2017-08-16 11:33:00

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያምን የተመለከቱ አራቱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን አንቀጸ-እምነት በአጭሩ


እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያምን የተመለከቱ አራቱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን

አንቀጸ-እምነት

እንደ አገራችን ሥርዓተ አምልኮና መንፈሳዊ ልማድ በእመቤታችን በኩል እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ስለገለጠው ተስፋና በእርስዋም ጸጋ መሞላት ላደረገልን ቸርነት በተለየ ሁኔታ በየዓመቱ ለ16 ቀናት የሚዘለቀወን ጾምና ምህለላ የምናደርግበት የፍልሰታ ዘመን ላይ እንገኛለን። እግዚአብሔር አብ በእርሱ ለኖሩት ሁሉ ሊያደርግላቸው ቃል የገባውን እውነታ እርሱ በፈቀደው መልኩ በእመቤታችን የተገበረበትን ጸጋ እንወድሳለን፤ ለእኛም ይሆንልን ዘንድ “ሰአሊ ለነ ማርያም ኀበ ወልደኪ ኄር መድኃኔ ዓለም” /ማርያም ሆይ! ቸር፣ የሰው ልጆች ሁሉ አዳኝ ወደ ሆነው ልጅሽ ለምኝልን/ በማለት የእናትነት አማላጅነቷን እንማጠናለን።

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን እመቤታችን ቅድስት ደንግል ማሪያም በደኅንነት ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ አስትዋጾ በእግዚኣብሔር እንደተሰጣት ታምናለች፣ ታስተምራለችም። በዚሁ ምክንያት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ካላት አክብሮት እና ፍቅር በመነሳት በቤተክርስቲያኗ የእመነት ዶግማ ወይም አንቀጸ-እምነት ውስጥ ማሪያምን የተመለከተ 4 ዶግማዎች ወይም አንቀጸ-እምነት የማይሻር የማይለወጥ የቤተክርስቲያን አስተምህሮ ውስጥ እንዲካተቱ አድርጋላች። እነዚህ ማሪያምን የተመለከቱ ዶግማ ወይም ደግሞ የማይሻር የማይለወት አንቀጸ-እምነት የሚባሉት የሚከተሉት ናቸው።

  1. ማሪያም የእግዚኣብሔር እናት ናት

ማሪያም ኢየሱስን በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ጸንሳ በመውለዱዋ የተነሳ እግዛኢብሔር የሆነው የኢየሱስ እናት በመሆኑዋ የተነሳ “የእግዚኣብሔር እናት ናት” ተብላ ትጠራላች። ይህም ዶግማ ወይም አንቀጸ-እምነት (የማይለወጥ የማይሻር የቤተክርስቲያን አስተምህሮ) እንደ አውሮፓዊያን የቀን አቆጣጠር በ431 በተደረገው የኤፌሶን ጉባሄ ከጸደቀ ቡኃላ እስከ ዛሬ ቀን ድረስ ቤተክርስቲያን ይህንን አስተምህሮ በማስተማርና በመጠበቅ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ያላትን አክብሮት በመግልጽ ላይ ተገኛለች።

2. ማሪያም ለዘለዓለም ድንግል ናት

ማሪያም ኢየሱስን ተፈጥሮአዊ በሆነ መልኩ እኛ በተወለድንበት መንገድ ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ጸንሳ በመውለዱዋ የተነሳ ለዘለዓለም ድንግል ሆና ትኖራለች የሚለውና እንደ አውሮፓዊያን የቀን አቆጣጠር በ649 ዓ.ም. በላቴራን ጉባሄ የጸደቀው ዶግማ ወይም አንቀጸ-እምነት ነው።

3. ማሪያም ያለ አዳም ኃጢኣት የተጸነሰች ናት

በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ማሪያም ያለ አዳም ኃጢኣት የተጸነሰች ናት የሚለው ነው። በዚህም በማይለወጥ እና በማይሻር አንቀጸ-እምነት አስተምህሮ ማሪያም ቀደም ሲልም ቢሆን በእግዚኣብሔር የማዳን እቅድ ውስጥ በመኖሩዋ የተነሳ የእርሱ ማለትም የእግዚኣብሔር ልጅ ማደሪይ ትሆን ዘንድ አስቀድሞ ስለመረጣት እኛ ሁላችን ከአዳም የወረስነውንና በጥምቀታችን ቀን ከሚደመሰሰው ኃጢኣት ነጻ ሆና እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያ እንድትወለደ እግዚኣብሔር በማድረጉ የተነሳ እመቤታችን “ካለአዳም ኃጢያት ተጸንሳ የተወልደች ነች” የሚለው ዶግማ ወይም አንቀጸ-እምነት እንደ የአውሮፓዊያኑ የቀን አቆጣጠር በ1854 ዓ.ም. በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮ 9ኛ ጸድቆ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ዶግማ ወይም አንቀጸ-እምነት የማይሻር የማይለወጥ አስተምህሮ እንዲሆን ተደርጉዋል።

4. ማሪያም በሥጋ እና በነብስ ወደ ሰማይ ፈልሳለች

በአራተኛ እና በመጨረሻ ደረጃ የምናገኘው ደግሞ ከ6ኛ ክፍለ ዘመን አንስቶ እስከ ዛሬው ቀን ደረስ በምስራቃዊያን የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናትና በካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናትም ጭምር እየተከበረ የሚገኘው ማሪያም በሥጋ እና በነፍስ ወደ ሰማይ ወጣች የሚለውና በአሁኑ ጊዜ እኛ እየጾምነው የምንገኘውን የፍልሰታ ቀን የሚያስታውሰን ዶግማ ወይም አንቀጸ-እምነት ምንም እንኳን ከስድስተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ እየተከበረ፣ እየተዘከረ የሚገኝ ክብረ በዓል ቢሆንም የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ዶግማ ወይም አንቀጸ-እምነት የማይለወጥ የማይሻር አስተምህሮ ተደርጎ በሕግ ውስጥ የሰፈረው ግን እንደ አሮፓዊያኑ የቀን አቆጣጠር በ1950 ዓ.ም. በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ ከጸደቀ ቡኃላ ነው።  

ኢየሱስ ወደ ዚህ ምድር መቶ ተስቃይቶ ተሰቅሎ መሞቱን እና በሦስተኛው ቀን ከሙታን መነሳቱን በሚዘከርበት የእርገት ቀን መካከል እና ማሪያም ወደ ሰማይ የፈለሰችበት አጋጣሚዎች ግን የተለያዩ እንደ ሆነ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጠንቅቀን እንድንረዳ አደራ ትለናለች። የእግዚኣብሔር ልጅ የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣  ሞትን ድል ነስቶ ወደ ሰማይ የወጣው በመለኮታዊ ኃይሉ አማክይነት ሲሆን ነገር ግን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያ ወደ ሰማይ የፈለሰቺው በእግዚኣብሔር መለኮታዊ ኃይል እንደ ሆነ ልብ ሊባል ይገባል።

(አባ መብራቱ ኃይለጊዮርጊስ)

 

 








All the contents on this site are copyrighted ©.