Social:

RSS:

የቫቲካን ሬድዮ

ከዓለም ጋር የሚወያይ የር.ሊ.ጳጳሳትና የቤተ ክርስትያን ድምጽ

ቋንቋ:

ኅብረተሰብ \ ምጣኔ ሃብትና ፖሎቲካ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ፔትሮ ፓሮሊን በራሻ አድርገውት የነበረውን የአራት ቀን ጉብኝት ማጠናቀቃቸው ተገለጸ።

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ካ. ፔትሮ ፓሮሊን በርሻ ከቬላድሚር ፑቲን ጋር በተገናኙበት ወቅት። - REUTERS

28/08/2017 09:26

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ የሆኑት ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ከነሐሴ 15-18/2009 ዓ.ም ለአራት ቀናት ያህል የሚቆይ ይፋዊ ጉብኝት ለማድረግ ወደ ራሻ ባለፈው ሰኞ እለት ማቅናታቸውን የሚታወስ ሲሆን  በዚሁ የአራት ቀን ግብኝታቸው በቅድሚያ ከሞስኮ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ሀላፊ ከሆኑትና የሞስኮ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክን በመወከል ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጋር የሚደረገውን ግንኙነት በበላይነት እንዲመሩ ሃላፊነት ከተሰጣቸው ሊቀ ጳጳስ ሂላሪኦን ጋር ተገናኝተው ለሁለት ሰዓታት ያህል መወያየታቸው የተገለጸ ሲሆን አድርገውት የነበረው ውይይት በጣም ገንቢ እንደ ነበረም ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን መግለጻቸውም ታውቁዋል።

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ የሆኑት ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በቀጣይነት ከራሻ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ሴርጌ ላቭሮቪ ጋር ቆይታ ማድረጋቸው የታወቀ ሲሆን በግንኙነታቸው ወቅት ዓለማቀፋዊ ስለሆኑ ጉዳዮች እና በቫቲካን እና በራሻ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ከቪዛ-ነዛ የሆነ ዝውውር ማድረግ የሚቻልበትን መንገድ በተመለከተም መወያየታቸውም ተገልጹዋል።

ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊንና የራሻው የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በግል ካደረጉት ውይይት ቡኃላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደ ገለጹት የቫቲካን እና የራሻ ፌዴሬሽን የዲፕሎማቲክ ፓስፖርት የያዙ ሰዎች ያለምንም የቪዛ መስፈርት በሁለቱ ሀገራት ውስጥ በነጻ መዘዋወር የሚያስቻላቸውን ስምምነት መፈራረማቸውን ገልጸዋል።

ከፊርማው ስነ-ስራዓት ቡኃላ ካርዲና ጴትሮ ፓሮሊን እንደ ገለጹት ይህ አሁን የተፈረመው ስምምነት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት እንዲጠናከር ካለው ፍላጎት የመነጨ መሆኑን ገልጸው ይህም ሁለቱ ሀገራት በተናጥል እና በጋራ ዓለማቀፋዊ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ እንዲሰሩ መንገድ ይከፍታል ብለዋል።

በራሻ የሚገኙ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናንን ሕይወት እና ተግባር በተመለከተ ከራሻ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ሴርጌ ላቭሮቭ ጋር መወያየታቸውን የገለጹት ካርዲናል ጴትሮ ፓሮሊን በተለይም ደግሞ የራሻ ዜግነት የሌላቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት በራሻ ለመቆየት ወይም ለመሥራት የሚያስችላቸው የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት እንደ ሚቸገሩና በተጨማሪም ለካቶሊክ እምነት ተከታይ ምዕመናን መንፈሳዊ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናትን ለመገንባት የሚያስችል ፈቃድ ማግኘት በአሁኑ ወቅት በቫቲካን እና በራሻ ፌዴሬሽን መካከል የሚታዩ ችግሮች መሆናቸውንም የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ የሆኑት ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ጨምረው ገልጸዋል።

