2017-09-20 15:38:00

ሰብአዊ ክብረቱን ለማስመለስ የተቸገረንና የሚሰቃይ ሰውን መሸኘት ያስፈልጋል! ር.ሊ.ጳ


ቅ.ኣ.ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ትናንትና ማክሰኞ መስከረም 9 ቀን 2010 (19.09.2017 እ.ኤ.አ) በቅድስት ማርታ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ‘ዓለማችን በተለያዩ ምክንያቶች በስቃይ በሚገኙ ሰዎች ሞልታለች! ጌታ ለእነዚህ ሰዎች የምንራራለት ጸጋ እንዲሰጠንና እጐናቸውን ሆነን በእጃቸው ኣንስተን ጌታ ወደመደበላቸው የክብር ቦታ እንድንሸኛው እንዲረዳን እንጸልይ’ ሲሉ ስለዋነኛው የክርስትያን ምግባረ ሰናይ ሰብከዋል፣

የላቲኑ ሥርዓተ ኣምልኮ በምትከተል ካቶሊካዊት ቤተክርስትያን ትናንትና የተነበበው ወንጌል ከሉቃስ 7.16 ሲሆን ናይን በሚባል መንደር የምትኖር የነበረች ኣንዲት መበለት ሴት ኣንድያ ልጅዋ ሞቶባት ወደ ቀብር ሲሄዱ ጌታ ኢየሱስ ማንም ሳይጠይቀው ሁኔታው ሆዱን ስለበላውና ለሴቲቱም ስለራራላት ሬሳውን ተሸክመው ለመቅበር ይጓዙ የነበሩትን ኣቁሞ የወጣቱን ሬሳ በመንካት ኣንተ ጐበዝ ተነሥ እልሃለሁ ባለው ግዜ ልጁ ከሞት ተነሥቶ መናገር እንደጀመረና ጌታ ኢየሱስም ልጁን ለእናቱ እንደሰጣት የሚገልጥ ክፍል ነበር፣ በወንጌሉ ትረካ ‘ሁሉንም ፍርሃት ያዛቸውና። ታላቅ ነቢይ በእኛ መካከል ተነሥቶአል፥ ደግሞ። እግዚአብሔር ሕዝቡን ጐበኘ እያሉ እግዚአብሔርን አመሰገኑ።’ይላል፣

ቅዱስነታቸው በታሪኩ ተመርኲዘው ምስኪኖች በመጽሓፍ ቅዱስ በብዙ ቦታ የምናገኛቸው ትውክልታቸውም በእግዚኣብሔር ሆኖ በበጎ ሰዎች ኣማካኝነት እንደሚረዳቸው በማሳሰብ እነኚህ ምስኪኖች በተለይ በብሉይ ኪዳን የምናገኛቸው መበለቶች እናት ኣባት የሌላቸው እጓለማውቶች ስደተኞች እና የማይታወቁ እንግዶች እንደነበሩ ገልጠዋል፣ በብዙ የመጽሓፍ ቅዱስ ገጾችም እነኚህን ወገኖች የሚረዱ በማሕበረሰቡ ቦታ እንዲኖራቸው ኣደራ የሚሉ ኣንቀጾች ኣሉ፣ ኢየሱስም በዓይነ ልቡናው ስለሚመለከት ነገሮችን በዝርዝር ለማየትና ለመረዳት ይችላል፣ ኣንድን ነገር ኣይቶ ለመረዳትና የሚያስፈልገውን እርዳታ ለማቅረብ የሚያንቀሳቅስ ስሜት የልብ ስሜት ነው፣ ከሆድ የሚነሳና ሁሉን የሚያስተጋባ ስሜት ነው፣ ሆደ ባባ እንደሚለው ለማለት ነው፣ ይህ ሁኔታ በቃል ብቻ ምስኪን እንዴትስ ያሳዝናል ብሎ የሚታለፍ ሳይሆን ወደ ድርጊት የሚገፋፋ እና በሁኔታው ለመሳተፍና ኣንድ ኣበርክቶ ለማድረግ የሚያስችል ነው፣ ይህም ርህራሄ ይባላል፣ በወንጌል ታሪክ ያለው እውነታም ኢየሱስ ኣንዲት መበለትና ኣንድያ ልጅዋን ያያል ልቡም ይነካል፣ ምናልባት የሆነ ሰው ኣባ! የዚህ ዓይነት ሁኔታዎች በየዕለቱ የሚከናወኑ የሕይወት ክፍል በመሆናቸው ኢየሱስ በተናጠል ከመመልከት ይልቅ ለምን በቦታው ለነበረው ሕዝብ ኣልተቸገረም ኣላስተማረም ብሎ ሊጠይቅ ይችላል፣ ነገር ግን ኢየሱስ በቦታው ከነበረው ብዙ ሕዝብ የዛች መበለትና ኣንድያ ልጅዋ ሁኔታ ኣሳሰበው ቅድምያም ለዛ ጉዳይ ሰጠ፣ ሆዱ ባባ ልቡም ወደዛ ኣዘነበለ፣ ራራ! ርህራሄ ሲባልም መቅረብና መሸኘትን ያመለክታል፣ ብዙ ነገሮች እናያለን! ማየትና ቀረብ ብሎ መርዳትም የተለያዩ ነገሮች ናቸው፣ ወደ ሁኔታው ቀረብ ብሎ በእጅ መንካት እንጂ በሩቅ መመልከት ኣይደለም፣ ኢየሱስ በመጀመርያ በሁኔታው ልቡ እንደተነካ እናዳዘነ ሲመለከት በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ቀረብ ብሎ ሬሳውን እንደነካ በሶስተኛ ደረጃም በሉ ደህና ሁኑ ብሎ ኣይደለም የሄደው! ኣንተ ጐበዝ ተነስ ኣልሃለሁ ብሎ ታላቁን ከሙታን የማንሳት ተኣምር ፈጽሞ ልጁን ለእናቱ ያስረክባል! ይሰጣል! ሶስት ቃላት ራራ ወይም ኣዘን ኣንዱ ሲሆን ቀረበ ሁለተኛ ሲሆን ሶስተኛው ደግሞ ሰጠ የሚሉ ቃላት ሁሉን ይገልጣሉ፣

