Social:

RSS:

የቫቲካን ሬድዮ

ከዓለም ጋር የሚወያይ የር.ሊ.ጳጳሳትና የቤተ ክርስትያን ድምጽ

ቋንቋ:

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ \ ስብከቶች

በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ ክርስቲያኖች የሚያሰሙትን የመከራ ጩኸት ማዳመጥ ይገባል።

በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ ክርስቲያኖች የሚያሰሙትን የመከራ ጩኸት ማዳመጥ ይገባል። - RV

05/08/2017 09:46

“ማንኛችንም ብንሆን በመካከለኛው ምሥራቅ "በፖሌቲካዊ ልዩነቶች ምክንያት በተፈጠሩ ጦርነቶች ሆነ የሃይማኖት አክራሪዎች በሚያደርሱት ጥቃት ምክንያት ቤታቸውን ጥለው ለመሰደድ ወይም ሀገራቸውን ለመልቀቅ እየተገደዱ ያሉትን ወንድሞቻችን ላይ እና እህቶቻችን ላይ የሚደርሰውን መከራ እያየን አንዳለየ መሆን የለብንም”። ይህንን ቀደም ሲል የተጠቀሰውን ምልእክት የተናገሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ ሲሆኑ፣ ቅዱስነታቸው ይህንን መልእክት ያስተላለፉት በቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ጴትሮ ፓሮሊን በኩል ከሐምሌ 25-27/2009 ዓ.ም. በእግዚኣብሔር ፍቅርና ኃይል እንታመናለን በሚል መሪ ቃል 135ኛው አመት የምሥረታ በዓላቸውን በማክበር ላይ ለነበሩ የኮሎንቦስ ፈረስኞች ማሕበር እባላት ካስተላለፉት የጽሑፍ መልእክት የተወሰደ ነው።

የዚህን ዘገባ ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ለማዳመጥ ትችላላችሁ!

 

ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው እነዚህ የኮሎንቦስ ፈረሰኞች ማሕበር አባላት ለስደተኞች እያደረጉት ለሚገኘው  ድጋፍ ከፍተኛ ምስጋና ማቀረባቸው የታወቀ ሲሆን በተጨማሪም "ለተቸገሩ ሰዎችና እኒድሁም በመላው ዓለም የሚኖሩ ሰዎች መንፈሳዊ የልብ ለውጥ ያደርጉ ዘንድ እንዲጸልዩ ከአደራ ጭምር የጋበዙዋቸው መሆኑ የታወቀ ሲሆን፣ በተጨማሪም የዓመፅ ግጭቶች ያበቁ ዘንድ፣ ጥላቻ ተወግዶና ፍትህ ይሰፍን ዘንድ በተለይም በመካከለኛው ምስራቅ አከባቢ ለሚገኙ ሰዎች መጸለይ እንደ ሚገባ ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው ጨምረው ገልጸዋል።

ቅዱስነታች በዚሁ መልእክታቸው ካስተላለፉት የመልካም ምኞትና ምስጋና ባሻገር ይህ የኮሎንቦስ ፈረሰኞች ማኃበር በእግዚኣብሔር ፍቅር እና ኃይል በመታመን እስከ ዛሬው ቀን ድረስ በታሪክ ሂደት ውስጥ ያሳዩቱን ታማኝነት አጠናክረው በመቀጠል በዓለም ውስጥ “የወንድማማችነት ትብብር እንዲጎለብትና ምዕመናን፣ ሠራተኞች፣ ባለትዳሮች እንዲሁም አባቶች  የፍቅር ተግባራትን አጠናክረው” ይቀጥሉ ዘንድ ጥሪ አድረገዋል።

“እግዚኣብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ሊቃወመን ይችላል” የሚለውን በሁላችንም ዘንድ በስፋት የሚታወቀውን ቅዱስ ሐዋሪያው ጳውሎስ ወደ ሮም ሰዎች በጻፈው መልእክቱ 8:31 ላይ የሚገኘውን በመጥቀስ መልእክታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “በአሁኑ ወቅት በዓለማችን ውስጥ እየታየና በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ የሚገኘውን፣ ብሎም አቅመ ደካማ የሆኑ እህትና ወንድሞቻችን ላይ ጥቃት በሚደርስበት ወቅት ዓለም እያሳየ የሚገኘውን የምን አገባኝ ወይም ደግሞ የግድዬለሽነት ስሜት መዋጋት እንደ ሚገባቸው ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው ገልጸዋል።

“ይህ የኮሎንቦስ ፈረሰኞች ማኅበር ፍቅር በተሞላበት መልኩ በተስፋና ዘላለማዊ በሆነው በእግዚኣብሔር ኃይል በመታገዝ የምን አገባኝ ወይም የግድዬለሽነት ስሜት በመዋጋት የዚሁ ማኅበር አባላት የሆኑ ምዕመናን፣ ወንጌላዊ የሆነ መንፈስ በመላበስ፣ በእየእለቱ ኃላፊነታችውን በመወጣትና፣ በራሳቸው ሕይወት ውስጥ ክርስቶስ እንዲገለጽ በማድረግ፣ ዓለምን ለማንጻት የተሰጣቸውን መንፈሳዊ ተልእኮ በመወጣት፣ የሰዎች ልብ እንዲቀየር በማድረግ፣ ሰላምን ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት ማገዝ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

ይህ የኮሎንቦስ ፈረሰኞች በመባል የሚታወቀው ማኅበር እንደ አውሮፓዊያኑ የቀን አቆጣጠር በ1882 ዓ.ም. በአሜርካ የተመሠረተ ማኅበር እንደ ሆነ የሚታወቅ ሲሆን የመጠሪያ ስሙን ያገኘው አሳሽ፣ መርከበኛ እና አውሮፓዊያን ቅኝ ገዢ እንዲሆን ፈር የቀደደ በ15ኛው ክፍለ ዘመን ረጃጅም የሚባሉ የባሕር እና የሐይቅ ላይ ጎዞዎችን በማድረግ እንደ አሮፓዊያን አቆጣጠር 1492 ዓ.ም. ለመጀመሪያ ጊዜ አሜረካ የሚባል ሀገርን ለዓለም ባስተዋወቀው በጣሊያንዊው ክርስቶፈር ኮሎንቦስ ስም የተሰየመና በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጥላ ስር የሚተዳደር የወንድማማችነት መንፈስ እንዲጠናከር የሚሠራ መንፈስዊ ማኅበር መሆኑን ለመረዳት ተችሉዋል።

ይህ የኮሎንቦስ ፈረሰኞች ማኅበር በአሁኑ ወቅት በዓለም ዙሪያ 15,000 የመማክርት አባላትን ጨምሮ ከ1.8 ሚልዮን በላይ አባላት ያሉት ማኅበር ሲሆን በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚያገለግሉ 200 አማካሪ አባላት እንዳሉትም ይታወቃል። የዚህ ማኅበር አባል ለመሆን የሚፈልግ ማንኛውም ሰው እድሜው ከ18 አመት በላይ ወንድ መሆን እንዳለበት ከዚሁ ማኅበር የመተዳደሪያ ሕግ ለመረዳት ተችሉዋል።

05/08/2017 09:46