Social:

RSS:

የቫቲካን ሬድዮ

ከዓለም ጋር የሚወያይ የር.ሊ.ጳጳሳትና የቤተ ክርስትያን ድምጽ

ቋንቋ:

ቤተ ክርስትያን \ ኢትዮጵያ

የካቶሊክ እምነታችን ምንነት ክፍል ሁለት

የካቶሊክ እምነታችን ምንነት ክፍል ሁለት - RV

16/08/2017 16:05

የካቶሊክ እምነታችን ምንነት ክፍል ሁለት

እኛ ካቶሊካዊያን የክርስቶስ መስቀልና የቅዱሳንን ምስሎች እንወዳለን እናከብራለንም

ወደ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ስንገባ ሁል ጊዜ የክርስቶስ ቅዱስ መስቀልና የቅዱሳንን ምስል እናያለን። በቤታችንም ቢሆን የክርስቶስ መስቀልና የቅዱሳን ሰዎች ምስል ወይም ስዕል ማስቀመጥ የተለመደ ነው። ይህንን በማድረጋችን የተነሳ የሚወቅሱንና የሚነቅፉን ሰዎች አሉ። “እናንተ ካቶሊኮች የእንጨት መስቀልና የድንጋይ ሃውልት ታመልካላችሁ” መጽሐፍ ቅዱስ ግን በዘለዋዊያን 26:1 “ትሰግዱላቸው ዘንድ ጣዖታትን አታብጁ፤ ምስል ወይም የማምለኪያ ዐምድ አታቁሙ፤ በምድራችሁም ላይ የተቀረጸ ድንጋይ አታኑሩ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ” ይላል ይሉናል። ይህን እና ይህንን ለመሳሰሉ ጥያቄዎች በአክብሮት እንዲህ እያልን እንመልሳለን።

እኛ ካቶሊኮች የእኝጨት መስቀል ወይም የድንጋይ ሐውልት ብፍጹም አናመልክም፣ እኛ የምናመልከው እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ከእኛ ጋር ያለውን እና ሕያው የሆነውን ክርስቶስን ብቻ ነው። የሆነ ሆኖ በመስቀል ስለ እኛ ተሰቅሎ የሞተውን ጌታችንን የሚያስታውሰን እና እርሱን የበለጠ እንድንወደው የሚረዳን ማስታወሻ እንጂ ማምለኪያ አይደለም።

እስቲ ለአፍታ ይህል በየቤቶችችን የምንሰቅላቸውን የቤተሰቦቻችንን ፎቶ እናስብ። የእነርሱን ፎቶዎች በምንመለከትበት ጊዜ በሕይወት እያሉ ለእኛ የነበራቸውን ፍቅር እና መልካም ሥራ ሁሉ እናስታውሳለን። በተመሳሳይ መልኩ በግርግዳ ላይ የምንሰቅለው የክርስቶስ መስቀል ወይም የእርሱ ምስል ክርስቶስ ለእኛ ያለውን ፍቅርና እርሱ ለእኛ ያደረገውን መልካም ሥራዎች ሁሉ ያስታውሰናል ማለት ነው።

እኛ ካቶሊኮች በዚህ መልኩ የቅዱሳን ምስሎችን፣ ለምሳሌም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማሪያምን፣ የቅዱስ ዮሴፍን፣ የቅድስት ትሬዛን ወዘተርፈ ስዕሎችን ወይም ምሥሎችን በቤታችን ማስቀመጥ እንወዳለን። አሁንም ይህንን የምናደርገው እነዚህን ሰዎች ስለምናመልካቸው ሳይሆን ስለምንወዳቸው ነው። በእምነት ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ስለሆኑ ነው፣ አንድ አንዴም በእምነት ቅድመ አያቶቻችን ናቸው ብለን እንጠራቸዋለን። እነርሱም መልካም አረአያዎቻችን ናቸው። ታዲያ የእነዚህን ሰዎች ምስል በቤታችን ብናስቀምጥ ምን ችግር አለው? በአጭሩ እኛ ካቶሊኮች ሞትን ድል አድርጎ ከሙታን የተነሳውን ከክርስቶስ በቀር ማንንም አናመልክም።

የእንጨት መስቀል ለእኛ ሲል በመስቀል ተሰቅሎ የሞተውን ክርስቶስን የሚያስታውሰን ማስታወሻ ነው። ክርስቶስን የበለጠ እንድነወደውና በእየለቱም መስቀሎቻችንን ከእርሱ ጋር ሆነን በመሸከም ክርስቲያናዊ ጉዞዎችንን በጽናት እንድጓዝ ያደርገናል።

በተጨማሪም የቅዱሳን ሰዎች ምስል ልክ የቤተሰብ የፎቶ ማስቀመጫ አልበም ቤተሰቦቻችንን እንደ ሚያስታውሰን በእመነት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሆኑ ሰዎች ከነሥራቸው የሚያስታውሰን ነው። በተጨማሪም ክርስቶስን እነርሱ በተከተሉት መንገድ እንድንከተለው ያበረታቱናልና በዚሁ ምክንያት እኛም ካቶሊኮች የቅዱሳን ሰዎችን ምስል በቤታችን ማስቀመጥ የምንወደው።

መጽሐፍ ቅዱስ እና ምስሎች ምን ይላል!

መጽሐፍ ቅዱስ በኢየሩሳሌም ቤተ መቅድስ ውስጥ ስለነበረው ከእጨት ስለተሠራው ምስልና ሙሴ በእግዚኣብሔር ትዕዛዝ ሠርቶት በበረሃ ስለሰቀለው የነሐስ እባብ ይናገራል። በአንደኛው መጽሐፈ ነገሥት 6:23-28 እንዲህ የሚል ነገር እናገንእለኝ። “የእያንዳዳቸው ቁመት አራት  ሜትር ከአርባ ሳንቲ ሜትር የሆነ ከወይራ እንጨት በሁለት ኪሩቤል አምሳል የተቀረጹ ምስሎችን በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ሠራ” ይላል።

ንጉሥ ሰለሞንና ሕዝቡ እነዚህን ምስሎች አላመለኩዋቸውም፣ ነገር ግን እነዚህ ምስሎች በጊዜው የነበሩትን ሰዎች ሁሉ በመላእክት ተከበበው በእግዚኣብሔር ጥበቃ ሥር እናድሉ እግዚኣብሔርም ከእነርሱ ጋር እዳለ እንዲረዱ፣ ያ ስሜት በውስጣቸው እንዲፈጠር ረድቷቸዋል። 

ከዚህ በላይ በተጠቀሰው ምክንያት ነው እኛ ካቶሊኮች የእንጨት ምስሎችንና ሥዕሎችን ይምንሠራው፣ መስቀል ስናይ ከሙታን የተነሳው ክርስቶስ ስለእኛ የተሰቀለው እና የሞተው ክርስቶስ አሁንም በመካከላችን እንዳለ ይሰማናል። የቅዱሳን ሰዎች ምስልም እነርሱ ክርስቶስን በተከተሉበት የቅድስና መንገድ እንድንከተል ያነሳሳናል።  

ምንጭ፣-የካቶሊክ እምነታችንን ምንነት፣ የኢትዮጲያ ካቶሊካዊት ጠቅላይ ጽህፈት ቤት ሐዋሪያዊ ሥራዎች ኮሚሽን በ2007 ዓ.ም. ካሳተመው መጽሐፍ ከገጽ ግጽ 20, 21 የተወሰደ! የዚህን አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል በሚቀጥለው ረዕቡ እናቀርብላችኃለን።

 

16/08/2017 16:05