Social:

RSS:

የቫቲካን ሬድዮ

ከዓለም ጋር የሚወያይ የር.ሊ.ጳጳሳትና የቤተ ክርስትያን ድምጽ

ቋንቋ:

ቤተ ክርስትያን \ ኢትዮጵያ

የሰኔ 4/2009 ዓ.ም. የቅድስት ሥላሴ ሰንበት አስተንትኖ በክቡር አባ ቶማስ ወልደሥላሴ!

የሰኔ 4/2009 ዓ.ም. የቅድስት ሥላሴ ሰንበት አስተንትኖ በክቡር አባ ቶማስ ወልደሥላሴ! - RV

12/06/2017 08:57

ሰንበት ዘቅድስት ሥላሴ

የእለቱ ምንባባት

ኦሪት ዘፀአት፡- 34:4-6,8, 9

2ቆሮንጦስ፦ 11-13

ዩሐንስ፦ 3.16-18

በቅድስት ስላሴ ምስጢር የተዋጃችሁ ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

የቅድስት ሥላሴ ሕይወት በሦስት ነገሮች ሊገለጥ ይችላል፡፡ እነዚህም ፍቅር፣ ሰላምና ደስታ  ናቸው፡፡

የዚህን አስተንትኖ ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

ሰንበት ዘቅድስት ሥላሴ

የእለቱ ምንባባት

  • ኦሪት ዘፀአት፡- 34:4-6,8, 9

  • 2ቆሮንጦስ፦ 11-13

  • ዩሐንስ፦ 3.16-18

በቅድስት ስላሴ ምስጢር የተዋጃችሁ ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

የቅድስት ሥላሴ ሕይወት በሦስት ነገሮች ሊገለጥ ይችላል፡፡ እነዚህም ፍቅር፣ ሰላምና ደስታ  ናቸው፡፡

በመጀመሪያ የቅስት ሥላሴ ሕይወት ፍቅር መሆኑ ስንመለከት ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ (1ዮሓ 4፡8) እግዚኣብሔር ፍቅር ነው ይላል፡፡ ፍቅር ደግሞ እንደሚታወቀው ሁሉ ጊዜ ወደ ሌላ ያተኮረ ነው፡፡ ይህ ማለት የፍቅርን ትርጉም በእውነት ከተረዳን ራሳችንን ማፍቀር አንችልም፡፡ ለዚህም ነው አምላካችን በሦስት አካላት የተዋቀረው፡፡

ሶስት አካላት ስንል ደግሞ፡ ግኑኝነት የሌላቸው ሦስት አካላት ማለታችን አይደለም። አብ ወልድና መንፈስ ቅዱስ የአንድት መለኮታዊት ቤተሰብ አባላት ናቸው፡፡ የቤተሰብ አባላት እንደመሆናችን በቤተሰብ ውስጥ በአባት፣ በእናትና በልጆች መሃከል ያለው ፍቅር ምን እንደሚመስል ሁላችን እናውቃለን፡፡ የቅድስት ሥላሴ አባላት ደግሞ እርስ በርሳቸው ለቤተሰብ ሕይወት አብነት መሆን የሚችል ፍቅር አላቸው፡፡ እንግድህ የቅድስት ሥላሴ ሕይወትን በተወሰነ ደረጃ ለመረዳት በቤተሰባችን ውስጥ ያለውን ፍቅር ማሰብ አለብን፡፡ ፍቅር ያለው ቤተሰብ ሁሉ ስለ ሌላው ያስባል፣ ስለ ሌላው ይቸገራል፡፡ የቅድስት ሥላሴ ሕይወትም እያንዳንዱ አካል በፍቅር ያለውን መልካም ነገር ከሌላው ጋር የመጋራት ሕይወት ነው፡፡  

