2017-05-13 11:31:00

መንፈሳዊ ጉዞ የሚደረግባቸው የማሪያም ቤተ መቅደሶች መንፈሳዊ ሕክምና መስጫ ተቋማት ናቸው።


ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቼስኮ ግንቦት 4 እና 5/2009 ዓ.ም. 19ኛውን ሐዋሪያዊ ጉብኝት ለማድረግ በፖርቹጋል ሀገር ፋጢማ በሚባል ልዩ ስፍራ የሚገኘውን እና የዛሬው 100 አመት ገደማ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም በወቅት እረኛ ለነበሩ 3 ሕጻናት የተገለጸችበት ሥፍራ የሚገኘውን የፋጢማ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማሪያም ቤተ መቅደስን ለመሳለም በትላንትናው እለት ማለትም በግንቦት 4/2009 ዓ.ም. እረፋዱ ላይ ወደዚያው አቅንተዋል። ቅዱስነታቸው ቀደም ሲል ይህንን ጉብኝታቸውን አሰመልክተው እንደ ገለጹት ይህ ጉዞዋቸው ከዚህ ቀደም እንደ አደረጉዋቸው ዓይነት ሐዋሪያዊ ጉብኝት ሳይሆን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ያላቸውን ክብር የሚገልጹበት እና በግል ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ጸሎት የሚያደርጉበት መንፈሳዊ ይዘት ያለው ጉብኝት መሆኑን ማስታወቃቸውም ይታወሳል።

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ የሆኑት ካርዲናል ጴትሮ ፓሮሊን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በፖርቹጋል ሀገር ፋጢማ በሚባል ሥፍራ የሚገኘውን የመቁጠሪያይቷ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያምን ቤተ መቅድስ ለመሳለም የሚያደርጉትን መንፈሳዊ ጉዞ አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ እንደ ገለጹት ቅዱስነታቸው በዚህ መንፈሳዊ ጉዞዋቸው ለማሪያም ያላቸውን ፍቅር እና እምነት የሚገልጹበት ጉዞ ነው ማለታቸው ተገልጹዋል። ካርዲናል ጴትሮ ፓሮሊን ጨምረው እንደ ገለጹት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ ማንኛውንም ሐይነት ሐዋሪያዊ ጉዞ ከመጀመራቸው በፊት እና ሐዋሪያዊ ጉብኝት አድርገው ከተመለሱም ቡኃላ በሮም ከተማ የሚገኘውን የቅድስት ድንግል ማሪያም ዐብይ ቤተ መቅደስ (Santa Maria Maggiore) በመሳለም ምስጋናቸውን እና ልመናቸውን የሚያቀርቡበት ምክንያት ለማሪያም ያላቸውን ከፍተኛ የሆነ ፍቅር፣ በጥበቃዋ እና በአማላጅነቷ እንደ ሚመኩ ያሳያል ብለዋል።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ለ3 እረኛ ለነበሩ ሕጻናት እንደ አውሮፓዊያኑ የቀን አቆጣጠር በግንቦት 13/1917 ዓ.ም. ለመጀመሪያ ጊዜ ተገልጻ እንደ ነበረ ያስታወሱት ካርዲናል ጴትሮ ፓሮሊን የመቁጠሪያይቱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም በቀዳሚነት የተገለጸችው ለሐብታም፣ ለባለስልጣናት ወይም ደግሞ ተጽኖ ፈጣሪ ለሆኑ ሰዎች ሳይሆን አለመታደል ሆኖ በማሕበረሰቡ የተናቀ ስፍራ ለነበራቸው እና በእረኝነት ለሚተዳደሩ ሕጻናት ነበር ብለዋል።

ፋጢማ በሚባል ልዩ ስፍራ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ለእነዚህ 3 ሕጻናት እረኞች የተገለጸችበት ወቅት ዓለማችን በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት እየታመሰች በምትገኝበት ወቅት እንደ ነበረ ያስታወሱት ካርዲናል ጴትሮ ፓሮሊን በወቅቱ የነበረው ይጥላቻ፣ የክህደት፣ የጠላትነት ስሜቶች ይታዩ እንደ ነበረም ገልጸዋል። የቀድሞ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት በኔዴክቶስ 16ኛ እንደ የውሮፓዊያን የቀን አቆጣጠር በግንቦት 13/2010 ዓ.ም. ይህንን የመቁጠሪያይቱ ቅድስት ድንግል ማሪያምን ቤተ መቅደስ በጎበኙበት ወቅት እንደ ገለጹት የመቁጠሪያይቱ ማሪያም በግልጸቱ ወቅት ለ3 እረኞች ያስተላፈችው መልእክት  የወቅቱን አስቸጋሪ ሁኔታ ከመገንዘቧ የተነሳ ፍቅር እንዲኖር፣ ይቅርታ መደራረግ እንዲለመድ፣ ራስን ለሌሎች መስዋዕት ማድረግ እና ራሳችንን ለሌሎች ስጦታ አድርገን ማቅረብ እንደ ሚገባ ለእረኝእ ሕጻናቱ አሳስባ እንደ ነበረ መግለጻቸውን ካርዲናል ጴትሮ ፓሮሊን አስታውሰዋል።

