2017-05-15 10:53:00

እግዚአብሔር ለእስራአኤል ሕዝብ የገባው የመዳን ተስፋ ጊዜ ሲደርስ ከሴቶች ሁሉ መካከል ድንግል ማርያምን መረጣት።


ቅዱስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እስካሁን ባደረጓቸው ሐዋርያዊ ጉብኝቶች ውስጥ ልዩ ሥፍራን የተሰጠለት ጉብኝት ለማድረግ ወደ ፖርቱጋል መሄዳቸዉን አስቀድመን ዘግበናል። የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት ዋና ዓላማ በዚያች አገር ፋጢማ በምትባል ሥፍራ እመቤታችን ቅድስት ድልግል ማርያም በእረኝነት ተሰማርተው ለነበሩ ሦስት አዳጊ ሕጻናት የተገለጸችበትን መቶኛ ዓመት ክብረ በዓል ከመላው ምእመናን ጋር ሆነው በጸሎትና በመስዋዕተ ቅዳሴ ለማክበር እና ለማስታወስ ነው። የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ተጨማሪ ዓላማ በጊዜው እመቤታችን ቅድስት ድልግል ማርያም ከተገለጸችላቸው ሦስት እረኞች መካከል የሁለቱን ለቅድስና መብቃታቸውን ለዓለም ምዕመናን ይፋ ለማድረግ ነው። ሦስተኛዋም ለቅድስና የምትበቃበት ጊዜ በሂደት ላይ እንደሆነ ይታወቃል። ቅዱስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ፖርቱጋል ስላደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ዓላማ በአጭሩ ይህን ካልን ወደሚቀጥለው መልዕክት እናመራለን።   

የዚህን አስተምህሮ ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

እግዚአብሔር ለእስራአኤል ሕዝብ የገባው የመዳን ተስፋ ጊዜ ሲደርስ ከሴቶች ሁሉ መካከል ድንግል ማርያምን መረጣት። ከመረጣትም በኋላ መንፈስ ቅዱስ በእርሷ ላይ እንደሚመጣ፣ የእግዚአብሔርም ኀይል በእርሷ ላይ እንደሚሆን በመልአኩ ገብርኤል በኩል ነገራት። መልአኩ ገብርኤል እንዳበሰራት ሁሉ፣ የዓለም መድኃኒት ከእርሷ መወለድ የእግዚአብሔር ፈቃድ ከሆነ፣ እንደ እርሱ ፈቃድ ይሁን በማለት ማርያም በደስታ ተቀበልች። ድንግል ማርያም የእግዚአብሔር ኀይል የሆነው መንፈስ ቅዱስ በእርሷ ላይ ከሆነ በኋላ እንዲሁ ዝም ብላ አልተቀመጠችም። በተለያዩ ምክንያቶች ተስፋ ወደ ቆረጡት፣ ወደ ተከዙት፣ ወደ ተቸገሩት፣ ወዳዘኑት፣ ኑሮ ወደ ከበዳቸው ሰዎች ዘንድ እየሄደች ታጽናናቸው እና ትጎብኛቸው ነበር። በሉቃስ ወንጌል በምዕ. 1 ላይ ተጠቅሶ እንደምናገኘው ለብዙ ዓመታት ሳትወልድ ቆይታ ተስፋ ቆርጣ የኖረች፣ ነገር ግን እግዚአብሔር በስተእርጅናዋ የባረካትን ኤልሳቤጥ ልትጎብኛት ተነስታ ሄደች። ኤልሳቤጥም ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ቤቷ ሄዳ በጎበኘቻት ወቅት የተሰማትን ታላቅ ደስታ እንዲህ በማለት ገለጸች “የጌታዬ እናት ልትጎበኘኝ መምጣትዋ ለእኔ እንዴት ያለ ታላቅ ክብር ነው!” በማለት የተሰማትን ደስታ ገለጸች።

በእርግጥ ይህ ታሪክ በአዲስ ኪዳን መጽሐፍ፣ በሉቃስ ወንጌል የተገለጸ ይሁን እንጂ ቅድስት ድንግል ማርያም ዛሬ በዘመናችንም በተለያየ ጊዜና ቦታ ሆነው የእርሷን እገዛ የሚጠይቁትን ትጎበኛቸዋለች። ተስፋ የቆረጡትን፣ በጦርነት፣ በበሽታ፣ በድህነት እንዲሁም በሌሎች ምክንያቶች የሚሰቃዩትን መጎብኘት አላቋረጠችም። በሕይወታችን የሚያጋጥሙንን የተለያዩ ችግሮች በአሸናፊነት የምንወጣበትን ኀይል በጸሎት እንድንቀበል ትመክረናለች። ምክንያቱም እርሷ አስቀድሞ በእግዚአብሔር የተመረጠችና በመንፈስ ቅዱስ የተሞላች፣ የእግዚአብሔርም ኀይል በሙላት የተሰጣት ናትና።  በጸሎት የምንለምነው እንደ እግዚአብሔር ፍቃድ መሆን እንዳለበት ቅድስት ድንግል ማርያም ትመክረናለች። በመጀመሪያው የሐዋርያው ዮሐንስ መልዕክት ምዕራፍ 5 ቁጥር 14 እና 15 ላይ “ማንኛውንም ነገር እንደ እርሱ ፈቃድ ብንለምን እንደሚሰማን እርግጠኞች ነን፤ ስለዚህ በእግዚአብሔር ፊት ድፍረት አለን። የምንለምነውን ሁሉ እንደሚሰማን ካወቅን ከእርሱ የምንለምነውን ሁሉ አሁኑኑ እንደምንቀበል እናውቃለን” ይላል።

የዛሬ መቶ ዓመት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በፖርቱጋል ለሦስት አዳጊ ሕጻናት በመገለጥ የለገሰቻቸው ምክር እና የሰጠቻቸው አደራም “ባለማቋረጥ ጸልዩ፣ ለሠራችሁት በደልና ኃጢአት ንስሐን በመግባት ምሕረትን ለምኑ” የሚል ነበር። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የመድኃኔ ዓለም እናት፣  የምሕረት እናት፣ የክርስቲያኖች ረዳት፣ የኃጢአተኞች መማጠኛ በመሆኗ፣ አማላጅነቷን ከፈለጉ፣ እርዳታዋን ከለመኑ ሰዎች መካከል አንድ እንኳ የተኮነነ እንዳልተሰማ በማመን፣ እኛም በዚህ እምነት ተጽናንተን፣ በኃጢአታችን ተጨንቀን፣ የቃለ እግዚአብሔር እናት ቅድስት ድንግል ማርያም ጸሎታችንን እንድትቀበል ወደ እርሷ እናቀርባለን።

በአቶ ዩሐንስ መኮንን የተዘጋጀ

 








All the contents on this site are copyrighted ©.