2017-05-29 16:54:00

የክርስቶስ ዕርገት የወልድ ምድራዊ ተልዕኮ ማብቃቱን እና ቤተ ክርስትያን ይህንን ተልዕኮ ማስቀጠል መጀመሯን ያመለክታል


ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ከተነሳ ቡኃል በተለያዩ አጋጣሚዎች ለሐዋሪያቱ ሲገለጽ ቆይቶ ከዓርባ ቀናት ቡኃላ ወደ ሰማይ ያረገበት የዕርገት በዓል በመላው ክርስትያኖች ዘንድ በትላንትናው እለት ተከብሮ አልፉዋል። በትላንታንው እለት ማለትም በግንቦት 20/2009 ዓ.ም ይህንን የዕርገት በዓል ለማክበር  በርከት ያሉ ምዕመናን እና የሀገር ጎብኝዎች በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ተገኝተዋል። በእለቱም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ  ከማቴዎስ ወንጌል 28፡16-20 በተነበበው የእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ባተኮረው አስተምህሮዋቸው እንደ ገለጹት ከሙታን የተነሳው ጌታ በገሊላ ለደቀ መዛሙርቱ ተልዕኮውን ካስረከባቸው ቡኃላ ወደ ሰማይ በክብር ማዕረጉን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል።

የዚህን ዜና ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

ዐሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ እንዲሄዱ ወደ አመለከታቸው በገሊላ በሚገኘው ተራራ የነበረው ትዕይንት የዚህ አዲስ ማኅበረሰብ አስኳል የነበረ ትዕይንት ነበር በማለት አስተንትኖዋቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ደቀ መዛሙርቱ ወደ እዚያው ተጉዘው የነበሩት በክርስቶስ ስቃይ እና ከሙታን መነሳት ስሜት ውስጥ ሆነው እንደ ነበረ ጠቅሰው ኢየሱስን ባዩት ጊዜ ወድቀው እንደ ሰገዱለትም ገልጸዋል።

ነገር ግን ከደቀ መዛሙርቱ አንድአንዶቹ ከፍተኛ የሆነ ጥርጣሬ አድሮባቸው እንደ ነበረ በመግለጽ አስተንትኖዋቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ኢየሱስ ለዚህ በጥርጣሬ እና በፍርሃት ለተሞላ ማኅበረሰብ ነበር ቅዱስ ወንጌልን ለዓለም የመስበክ ኅላፊነትን የሰጠው ካሉ ቡኃል በአብና በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እንዲያጠምቁ ትእዛዝ ሰጥቶዋቸው እንደ ነበረም ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል።

የክርስቶስ ወደ ሰማይ ማዕረግ የወልድ ምድራዊ ተልዕኮ ማብቃቱን እና ቤተ ክርስትያን ይህንን የክርስቶስ ተልዕኮ ማስቀጠል መጀመሯን ያመለክታል ያሉት ቅዱስነታቸው ከዚያን ጊዜ ቡኃላ ክርስቶስ በደቀ መዛሙርቱና በእርሱ አምነው እርሱን በዓለም በሚያውጁ ሰዎች ሁሉ አማክይነት በዓለም ውስጥ መኖሩን ቀጥሉዋል ብለዋል።

ከሙታን ለተነሳው ለክርስቶስ መለኮታዊ ድጋፍ ምስጋና ይግባውና የእርሱ ተልዕኮ እስከ ዓለም ፍጻሜ ይቀጥላል በማለት አስተንትኖዋቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ይህንንም ኢየሱስ በቃሉ “እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁሉ ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” በማለት የማረጋገጫ ቃል ሰጥቶናል ብለዋል።

ቅዱስነታቸው አስተንትኖዋቸውን በቀጠሉበት ወቅት እንደ ገለጹት ኢየሱስ ከእኛ ጋር እስከ ዓለም ፍጻሜ እንደ ሚኖር የሰጠን ማረጋገጫ በስደት ውስጥ ለሚገኙ ክርስትያኖች ጥንካሬን፣ በስቃይ ውስጥ ለሚገኙ ክርስትያኖች ደግሞ መጽናናትን፣ እንዲሁም አስቸጋሪ በሚባል ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙት ክርስትያኖች ደግሞ  ድጋፍን ይሰጣቸዋል ብለዋል።

የኢየሱስ ዕርገት አሉ ቅዱስነታቸው የኢየሱስ ዕርገት ኢየሱስ እንደ ሚረዳን እና የምንተማመንበት እርሱ የሚሰጠን መንፈስ ቅዱስ ክርስትያናዊ ምስክርነትን በዓለም ውስጥ ማከናውን እንድንችል እንደ ሚረዳን ያስታውሰናል ያሉት ቅዱስነታቸው ይህም ቤተ ክርስትያን የተመሰረተችው ቅዱስ ወንጌልን ለዓለም ለማብሰር መሆኑንም ያስረዳናል ብለዋል።

የቤተ ክርስትያን ደስታ የሚመነጨው ወንጌልን ከመስበክ ብቻ መሆኑ መረሳት የሌለበት ዋነኛው ጉዳይ ነው ያሉት ቅዱስነታቸው ቤተ ክርስትያን ማለት ሁሉንም የተጠመቁ ክርስትያኖችን ያጠቃልላል፣ በተለይም ዛሬ እግዚኣብሔር ለእኛ ይህንን ቅዱስ ወንጌልን ለዓለም የማወጅ እና ለሰው ልጅ ዘር ሁሉ ተደራሽ የማድረግ ታላቅ ክብር እና ኅላፊነት እንደ ሰጠን መረዳት እንደ ሚያስፈልግም ቅዱስነታቸው ጨመረው ገልጸዋል።

ቅዱስነታቸው አስተንትኖዋቸውን በቀጠሉበት ወቅት እንደ ገለጹት በእዚህ በዕርገት ቀን ክርስቶስ ያረገበት እና በአባቱ ቀኝ የተቀመጠበት ሰማይን በማሰብ እንቃትታለን ያሉት ቅዱስነታቸው ጠንካሮች እንሁን፣ ታላቅ የሆነ ፍላጎትም ይኑረን፣ በምድራዊ ኑሮዋችንም ብርታት ይኑረን፣ የመመስከር ተልዕኮዋችንን በማጠናከር በማንኛውም ሥፍራ እና ሁኔታ በሕይወታችን ቅዱስ ወንጌልን መመስከር ይገባል ብለዋል።

ይህ ተግባር በራሳችን ኅይል እና ብርታት ብቻ የሚከናወን ነገር አለመሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ያሉት ቅዱስነታቸው ይህም ተግባር ድርጅታዊ ክህሎቶች እና ሀብት በመጠቀም የምንወጣው ተግባር አይደለም፣ በመንፈስ ቅዱስ በሚገኝ ብርሃን እና ብርታት ታግዘን ብቻ ነው የኢየሱስን ፍቅር እና ርኅራኄ በተሳካ መልኩ ማወጅ የሚቻለው ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በስብከታቸው ማገባደጃ ላይ እንደ ጠቀሱት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቃል የገባልንን ሰማያዊ የሆኑ ነገሮችን ብቻ ማሰላሰል እንድንችልና ታማኝ የክርስቶስ ትንሥኤ መስካሪዎች እንድንሆን፣ ይህንንም በሕይወታችን መመስከር እንድንችል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ትረዳን ዘንድ መጸለይ ያስፈልጋል ካሉ ቡኃል ለእለቱ ያዘጋጁትን አስተንትኖ አጠናቀዋል።    

 








All the contents on this site are copyrighted ©.