ፍቅር ሁሉ ጊዜ ያለውን ለሌላ ማጋራት ባህሪው ከመሆኑም የተነሣ ፍቅራቸውን ሃብታቸውን ሕይወታቸውን፣ ደስታቸውን፣ ሰላማቸውን፣ ወ.ዘ.ተ. ለሌላ ለማጋራት ሲሉ ነው ቅድስት ሥላሴ ዓለምን የፈጠሩት፡፡ የፍቅርን ትርጉም አውቀው ደግሞ ፍቅር መስጠትና መቀበል የሚችሉ እንዲኖሩ ብለው ነው ቅድስት ሥላሴ፡ በአምሳያቸው ሰዎችን፡ እኛን የፈጠሩት፡፡ ቅድስት ሥላሴ ክርስቶስንም ወደ ዚህ ዓለም የላኩት፣ ክርስቶስም በመስቀል እስከ መሞት የደረሰው፡ በፍቅር ነው፡፡ ባለፈው እሁድ በዓለ የጰራቅሊጦስ በዓል ያከበርንለት መንፈስ ቅዱስም ወደ ዚህ ዓለም የተላከው ከኛ ጋርም የሚኖረው በፍቅር ነው፡፡

ከኛ የሚጠበቀውም፡ አምላካችንን ሆነ እርስ በርሳችን ማፍቀር ነው፡፡ እግዚኣብሔር የሚፈልገው፡ ፍቅር መቀበልና መሠጠት የሚንችል እንዲንሆን ነው፡፡ ስለ በመንግሥተ ሰማይና ገሃነመ እሳት ውስጥ ስላሉ ሰዎች የሚነገር ታሪክ አለ፡፡ ታሪኩም፡ አንድ ሰው በመንግስተ ሰማይና ገሃነመ እሳት ውስጥ ያለ ሁኔታ ማየት እንደቻለ ይናገራል፡፡ መጀመሪያ ወደ ገሃነመ እሳት ገባና፡ እዛ ያሉ ሰዎች ብዙ ምግብ የተቀመጠበትን ገበታ ከበዋል፡፡ ሰዎቹ ሁላቸው በረሃብ ልሞቱ ያሉ፣ እርስ በርሳቸው የማይነጋገሩና፡ ሃዘን በፍታቸው የሚነበብ መሆናቸው ያያል፡፡ እዛ ያሉ ሰዎች፡ እያንዳንዳቸው፡ በእጃቸው የታሰረ፡ ኣንድ ሜትር የሚረዝም ማንክያ ኣላቸው፡፡ ከምግቡ በማንክያ ወስደው ለመጉረስ ይሞክራሉ፡፡ ግን ማንክያቸው ከእጃቸው ስለሚረዝም፡ ምግብን ወደ ኣፋቸው ለማድረስ ኣይችሉም፡፡ ለዚህም ነው ሁላቸው የተራቡ፣ የተጎሳቊሉና ሃዘንተኞች የሆኑት ተብሎም ይነገረዋል፡፡ ሰውየው፡ በገሃነመ እሳት ባየው እያዘነ ይወጣና፡ በመንግሥተ ሰማይ ያለ ሁኔታ ለማየት፡ ወደ መንግስተ ሰማይ ይገባል፡፡ እዛ ያሉ ሰዎች፡ ምንም ረሃብ ምልክት የሌላቸው፣ የሚነጋገሩና፡ ደስተኞች መሆናቸው፡ ወድያውኑ ይገነዘባል፡፡ የሚገርመው ነገር ግን፡ ሰዎቹ ዙሪያውን የከበቡት ገበታ ሆነ፡ በላይዋ ላይ ያለው ምግብ፡ በገሃነም ውስጥ ካየው፡ ምንም ልዩነት የለውም፡፡ በሰዎቹ እጅ ደግሞ፡ ልክ እንደ በገሃነመ እሳቱ፡ ኣንድ ሜትር የሚረዝም ማንክያ ታስሯል፡፡ ታድያ እንዴት ነው የሰዎቹ ሁኔታ፡ እንድህ ጥሩ የሆነው፡ ብሎ ስጠይቅ ግን፡ በመንግስተ ሰማይ፡ ሰዎቹ፡ እርስበርሳቸውን ነው የሚጎራረሱት፡፡ የማንክያው ርዝመት ደግሞ፡ ለመመገብ ኣይከለክላቸውም፡ ስለዝህም ነው እንዲህ ደስተኞች የሆኑት፡ የሚል ምላሽ ተሰጠው ይባላል፡፡ ባጭሩ፡ የታሪኩ ትርጉም፡ የገሃነመ እሳት ሰዎች ግለኝነት፣ ንፍገትና ራስ-ወዳድነት ስለሚያጠቃቸው፡ በሃዘን እንዲኖሩ በራሳቸው የፈረዱ መሆናቸው ነው፡፡ የመንግሥተ ሰማይ ሰዎች ግን፡ ፍቅር፣ መተሳሰብና መተባበር ስለመረጡ ደስተኞች ናቸው የሚል ነው፡፡