እመቤታችን ይህንን የፍቅር፣ የሰላም፣ እና የመስዋዕትነት መልእክት ያስተላለፈችው ታላላቅ ለሚባሉ የማሕበረሰብ ክፍል አባላት ሳይሆን በጊዜው በማሕበረሰቡ በጣም መጨረሻ የተባለ ስፍራ ተሰጥቶዋቸው ለነበረው እረኞች እንደ ነበረም ካርዲናል ጴትሮ ፓሮሊን አስታውሰዋል። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም እራሱዋ ከመልአኩ ገርኤል ብስራት ቡኃላ እግዚኣብሔር በእርሷ ባከናወነው ታላቅ ነገር ስለተደነቀች “እኔን ዝቅተኛውን አገልጋዩን ተመልክቱዋል እና ስሙ ለዘልዓለም ቅዱስ ነው” ብላ የምስጋና መዝሙር ለእግዚኣብሔር አቅርባ እንደ ነበር ያስታወሱት ካርዲናል ጴትሮ ፓሮሊን ይህም እግዚኣብሔር በዘመናት ሁሉ ውስጥ ዝቅተኛ የተባሉ ሰዎችን ከፍ እንደሚያደርጋቸው፣ የተናቁትን እንደ ሚጎበኛቸው ለዓለም መልእክት የሚያስተላልፍ ምስጢር ነው ብለዋል።

ሁላችንም እንደ ምናውቀው ሁሉም መንፈሳዊ ጉዞ የሚደረግባቸው ቤተ መቅደሶች መንፈሳዊ ህክምና የመስጫ ስፍራዎች ናቸው ያሉት ካርዲናል ጳትሮ ፓሮሊን በተለይም ደግም በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ስም የተሰየሙ መንፈሳዊ ጉዞ የሚደረግባቸው ስፍራዎች ለዚህ አባባል በማሳያነት መጠቀስ የሚችሉ መንፈሳዊ ህክምና መስጫ ተቋማት ናቸው፣ ምክንያቱ በእነዚህ በተመቅደሶች ውስጥ አሁንም ቢሆን መልአኩ ገብርኤል ማሪያምን ባበሰራት ወቅት “ለእግዚኣብሔር የሚሳነው ነገር የለም” ብሎዋት የተናገረው ድምጽ አሁንም በማሪያም ቤተ መቅደሶች ውስጥ በድጋሚ ስለምያስተጋባ ነው ብለዋል።

የማሪያም ቤተ መቅደስ የሰው ልጆች ሁሉ በመንፈስዊ ሕይወታቸው የሚያድጉበት ስፍራ ነው ያሉት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ካርዲናል ጴትሮ ፓሮሊን ምክንያቱ ምዕመናንም እንደ ማሪያም “እንዳልከኝ ይሁንልኝ” ብለው እንዲመልሱ ስለሚረዳቸው ነው ብለዋል። በዚህም ስፍራ “ለእግዚኣብሔር የሚሳነው ምንም ነገር የለም” የሰው ልጆች ሁሉ በእግዚኣብሔር በሚተማመኑበት ወቅቶች ሁሉ ምንም የማይሳነው እግዚኣብሔር ያቀዱትን ነገሮች ሁሉ ያጎጽፋቸዋል ብለዋል። በእግዚኣብሔር የተማመነ ሰው በመከራዎች ውስጥ ቢገባም እንኳን ምንም የማይሳነው እግዚኣብሔር በፍቅሩ ይጎበኘዋል ያሉት ካርዲናል ጴትሮ ፓሮሊን ለእግዚኣብሔር ርኅራኄ፣ ምሕረት፣ ፍቅር ምስጋና ይግባውና እግዚኣብሔር ከማንኛውም ዓይነት መከራ ነጻ የማውጣት ብቃት እንዳለው የምንማርበት ስፍራ ነው ብለዋል። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም እግዚኣብሔር ላቀረበላት ጥሪ “እንዳልከኝ ይሁንልኝ” በማለት መልስ ስጥታ እንደ ነበረ ያስታወሱት ካርዲናል ጴትሮ ፓሮሊን ይህ አሁን ቅዱስነታቸው መንፈሳዊ ጉዞ በማድረግ ላይ የምገኙት የመቁጠሪያይቷ የቅድስት ማሪያም ቤተ መቅደስ ይህንን የእግዚኣብሔር እቅድ እንድንረዳ ያግዘናል ካሉ ቡኃላ እግዚኣብሔር የሚሳነው ነገር የለም የሚለው ሀረግ ምላሽ በምንሰጥበት ወቅቶች ሁሉ በሕይወታችን ውስጥ ታላላቅ ነገሮች ሊከሰቱ ይችላሉ ብለዋል።

 








All the contents on this site are copyrighted ©.