Social:

RSS:

የቫቲካን ሬድዮ

ከዓለም ጋር የሚወያይ የር.ሊ.ጳጳሳትና የቤተ ክርስትያን ድምጽ

ቋንቋ:

ቤተ ክርስትያን \ ኢትዮጵያ

በኢትዮጲያ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን አጠቃላይ ጽሕፈት ቤት የተዘጋጀ የ2 ቀን የወጣቶች አወደ ጥናት ተጠናቀቀ።

በኢትዮጲያ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን አጠቃላይ ጽሕፈት ቤት የተዘጋጀ የ2 ቀን የወጣቶች አወደ ጥናት ተጠናቀቀ። - RV

21/08/2017 14:26

በሮም ጥቅምት ወር 2011 ዓ.ም. በወጣቶች ጉዳይ ዙሪያ ለሚወያየው ለመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ሲኖዶስ ዝግጅት ይሆን ዘንድ ፣ የምሥራቅ አፍሪቃ ካቶሊካዊ ጳጳሳት ጉባኤ ኅብረት ሐዋርያዊ ሥራ መምሪያ፣ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ  ከነሐሴ 5 ቀን ጀምሮ ሁለት ቀን የወሰደ አውደ ጥናት ፣ በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ፣ የጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ውስጥ ማዘጋጀቱን ከሥፍራው የደረሰን ዜና ገለጸ።  

የዚህን ዘገባ ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

በአውደ ጥናቱ 30 ተሳታፊዎች የተገኙ ሲሆን ከነዚህም መካከል 25ቱ በኢትዮጵያ በሚገኙ ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች ሥር ከታቀፉ ቁምስናዎች የተወጣጡ የወጣት ማኅበር አባላት ሲሆኑ የተቀሩት ፭ አባላት ደግሞ ከካቶሊካዊ ቤተሰብ የተጋበዙ እንደሆነ ታውቋል። ይህ አውደ ጥናት በሌሎችም የምሥራቅ አፍሪቃ ካቶሊካዊ ጳጳሳት ጉባኤ ኅብረት አገሮች የሚካሄድ እና በዓይነቱ የመጀመሪያ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

በሌሎችም የምሥራቅ አፍሪቃ ካቶሊካዊ ጳጳሳት ጉባኤ ኅብረት አገሮች እንዲካሄዱ የታቀዱት ተመሳሳይ አውደ ጥናቶች ቀዳሚ ዓላማ ፣ በ2011 ዓ.ም.  ሮም ላይ በሚደረገው እና  በወጣቶች ጉዳይ ዙሪያ በሚመክረው የጳጳሳት ሲኖዶስ ላይ፣ ወጣቶች በቅድሚያ በቂ ውይይትና ዝግጅት እንዲያደርጉ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባቀረቡት ሐዋርያዊ ጥሪ መሰረት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።  

የቅድመ ዝግጅቱ ሠነድ እንደሚለው፣ መላዋ ቤተ ክርስቲያን፣ በጳጳሳቱ ሲኖዶስ አማካይነት፣ በማንኛውም ወጣት መካከል ልዩነት ሳታደርግ፣ ጉዳያቸውን በጥንቃቄ ለመመልከት፣ አብራቸው ለመጓዝና አስፈላጊዉን እንክብካቤን ሁሉ ለማድረግ ጽኑ ፍላጎት አላት ብሏል።

በሮም፣ ጥቅምት ወር 2011 ዓ.ም. የሚካሄደው የጳጳሳት ሲኖዶስ፣ በ15ኛው ጠቅላላ ጉባኤ መሪ ቃሉን “ወጣቶች፣ እምነትና፣ የጥሪ ሃሳብ” የሚል እንደሆነ ጥቅምት ወር 2009 ዓ.ም. ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

