2017-06-08 09:21:00

ክርስቲያኖች ማንኛውንም ዓይነት የግብዝነትና የማቆለማመጥ ፈተናዎችን አስወግደው በምትኩም ታማኝ ክርስቲያኖች ሊሆኑ ይገባል።


ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቼስኮ ክርስቲያኖች ሁሉ ማንኛውንም ዓይነት የግብዝነትና እና የማቆለማመጥ ፈተናዎችን አስወግደው በምትኩም ታማኝ ክርስቲያኖች ይሆኑ ዘንድ ማሳሰባቸው ተገለጸ። ቅዱስነታቸው ይህንን ማሳሰቢያ የሰጡት በግንቦት 29/2009 ዓ.ም. በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት እንደ ሆነም ተዘግቡዋል።

የዚህን ዝግጅት ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

ግብዝነት የሚለው ቃል በፍጹም የኢየሱስ ወይም የክርስቲያኖች ቃል አይደለም በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው እርግጥ ግብዝነት ማኅበረሰብን የሚያፈራርስ ተግባር ነው ብለዋል። ኢየሱስ በቅዱስ ወንጌል ውስጥ ግብዝነት የሚለውን ቃል በብዛት የተጠቀመው የሕግ ምሁራንን በተመለከቱ ጉዳዩች ላይ እንደ ነበረ በመግለጽ ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ምክንያቱም ግብዝነት የሚለው ቃል ሥር መሰረቱ ከሌሎች በተሻለ መልኩ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መሆን ወይም ደግሞ በእምነት ከሌሎች በተሻለ ደረጃ ጠንካራ መሆን የሚለውን ሐሳብ የሚያሰማ በመሆኑ ነው ካሉ ቡኃላ ሐሳባቸውን እና ውሳኔዎቻቸውን ትክክል እንደ ሆነ አድርገው ያቀርባሉ ነገር ግን እውነታው ከእዚያ የተለየ እና ሐሰት ነው ብለዋል።

በእለቱ በላቲን የስርዓተ አምልኮ አቆጣጠር መሰረት በተነበበው እና ከማርቆስ ወንጌል ከምዕራፍ 12 በተወሰድደው ምንባብ ላይ ተመስርተው “ግብዞች ሁል ጊዜ የማቆለጳጰሻ ቆንቋዎችን ይጠቀማሉ” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ከፈሪሳዊያን እና ከሂሮድስ ወገን የሆኑ አንዳንድ ሰዎች ኢየሱስን በንግግሩ ለማጥመድ አቅደው መምህር ሆይ አንተ እውነተኛ መሆንህን እናውቃለን በማለት በማቆለጳጰስ ንግግራቸውን ጀምረው እንደ ነበር ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል።

“ግብዞች ሁል ጊዜም ቢሆን ንግግራቸውን የሚጀምሩት ከመጠን በላይ በሆነ መልኩ በማወደስ ነው” በማለት  ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “እውነታን በማጋነን ሰዎች በኩራት ላይ ኩራትን እንዲጨምሩ ያደርጋሉ” ብለዋል።

ኢየሱስ እውነታን ከግብዝነት እና ከምናባዊ አስተሳሰብ ተቃራኒ በሆነ መልኩ እንድንመለከት ያደርገናል  ያሉት ቅዱስነታቸው በአንጻሩም ቁልምጫ ሁልጊዜም ቢሆን ከመጥፎ ልቦና የሚመነጭ እንደ ሆነ ጠቅሰው ይህንንም ዛሬ ከተነበበል የወንጌል ቃል ውስጥ የተገለጹት ፈሪሳዊያን ኢየሱስን “መምህር ሆይ! አንተ እውነተኛ መሆንህን እናውቃለን” በማለት ንግግራቸውን መጀመራቸው እና ይህንን ቁልምጫ ተከትሎ ደግሞ “ለቄሳር ግብር መክፈል ይገባናል ወይ?” የሚል ጥያቄ ማስከተላቸው ኢየሱስን ወደ አልተጋባ የስህተት መንገድ ለመምራት አስበው የፈጸሙትን ተግባር እንደ ሆነ በማሳያነት መውሰድ ይቻላል ብለዋል።

“እነዚህ ግብዝ ፈሪሳዊያን ሁለት የፊት ገጽታን ተላብሰው ኢየሱስን መቅረባቸውን” የገለጹት ቅዱስነታቸው ኢየሱስም ይህንን ተንኮላቸውን አውቆባቸው “ለምን ልታጠምዱኝ ትፈልጋላችሁ? እስቲ ገንዘቡን አምጡና አሳዩኝ” ብሎ መልሶላቸው   እንደ ነበረ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ኢየሱስ በዚህ ጥበባዊ አመላለሱ የቄሳርን ለቄሳር የእግዚኣብሔርን ለእግዚኣብሔር መስጠት እንደ ሚገባ ግልጾላቸው ነበር ብለዋል።

“የግብዞች ቋንቋ በአታላይነት የተሞላ ነው” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ይህም “እባቡ ሄዋንን ለማታለል ከተጠቀመበት ቋንቋ ጋር ተመሳሳይነት” አለው ያሉት ቅዱስነታቸው ሰዎችን በማቆለማመጥ ይጀምርና በመጨረሻም ሕይወታቸውን፣ ማንነታቸውን እንዲሁም ነብሳቸውንም ሳይቀር እንዲበላሽ ያደርጋል ካሉ ቡኃላ ይህም በአጠቃላይ ማሕበረሰቡን ያውካል ብለዋል።

ግብዝነት ቤተ ክርስቲያንን ያፈርሳል ያሉት ቅዱስነታቸው ከእዚህ ክፉ ነገር ተጠብቀን፣ እውነተኛ ክርስቲያኖች እንድንሆን ይህንንም መሆን ካልቻልን ግብዝነትን አስወግደን ከሁሉም ነገር ተቆጥበን በዝምታ መኖር እንችል ዘንድ ጌታ እንዲረዳን መጸለይ ይገባል ካሉ ቡኃላ ለእለቱ ያዘጋጁትን ስብከት አጠናቀዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.