Social:

RSS:

የቫቲካን ሬድዮ

ከዓለም ጋር የሚወያይ የር.ሊ.ጳጳሳትና የቤተ ክርስትያን ድምጽ

ቋንቋ:

ቤተ ክርስትያን \ ኢትዮጵያ

ዘመነ ጽጌ 5ኛ ሰንበት ቃለ እግዚኣብሔር በክቡር አባ ግርማቸው ተስፋዬ

ዘመነ ጽጌ 5ኛ ሰንበት ቃለ እግዚኣብሔር በክቡር አባ ግርማቸው ተስፋዬ - RV

07/11/2017 09:18

ዘመነ ጽጌ 5 ሰንበት

ጥቅምት 26/2010 ዓ.ም ቃለ እግዛኢብሔር በክቡር አባ ግርማቸው ተስፋዬ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ካህን

ቆላስይስ 1:1-11

በእግዚአብሔር ፈቃድ የክርስቶስ ኢየሱስ ሐዋርያ ከሆነው ከጳውሎስና ከወንድማችን ከጢሞቴዎስ፤በቈላስይስ ለሚኖሩ፣ በክርስቶስ ለሆኑ ቅዱሳንና ታማኝ ወንድሞች፤ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።

ምስጋናና ጸሎት

ስለ እናንተ በምንጸልይበት ጊዜ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አባት እግዚአብሔርን ሁል ጊዜ እናመሰግናለን፤ ምክንያቱም በክርስቶስ ኢየሱስ ስላላችሁ እምነትና ለቅዱሳን ሁሉ ስላላችሁ ፍቅር ሰምተናል፤ ይህም የሆነው በሰማይ ተዘጋጅቶ ከተቀመጠላችሁ ተስፋ የተነሣ ነው፤ ስለዚህ ተስፋ በወንጌል የእውነት ቃል አስቀድማችሁ ሰማችሁ፤ ይህም ወደ እናንተ ደርሶአል። ይህንም ወንጌል ከሰማችሁበትና የእግዚአብሔርን ጸጋ በእውነት ከተረዳችሁበት ቀን ጀምሮ በዓለም ዙሪያ እየሠራ እንዳለ ሁሉ በእናንተም ዘንድ ፍሬ እያፈራና እያደገ ነው። ይህንም ስለ እኛ። የክርስቶስ ታማኝ አገልጋይ የሆነው፣ አብሮንም በአገልግሎት የተጠመደው ተወዳጁ ኤጳፍራ አስተማራችሁ፤ ደግሞም በመንፈስ ስላላችሁ ፍቅር ነገረን።

ከዚህ የተነሣ እኛ ደግሞ ይህን ከሰማንበት ቀን ጀምሮ እግዚአብሔር የፈቃዱን ዕውቀት በመንፈሳዊ ጥበብና መረዳት ሁሉ ይሞላችሁ ዘንድ ስለ እናንተ መጸለይና መለመን አላቋረጥንም፤ የምንጸልየውም ለጌታ እንደሚገባ እንድትኖሩና በሁሉም ደስ እንድታሰኙት ነው፤ ይኸውም በመልካም ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁ እግዚአብሔርን በማወቅ እያደጋችሁ፣ ታላቅ ጽናትና ትዕግሥት ይኖራችሁ ዘንድ፣ እንደ ክቡር ጒልበቱ መጠን በኀይል ሁሉ እየበረታችሁ፣ ደስ እየተሰኛችሁ።

ያዕቆብ 1:1-12

የእግዚአብሔርና የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ የሆነው ያዕቆብ፤ ለተበተኑ ለዐሥራ ሁለቱ ነገዶች፤ ሰላም ለእናንተ ይሁን።

መከራና ፈተና

ወንድሞቼ ሆይ፤ ልዩ ልዩ መከራ ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቍጠሩት፤ ምክንያቱም የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንደሚያስገኝ ታውቃላችሁ። ምንም የማይጐድላችሁ ፍጹማንና ምሉኣን እንድትሆኑ ትዕግሥት ሥራውን ይፈጽም። ከእናንተ ማንም ጥበብ ቢጎድለው፣ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉም የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፤ ለእርሱም ይሰጠዋል። ዳሩ ግን ሳይጠራጠር በእምነት ይለምን፤ ምክንያቱም የሚጠራጠር ሰው በነፋስ እንደሚገፋና እንደሚናወጥ የባሕር ማዕበል ነው። ያ ሰው፣ ከጌታ አንዳች ነገር አገኛለሁ ብሎ አያስብ፤ እርሱ በሁለት ሐሳብ የተያዘና በመንገዱ ሁሉ የሚወላውል ነው።

