2017-05-11 15:55:00

ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮ እና ር.ሊ.ጳ. ቴውድሮስ ዳግማዊ በመጋቢት 20/2009 ዓ.ም. የተፈራረሙት የጋራ የመግባቢያ ሰነድ።


የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ እን የግብፅ የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በሆኑት ቴውድሮስ ዳግማዊ መካከል የተፈረመው የጋራ የመግባቢያ ሰንድ

በካቶሊክ ቤተ ክርስትያን ርዕስ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራቸስኮ እና በግብፅ የኮፕቲክ ቤተ ክርስትያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በሆኑት ቴውድሮስ ዳግማዊ መካከል ለመጀመሪያ ጊዜ አንዱ ቤተ ክርስቲያን በሌላኛው ቤተ ክርስቲያን የሚሰጠውን ምስጢረ ጥምቀት እውቅና ሰጥተው ይህንንም እውቅና በተፈራረሙት የጋራ ሰነድ ማረጋገጣቸው ተገለጸ። ይህም ማለት ለምሳሌ በኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን ውስጥ የተጠመቀ አንድ ሰው በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ካቶሊክ ለመሆን ቢፈልግ ወይም አንድ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተጠመቀ ሰው የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ምዕመን ለመሆን ቢፈልግ አንዱ ቤተ ክርስቲያን በሌላኛው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚፈጸመውን ምስጢረ ጥምቀት እቅና በመስጠቱ የተነሳ ይህ ምዕመን በድጋሜ የመጠመቅ ግዴታ የለበትም ማለት ነው።

ይህ የጋራ የስምምነት ሰንድ ይፋ የሆነው በሚያዝያ 20/2009 ዓ.ም. ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ እና የግብፅ የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የሆኑት ቴውድሮስ ዳግማዊ በግብፅ በተገናኙበት ወቅት ነው። ይህ በሁለት ታላላቅ አብያተ ክርስትያናት መሪዎች መካከል የተደረገው ግንኙነት ከዛሬ 44 ዓመታት በፊት እንደ አውሮፓዊያኑ የቀን አቆጣጠር በግንቦት ወር 1973 ዓ.ም. በወቅቱ የካቶሊክ ቤተ ክርስትያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነበሩት በጳውሎስ ስድስተኛ እና የኮፕቲክ ቤተ ክርስትያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት ሽኑዳ 3ኛ መካከል ከተደረገው ግንኙነት በመቀጠል የተደረገ ግንኙነት በመሆኑ ይህንን  ታሪካዊ ያስብለዋል።

ይህ በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ እና የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በሆኑት ቴውድሮስ ዳግማዊ መካከል የተደረገው ግንኙነት ለምዕተ አመታት በሁለቱ አብይት ቤተ ክርስትያን መካከል የነበረውን ልዩነት ለማስወገድ የተደረገ ከፍተኛ ጥረት ውጤታማ መሆኑን የሚያሳይ ታሪካዊ ግንኙነት እንደ ሆነም ጨምሮ የተገለጸ ሲሆን ይህም በሁለቱ አብያተ ክርስትያናት የጋራ የስነ መለኮት ኮሚቴዎችን በማዋቀር ከፍተኛ የሆነ ውይይት በማድረግ የተገኘ ውጤት መሆኑንም ለመረዳት ተችሉዋል።

የሁለቱ ታላላቅ አባያተ ክርስትያናት መሪዎች ይህንን የጋራ ስምምነት በተፈራረሙበት ወቅት እንደ ገለጹት “ሁሉቱ አብያተ ክርስትያናት የሚጋሩትን መሠረታዊ የሆኑ የእምነት አስተምህሮችን በጸሎት ለማዳበር እንደ ሚፈልጉም” ጨምረው ገልