2017-07-24 09:34:00

የካቶሊካዊ ተሃድሶ እንቅስቃሴ አጀማመርና ዓላማ ክፍል 7 አስተምህሮ በክቡር አቶ ዩሐንስ መኮንን።


የካቶሊካዊ ተሃድሶ እንቅስቃሴ አጀማመርና ዓላማ ክፍል 7

የተወደዳችሁ አንባቢዎቻችን ባለፉት ሳምንታት ስለ ካቶሊካዊ ተሃድሶ እንቅስቃሴ አጀማመር እና ዓላማ አስመልክተን ተከታታይ ዝግጅቶችን በማቅረብ በመጠኑም ቢሆን ግንዛቤን እንዳስጨበጥናችሁ ተስፋ እናደርጋለን። በዛሬው ዝግጅታችንም በእንቅስቃሴው ዋና ዓላማ በሆነው በመንፈስ ቅዱስ ስለ መታደስ፣ ክርስቲያናዊ ሕይወታችንም ከዕለት ወደ ዕለት በመንፈስ ቅዱስ በመታገዝ እግዚአብሔር አምላካችን የሚደሰትበትን መልካም ሥራዎቻችንን ለማከናወን እና መላዋ ቤተክርስቲያንን ወደ እውነተኛው መንገድ ለመምራት መንፈስ ቅዱስ አምላካዊ ተልዕኮና ኃይል እንዳለው እንመለከታለን። ቆይታችሁን ከእኛ ጋር በማድረግ ይህን ዝግጅት እንድትከታተሉ እንጋብዛችኋለን።

የዚህን አስተምህሮ ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

ኢየሱስ ክርስቶስ በትንሳኤው የሞትን ኃይል አሸንፎ ወደ አባቱ ዘንድ ካረገ በኋላ በእርሱ የምናምን፣ ወደ ፍጹም እውነት የምንመራበትን አጽናኝ እና አስተማሪ የሆነውን፣ ለዘለዓለም ከእኛ ጋር የሚሆነውን መንፈስ ቅዱስን ወደ ዓለም በመላክ ዘወትር ይቀድሰናል። የሚከተለውን የወንጌል ጥቅስ እናነባለን፦ “ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፥ ይህን ሁሉ ከአሁን በፊት ያልነገርሁአችሁ ከእናንተ ጋር ስለ ነበርሁ ነው። አሁን ግን ወደ ላከኝ መሄዴ ነው፤ ሆኖም ከእናንተ ‘ወዴት ትሄዳለህ’ ብሎ ይሚጠይቀኝ የለም። ይሁን እንጂ ይህን ሁሉ ስለነገርሁአችሁ ልባችሁ በሐዘን ተሞልቶአል። እኔ ግን እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የእኔ መሄድ ለእናንተ ይጠቅማችኋል፤ ምክንያቱም እኔ ካልሄድሁ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣም፤ እኔ ከሄድሁ ግን ወደ እናንተ እልከዋለሁ። እርሱ በመጣ ጊዜ ስለ ኃጢአት፥ ስለ ጽድቅና ስለ ፍርድም ሰዎችን ያስረዳል። ስለ ኃጢአት የሚያስረዳው በእኔ ስለማያምኑ ነው፤ ስለ ጽድቅ የሚያስረዳው ወደ አብ ስለመሄዴና ከእንግዲህ ወዲህ ስለማታዩኝ ነው። ስለ ፍርድ የሚያስረዳው የዚህ ዓለም ገዥ (ሰይጣን) ስለተፈረደበት ነው። የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ ምክንያቱም እርሱ የሚናገረው የሰማውን እንጂ የራሱን አይደለም። የእኔ ከሆነው ወስዶ ስለሚነግራችሁ፥ እኔን ያከብረኛል። የአብ የሆነው ሁሉ የእኔ ነው፤ ‘የእኔ ከሆነው ወስዶ ይነግራችኋል’ ያልሁአችሁ ስለዚህ ነው።” (የዮሐንስ ወንጌል በምዕ. 16 ከቁ. 4-15)

