2017-08-20 10:22:00

"የሰማይ ንግሥት ሆይ ለምኝልን!"


እንደ አገራችን ሥርዓተ አምልኮና መንፈሳዊ ልማድ በእመቤታችን በኩል እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ስለገለጠው ተስፋና በእርስዋም ጸጋ መሞላት ላደረገልን ቸርነት በተለየ ሁኔታ በየዓመቱ ለ16 ቀናት የሚዘለቀወን ጾምና ምህለላ የምናደርግበት የፍልሰታ ዘመን ላይ እንገኛለን።

የዚህን አስተምህሮ ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

 እግዚአብሔር አብ በእርሱ ለኖሩት ሁሉ ሊያደርግላቸው ቃል የገባውን እውነታ እርሱ በፈቀደው መልኩ በእመቤታችን የተገበረበትን ጸጋ እንወድሳለን፤ ለእኛም ይሆንልን ዘንድ “ማርያም ሆይ! ቸር፣ የሰው ልጆች ሁሉ አዳኝ ወደ ሆነው ልጅሽ ለምኝልን/ በማለት የእናትነት አማላጅነቷን የምንማጽንበት የፍልሰታ ወቅት ላይ እንገኛለን።

ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የሚናገረው ይህ ጽሑፍ በኢትዮጵያ ካቶሊካዎት ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ መገናኛ መምሪያ ቢሮ በየወሩ ከሚታተመው "ፍቅርና ሰላም" ከተሰኘው ጋዜጣ ግንቦት/ሰኔ 2001 ዓ.ም. እትም "የሰማይ ንግሥት ሆይ ለምኝልን!" ከሚል ርእስ በከፊል የተወሰደ ነው።

"የሰማይ ንግሥት ሆይ ለምኝልን!"

በቅዱስ ሉቃስ ወንጌል ላይ የተገለጸው የመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ብሥራት የሚተርከው ማርያም የልዑል እግዚአብሔርን ልጅ እንደምትወልድና እርሱም በብሉይ ኪዳን ስለ መሲሑና ዘላለማዊ መንግሥቱ  ተነግሮ የነበረው ተስፋ እንዲፈጸም እንደሚያደርግ ነው። (2ሳሙ.7:፤ መዝ.2:72፣89፤ ሉቃ.1:33)።

ጥንታዊ አይሁዳውያን አንዲት እናት ከዳዊት ዘር የሆነና ወደፊት በንጉሡ ዙፋን ላይ ሊቀመጥ የሚችል (አልጋ ወራሽን) የወለደች እንደሆነ ወዲያውኑ ንግሥት እንደሆነች አድርገው ይቀበሏታል። ማርያምም በብሥራቱ ጊዜ የተቀዳጀችው ይህንኑ አክሊል ነበር። እርሷ ባባቱ በዳዊት ዙፋን የሚቀምጥና ለመንግሥቱም ማለቂያ የሌለውን ኢየሱስን ጸንሳለችና።

የቅድስት ድንግል ማርያም የእናት ንግሥትነት ማዕረግ የበለጠ ጉልህ ሆኖ የሚታየው ደግሞ በ ሉቃ.1:43 ላይ ነው። ይህም ቅድስት ኤልሳቤጥ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ድምጽ በሰማች ጊዜ የመሰከረችው ነው። "የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል!"። ይህ የኤልሳቤጥ "የጌታዬ እናት" የሚለው አባባል የመነጨው በጥንት ጊዜ በንጉሡ ሸንጎ ፊት "ጌታዬ ሆይ!" ማለት "ንጉሥ ሆይ!" እንደማለት የነበረ በመሆኑ ነው። "የጌታዬ እናት" ማለቷ ኤልሳቤጥ የንጉሡ እናት ንግሥቲቱ ቤቷ ድረስ መምጣቷ አስገርሟትም አስደንግጧትም ጭምር ነው። በንግሥት መጎብኘት ያውም እቤት ድረስ መጥታ ያስደንግጣልና ነው። በመሆኑም ኤልሳቤጥ የማርያምን ልዕልና የተረዳችና የመሰከረች ሰው ናት።

ሌላው ቢዚህ የማርያም ንግሥትነት ላይ ብርሃን የሚፈነጥቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ደግሞ ራዕይ 12:1-2 ነው። "ታላቅ ምልክት በሰማይ ታየ ፤ ፀሐይን ተጎናጽፋ ጨረቃ ከእግሮቿ በታች ያላት በራስውም ላይ የአስራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት አንዲት ሴት ነበረች፤ እርሷም ጸንሳ ነበር።"

ይህች ሴት ማናት? አንዳንዶች እስራኤልን ወይም ቤተ ክርስቲያንን የምትወክል ሴት ናት ይላሉ። ነገር ግን ይኸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በ12:5 ላይ ይህች ሴት የመሲሑ እናት እንደሆነች ይገልጻል። "አሕዛብን ሁሉ በብረት በትር ይገዛቸው ዘንድ ያለውን ወንድ ልጅ ወለደች፤ ልጇም ወደ እግዚአብሔርና ወደ ዙፋን ተነጠቀ።" ስለዚህ ይህ "አሕዛብን ሁሉ በብረት በትር ይገዛቸው ዘንድ ያለው" ተብሎ የተገለጸለት ንጉሥ ማነው? ንጉሡ ኢየሱስ ነው። ሴቲቱ ደግሞ እናት ንግሥቲቱ እምነ ማርያም ናት።

ቅድስት ድንግል ማርያም በዮሐንስ ራዕይ ላይ የተገጸችው በሰማያት እንደተቀመጠች ንግሥት ነው። በደፋችው ዘውድ ላይ 12 ከዋክብት ከ12ቱ የእስራኤል ንገዶች በተወለደችው በ12ቱ ሐዋርያት ላይ በታነጸችው ቤተ ክርስቲያን ላይ ያላትን የንግሥትነትን ማዕረግ ይገልጻሉ። ፀሐይን መልበሷ ደግሞ የእግዚአብሔር ክብር በርሷ እንደሚገለጽ ያስረዳል። ጨረቃን ከእግሮቿ በታች ማድረጓ የንግሥትነት ሥልጣኗን ይገልጻል (መዝ.8:6፤ 110:1)።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዛሬም በእግዚአብሔር መንግሥት የምእመናን ጠበቃ ሆና ታገለግላለች። በልጇ ዙፋን ፊትም የኛን ጸሎታና ለመና በማቅረብ ጎልህ ሚና የምትጫወት ጽኑ አማላጅ ናት። ጸሎታችንን ይዘን "አያሳፍርሽምና" በሚል መተማመን ወደ መንበሯ እንቅረብ። ኢየሱስም ሰሎሞን ለቤርሳቤህ እንደመለሰላት "እናቴ ሆይ! አላሳፍርሽምና ለምኚ" በሚል ማረጋገጫ ቃል ጸሎታችንን ከአንደበቷ ይቀበላል(1ነገ.2:20)።

 








All the contents on this site are copyrighted ©.