በቅድመ ዝግጅቱ ሠነድ መሠረት ከላይ የተጠቀሰውን መሪ ቃል በመምረጥ፣ የወንጌልን ቃል በብቃት ማብሰር እንዲቻል ምቹ የሚሆነውን መንገድ በመጠቆም ወጣቶች የበኩላቸውን እገዛ እንዲያደርጉ ቤተ ክርስቲያን እንደምትፈልግ ታውቋል።

በአውደ ጥናቱ ፍጻሜ ላይ ወጣቶቹ ባቀረቡት ጥያቄ በኩል፣ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናንን ለማዘጋጀት ከዚህ በፊት የምትጠቀምበትን መንገድ፣ በተለይም ትምህርተ ክርስቶስን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርትን እና አጠቃላይ በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ማኅበራዊ ትምህርቶች አሰጣጥ ላይ አሁንም እንድታስብበት ጠይቀው ይህም በእምነት ለመጠንከር እና አንዳንድ ጊዜ የሚሰነዘርባቸዉን ማኅበራዊና መንፈሳዊ ጥቃቶችን ለመቋቋም መሣሪያ እንደሚሆናቸው ወጣቶች አስረድተዋል።

ክቡር አባ ሐጎስ ሐይሽ ፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ በበኩላቸው ፣ አውደ ጥናቱን ለማዘጋጀት የተባበሩትን የምሥራቅ አፍሪቃ ካቶሊካዊ ጳጳሳት ጉባኤ ኅብረት ሐዋርያዊ ሥራ መምሪያን አመስግነው ፣ በአውደ ጥናቱ ወቅት ከተሳታፊዎች የቀረቡት ጥያቄዎች በእርግጥም አስፈላጊ እንደነበሩ ገልጸው እነዚህን ጥያቄዎች ወደ ኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ዘንድ እንደሚያቀርቧቸው ቃል ገብተዋል።  

ዋና መቀመጫዉን ኬንያ ላይ ያደረገው የምሥራቅ አፍሪቃ ካቶሊካዊ ጳጳሳት ጉባኤ ኅብረት ሐዋርያዊ ሥራ መምሪያ ቡድን በበኩሉ ፣ የአውደ ጥናቱን አዘጋጆች፣ ክቡር አባ ሐጎስ ሐይሽን፣ ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት አቶ አቤል ሙሴን፣ ከምሥራቅ አፍሪቃ ካቶሊካዊ ጳጳሳት ጉባኤ ኅብረት ሐዋርያዊ ሥራ መምሪያ ክፍል ሃላፊ የሆኑት ወይዘሮ ፖሊን ዋኪቢሩንና የምስራቅ አፍሪቃ ካቶሊካዊ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑ ሲስተር ኤሊዛበት ንኩዱን እና የአውደ ጥናቱን ተሳታፊዎች በሙሉ ላበረከቱት አስተዋጽዖ አመስግነዋል።

በማከልም የአውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች የሌሎችንም ወጣቶች ሃሳብ ነጻ በሆነ መንገድ እንዲያቀርቡ የማድረግ ምኞት እንደነበራቸው ገልጸው፣ ይህን ለማድረግ ተሳታፊዎች ብርታትን እንዳገኙና ወደየመጡበት ቁምስና ሲመለሱም የመሪነት ሚናን በብቃት እንዲወጡ አሳስበዋል። በተጨማሪም የጳጳሳት ሲኖዶስ ከመጀመሩ በፊት ባለው ጊዜ ውስጥ የተወያዩበትን ርዕስ መነሻ በማድረግ ቤተክርስቲያን በምታደርገው ዝግጅት በንቃት እንዲሳተፉ ወጣቶችን አደራ ብለዋል። ቀጣዩ አውደ ጥናት ነሐሴ 12 እና 13 ማላዊ ላይ፣ እንዲሁም ነሐሴ 15 እና 16 2009 ዓ.ም. ዛምቢያ ላይ እንደሚደረግ ታውቋል።

ይህ አውደ ጥናት የተካሄደው ፣ የአሜሪካ ካቶሊካዊ ጳጳሳት ጉባኤ ባደረገው የገንዘብ ድጋፍ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

21/08/2017 14:26