ዝቅ ያለው ወንድም ከፍ በማለቱ ይመካ። ባለ ጠጋውም ዝቅ በማለቱ ይመካ፤ እንደ ሣር አበባ ይረግፋልና። ፀሓይ በነዲድ ሙቀቷ ወጥታ ሣሩን ታጠወልጋለችና፤ አበባው ይረግፋል፤ ውበቱም ይጠፋል፤ እንዲሁም ባለጠጋ ሰው፣ በዕለት ተግባሩ ሲዋትት ሳለ ይጠፋል።

በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፤ ምክንያቱም ፈተናን ሲቋቋም እግዚአብሔር ለሚወዱት የሰጠውን ተስፋ፣ የሕይወትን አክሊል ያገኛል።

 

ማቴ። 6: 25-34

አለመጨነቅ

 “ስለዚህ እላችኋለሁ፣ ስለ ኑሮአችሁ ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? በማለት አትጨነቁ። ሕይወት ከምግብ፣ ሰውነትስ ከልብስ አይበልጥምን?እስቲ የሰማይ ወፎችን ተመልከቱ፤ አይዘሩም፤ አያጭዱም፤ በጐተራም አያከማቹም፤ ይሁን እንጂ የሰማዩ አባታችሁ ይመግባቸዋል። እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን? ለመሆኑ ከእናንተ መካከል ተጨንቆ በዕድሜው ላይ አንዲት ሰዓት መጨመር የሚችል አለን?

 “ደግሞስ ስለ ልብስ ለምን ትጨነቃላችሁ? እስቲ የሜዳ አበቦችን ተመልከቱ፤ አይለፉም፤ ወይም አይፈትሉም። ስለዚህ እላችኋለሁ፤ ያን ያህል ክብር የነበረው ንጉሥ ሰሎሞን እንኳ ከእነዚህ አበቦች እንደ አንዲቱ አልለበሰም። እናንተ እምነት የጐደላችሁ እግዚአብሔር ዛሬ ታይቶ በነጋታው እሳት ውስጥ የሚጣለውን የሜዳ ሣር ይህን ያህል ካለበሰ እናንተንማ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁ? ስለዚህ፣ ‘ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን?’ ብላችሁ አትጨነቁ፤ አሕዛብ እነዚህን ነገሮች ሁሉ ለማግኘት ይጨነቃሉና፤ የሰማዩ አባታችሁም እነዚህ ሁሉ ለእናንተ እንደሚያ ስፈልጓችሁ ያውቃል።ከሁሉ አስቀድማችሁ ግን የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቁን እሹ፤ እነዚህ ሁሉ ይጨመሩላችኋል። ስለዚህ ለነገ በማሰብ አትጨነቁ፤ የነገ ጭንቀት ለነገ ይደር፤ እያንዳንዱ ዕለት የራሱ የሆነ በቂ ችግር አለውና”።

 

አስተንትኖ በክቡር አባ ግርማቸው ተስፋዬ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ካህን

 

በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ዛሬም በዚህ እለት በቤቱ ስብሰቦ የቃሉ ተካፋይ እንድንሆን ያደረገን እግዚአብሔር አምላካችን ስሙ ከዘለአለም እስከ ዘለአለም የተመሰገነ ይሁን።

ቅዱስ ሐዋሪያው ጳውሎስ ለቆላስያስ ሰዎች በጻፈው መልእክት ውስጥ እርስ በርሳቸው ስላላቸው ፍቅር ስለ እምነታቸው ጠንካራነት እግዚአብሔርን ሲያመሰግን ሰምተናል።

እነዚህ ሁለቱ ቃሎች ማለትም እምነትና ፍቅር አይነጣጠሉም። እግዚአብሔርን የሚወድ ወንድሙንና እህቱን ይወዳል። በእግዚአብሔር የሚታመን ወንድምና እህቱን ያፈቅራል። በዐይን የሚታየውን ወንድሙን የሚጠላ በዐይን ያላየውን እግዚአብሔርን ግን እወዳለሁ  ወይም አፈቅራለሁ የሚል ሰው ሐሰት ይናገራል ይላል 1ኛ ዮሐ 4፡20

