2017-11-02 10:53:00

"ቅዱሳን ከሰው ሁሉ በላይ የሆኑ ሰዎችም አልነበሩም፣ ነገር ግን የሚያጋጥማቸውን ፈተናዎችን እየታገሉ የኖሩ ሰዎች ነበሩ"


ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በጥቅምት 21/2010 ዓ.ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት እንደ ገለጹት ይህ ዛሬ እያከበርነው የምንገኘው የቅዱሳን በዓል የእኛም በዓል ነው ካሉ ቡኃላ ይህም የሚሆንበት ምክንያት እኛ መልካም እና ብርቱ ሰዎች ስለሆንን ሳይሆን ቅዱስ የሆነው የእግዚኣብሔር ሕልውና የእኛንም ሕይወት ስለ ሚነካ ነው ብለዋል።

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ታዳሚዎች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የቅዱሳንን አመታዊ በዓል ለማክበር ለተገኙ ምዕመናን እና የሀገር ጎብኚዎች በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተመርኩዘው ያደረጉትን የወንጌል አስተንትኖ እንደ ሚከተለው ተርጉመናዋል አብራችሁን በመሆን እንድትታደሙት ከወዲሁ እንጋብዛለን።

የዚህን አስተንትኖ ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ! መልካም በዓል እንዲሆንላችሁም እመኛለሁ።

ዛሬ የምናከብረው  ታላቁ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓል የእኛም "በዓል" ነው። ይህም የሆነው እኛ መልካም ስለሆንን ሳይሆን የእግዚአብሔር ቅድስና እኛንም ሕይወት ስለሚነካ ነው። ቅዱሳኖች ፍጹም የሆነ የሕይወት አብነት አሳይተውን ያለፉ ሰዎች አልነበሩም፣ ነገር ግን በእግዚአብሔር ሕልውና ውስጥ ያለፉ ሰዎች ናቸው። ይህንንም በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ከሚታዩ ብርሀን ከሚፈነጥቁ መስኮቶች ጋር ማነፃፀር እንችላለን። እነርሱም የተለያዩ ዓይነት ቀለሞችን ይፈነጥቃሉ። ቅዱሳን የእግዚኣብሔርን ብርሃን በልባቸው የተቀበሉ እና  እንደየባሕሪያቸው እና እንደየችሎታቸው ይህንን ብርሃን ለዓለም ያሰራጩ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ናቸው። ነገር ግን ሁሉም ግልጽ የሆኑ ሰዎች በመሆን  እንቅፋቶችን እና የኃጢአትን ጨለማ ለማሰውገድ በመታገል፣ የእግዚኣብሔር ደማቅ ብርሃን በሕይወታቸው እንዲያልፍ ያደርጉ ነበር፣ ይህም ለእኛ የሕይወታችን ዋነኛው ዓላማ ሊሆን ይገባዋል።

በእርግጥ ኢየሱስ ዛሬ በተነበበልን የወንጌል ቃል ውስጥ (ማቴ. 5.3) የእርሱ ለሆንን ለእኛ ሁላችን “ብጹዐን” በማለት ሲጠራን ሰምተናል። ኢየሱስ የወንጌል ስብከቱን የጀመረው በዚሁ ቃል ሲሆን ይህም ቅዱስ “ወንጌል” መልካም ዜና መሆኑን ያሳያል ምክንያቱም ወደ ደስታ የሚመራን መንገድ እርሱ ብቻ በመሆኑ የተነሳ ነው። ከኢየሱስ ጋር የሚኖር ሰው ብጹዕ እና ደስተኛ ሰው ይሆናል። ደስታ የሚገኘው የተለያዩ ነገሮች በማጋበስ ወይም ደግሞ ሌላ ሰውን ለመምሰል በመሞከር አይደለም! በፍጹም አይደለም። ደስታ የሚመነጨው ወይም ደግሞ ደስታን የምንጎናጸፈው ከጌታ ጋር በምንሆንበት ወቅት እና በፍቅር ስንኖር ብቻ ነው። በእውኑ ይህንን ታምናላችሁን? ስለዚህም ሕይወታችን ጣዕም እንዲኖረው የሚያደርጉ ንጥረ ነገሮች እየሱስ በማቴዎስ ወንጌል 5። 3-12 ስለተባረኩ ሰዎች የተናገራቸው ቃላቶች ናቸው፣ በመንፈስ ራሳቸውን ዝቅ በማድረግ ለእግዚኣብሔር ቦታ ይሰጣሉ፣ ለሌላ ሰዎች መጸለይን ያውቁበታል፣ ራሳቸውም ለሠሩት ስህተት ይጸልያሉ፣ የዋሆች ናቸው፣ ለፍትህ ይታገላሉ፣ ለሁሉም ምሕረትን ያደርጋሉ፣ ንጹህ ልብ አላቸው የልባቸውንም ንጽህና ይጠብቃሉ፣ በሰዎች መካከል ሰላም እንዲፈጠር ይጥራሉ፣ በደስታም ይኖራሉ፣ ማንንም አይጠሉም፣ መክራን በሚቀበሉበት ወቅት ሁሉ ክፉን በክፉ ሳይሆን ክፉን በመልካም ይመልሳሉ።

