2017-06-20 12:37:00

ክቡር የሆነው የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም የሚዘከርበት አመታዊ ክብረ በዓል በደመቀ ሁኔታ ተክብሮ ማለፉ ተገለጸ።


በሰኔ 11/2009 ዓ.ም. በመላው ዓለም በሚገኙ የላቲን ሥርዓተ አምልኮ አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናኖች ዘንድ ክቡር የሆነው የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋው እና ክቡር ደም የሚዘከርበት አመታዊ ክብረ በዓል በደመቀ ሁኔታ ተክብሮ ማለፉ ይታወቃል። ይህ ታላቅ እና ክቡር የሆነ በዓል በሁለት ምዕራፎች ተከፍሎ መከበሩ የተግለጸ ሲሆን በቅድሚያም በቫቲካ በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን እና የሀገር ጎብኝዎች ቅዱስነታቸው በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተመርኩዘው የክርስቶስ ክቡር ሥጋ እና ክቡር ደም በተመለከተ የታወቀ ሲሆን በማስከተለም በሮም ከተማ በሚገኘው የቅዱስ ዩሐንስ ላቴራን ባዚልካ ተገኝተው መስዋዕተ ቅዳሴን ካሳረጉ ቡኃላ የአዲስ ኪዳን ታቦት የሆነውን  የሆነውን የክርስቶስን ክቡር ሥጋ በመያዝ ከቅዱስ ዩሐንስ ባዚሊካ በመነሳት ብሮም ከተማ በጥንታዊነቱ ወደ ሚታወቀው በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ስም ወደ ተሰየመው ባዚሊካ መንፈሳዊ ሁደት መደረጉም ተገልጹዋል።

የዚህን ዜና ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

ርዕሰ ሊቃን ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን እና የሀገር ጎብኝዎች ክቡር የሆነውን የክርስቶስ ሥጋ እና ደም በተዘከረበት ዓመታዊ ክብረ በዓል በእለቱ በላቲን ስርዓተ አምልኮ አቆጣጠር ደንብ መሰረት በተነበበውና ከዩሐንስ ወንጌል 6፡51-58 በተወሰደው ቅዱስ ወንጌል ላይ መሰረቱን ያደረገ አስተንትኖ ማድረጋቸው የተገለጸ ሲሆን “ኢየሱስ ከሰማይ የወረደ የሕይወት እንጀራ” እንደ ሆነ ለታዳሚዎች ገልጸዋል።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ በማለት አስተንትኖዋቸውን የጀመሩት ቅዱስነታቸው ሁልጊዜ እሁድ እሁድ የቤተ ክርስቲያን ማህበረሰብ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጨረሻው ራት ላይ የመሰረተውን ቅዱስ ቁርባንን ለመዘከር በቅዱስ ቁርባን ዙሪያ ይሰበስባል በማለት አስተንትኖዋቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ከሁሉም በላይ ደግሞ በእየ አመቱ የእምነታችን መአከል የሆነውን የክርስቶስ ክቡር ሥጋ እና ክቡር ደሙን በደስታ በመዘከር እርሱ ለእኛ መንፈሳዊ ምግብ እና መጠጥ እንዲሆን ለሰጠን ክቡር ሥጋውና ክቡር የሆነ ደሙ አምልኮና ስግደት የምናደርገውም በዚሁ ምክንያት ነው ብለዋል።

በዩሐንስ ወንጌል 6፡51-58 ላይ ትኩረታቸውን ባደረገው አስተንትኖዋቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው እግዚኣብሔር አብ ልጁን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለእኛ ለሰዎች የሕይወት እንጀራ ይሆነን ዘንድ ከሰማይ ወደ ምድር ልኮታል ካሉ ቡኃላ በዚህም ምክንያት ነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ራሱን መስዋዕት በማድረግ ሥጋውን እና ደሙን ለእኛ የሰጠን ብለዋል።

