2017-05-20 11:47:00

የዓለምን ፍቅር መከተል አቁመን ወሰን የሌለውን የክርስቶስ ፍቅር መከተል ይኖርብናል።


ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በትላንትናው እለት ማለትም በግንቦት 10/2009 ዓ.ም. በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት ምዕመናንን እንዳሳሰቡት “የኢየሱስ ፍቅር እንደ ዓለም ፍቅር ለስልጣን እና ለእብሪት እንድንጓጓ የሚያደርገን ዓይነት ፍቅር ሳይሆን፣ የኢየሱስ ፍቅር ዘለዓለማዊ እና እውነተኛ ፍቅር ነው” ካሉ ቡኃላ የክርስትያን ተልእኮ ሊሆን የሚገባው ደስታን በሰዎች ዘንድ መፍጠር እና የእግዚኣብሔር ፍቅር የክርስትያኖች እውነተኛ ሕይወት አለኝታ መሆኑን መመስከር ነው ማለታቸው ተገልጹዋል።

የዚህን ዜና ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚባለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

“አብ እኔን እንደ ወደደኝ፣ እኔም እናንተን ወደድኃችው” የሚለውን በእለቱ ከዩሐንስ ወንጌል ከምዕራፍ 15፡9-11 የተነበበውን ቅዱስ ወንጌል ቃል በመጥቀስ ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው የኢየሱስ ፍቅር ዘለዓለማዊ ነው ብለዋል።

ጌታ ለእርሱ ቅርብ እንድንሆን እና ትእዛዛቱን እንድናከብር ይጠይቀናል በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “ዐስርቱ ትእዛዛት መሰረታዊ የሆኑ ትእዛዛት ናቸው፣ ነገር ግን እኛ የተጠራነው ኢየሱስ የምያስተምረንን መንገድ እንድንከተልና የክርስትና ሕይወታችንን ልያጸባርቅ የሚችሉትን ትእዛዛትን እለት በእለት በኑሮዋችን ማንጸባረቅ እንድንችል ነው ብለዋል።

ቅዱስነታቸው ስብከታቸውን በቀጠሉበት ወቅት እንደ ገለጹት ምንም እንኳን የኢየሱስ ትእዛዛት በጣም ሰፊ የሚባል ሕብረ ቀለማትን የሚሸፍኑ ቢሆንም ቅሉ፣ የእነዚህ ሁሉ ሥር መሰረት የሆነው ግን “እርሱ ለአብ ያለው ፍቅር እና አብ ለልጁ ያለው ፍቅር” ነው ማለታቸውም ተዘግቡዋል።

“ከዚህ ውጭ የሆኑ ብዙ የፍቅር ዓይነቶች አሉ። ዓለማችን ለምሳሌም የገንዘብ፣ የግብዝነት፣ የትዕቢት፣ የኩራት፣ ሌላ ተጨማሪ ስልጣን ልያጎናጽፈን የሚችል የስልጣን ጥማት የመሳሰሉትን የፍቅር ዓይነቶች ለእኛ በስጦታነት ያቀርብልናል” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው እንደ እነዚህ ዓይነት ፍቅሮች  ከኢየሱስ እና ከአብ ፍቅር ጋር በፍጹም ቢሆን ግንኙነት የላቸውም ካሉ ቡኃላ እንደ እነዚህ ዓይነት ፍቅሮች በእርግጠኝነት ከእግዚኣብሔር ያርቁናል ብለዋል።

የእግዚኣብሔር ፍቅር ሊለካ የማይችል ዘለዓለማዊ ፍቅር ነው በማለት ስብከታቸውን የቀተሉት ቅዱስነታቸው ዓለም እንደ ሚሰጠን ዓይነት ፍቅር ለብ ያለ ወይም ጥቅማችንን ብቻ የሚያሳድድ የፍቅር ዓይነት አይደለም ካሉ ቡኃላ “ኢየሱስ የሰጠን ትእዛዝ፣ በእርሱ እና በአብ ዘለዓለማዊ ፍቅር እንድንኖር ነው” ብለዋል።

በእርግጥ አሉ ቅዱስነታቸው “ይህንን ለምንድነው የምታስታውሰን? ልትሉኝ ትችሉ ይሆናል” በማለት ጥያቄን በማንሳት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ይህንንም የምላችሁ በጌታ ደስታ እንድትኖሩ እና ደስታችሁ ምልአት ይኖረው ዘንድ ነው” ካሉ ቡኃላ “ኢየሱስ ዓለማዊ የሆኑ የፍቅር ዓይነቶችን ወደ ጎን በመተው ያለገደብ መውደድ የሚችል የተከፈተ ልብ ይኖረን ዘንድ የሚረዳንን የፍቅር መንገድ ያስተምረናል” ብለዋል።

እግዚኣብሔርን መውደድ እና ሰዎች ደስታን እንዲጎናጸፉ ማድረግ የሚሉት ጽንሰ ሐሳቦች የክርስትያን ተልእኮ ዋንኛው ዓላማ ሊሆን የገባል በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ስለዚህም “ የፍቅር እና የደስታ ስጦታዎችን ይሰጠን ዘንድ እግዚኣብሔርን መለመን ይገባናል” ካሉ ቡኃላ በቅርብ ጊዜ የጵጵስናን መዐረግ የተቀበሉ አንድ ጳጳስ የገጥሞዋቸው የነበረውን ገጠመኝ ቅዱስነታቸው እንዲ በማለት ገልጸዋል፣

“አንድ በቅርቡ ጳጳስ ሆኖ የተሾመ ሰው ይህንን ዜና ለማብሰር በእድሜ ወደ ገፉ አባታቸው ይሄዱና ‘አባቴ ሆይ! ጳጳስ ሆኜ ተሹምያለሁኝ’ ይላቸዋል። አባትዬው ትምህርት ቀመስ ያልሆኑ ሰው የነበሩ ቢሆኑም፣ ነገር ግን በእድሜ ብዛት ሕይወት ያጎናጸፈቻቸው እና ከሕይወት ተመክሮ ያካበቱት ጥበብ ነበራቸው እና ይህንን የልጃቸውን ጳጳስ ሆኖ የመሾማቸውን ዜና ከሰሙ ቡኃላ “ልጄ ሆይ ሁለት ነገሮችን በሕይወትህ እንድትተገብር አደራ እላለሁኝ” በመጀመሪያ “ታዛዥ እንድትሆን ነው” በመቀጠልም “ሕዝቡን ደስተኛ እንድታደርጋቸው አደራ እልሀለሁኝ” ብለው ተናግረው እንደ ነበረም ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል።

ቅዱስነታቸው በስብከታቸው ማጠቃለያ ላይ እንደ ገለጹት “ምዕመናን፡ ካህናት፣ ገዳማዊያን/ያት፣ ጳጳሳት በአጠቃላይ እኛ ክርስትያን የሆንን ሁላችን ሕዙቡ ደስታን ይጎናጸፍ ዘንድ መርዳት ይኖርብናል፣ ዘለዓለም የሆነ የክርስትና ተልእኮዋችን ሕዝቡን ማስደሰት ሊሆን ይገባል” ካሉ ለእለቱ ያዘጋጁትን ስብከት አጠናቀዋል።

 








All the contents on this site are copyrighted ©.