የካቶሊካዊ ተሃድሶ እንቅስቃሴ ዓላማ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ባለን ሙሉ ሕይወት፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ በቅድስና ማደግ እንድንችል፣ የእያንዳንዳችን ሕይወት በመንፈስ ቅዱስ የማያቋርጥ መታደስን እንዲያመጣ ማገዝ ነው።

በሁሉም ውስጥ የሚኖረው፣ አንድና የማይከፋፈለው የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ መላዋ ቤተክርስቲያንን በማስተዳደር፣ በምዕመናን መካከል ያለውን አንድነት ይጠብቃል። ክርስቲያኖችን ወደ መንፈሳዊ ኅብረት በመምራት በተለይ ከሌሎች የክርስትና እምነት ተከታዮች ጋር በፍቅርና በሰላም በመተባበር ወደ ቅድስና የሚመራንን ሐዋርያዊ ተልዕኮ በኅብረት እንድናከናውን ያግዛል። ክርስቲያናዊ ሕይወታችን በኃጢአት ብዛት ቢጎዳ፣ ከማይመች የጥፋት መንገድ ተመልሰን የቅድስናን የፍቅርን፣ የደስታን፣ የትዕግስትን፣ የቸርነትን፣ የበጎነትን፣ የታማኝነትን፣ የገርነትን እና ራስን የመግዛትን ሕይወት ለመኖር የሚያስችለንን ኃይልና ጥበብ የምናገኘው ከመንፈስ ቅዱስ ነው።

ዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ ተሃድሶ እንቅስቃሴን በማስመልከት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ የሚከተለውን ሐዋርያዊ መልዕክት አስተላልፈው ነበር። “ባለፉት ዓመታት በምዕመናን መካከል በግልም ሆነ በመንፈሳዊ ማኅበራት ውስጥ መታደስን በማምጣት ብዙ መልካም ፍሬን እንድናገኝ የረዳንን እግዚአብሔር እናመሰግነዋለን። ስፍር ቁጥር የሌለው የምዕመናን ወገን፣ ቅዱስ ወንጌል ለክርስትና ሕይወት እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ተገንዝበዋል። ለጸሎትም ልዩ ትኩረትን በመስጠት በቅድስና ሕይወት ለመኖር ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ብዙዎች ወደ ቅዱሳት የቤተክርስቲያን ምስጢራት ተመልሰዋል። ስለ ምስጢረ ጥምቀት ሰፊ ግንዛቤን በማግኘት፣ የቤተክርስቲያን ተልዕኮ ፍሬያማ እንዲሆን ለማድረግ በሐዋርያዊ አገልግሎት ተሰማርተዋል።” ብለው ነበር።

ይህን ዝግጅት ከመፈጸማችን በፊት የሚከተለውን የሐዋርያው የጳውሎስ መልዕክት እንነባለን። “በፍቅር እርስ በርሳችሁ እየተረዳዳችሁ ዘወትር በትሕትና፣ በገርነትና በትዕግስት ኑሩ። በሰላም ተሳስራችሁ ከመንፈስ ቅዱስ የሚገኘውን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ። በተጠራችሁ ጊዜ ለአንድ ተስፋ እንደተጠራችሁ ሁሉ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ።እንዲሁም አንድ ጌታ፥ አንድ እምነትና አንድ ጥምቀት አለ። ደግሞም ከሁሉ በላይ የሆነ፥ በሁሉም የሚሠራ፥ በሁሉም የሚኖር፥ የሁሉም አባት የሆነ አንድ አምላክ አለ።” (የሐዋርያው የጳውሎስ መልዕክት ወደ ኤፌሶን ሰዎች በምዕራፍ 4 ከቁ. 2 – 6)

የተወደዳችሁ አድማጮቻችን፣ ስለ ካቶሊካዊ ተሃድሶ እንቅስቃሴ ዓላማ የተመለከተውን ዝግጅት በዚህ እናጠቃልላለን፣ ሳምንት እስከምንገናኝ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሰላም እና የመንፈስ ቅዱስ አንድነት ከሁላችን ጋር ይሁን።   አሜን።

ከዮሐንስ መኰንን

 








All the contents on this site are copyrighted ©.