Social:

RSS:

የቫቲካን ሬድዮ

ከዓለም ጋር የሚወያይ የር.ሊ.ጳጳሳትና የቤተ ክርስትያን ድምጽ

ቋንቋ:

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ \ አጠቃላይ ትምህርተ ክርስቶስና የመልአከ እግዚአብሔር ጉባኤ አስተምህሮ

መሥዋዕተ ቅዳሴ ጸሎተ ምስጋና እንጂ ለእይታ የሚቀርብ ትዕይትን ኣይደለም! ር.ሊ.ጳ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቅ.ጴጥሮስ ኣደባባይ - ANSA

08/11/2017 15:32

‘እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው።  የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ።  አባቶቻችሁ በምድረ በዳ መና በሉ ሞቱም፤  ሰው ከእርሱ በልቶ እንዳይሞት ከሰማይ አሁን የወረደ እንጀራ ይህ ነው።  ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ፤ ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል፤ እኔም ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው።’ (ዮሓ 6.47-51)

ውድ ወንድሞችና እህቶች እንደምን ኣደራችሁ!

በዛሬው ዕለት ኣዲስ የትምህርተ ክርስቶስ ዙርያ እንጀምራለን! የቤተክርስትስያን ኣንኳር ስለሆነው ስለ ቅዱስ ቊርባን እንመለከታለን፣ ከእግዚኣብሔር ያለን ግኑኘታችን ዘወተር በሚገባ ለመኖር ለእኛ ለክርስትያኖች የመሥዋዕተ ቅዳሴ ዋጋና ትርጉም በሚገባ መረዳት መሠረታዊ ግዳጅ ነው፣

በመላው ዓለም የሚገኙ ብዙ ክርስትያኖች እና ላለፉት ሁለት ሺህ ዓመታት በታሪክ ውስጥ ቅዱስ ቊርባንን ለመከላከል ብዙ ክርስትያኖች እስከ ሕይወታቸውን መሥዋዕተ ለማድረግ እንደታገሉ መርሳት የለብንም፣  ኣሁንም ቢሆን ብዙ ክርስትያኖች የእሁድ ቅዳሴ ለማስቀደስ ሕይወታቸውን ለኣደጋ የተጋለጡ እንዳሉም ኣለመዘንጋት ያስፈልጋል፣ በ304 ዓም በድዮክለስያን ስደት በሚታወቀው ወቅት በሰሜን ኣፍሪቃ በኣንድ ቤት ውስጥ ሲያስቀድሱ የነበሩ ክርስትያኖች እንደታሰሩ እና ያኔ የሮማ መንግሥት ኣስተዳዳሪ የነበረው  ‘ይህ ጉዳይ በጥብቅ የተከለከለ መሆኑን እያወቃችሁ ለምንድር ነው ሕገወጥ ነገር ለማድረግ የወሰናችሁ’ ብሎ በጠየቃቸው ግዜ ‘ሰንበት ሳናስቀድስ ለመኖር ኣንችልም’ ብለው መለሱለት፣  በሌላ ኣነጋገር ያላስቀድስንና ያልቆረብን እንደሆነ ለመኖር ኣንችልም የክርስትና ሕይወታችንም ትሞታለች ነው ያሉት፣ ለዚህም ነው ኢየሱስ ለሓዋርያት ‘እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም። ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ። ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና። ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ።’ ያለውም ለዚህ ነው፣

እነኚህ የሰሜን ኣፍሪቃ ክርስትያኖች ቅዳሴ ለማስቀደስና ቅዱስ ቊርባን ለመቀበል ሲሉ ተግድለዋል፣ ለቅዱስ ቊርባን ሲሉ ምድራዊ ሕይወትን መሥዋዕት ማድረግ እንደሚቻል ምስክርነት ትተዋል ምክንያቱም ቅዱስ ቊርባን ዘለዓለማዊ ሕይወት በመስጠት ጌታ ኢየሱስ በሞት ባደረገው ድል እንድንሳተፍ ያደርገናልና፣ ይህ ምስክርነት ለእያንዳንዳችን የሚያቀርበልን ጥያቄ ‘በመሥዋዕተ ቅዳሴ መሳተፍ እና በቅዱስ ቁርባኑ ማእድ መቅረብ ምን ትርጉም ይሰጠናል’ ሆኖ የግድ መልስ መስጠት እንዳለብንም ነው፣ ያ ለሳምራዊት ሴት ኣንደመልስ የተሰጠ ‘የዘለዓለም ሕይወት የሚሰጥ የሕይወት ውሃ ከከርሱ የሚያጐርፍ’ የሚለውን ምንጭ እየፈለግን ነው፣ ይህ የሕይወት ውሃ ሕይወታችንን መንፈሳዊ የኣምልኮና የምስጋና መሥዋዕት በማድረግ ከክርስቶስ ጋር ኣንድ ኣካል እንደምንሆን የሚያደርገንን እንፈልጋለን! የመሥዋዕተ ቅዳሴና የቅዱስ ቊርባን ጥልቅ ምሥጢርና ትርጉምም ይህ ነው፣ ቊርባን ማለት ምስጋና ማለት ነው፣ በቅድስት ሥላሴ ሕይወት የሚጨምሩንና ወደ የፍቅሩ ውህነት የሚለውጠን ለእግዚብሔር ኣብ ወልድና መንፈስ ቅዱስ የሚቀርብ ምስጋና ነው፣

