልም ወደምትፈልገው ቦታ ለመድረስ የአንድ ሰዓት የመኪና መንገድ እንደሚጠይቅ ይነግራታል። መምሸቱን እያሰበች ትደነግጣለች። እንባዋ ይመጣል። የሚደርስላት ባልንጀራ ይኑር አይኑር አታውቅም። ሰውየው ግን ሐዘንዋን ተመልክቶ አረጋጋት። ሥራ እንደጨረሰ፣ ወደ ቤቱም በራሱ መኪና እንደሚገባ፣ ነገር ግን ወደምትፈልገው ቦታ ሊያደርሳት ፈቃደኛ መሆኑን ነገራት። አሁንም እየፈራች ወደ መኪናው ገባች። የተነገራት በፍጹም እነዚያ ሰዎች መኪና ውስጥ መግባት አደገኛ እንደሆነ ነበር። ሰውየው ወዳጆቿ በራፍ ላይ ሲያደርሳት ፍርሃቷ ወደ መረጋጋት፣ ኃዘኗ ወደ ደስታ ተለወጠ። ለማመስገን ብላ የነዳጅ ገንዘብ ለመክፈል ጠየቀች። ሰውየው ግን ገንዘብ እንደማይቀበል ነግሮአት በፈገግታ ሸኛት። እውነተኛ ባልንጀራ ሆናት።

“እንዴት የሚገርም ታሪክ ነው ባክሽ፤ ለካ በዘመናችንም ደጉ ሳምራዊ መሆን ይቻላል!”፣ አለ ጥበቡ።

“እንዴታ፤ አለች” ኅሊና።

ጥበቡም “አሁን፣ ሳስብ እኔም አንድ ነገር ትዝ አለኝ” አለና በተራው የሚከተለውን ነገራት፦ “በጦር ሜዳ አካባቢ በጥቁሮች አገር፣ በፈንጂ ምክንያት ወላጆቻቸውን ያጡና የቆሰሉ ሕፃናት ነበሩ፤ ታዲያ ከእነኚህ አንዱን የአካል ጉዳተና ሕፃን አንዲት ነጭ ሴት ልታሳድገው ወሰደችው። እንደ ወላጅ እናት አፈቀረችው። ለልጁ ከማንም በላይ ደረሰችለት”። ጸጥታ ሰፈነ፤ ሁለቱም ተክዘው ቀሩ። ሰዓት ማለፉም አልታወቃቸውም።

ባልንጀራዬ ማነው"? በአባ ዳንኤል አሰፋ  (ከካፑቺን ፍራንቸስካዊ የምርመርና የጽሞና ማእከል)

 








All the contents on this site are copyrighted ©.