ኢየሱስ “ከሰማይ የወረደ የሕይወት እንጀራ ነኝ (. . .) ለዓለም ሕይወት እንዲሆን እኔ የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው” ብሎ እንደ ነበረ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው በእርግጥ ኢየሱስ እኛን ከኃጢኣት ባርነት ለማውጣት በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ወደ ተስፋይቱ ምድር የምናደርገውን ጉዞ በድጋሚ አለምልሞታል ብለዋል። የክርስቶስ ክቡር ሥጋው እና ክቡር ደሙ ዓለም በሕይወት እንዲኖር ያደርጋል ያሉት ቅዱስነታቸው ይህንን ክቡር ሥጋ እና ደም የሚቀበል ሰው በኢየሱስ ውስጥ ይኖራል ኢየሱስም በእርሱ ይኖራል፣ ኢየሱስን መምሰል ማለት ደግሞ እርሱን መሆን ማለት ነው በልጁ አማክይነት የእግዚኣብሔር ልጅ መሆን ማለት ነው ብለዋል።

በኢየሱስ ሞት አማክይነት ተስፋ ቆርጠው ወደ  ኤማሁስ በመጓዝ ላይ የነብሩ የእርሱን ደቀ መዛሙርት እንጀራውን በቆረሰ ጊዜ እንዳወቁት እና እንደ ቀረቡት ሁሉ እኛንም በቅዱስ ቍርባኑ አማካይነት ወደ እኛ በመቅረብ እምነታችንን በመንፈሳዊ ምግብ ይመግባል፣ ተስፋችንን እና ፍቅራችንን ያለመልማል፣ በመካራዎች እና በፈተናዎቻችን ወቅቶች ሁሉ ያጽናናናል፣ ለፍትህና ለሰላም መስፍን እንድንሥራ ይረዳናል ብለዋል።

ክርስቶስ እኛ ትእዛዛቱን በተግባር መኖር እንችል ዘንድ ለመርዳት መንፍሳዊ ጥንካሬን እናገኝ ዘንድ በቅዱስ ቁርባኑ አማክይነት ራሱን በመስዋዕትነት ያቀርባል ያሉት ቅዱስነታቸው እርሱ እንደ ሚወደን እኛም እንድንዋደድ፣ እንግዳ ተቀባይ የሆነ ማኅበረሰብ እንሆን ዘንድና ለሰው ልጆች ፋጎቶች በተለይም ለጥቃት ተጋላጭ ለሆኑ፣ ለድኾች እና እርዳታችንን ለሚሹ ሰዎችን ሁሉ ለመርዳት እንድንዘጋጅ ያግዘናል ብለዋል።

የክርስቶን ክቡር ሥጋና ክቡር ደሙን መመገብ ማለት የራሳችን የግል ፍላጎቶች ወደ ጎን በመተው በተቃራኒው ጌታ ይመራን ዘንድ ራሳችንን ለጌታ ፈቃድ ማስገዛት ማለት ነው በማለት አስተንትኖዋቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው በዚህ መልኩ ከኢየሱስ ዘንድ በነጻ የተሰጠን ፍቅር፣ በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ አማክይነት ለእግዚኣብሔር እና ለእህት ወንድሞቻችን ያለን ፍቅር እንዲጨምር ያደርጋል ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በአስተንትኖዋቸው ማገባደጃ ላይ እንደ ጠቀሱት ክቡር የሆነውን የኢየሱስን ሥጋ እና ደም መቀበል ማለት ኢየሱስ መምሰል ማለት እንደ ሆነ የገለጹት ቅዱስነታቸው ይህም የክርስቶስ ምሥጢራዊ አካል ተጨባጭ በሆነ መልኩ እንድንቀርብ ያደርገናል ካሉ ቡኃላ  “የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? የምንቈርሰውስ እንጀራ ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? እንጀራው አንድ እንደሆነ፣ እኛም ብዙዎች ሆነን ሳለ አንድ አካል ነን፤ ሁላችን አንዱን እንጀራ እንካፈላለንና” ከሚለው ሐዋሪያው ጳውሎስ ወደ ቆሮንጦስ ሰዎች በጻፈውን በመጀመሪያ መልእክቱ 10፡16,17 ላይ የተወሰደውን ከጠቀሱ ቡኃላ ለእለቱ ያዘጋጁትን አስተንትኖ አጠናቀዋል።

 








All the contents on this site are copyrighted ©.