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሴርጌ ላቭሮቭ በበኩላቸው እንደ ገለጹት በመካከለኛው ምስራቅ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች በተለየ መልኩ መፍትሔ እንደሚያስፈልጋቸው ገልፀው በተመሳሳይ መልኩም በሊቢያ እና በኢራቅ በሚገኙ የተለያዩ የጎሳ እና የሃይማኖት ቡድኖች መካከል ሚዛናዊ የሆነ ተመሳሳይ መፍትሔ ይመጣ ዘንድ የበኩላችንን ጥረት ልናደርግ ይገባል ብለዋል።

በእነዚህ ጉዳዮች ዙሪያ በሩሲያ እና በቅድስት መንበር መካከል ልዩነት እንዳለ እንደ ሚገነዘቡ የጠቀሱ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ሆኖም ግን ሁለቱም ሀገራት በመካከለኛው ምስራቅ እና በአንድ አንድ የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ የሚኖሩ ክርስቲያኖች ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን ሁለቱም ሀገራት የሚጋሩት ጉዳይ መሆኑንም ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በቬንዙዌላ የሚታየውን ፖሌቲካዊ ቀውስ በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ የሰጡት ካርዲናል ጴትሮ ፓሮሊን በአሁን ወቅት ይህንን ጭግር ለመፍታት ቫቲካን እያደርገች የምትገኘውን ጥረት የራሻ ፌዴሬሽን እንደ ሚያግዝ እምነታቸው መሆኑን ገልጸው በተለያዩ የፖሌቲካ አንጃዎች መካከል ያለው ልዩነት በውይይት እንዲፈታ ለማድረግ የሚደረገውን ውይይት የራሻ እገዛ እንዲታከልበትም የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ የሆኑት  ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ጥሪ አድርገዋል።

በመቀጠልም የሞስኮ እና የመላው ራሻ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ከሆኑት ፓትሪያርክ ቅሪሎስ ጋር በመኖሪያ ቤታቸው በተገናኙበት ወቅት አድርገውት በነበረው ግንኙነት መደሰታቸውን የገለጹት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ የሆኑት ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በግንኙነት ወቅት በቅድሚያ “የሞስኮ ፓሪያርክ ለሆኑት ወንድሜ ፓትሪያርክ ቅሪሎስ እና ለመላው የራሻ ሕዝብ ሰላምታዬን አቀርባለሁ” የሚል መልእክት ያዘለ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮን ምልእክት በቅድሚያ እንዳደረሱላቸው ገልጸዋል።

በተለይም ደግሞ በአሁኑ ወቅት የጣሊያን ግዛት በሆነችው በባሪ ከተማ ይገኝ የነበረው የቅዱስ ኒኮላስ ቅዱስ አጽም በራሻ ምዕመናን ዘንድ ከፍተኛ የሆነ አክብሮ የሚሰጠው በመሆኑ በዚሁ መሰረት ለተወሰኑ ጊዜያት ቆይታን ለማድረግ ወደ እዚያው መጓዙ የሚታወቅ ሲሆን ይህም ተግባር በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለውን ግንኙነት በሚገባ የሚያጠናክር መሆኑን በግንኙነቱ ወቅት መገለጹም ተጠቁሙዋል።

“ቅዱሳን አንድ ያደርጉናል” በማለት በግንኙነቱ ወቅት የተናገሩት የቅድስት መነበር ዋና ጸሐፊ ፔትሮ ፓሮሊን ምክንያቱም እነርሱ ለእግዚኣብሔር ቅርብ በመሆናቸው የተነሳ መሰናክሎችን እንድንወጣ፣ ያልፉ ጊዜያት የነበሩ ችግሮቻችንን በመፍታት ግንኙነቶቻችንን እንድናጠናክር ሁል ጊዜም ቢሆን በወድማማችነት በመተቃቀፍ በጋር አብረን ወደ ፊት እንድንጓዝና በጌታ ራት ወይም በቅዱስ ቁርባን ዙሪያ በአንድነት መሰብሰብ እንችል ዘንድ ብርታት ይሰጡናል ብለዋል።