ወንድሞቼና እህቶቼ፡ አምላካችን ፍቅር ነው፡፡ በፍቅር ምክንያት ነው የፈጠረን፡፡ ከእርሱ ጋራ ሆነ፡ እርስ በርሳችን፡ በፍቅር እንድንኖር ይፈልጋል፡፡ ስስት፣ ግለኝነትና አሉታዊ ኣስተሳሰብ ከህይወታችን ማራቅ አለብን፡፡

2. በሁለተኛ ደረጃ፡ ከፍቅር በተጨማሪ የቅድስት ሥላሴ ሕይወት መገለጫ ይሆናል ያልነው፡ ሰላም ነው፡፡ ቅዱስ አጎስጢኖስ፡ እግዚኣብሔር የሚያጣጥመው ሰላም፡ እኛ ሆነ መላእክት፡ ልናስበው ከምንችለው በላይ ነው ይላል፡፡ መጀመሪያው መጽሐፈ ነገስት (19፡11-13)፡ ስለ እግዚኣብሔር እንዲህ ይላል፤ "ትልቅና ብርቱ ነፋስ ተራሮቹን ሰነጠቀ፡ ዓለቶቹንም ሰባበረ፥ እግዚአብሔር ግን፡ በነፋሱ ውስጥ፡ አልነበረም። ከነፋሱም በኋላ፡ የምድር መናወጥ ሆነ፥ እግዚአብሔር ግን፡ በምድር መናወጥ ውስጥ፡ አልነበረም። ከምድር መናወጥ በኋላ፡ እሳት ሆነ፥ እግዚአብሔር ግን፡ በእሳቱ ውስጥ፡ አልነበረም። ከእሳቱም በኋላ፡ ትንሽ የዝምታ ድምፅ ሆነ። ኤልያስም፡ ያን በሰማ ጊዜ፡ ፊቱን በመጐናጸፊያው ሸፈነ፥ ወጥቶም በዋሻው ደጃፍ ቆመ። እነሆ፡ ኤልያስ ሆይ፥ በዚህ ምን ታደርጋለህ? የሚል ድምፅ ወደ እርሱ መጣ።"

የተከበራቹህ የእግዚኣብሔር ቤተሰብ፡ በዚህች የመጽሓፍ ቅዱስ ጥቅስ፡ እግዚኣብሔር፡ በትንሽ የዝምታ ድምፅ ተመስሏል፡፡ እርግጥ ነው፡ ሰላምና እርጋታ፡ የማይመኝ የለም፡፡ ሰላም ማጣጣም የምንጀምረው ደግሞ፡ ነገሮች ሲሳኩልን፣ ነገሮች፡ መስመር ሲይዙልን ነው፡፡ ለእግዚኣብሔር፡ ሁሉ የተስተካከለና የተሳካ ነው፡፡ ስለዚህ እሱ ፍጹም ሰላም አለው፡፡ በትንሣኤ ወቅት፡ ክርስቶስ ተንሥኣ እም ሙታን፡ በዓቢይ ኃይል ወሥልጣን፡ ኣሰሮ ለሰይጣን፡ ኣግኣዞ ለኣዳም፡ እምይእዜሰ ኮነ ፍሥሓ ወሰላም፡ እንላለን፡፡ እምይእዜሰ ኮነ ፍሥሓ ወሰላም፡ የሚንለው፡ ሰይጣንና ተንኵሉ ስለተሸነፈ ነው፡፡ እግዚኣብሔር ዘለዓለማዊ ሰላሙንና፡ እርካታውን እንዲንጋራ፡ ስለፈለገ ነው የፈጠረን፡፡ በዚህ ዓለም ይሁን በምመጣው ዓለም፡ የዚህ፡ የቅድስት ሥላሴ ሰላም መጋራት የምንችለው፡ ወደ ቅድስት ሥላሴና እርስ በርሳችን ፍቅር ካለን፡ ሰይጣንንና ምክሮቹን ወደ ራሳችን ካላስጠጋን ነው፡፡

