2017-08-04 16:23:00

ድቁና፥ ስደተኞንና ህሙማንን ለማገልገል


እ.ኤ.አ. ከነሐሴ 2 ቀን 2017 ዓ.ም. የቸፋሉ ሰበካ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቪቸንዞ ማንዘላ ባሰሙት ንግግር የተጀመረው “ዲያቆናት ሰደተኛውንና ኅሙማንን ለማስተናገድ የሚታነጹ ናቸው” በሚል ርእስ ሥር የተጠራ በኢጣሊያ ለምትገኘው ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ቋሚ ዲያቆናት ማኅበረሰብ ዓውደ ጉባኤ በፓለርሞ ክፍለ ሃገር በምትገኘው በቸፋሉ ከተማ በመካሄድ ላይ ሲሆን። ይኽ ዓውደ ጉባኤ ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮ ዓለም ዓቀፍ የስደተኞች ቀንና ከዛም 25ኛው ዓለም አቀፍ የህሙማን ቀን ምክንያት ያስተላለፉት መልእክት ላይ ያማከለ የድቁና ጥልቅ ትርጉሙ በጥልቀት እንዲስተዋል የሚያደርግ መሆኑ የኢጣሊያ ብፁዓን ጳጳሳት ጉባኤ ያስራጨው መግለጫ ይጠቁማል።

ይኽ ነገ እ.ኤ.አ. ነሐሴ 5 ቀን 2017 ዓ.ም. የሚጠናቀቀው ዓውደ ጉባኤ ድቁና ድኾችን የተረሱትን በተጎሳቆለ ሕይወት የሚገኙትን በማገልገል የሚኖር ማዕርግ ሲሆን፡ ማዕርግ የሚያስብለውም የሚሰጠው አገልግሎት መሆኑ ላይ በማተኮር ይኽ ግንዛቤ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዳይዘነጋና በተለይ ደግሞ ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮ፥ ድቁና በከተሞቻችንና በህልውና ጥጋ ጥግ የሚገኙትን ቅርብ ለመሆንና ለእነዚህ የሕብረተሰብ ክፍል ለመደገፍ ቤተ ክርስቲያን የምትሰጠው ወደ ክህነት የሚያድረስ ወይንም ደግሞ በቋሚነት የሚሰጥ ሆኖ የቤተ ክርስቲያን ለድኾች ቅርብ የመሆንዋ አገልግሎት ምስክር ነው በማለት የሰጡት ምዕዳን ላይ ሰፊ ውይይት የሚካሄድበትና  በዚህ በአሁኑ ሰዓት ያንን በባህል በቋንቋ በሃይማኖትም ይሁን ካንተ የተለየውን በፍርሃት ተመልከት የሚለውን ባህል በዚያ መቀራረብ መደጋገፍና መተሳሰብ በሚለው ባህል እንዲተካ የሚያግዝ መሆኑ በአጽንኦት የሚያብራራ ዓውደ ጉባኤ መሆኑ የኢጣሊያ ብፁዓን ጳጳሳት ጉባኤ ባወጣው መግለጫ አምልክቷል።

ድቁና ወደ ማዕርገ ክህነት የሚያሸጋግር ቢሆንም በቋሚነት ሊሰጥ የሚችል ማዕርግ መሆኑና በተለይ ደግሞ ለክህነት የሚሰናዱት ከማዕርገ ክህነት በፊት የሚቀበሉት ማዕርግ ነው። ሆኖም የድቁናውን ማዕርግ በሚገባ ሊኖሩት ይገባል በመሆኑ እንዲኖር የሚያበቃው ጊዜና ቦታም ሊሰጠው ይገባል። ስለዚህ ለክህነት ማሰናጃ ነው ተብሎ ሳይኖር ሊታለፍ አይገባውም። ድቁናውም በክህነት ህይወት ሊገለጥና ሊኖር የሚገባው በመሆኑ ቀጣይነቱ የማያቋርጥ አገልግሎት ነው። ይኸንን ደግሞ ሁሉም የተለያዩ መንፈሳውያን ማኅበራትና ገዳማት ሊያስተሉት ይገባል ሲል ዓውደ ጉባኤው እያስገንዘበ መሆኑ የገለጠው የኢጣሊያ ብፁዓን ጳጳሳት ጉባኤ መግለጫ በማስከተል፥ ይኽ የማዕርገ ድቁና ጥልቅ ትርጉም ዳግም በማነቃቃት ቤተ ክርስቲያን ልትኖረው እንደሚገባት በቲዮሎጊያ በቅዱስ መጽሓፍና በቤተ ክርስቲያን አበው ትምህርትና የቤተ ክርስቲያን ሥልጣናዊ ትምህርት ሥር የሚያብራራ መሆኑ ያመልክታል።  








All the contents on this site are copyrighted ©.