2017-05-13 16:10:00

በዓለማችን ሰላም ይሰፍን ዘንድ የመቁጠሪያ ጸሎት በየቀኑ መድገም ያስፈልጋል


ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በፖርቹጋል ሀገር ፍጢማ በሚባል ልዩ ስፍራ የሚገኘውን የመቁጠሪያይቱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ቤተ መቅደስ ከግንቦት 4/2009 ዓ.ም. ጀምሮ መንፈሳዊ ጉብኝት እያደረጉ እንደ ሚገኙ ይታወቃል። በትላንትናው ምሽት ማለትም በግንቦት 4/2009 ዓ.ም. በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ምዕመናን በተገኙበት በእርሳቸው መሪነት የመቁጠሪያ ጸሎት መደረጉ ይታወሳል። እንደ የአውሮፓዊያኑ የቀን አቆጣጠር በግንቦት 13/1917 ዓ.ም. በወቅቱ እረኛ ለነበሩ 3 ሕጻናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም የተገለጸችበትን አንድ መቶ አመት ለመዘከር አስበው ያደረጉት መንፈሳዊ ጉዞ ሲሆን በተጨማሪም በወቅቱ በግልጸቱ ወቅት ከነበሩ ሕጻናት እረኞች መካከል ዣሽንታ እና ፍራንቸስኮ ለተባሉ ሁለት እረኞች የቅድስና ማዕረግ እንደ ሚሰጣቸውም ታውቁዋል።

በግንቦት 4/2009 ዓ.ም. በመቁጠሪያይቱ የፋጢማ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ቤተ መቅደስ ውስጥ በቅዱስነታቸው መሪነት ከተደረገው የመቁጠሪያ ጸሎት ቡኃላ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ የሆኑት ካርዲናል ጰትሮ ፓሮሊን መስዋዕተ ቅዳሴን አሳርገዋል።

በወቅቱ የተደርገው የመቁጠሪያ ጸሎት “የደስታ ምስጢር” ላይ ያተኮረ እንደ ነበረ የታወቀ ሲሆን በዚህም መሰረት አምስቱ የደስታ ምስጢራት በተለያዩ አምስት ቋንቋዎች መደገማቸው ተገልጹዋል። የመጀመሪያው የደስታ ምስጢር በአረብኛ ቋንቋ፣ ሁለተኛው በእስፓኒሽና በዩክሬይን ቋንቋዎች፣ ሦስተኛው በጣሊያነኛ እና በቻይንኛ ቋንቋዎች፣ አራተኛው የደስታ ምስጢር ደግሞ በእንግሊዜኛ እና በፈረንሳይኛ ቋንቋዎች፣ የመጨረሻው የደስታ ምስጢር ደግሞ በጀርመን እና ፖሊሽ ቋንቋዎች መደገማቸው ተገልጹዋል።

የመቁጠሪያ ጸሎት በሚደገምበት ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም የዛሬ መቶ አመት ገደማ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሦስት እረኛ ሕጻናት በተገለጸችበት ስፍራ ላይ በተተከለው የማሪያም ሐውልት ስር ተቀምጠው በትኩረት እና በዝምታ ሐውልቱን ይመለከቱ እንደ ነበረም ተገልጹዋል።

በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን በታላቅ መንፈሳዊነት በተለያዩ የዓለማችን ቋንቋዎች የመቁጠሪያ ጸሎት ስደግሙ መስማት፣ አንድ አንዴም በታላቅ ዝምታ ሲዋጡ እና በምያስገርም ጥበብ የተዋበ መንፈሳዊ መዝሙሮችን ማዳመጥ፣ መጸለይ የመሳሰሉትን መንፈሳዊ ተግባራትን ሲከናወኑ መመልከት በጣም አስገራሚ እና ልብን የሚነካ ትይንት እንደ ነበረም ከስፍራው የደረሰን ዜና ያስረዳል።