ለወደፊቱ በምናደርጋቸው የትምህርተ ክርስቶስ ክፍለ ግዜዎች በቅዱስ ቁርባንና በቅዳሴ ዙርያ ለሚቀርቡና ለተረሱ ኣንዳንድ ጥያቄዎች እንደገና ለማግኘት ወይንም ኣዳዲስ ጥያቄዎችን በማግኘት ይህንን የእግዚኣብሔር ፍቅርን የሚያጸባርቅ ታላቅ የእምነት ምሥጢር ለመረዳት እንደምንችል እንመለከታለን፣

ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ክርስትያኖች የእምነትን ታላቅነት እንዲረዱና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መጋናኘት የሚሰጠውን ጣዕም እንዲያውቁት መንፈሳቸውን ለመቀስቀስ ብዙ ሰርተዋል፣ ለዚህም በመፈስ ቅዱስ መሪነት ሕዳሴ በተለይ ሥርዓተ ኣምልኮን በሚመለከት ቢተ ክርስትያን በእርሱ ሕይወት እንድታገኝና የተሰጥዋትን ጸጋዎች እንድታድስ ኣስፈላጊ መሆኑን ገለጡ፣ ለዚህም የመጀመርያ የሁለተኛ ቫቲካን ጉባኤ ሰነድ ስለሥርዓተ ኣምልኮ ይመለከታል፣

የጉባኤ ኣባቶች እንደ ዋነኛ ነጥብ ያነሱትም ሕዝበ ክርስትያንን በሥርዓተ ኣምልኮ ዙርያ ማስተማርና መኰትኰት ሲሆን በዚህም እውነተኛ ሕዳሴ ሊሆን እንደሚችል ኣምነው ነበር፣ ዛሬ የምንጀምረው የትምህርተ ክርስቶስ ኣስተምህሮ ኣንኳርም ይህ ነው፣ የዚሁ ታላቅ የእግዚኣብሔር ስጦታ ማለት በቅዱስ ቊርባን ኣማካኝነት ምግባችን እንዲሆን ራሱን የሰጠን ምስጢር እውቀት ለማሳደግ ነው፣

ምሥጢረ ጥቀ ቅዱስ ቊርባን ሕይወታችን የሆነው ጌታችን መድሃኒትችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመካከላችን የሚገኝበት ነው፣ በመሥዋዕተ ቅዳሴ መሳተፍም የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሕማማትና ኣዳኝ ሞት እንደገና መኖር ነው፣ ኣንድ የእግዚኣብሔር ግልጸት ሆኖ ጌታ ኢየሱስ በመንበረ ታቦት ቀርቦ ለመላው ዓለም ደህንነት ለእግዚብሔር ኣብ መሥዋዕት ሆኖ ይቀርባል፣ ጌታ እዛ ኣለ ነገር ግን ኣብዛኛውን ግዜ እዛ በምንሄድበት ግዜ ትኲረታችን በጌታ ከማድረግ ይልቅ ሌሎች ነገሮችን እየተመለከተንና ካህኑ ሲቀደስ እርስ በእርሳችን እየተናገርን ርቀን እንገኛለን፣ ጌታ መሆኑን የዘነጋን ይመስላል፣ ለምሳሌ ዛሬ እዚህ መካከላችን ኣሁኑኑ የኣገሪቱ ርእሰ ብሔር ወይንም በዚህ ዓለም ትልቅና ኣስፈላጊ ሰው እዚህ መካከላችን ቢደርስ እርግጠኛ ነኝ ሁላችን ኣጠገቡ ለመሆንና ሰላም እንድንለው በተሽቀዳደምን፣ እስቲ እሰቡት ለቅዳሴ ስንሄድ እዛ እኮ ጌታ ኢየሱስ ኣለ! ለምንድር ነው በሌላ ሃሳብ ተውጠን በግድየለሽነት የምንመላለሰው፣ ኣንዳንዶቹ ደግሞ ‘ኣባ ቅዳሴ የሚያሰለች ነው’ ይላሉ፣ አረ እባክህ ጌታ ያሰለቻል ኣኮ የምትለኝ እላቸዋለሁ፣ ኣይደለም ኣባ ቅዳሴው ሳይሆን ካህኑኑ ነው የሚሰለቸኝ ሊሉ ይችላሉ፣ እኔ ደግሞ ደግሜ እሺ ካህናትስ ለውጥ ያስፈልጋቸዋል እንበል በመንበረ ታቦቱ ያለው ጌታ ኣኮ ሁሌ እርሱ ነው፣ እላለሁ እባካችሁ ይህን ኣርትርሱ፣ ቅዳሴ ኣስቀድሱ የጌታን ሕማማትና ኣዳኝ ሞት እንደገና ኑሩት፣