የሰው ልጅን ለማዳን እግዚኣብሔር ያደረገውም ልክ እንዲህ ነበር፣ እግዚኣብሔር ለሰው ልጅ ራራለት! በኣንድያ ልጁም ቅርብ ሆነለት! የነበረንን የእግዚኣብሔር ልጆች የመሆን ክብር ዳግም ሰጠን፣ በዚህም ሁላችን እንደገና ተፈጠርን። ሲሉ የእግዚኣብሔር ርህራሄ ምን ያህል ታላቅ መሆኑን ገልጠዋል፣

በመጨረሻም ወደ ኣድማጮች መለስ ይሉና ምን ያስተምረናል እኛስ ምን እናድርግ በሚል ኣመለካከት በዓይናቸው ከቃኙ በኋላ ‘የኢየሱስ ምሳሌ ተከትሎ እርሱ እንዳደረገው ማድረግ! ከሩቅ መርዳት ሳይሆን ወደ ተቸገሩ ቀረብ ብሎ መንካት መሸኘት እና ኣስፈላጊውን እርዳታ መስጠት ያስፈልጋል፣ ኣብዛኛውን ግዜ የዜና ዝግጅቶችን በተለቪዥን መስኮት እንመለከታለን ወይንም ጋዜጦች እናነባለን በስደተኞችና በተለያዩ ችግሮች የተዘፈቁ ሰዎች ሁኔታ እንከታተላለን . . . ነገር ግን እርስ በእርሳችን ተመልከት በዛች ሃገር ያሉ ሕጻናት ምግብ የላቸውም! በሌላው ኣገር ደግሞ ሕጻናትን ለወታደርነት ይቀጥራሉ! በሌላውም ሴቶችን እንደባርያ ያያሉ ወዘተ እያልን በሩቅ እናወራለን፣ ተለቪዥን ሌላ ዝግጅት ሲጀምር ወይንም ከኣንዱ የጋዜጣ ገጽ ወደ ሌላው ስንሸጋገር ሁሉ ይረሳል፣ ይህ የክርስትያን ተግባር ኣይደለም፣ ኣሁን ልጠይቃችሁ የምፍለገው ሁላችንን እኔንም ሳይቀር የሚመለከት ነው፣ እኔ ርህራሄ ሊኖረኝ ይችላልን! ለመጸለይስ እችላለሁን! እነኚህን ሱኔታዎች በመገናኛ ብዙሓን እስከ ቤቱ ሲደርሱና ስመለከታቸው ሆዴን ያባባሉ ወይ ልቤን ያንቀሳቅሳሉ ወይ! የሰዎቹ ሁኔታ ልቤን ያባባል ወይ ሃዘን ይሰመኛል ወይ! ወይንስ መስኪን! ብየ ዝም እላለሁ! ለእነዚህ ሰዎች ትንሽ ሓዘንም ይሁን ተሰምቶን በርህራሄ ጌታ ሆይ ቢያንስ እንድራራልቸው በጸሎት እንዳስባቸው ጸጋህን ስጠኝ ብለን እንጸልይ። ስለዚህ ሌላ ነገር እንኳ ለማድረግ የማንችል ከሆንን ቢያን በጸሎት ለማማለድ እንደምንችል ኣምነንና ኣውቀን የክርስትና ስራችን ለመስራት ብስቃይ የሚገኙ ሰዎችን ለመርዳት ለእያንዳንዱ ኅብረተሰብ ለእያንዳንዱ የቤተስብ ሕይወትና የስራ ኑሮ ባጠቃላይ ለእያንዳንዱ ዕለታዊ ኑሮ ክብራቸው ተመልሶ እስኪሰጣቸው ድረስ ስለሁሉ ለመጸለይ እንሞክር፣ ሲሉ ስብከታቸውን ደምድመዋል፣








All the contents on this site are copyrighted ©.