የዩክሬንን ጉዳይ በተመለከተ “ቤተ ክርስቲያን ሰላም እንዲወርድ ለማድረግ የራሷን ድርሻ ከመጫወት የዘለለ ሌላ ተቀዳሚ ተግባር እንደ ሌላት” የገለጹት የሞስኮ እና የመላው ራሻ ኦርቶዶክ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ የሆኑት ፓትሪያርክ ቅሪሎስ “ግጭቶች ለዘላለም አይቀጥሉም፣ በዚህ ግጭት ውስጥ የተሳተፉ አንጃዎች ዛሬው ወይም ነገ ከዚህ ተግባራቸው ከታቀቡ ምፍትሄ ያማይገኝበት ምንም ምክንያት የለም ብለዋል።

በሁኑ ወቅት ሁለቱም አብያተ ክርስቲያናት የዩክሬይንን ጉዳይ በተመለከተ የጋር የሆነ አቋም ላይ ደርሰው ግጭቱን በሰላማዊ መንግድ ይፈታ ዘንድ የያዙት የጋራ አቋም በጣም የሚያስደስት ተግባር መሆኑን የገለጹት ፓትሪያርክ ቅሪሎስ ይህን ተግባራችንን አጠናክረን በመቀጠል የዩክሬይን ሕዝብ ሰላሙን መልሶ ይጎናጸፍ ዘንድ ጠንክረን ልንሰራ ትገባል ብለዋል።

የራሻ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እና የካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት በመካከለኛው ምስርቅ ለሚገኙ በጦርነት ለተጎሳቆሉ ክርስቲያኖች ሁለቱም አብያተ ክርስቲያናት በጋር እያቀረቡት የሚገኘው ሰብዓዊ እርዳታ  አንድነታችንን የሚያጠናክር አንድ ተግባር ነው ያሉት ፓትሪያርክ ቅሪሎስ ይህን እና ይህንን የመሳሰሉ መልካም ተሞክሮዎቻችን ግንኙነቶቻችንን ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጾ እንደ ሚያደርጉም ጨምረው ገልጸዋል።

ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ከፓትሪያርክ ቅሪሎስ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ካጠናቀቁ ቡሃላ ከራሻ ፕሬዚዳንት ቬላድሚር ፑቲን ጋር በሶቺ በሚገኘው የፕሬዚዳንቱ የመኖሪያ ቤት ተገናኝተው ቆያት የደረጉ መሆናቸው የታወቀ ሲሆን በዚሁ ለአንድ ሰዓት ያህል በቆየው ግንኙነታቸው የተለያዩ ዓለማቀፋዊ የሆኑ ጉዳዮች ላይ ገንቢ ውይይቶችን ማድረጋቸው የተገለጸ ሲሆን በሁለቱ ሀገራት መካከል ስላለውም የጋራ ግንኙነት አንስተው መወያየታቸውም ተገልጹዋል።

በግንኙነታቸው ማብቂያ ላይ የቅድስት መንበር ውና ጸሐፊ የሆኑት ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሎን ለፕረዚዳንት ቬላድሚር ፑትን የሰላም ምልክት የሆነውን ከነሀስ የተሠራ የወይራ ዛፍ ዝንታፊ በስጦታ መልክ መስጠታቸው የተገለጸ ሲሆን ፕረዚዳንት ቪላድሚር ፑቲን በበኩላቸው እንደ አውሮፓዊያኑ የቀን አቆጣጠር 2014 ዓ.ም. በሶቺዊ በተዘጋጀው የበጋ ኦሊምፒክ ላይ ጥቅም  ላይ ውለው የነበሩ የተለያዩ ሳንቲሞችን በስጦታ መልክ እንደ ሰጡዋቸውም ለመረዳት ተችልዋል።

 

28/08/2017 09:26