2017-06-18 16:09:00

የሰኔ 11/2009 ዓ.ም. ከጰራቅሊጦስ በኃላ ሁለተኛው ሰንበት አስተንትኖ በክቡር አባ ተወልደ ፉጅየ


ከጰራቅሊጦስ በኃላ ሁለተኛው ሰንበት ዮሐ. 14፡22-31.

በስመ አብ  ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች፣ የአምላካችን የመድሓኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ከሁላችሁ ጋራ ይሁን ፡፡

የዛሬን ሰንበት ከጰራቅሊጦስ በአል በኃላ ያለው ሁለተኛው ሰንበት ነው፡፡

የዚህን አስተንትኖ ሙሉ ይዜት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳምጥ ትችላላችሁ!

በዚህ ቀን ጌታ ለደቀመዛሙርቱ ትቶአቸው ሊሄድ ሲል የሰላም ቃል ኪዳን እንደሰጣቸው በእለቱ ከተነበበልን ወንጌል እንረዳለን፡፡ የሰጣቸውም የሰላም ቃል ኪዳን እንዲህ የሚል ነበር “ሰላሜን እሰጣችኃለሁ ሰላሜን እተውላችኃለሁ እኔ የምሰጣችሁ ሰላም ዓለም እንደሚሰጣችሁ ሰለም አይደለም” ዮሐ. 14፡27.

በዚህ የወንጌል ቃል ኢየሱስ ስለ ሰላም የተናገረው፣ ስለመንፈስ ቅዱስ ለደቀመዛሙርቱ ካብራራና ካስረዳ በኃላ ነው፡፡ ከዚህ የምንረዳው መንፈስ ቅዱስና ሰላም ለክርስቲያናዊ ህይወታችን አስፈላጊዎች መሆናቸውንና  በተለይም ለሰው ልጅ የመዳን ህይወት ወሳኝ የሆነ ሚና እንደሚጫወቱ እና ተመሳሳይነት እንዳላቸው ለመግለጽ ፈልጎ ነው፡፡

እግዚአብሔር ለሕዝቡ ሰላምንና ፈውስን እንደሚሰጥ አስቀድሞ  በነቢያት አማካኝነት ተናግሮአል ለአብነትም   ትንቢተ ኢሳያስ. 57፡19.ላይ እናገኛለን፡፡  እንደዚሁም ነቢያት የሰላም አለቃ እንደሚወለድም ተናግረው ነበር ኢሳ. 9፡6. ሰላም የተሞላበት መንግስት የሚመሰርት ንጉስ፣ የማይሻር፣ የማይለወጥ፣ የማይቀየር ፣ ዘለዓለም ነዋሪ የሆነ ንጉስ እንደሚመጣም ተናግረው ነበር ዘካ.9፡10.

በዚህ ንጉስ ግዛት ዘመን ሁሉ ሰላም እንደሚሰፍን ደግሞ ዘማሪው ዳዊት እንዲህ ሲል ተናግሮአል “በዘመኑም ጽድቅ ያብባል ጨረቃም እስኪያልፍ ድረስ ሰላም ብዙ ነው እያለ ምስክርነትን ሰጥቶአል” መዝ.72፡7.

ዛሬ ለእኛም የሚያስፈልገን ይህ አይነቱ ንጉስ ነው፡፡

 ከዚህ ንጉስ የሚሰጠን ሰላም ነው የሚጠቅመን፣ ኢየሱስ ዛሬ ልክ ደቀመዛሙርቱን ሰላሜን እሰጣችኃለሁ ብሎ በተናገረው መንፈስ ለእኛም ይናገረናል፣  ታዲያ ጆሮአችንን ከፍተን ልናዳምጠው ይገባል፣

 

ለምን?

እርሱ የሚሰጠን ሰላም ከህይወት ብርሃን፣ ከህይወት ውሃ ፣ ከህይወት እንጀራና ዘለዓለማዊ ከሆነው ፍጹም ደስታ ጋር ተመሳሳይነት ያለውና ለእኛ ለልጆቹ ያበረከተልን ልዩ ስጦታ ነው፡፡

ከኢየሱስ የሚሰጠን ሰላም ምንም ነገር ሊረብሸው እና ሊያውከው አይችልም ፡፡ ጭንቀት ይሁን ፍረሃት፣ ችግርም ሆነ መከራ፣ ረሃብም ሆነ ጥማት፣ አስራትም ሆነ እርዛት ፍጹም አያውኩትም፡፡  በዚህም ኢየሱስ የሰላም ባለቤት መሆኑን እንረዳለን፡፡  የኢየሱስ ሰላም ውጫዊ ወይም ውስጣዊ በሆኑ ችግሮችና መሰናክሎች ሊናጋ የማይችል ነው፡፡

ሰላም ስንል የግጭት ወይም የጦርነት አለመኖርን ብቻ የሚያሳይ አይደለም፣  ብዙ ነገሮችን የሚያካትት ነው፡፡ ሰላም የነፍስ ጸጥታን፣  ውስጣዊ መረጋጋትን፣ ሙሉ ጤንነትን፣ ብልጽግናን ፣ እንዲሁም መልካም የሆነውን ሁሉ መመኘትን የሚገልጽ ነው፡፡ በተጨማሪም ሰላም ከእግዚአብሔር ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመስረትና በመለኮታዊ ጠባቂነቱ ተማምኖና ተስፋ አድርጎ መኖርን የሚያሳይ ነው፡፡