ከመቁጠሪያ ጸሎት በመቀጠል የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ በሆኑት በካርዲናል ጴትሮ ፓሮሊን መሪነት መስዋዕተ ቅዳሴ የተደርጎ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን በወቅቱም ባሰሙት ስብከት እንደ ገለጹት “የዛሬ መቶ አመት በታየው ግልጸት” ማሪያም እረኛ ለነበሩ ሕጻናት ዓለም መንፈሳዊ ለውጥ እንዲያመጣ እና ለሰላም እንዲጸልይ ይህንንም መልእክት ለሁሉም እንዲያደርሱ አዛቸው ነበር ያሉት ካርዲናል ጴትሮ ፓሮሊን “ዛሬ ሰላም ለብዙ ሰዎች  እንደ አንድ የቅንጦት ነገር ተደርጎ ይቆጠራል ነገር ግን በጣም ብዙ ለሚባሉ ሰዎች ግን ሰላም አሁንም ሕልም ሆኖ ቀርቷል” በማለት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራቸስኮ የተናገሩት እውነታ ያለው ሐሳብ ነው ብለዋል። በሚልዮን የሚቆጠር ሕዝብ አሁንም ቢሆን ትጉም የለሽ በሆነ ጦርነት ውስጥ ይገኛል፣ እንዲሁም በአንድ ወቅት ሰለም ነው ተብሎ በታመነባቸው አከባቢዎች እንኳን ሳይቀር በስጋት ውስጥ ይገኛሉ። በየጊዜው በሚታየው ሞት፣ እርዳታን እና እርቅን በመሻት የምጮሁ የንጹሐን ሰዎች ስቃይ፣ ውድ የሆኑ ወገኖቻቸውን በግጭቶች ምክንያት በማጣታቸው ምክንያት ያዘኑትን ሰዎች፣ ጦርነትን በመሸሽ የሚሰደዱትን እና በስደት ላይ እያሉም አሳዛኝ የሞት አደጋ የሚገጥማቸው ሰዎች አሉ ብለዋል። ለመጭው ጊዜ በመጨነቅ እና እርግጠኛ ያለመሆን መንፈስ የተነሳ እየተወዛገቡ የሚገኙ ብዙ ሰዎች መኖራቸውን የጠቀሱት ካርዲናል ጴትሮ ፓሮሊን “ዛሬ የፋጢማዋ ማሪያም ስለዚህ ጉዳይ ምን ትላለች”? በማለት ጥያቄን አንስተው ለእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማሪያም ንጹሕ ልብ ራሳችንን ማስገዛት ይኖርብናል ካሉ ቡኃላ በተጨማሪም ቀን በቀን የመቁጠሪያ ጸሎት መድገም ያስፈልጋል ብለዋል። እኛ ጸሎታችንን እያደረግን ባለንበት ወቅት ጦርነት ቢቀጥል ምን ማድረግ እንችላለን? በማለት ጥያቄን በማንሳት ስብከታቸውን የቀጠሉት ካርዲናል ጴትሮ ፓሮሊን ምንም እንኳን ቅጽበታዊ የሆነ ውጤት ባይታይም እንኳን ሳንታክት ጸሎታችንን ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል። መቼም ቢሆን ጸሎት ፍሬ አልባ ሆኑ አያውቅም፣ ዛሬ ይሁን ነገ ፍሬ ማፍራቱ ግን አይቀሬ ነው ብለዋል።

ጸሎት በእግዚኣብሔር መዳፍ ውስጥ የምናስቀምጠው ሐብት ነው ያሉት ካርዲናል ጴትሮ ፓሮሊን “መንገዱ ከእኛ በጣም ለየት ያለው እግዚኣብሔርም ጊዜውንና መንገዱን ጠብቆ ወደ መልካም ነገር ይቀይረዋል” ካሉ ቡኃላ ስብከታቸውን አጠናቀዋል።

 








All the contents on this site are copyrighted ©.