3. በሶስተኛ ደረጃና በመጨረሻ፡ የቅድስት ሥላሴ ሕይወት መገለጫ ይሆናል ያልነው፡ ደስታ ነው፡፡ አንድ ማየስተር አካርት የሚባሉ እውቁ ጀርመናዊ መኖክሴ፡ ስለ ቅድስት ሥላሴ፡ እንዲህ ይሉ ነበር፡፡ "እግዚኣብሔር ኣብ፡ ከእግዚኣብሔር ወልድ ጋር ሲስቅ፡ እግዚኣብሔር ወልድ ለእግዚኣብሔር ኣብ በሳቅ ይመልስለታል፡፡ ያ ሳቅ ደግሞ፡ እርካታ ይሰጣል፣ እርካታው፡ ደስታን ይሰጣል፣ ደስታው ደግሞ ፍቅር ይሰጣል፣ ይህ ፍቅር ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ነው" ይል ነበር፡፡ በእውነትም ቅድስት ሥላሴ በደስታ ልንመስላቸው እንችላለን፡፡ እስቲ በሆነ ምክንያት፡ እውነተኛ ደስታ የተሰማን አጋጣሚ እናስብ፡፡ ሰዎች ባሳዩን የፍቅር ምልክት ልሆን ይችላል፡ ወይም ሌል በሕይወታችን ባጋጠመ መልካም ነገር ልሆን ይችላል፡፡ በዛች የእውነተኛ ደስታ ኣጋጣሚ፡ የቅድስት ሥላሴ ደስታ እየተጋራን ነው ማለት ይቻላል፡፡ ወንድሞቼና እህቶቼ፡ እውነተኛ ደስታ ሁሉ ከእግዚኣብሔር ነው የሚመጣው፡፡

ቅድስት ሥላሴ እንዲንደሰት ይፈልጋሉ፡፡ ለዚህም ነው የፈጠሩን፡ እንዲሁም፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም የላኩት፡፡ ደግሞ ለዚህ ዓላማ ነው፡ መንፈስ ቅዱስም ከኛ ጋር የሚኖረው፡፡ ስለዚህ እግዚኣብሔር ምን ያክል እንደሚወደንና ከኛ ጋር መሆኑን እናስተውል፣ የሱ ሥራ እናድንቅ፣ ትእዛዛቱን እናክብር፣ የሰው ልጆች ሁላቸው በእግዚኣብሔር ዘንድ የተወደዱና ሁላቸው የተከበሩ መሆናቸው እንገነዘብ፡፡

ኣጭር ታሪክ ላካፍላቹህ፡፡ ኣንድ ኣዳኝ፡ የኣሞራ እንቁላል ያገኝና፡ ወደ ቤቱ ኣምጥቶ፡ ከዶሮ እንቁላል ጋር ያቀላቅለውና፡ የኣሞራ ጫጩት፡ ከዶሮ ጫጩቶች ኣብሮ ይፈለፈላል፡፡ ኣሞራው ከዶሮዎቹ ኣብሮ ስላደገ ዶሮ የሆነ ይመስላው ነበር፡፡ የሰማይ ንጉስ ኣሞራ፡ በሰማይ ስያንጃብብ ስያይ ደግሞ፡ ምነው እኔም እንደሱ በሆንኩ እያለ ስመኝ፡ ምንነቱን ሳያውቅና በሕይወቱ ሳይደሰት እንደዶሮ ሆኖ ኣለፈ ይባላል፡፡ እኛም በቅድስት ሥላሴ ኣምሳያ የተፈጠርን፣ ክርስቶስ በደሙ የተበጀን፣ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ የሆን፣ ያምላክ ልጆችና የመለኮታዊ ቤተሰብ ኣባላት መሆናችንን ባለመገንዘብ፡ ምንነታችን ልሰጠን የሚገባውን ደስታ ሳናጣጥም መኖር የለብንም፡፡

እናም፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለፊሊጲስዩስ ሰዎች እንደሚለው፡ ሁሉ ጊዜ በጌታ ደስ ይበለን፣ ኣምላካችን ቅርብ ነውና በኣንዳች ነገር ኣንጨነቅ፣ አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችን ውስጥ ይሁን፡፡ ሁሌ፡ አውነትን፣ ጽድቅን፣ በጎነትን፣ ንጽሕናን እና ፍቅርን እናስብ፡፡ መልካም እሁድ ያድርግልን፡፡

(በክቡር አባት ቶማስ ወልደስላሴ የተዘጋጀ)

 

12/06/2017 08:57