ይህ ነው የብጽዕና መንገድ! እጅግ በጣም ለየት ወይም ወጣ ያለ አካላዊ መግለጫዎችን አይጠቀሙም፣ ከሰው ሁሉ በላይ የሆኑ ሰዎችም አይደሉም፣ ነገር ግን በእየለቱ የሚያጋጥማቸውን ፈተናዎችን እና ችግሮችን  እየታገሉ የኖሩ ሰዎች ናቸው። ቅዱሳን የሚባሉት እንግዲህ እነዚህን የመሰሉ ሰዎች ናቸው። እንደ ማንም ሰው በዓለም ውስጥ ያለውን የተበከለ አየር እየሳቡ የኖሩ፣ ነገር ግን በጉዞዋቸው የሕይወትን መንገድ ሳይስቱ ኢየሱስ በማቴዎስ ወንጌል ላይ የጠቀሳቸውንና ያመለከታቸውን የክርስቲያን ሕይወት ፍኖተ ካርታ የሚያሳየውን መንገድ ጠብቀው የተጓዙ ሰዎች ናቸው። ዛሬ የምናክብረው የቅዱሳን በዓል የሚያሳየውም ይህንን የክርስቲያን ሕይወት ፍኖተ ካርታ ከግማሽ በላይ የተጓዙትን ሰዎች ነው፣ በቤተ ክርስቲያን የቅዱሳን እና የቅዱሳት መዝገብ ላይ የተመዘገቡ ቅዱሳንን ብቻ ሳይሆን እየዘከርን የምንገኘው ነገር ግን በጣም ብዙ የሚባሉ የምናውቃቸውን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ይህንን ገድል ታጋድለው ያለፉትን ሰዎችን ጭምር ነው።  ይህ በዓል የቤተሰብ በዓል ጭምር ነው። በጣም ብዙ የዋህ የሆኑና ብዙም የማይታወቁ ሰዎች ዓለማችን ጉዞዋን ወደ ፊት እንድትቀጥል በማድረግ ከእግዚኣብሔ ጋር እየተባበሩ ይገኛሉ። ዛሬም ቢሆን በእኛም ዘመን ይህንን የመሳሰሉ በጣም ብዙ ሰዎች ይገኛሉ።

ዛሬ ኢየሱስ በተራራ ላይ ሆኖ ያስተማረው  ትምህርት የጀመረው “በመንፈስ ራሳቸውን ዝቅ የሚያደርጉ ሰዎች የተባረኩ ናቸው በማለት ነው።ታዲያ ይህ ምን ማለት ይሆን? ስኬታማ ለመሆን አይደለም የኖሩት፣ ለስልጣን፣ ለገንዘብ ወዘተ. . . አልንበረም የኖሩት። “ለራሱ በምድር ላይ ሀብት የሚያከማች ሰው በእግዚኣብሔር ፊት ግን ድኻ የሆነ ሰው” . . . (ሉቃ. 12.21) እንደ ሆነም ጠንቅቀው ያውቃሉ። በተቃራኒው የልባቸው ሀብት ጌታ እንደ ሆነ አጥብቀው ያምናሉ፣ ለባልንጀራ ያለን ፍቅር ብቻ የማትረፊያ መንገድ እንደ ሆነም ያውቃሉ። አንድ አንድ ጊዜም የሆነ ነገር በሚጎለን ሰዓት እንከፋለን ወይም ደግሞ ነገሮች እኛ እንዳሰብነው በማይጓዙበት ወቅቶች ሁሉ እንጨነቃለን፣ እነዚህን እና እነዚህን የመሳሰሉትን ነገሮች በምንፈጽምባቸው ወቅቶች ሁሉ ኢየሱስ ካሰተማረን መስመር እየወጣን እንደ ምንገኝ ማስታወስ ግድ ይለናል። ነገር ግን በጌታ እና በፍቅር ብቻ ነው ኢየሱስ ያስተማረንን ትምህርት በተግባር ላይ ማዋል የሚቻለውም በዚሁ መንገድ ብቻ እንደ ሆነ ልብ ልንል ይገባል።

የእግዚኣብሔር እናት የሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ወደ ቅድስና የምናደርገውን ጉዞ በአማልጅነቷ ታግዘን አሜን!!








All the contents on this site are copyrighted ©.