እግዚአብሔርን መውደዳችን ማረጋገጫው መልካም ሥራችን ነው። ቅዱስ ሐዋሪያው ያእቆብ በመልእክቱ እንዲህ ይላል ያዕ 2፡14-17 ወንድሞቼ ሆይ አንድ ሰው እምነት አለኝ ቢል ሥራ ግን ባይኖረው ምን ይጠቅመዋል? እንዲህ ያለው እምነት ሊያድነው ይችላልን? አንድ ወንድም ወይም አንዲት እኅት የሚለብሱት ልብስም ሆነ የሚመገቡት ምግብ አጥተው ከእናንተ መካከል አንዱ በሰላም ሂዱ አይብረዳችሁ ጥገቡ ቢላቸው ለሰውነታቸው ግን የሚያስፈልጋቸውን ባይሰጣቸው ምን ይጠቅማቸዋል? እንዲሁ ሥራ የሌለው እምነት በራሱ የሞተ ነው ይላል።

ስለዚህም ቅዱስ ሐዋሪያው ጳውሎስ በቆላስያስ የሚኖሩትን ክርስቲያኖች እምነትና ፍቅር በማየት እግዚአብሔርን አመስግኗል። ወደ እኛ ህይወት መለስ ብለን ስንመለከትስ ፤ ቅዱስ ሐዋሪያው ጳውሎስ ዛሬ እኛ ባለን እምነትና ፍቅር እግዚአብሔርን ያመሰግን ይሆን?

በእምነታችን ጠንካሮችና ፤ እምነታችንንም በተግባር የምናውለው ከሆነ በእርግጥም እግዚአብሔርን ያመስግናል ፤ በፍቅር የምንኖር ከሆነ እግዚአብሔርን ያመሰግናል ፤ በመተሳሰብ የምንኖር ከሆነ እግዚአብሔርን ያመሰግናል ። ምን አልባት በእምነታችን ጠንካሮች ካልሆንንና ፤ እምነታችንንም በተግባር የማናውለው ከሆነ ደግሞ ፤ ለማስተካከል ጥረት ማድረግ እንደሚገባን ምክሩን ይለግሰናል።

በእምነቱ ጠንካራ የሆነ ሰው ፤ ዘወትር እግዚአብሔር በሚሰጠው ጸጋና ኃይል ስለሚመራ ፤ ሕይወቱ የተቀደሰና የተስተካከለ ነው። በሁለተኛው ንባብ ፤ ቅዱስ ሐዋሪያው ያእቆብ በእምነታችን ጠንካሮች መሆን እንዳለብን ያሰምርበታል። በአሸዋና በአለታማ (ድንጋያማ) መሠረት ላይ የተሰራውን ቤት እናስተውስ። ምን አልባት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስን በመከተላችን በጣም ብዙ ፈተና ሊገጥመን ይችላል፡ ሁሉንም በትእግስትና በፅናት የምናልፍ ከሆንን ደግሞ አሸናፊዎቹ እኛ ነን  አሸናፊ የሆነ ሰው ደግሞ ሽልማትን ይቀበላል ሽልማቱም ዘለዓለማዊ ሕይወት ነው፡፡

በማርቆስ ወይንም በሉቃስ ወንጌል ላይ እስከ መጨረሻ የሚፀና ግን ይድናል የሚለውም ይህንኑ ነው፡፡ሌላው ቅዱስ ሐዋሪያው ያእቆብ የሚነግረን ነገር ቢኖር እግዚአብሔርን ስንለምን ስንጠይቅ እንደሚያደርግልን ሙሉ በሙሉ እምነታችንን በእርሱ ላይ መጣል ያስፈልጋል፡፡ ሙሉ እምነት የታከለበት ልመና መልሱም እንዲሁ የፈጠነ ነው፡፡በጌታችን እየሱስ ክርስቶስን እነዛ ሁለቱ እውሮች እባክህ ራራልን ብለው ሲጠይቁት ምን ነበር ያላቸው?  ይህን ማድረግ እንደምችል ታምናላችሁን አላቸው እነርሱም አዎ እናምናለን አሉ እርሱም እንደ እምነታችሁ ይሁንላችሁ አላቸው ወዲያውኑም ተፈወሱ፡፡

ዛሬም እኛ በሙሉ እምነት ከጠየቅነው ከለመንነው እንደ እምነታችሁ ይሁንላችሁ ይለናል ስለዚህ በውስጣችን ያለው እምነታችን በሂወታችን ብዙ ነገሮችን ለመቀየር ዓይነተኛ ሚና ይጫወታልና የእምነታችንን ነገር ችላ ልንለው አይገባም፡፡