እስቲ ኣሁን ቀለል ቀለል ያሉ ጥያቄዎች እናቅርብ፣ ለምሳሌ ቅዳሴ ሲጀምር ለምንድር ነው በትእምርተ መስቀል የምናማትበው! ለምንስ በሓጢኣቶቻችን በመጸጸት ንስሓ የምንገባው! ለእግረ መንገዳችን ሕጻናት ትእምርተ መስቀሉን እንደሚያደርጉት ኣስተውላቸኋል ወይ! ትእምርተ መስቀልስ ይሁን ሌላ ምልክት ምን እንደሚያደርጉ ኣይታወቅም ነገር ግን ሕጻናትን ትእምርተ መስቀል እንዲህ ነው የሚደረገው ብሎ ማስተማርና ቅዳሴም ይሁን ሕይወት እንዲሁም ዕለቱ እንደዛ እንደሚጀመር ማስተማር ያስፈልጋል፣ ስለዚህ ሕጻናትን ትእምርተ መስቀል እንዴት እንደሚደረግ ኣስተምሩ፣ እሺ ጥያቄዎቹን እንቀጥል! በቅዳሴ የሚነበቡስ ለምንድር ነው እዛ ያሉት፣ ለምንስ በእሁድ ሶስት ንባቦች በሌሎች ቀኖች ደግሞ ሁለት ንባቦች ብቻ ያቀርባሉ! ንባባቱና በቅዳሴ ምን ያመልክታሉ፣ ለምን ይነበባሉ ምን ተራስ ኣላቸው! ለምንስ በቅዳሴ ግዜ ቄስ ኣልዕሉ ኣልባቢክሙ ልቦቻችሁን ወደ ሰማይ ከፍ ኣድርጉ ይላል! ተለፎኖቻችሁን ወደ ላይ ኣንስታችሁ ፎቶ ኣንሱ ኣይደለም የሚለው፣ ይህ መጥፎ ተግባር ነው፣ እዚህ በቅዱስ ጴጥሮስ በምቀድስበት ግዜ ምእመናን ብቻ ሳይሆኑ ኣንዳንድ ካህነት ጳጳሳትም ሳይቀር ፎቶ ለማንሳት የሚታገሉ ሳይ እጅግ ያሳዝነኛል፣ መሥዋዕተ ቅዳሴ ትዕይንት ኣይደለም፣ የጌታን ሕማማትና ሞት የምናስብበትና እንደገና የምንኖርበት ነው፣ ስለዚህ ካህን ኣልዕሉ ኣልባቢክሙ ሲሉ ተለፎኖቻችሁን ኣይደለም የሚለው ይህንን ኣትርሱ፣

ወደ መሰረታዊ ነገሮች መመለስ እጅግ ኣስፈላጊ ሆኖ ዋነኛውን ነገር በሚታየውና በሚጨበጠው ስርዓተ ምሥጢራት እንደገና ማግኘቱ ያስፈልጋል፣ ያ ቅዱስ ቶማስ ጌታን ከትንሣኤ በኋላ ‘የችንካሩን ምልክት በእጆቹ ካላየሁ ጣቴንም በችንካሩ ምልክት ካላገባሁ እጄንም በጎኑ ካላገባሁ አላምንም አላቸው።’ (ዮሓ 2025) በማለት የጠየቀው የእያንዳንዳችን ጥያቄ ስለሆነ ምሥጢራት ይህንን ለመመለስ የቆሙ ናቸው፣ ስለዚህ ምስጢራት በተለይ ደግሞ ምስጢረ ጥቀ ቅዱስ ቊርባን የእግዚኣብሔር ፍቅር ምልክት ሆነው ከጌታ ጋር እንድንገኛ የሚያደርጉት እጅግ የተከበሩ መንገዶች ናቸው፣

ስለዚህ በዚሁ ዛሬ በምንጀምረው ትምህርተክርስቶስ ይህ ምስጢር ኣምቆ ይዞዋቸው ያሉትን ቆንጆ ነገሮች ኣብረን እንደግና ልንዳስሳቸው እንጥራለን፣  በዚሁ ኣዲስ ጉዞ እመቤታችን ድንግል ማርያም ትርዳን በማለት የዕለቱን ትምህርተ ክርስቶስ ደምድመው በተለያዩ ቋንቋዎች ኣመስግነውና ሰላምታ ኣቅርበው በሓዋርያዊ ቡራኬ ተሰናብተዋል፣

 

 

08/11/2017 15:32