ይህ ሰላም የእግዚአብሔር መንግስት በምድር ላይ የመገለጡ ምልክት ነው ፡፡  ምክንያቱም የኢየሱስ ሰላም ዓለም ከሚሰጠው ሰላም በፍጹም የተለየ ስለሆነ ነው፡፡  ስለዚህ ይህ የኢየሱስ ሰላም ከስጦታዎች ሁሉ በላይ የሆነ ከሰማይ የተሰጠን ልዩ ገጸ በረከት መሆኑን ልንረዳውና ልንገነዘበው ይገባል፡፡

 ይህ ሰላም የተቀበለ ሰው በዚህ ሰላም የሚኖር ሰው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተሞልቶ እየሱስ በእውነት ጌታ ነው ብሎ መመስከር ይችላል በዛሬው ቀን ከተነበበልን የሐዋርያው የጳውሎስ መልዕክት የምንረዳውም ይህንኑ ነው፡፡

በአጠቃላይ ወንጌሉ የሚያስገነዝበን የኢየሱስ ወደ እግዚአብሔር አብ መመለስ ለመንፈስ ቅዱስ መምጣት ወሳኝ መሆኑ ነው ፡፡

ደቀመዛሙርቱ መሪአቸው ለጊዜው በአካል ከእነርሱ በመለየቱ ምክንያት እንዳይጨነቁ፣ እንዳይረበሹ የማይናጋው ሰላም ሊሰጣቸው ወደደ፡፡  እኛም የዚህ በረከት ተካፋዮች ነንና ታላቅነቱን፣  አባትነቱን፣ የሰላም አምላክ መሆኑን፣  በክርስቲያናዊ ኑሮአችን ልንመሰክር ይገባል፡፡

 የሰላሙ ባለቤት ሆነን ክርስቲያናዊ ህይወታችንን ፍጹም በሆነ በተረጋጋ መንፈስ ውስጥ ኖረን የእርሱ ልጆች መሆናችንን እንድንመሰክር ተጋብዘናል፡፡ የሰላም ሰው ከሆንን ከራሳችን አልፈን ለሌሎች አብነት በመስጠት የእግዚአብሔር ልጆች የሚሆኑበትን መንገድ እናበጃለን ማለት ነው የተጠራነውም ለዚህ ነውና፡፡

በመጨረሻም የተከበራችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ሰላማዊ ሰው መሆን በራሱ ጥሪ ነው፣ ጥሪ መሆኑን የተገነዘበው የአሲዚው ቅዱስ ፍራንቺስኮሰ፣ ሁላችንም ከአንደበታችን ሊጠፋ በማይችል መልኩ “ጌታ ሆይ የሳለም መሳርያ እንድሆን አድርገኝ” እያለ ስለ ሰላም አስፈላጊነትና ወሳኝነት ተናግሯል፡፡

ውድ ክርስቲያኖች ሆይ እንደምናውቀው ዘመናችን በተለያዩ ነገሮች ምስቅልቅልዋ ወጥቶአል፣ ሰላም በማጣት፣  በገንዘብ  እና በንዋይ ጥማት፣ በጭካኔና በክፋት፣  በመረበሽ እና ሰላም በማጣት ታውካለች ጆሮአችን መልካም ዜናን መስማት ተስኖታል ምክንያቱም ዓለም በሰዎች ከፋት የተነሳ መልካም ዜና ለመስማት አልታደለችም በዚህ የተነሳ ሁላችንም የጥበብ ረሃብ ይዞናል፣ ጌታን የመፈለግ ረሃብ፣ የእግዚአብሔርን ቃል የመስማት ረሃብ፣ ስለ ፍቅርና ስለ ሰላም የመኖርና ለሌሎች ምሳሌ የመሆን ረሃብ፣ ይዞናል ስለዚህ ጌታ ደቀመዛሙርቱን ትቶአቸው ሊሄድ ሲል የሰላም ቃል ኪዳን እንደሰጣቸው ዛሬም ለእያንዳንዳችን ይህንን ቃል ኪዳን ሊሰጠን ይፈልጋል ጆሮአችን ልንከፍትለት ይገባል፡፡

የእግዚአብሔር ቃል ለመስማት የተራበው ጆሮአችን ስለ ሰላምና ፍቅር ለመስማት የተጠማው ጎሮአችን ዛሬ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል መልካም ዜናን በመስማት የሰላምና የፍቅር ተምሳሌትና ባለቤት የሆነውን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በመስዋዕተ ቅዳሴ በስጋና በደም በእኛ አድሮ በክርስትና ህይወታችን ሙሉ ሆነን ረክተን እንድንኖር አልፎም ለሌሎች ምሳሌ በመሆን የጌታን መንገድ እንዲከተሉ በማድረግ ክርስቲያናዊ ግዴታችንን ለመወጣት በዛሬው የወንጌል ቃል አማካኝነት ቃል ኪዳን ሊሰጠን ይፈልጋልና፣  ይህንን ቃል ኪዳን ተቀብለን የምንፈጽምበት፣ የምንኖርበትና፣ ሌሎች ለዚህ ህይወት የምንጋብዝበትን ጸጋ እንዲሰጠን እርሱን እንጠይቅ፡፡

 ስለ ሚጠብቀን፣ ስለ ሚረዳንና ስለሚንከባከበን እንደዚሁም ስለ መልካም ስጦታው ሁሉ የአምካችን የእግዚአብሔር ስም የተመሰገነ ይሁን አሜን፡፡

(በኩብር አባ ተወልደ ፉጅየ እምድብር ሀገረስብከት የተዘጋጀ)

ሮማ ቫቲካን ከተማ

 

 








All the contents on this site are copyrighted ©.