ማቴ 6፡25-34

የማቴዎስ ወንጌል ስለምትበሉትና ስለምትጠጡት ነገር አትጨነቁ ይለናል፡፡ ይህ ማለት ስለ ወደፊት ኑሮአችሁ አታስቡ እቅድ አታውጡ ማለት አይደለም፡፡ እንደ ምሳሌ የሰማይ ወፎችን ተመልከቱ ብሎ አስቀምጦልናል ፤ እነርሱ አይዘሩም አያጭዱም ፤ የሰማይ አባታቸው ይመግባቸዋል ይላል፡፡

ነገር ግን ወፎችም ቢሆኑ የእለት ቀለባቸውን ለማግኘት ከቦታ ቦታ መዘዋወር አለባቸው፡፡ እንዲሁም እኛ የእለት ምግባችንን ለማግኘት መትከል መኮትኮት ማጠጣት ያስፈልጋል ፤ እግዚአብሔር በሰጠን በየትኛውም የሥራ መስክ በተገቢ መልኩ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል፡፡ ቅዱስ ሐዋሪያው ጳውሎስ በተሰሎንቄ መልአክቱ እንዲህ ሲል ያዛል ፤ ሊሰራ የማይወድ አይብላ ፤ እኛም ሌሊትና ቀን በድካምና በጥረት እየሰራን እንኖር ነበር 2ተሰሎንቄ 3፡10 ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ  ሲናገር ፤ አባቴ ይሠረል እኔም እሠራለሁ ይላል ፤ ሐዋርያቶችም ይሠሩ እንደነበር በተሰሎንቄ መልእክት አተናል ፤ ስለዚህ እኛም ሥራን መሥራት ግድ ይለናል፡፡

ብዙውን ጊዜ ሥራ በአዳምና በሔዋን ኃጢያት ምክንያት  ለሰው ልጅ የተሰጠ እዳ ተደርጎ ሊቆጠር ይችል ይሆናል ፤ ነገር ግን እውነታው ይህ አይደለም ፤ አዳምና ሔዋን ሥራ ይሰሩ ነበር ዘፍ 2፡15 "እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ወስዶ ያበጁትም ይጠብቁትም ዘንድ በኤደን ገነት አኖረው"።

ስለዚህ ሥራ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ የሰጠው ፀጋ ነውና ፤ ሁላችንን የየድርሻችንን  እንድንሰራ ያስፈልጋል። ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በወንጌሉ የሚያዘን ፤ ጭንቀትን እንድናስወግድና በቅድሚያ የእግዚአብሔርን ጽድቅ እንድንፈልግ እንጂ ፤  ሥራ ከመስራት እንድንቆጠብ አይደለም። የእግዚአብሔር ጸጋ ፤ የእግዚአብሔር ጽድቅ ካለ ፤ ሌላው የሚያስፈልገንን ሁሉ ያውቃልና በሙላት ይሰጠናል።

ሰው ከመጠን በላይ በመጨነቅ የሚጨምረው ነገር ባይኖርም ፤ የሚቀንሰው ነገር ግን አለ ፤ ይኽውም ሀሳብን፣ ተስፋ መቁረጥንና ብስጭትን ይጨምራል። እነዚህ ነገሮች ደግሞ ፤ ሰውን ወደ ህመምና ወደ ሞት ይወስዳሉ ፤ በእምነቱም ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ያሳድራሉ። ስለዚህ ጭንቀትን አስወግደን ፤ በቅድሚያ የእግዚአብሔርን ጽድቅ መሻት ፤ ከዛም የሚጠበቅብንን ሁሉ በተቻለን አቅም መሥራት ያስፈልጋል።

በተረፈው ደግሞ እግዚአብሔርን እንዲሞላበት ፤ በሙሉ እምነት እግዚአብሔርን መለመን ያስፈልጋል። የሰማይ ወፎች አይዘሩም አያጭዱም የሚለው የጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ብዙ ያስተምረናል። ለዚህም እናታችን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ፤ ከልጇ ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ  ጸጋን፣ በረከትን፣ ብርታትንና የእምነት መጠንከርን ታማልደን። የሰማነውን በልባችን ያሳድርልን፡፡

በክቡር አባ ግርማቸው ተስፋዬ የተዘጋጀ

07/11/2017 09:18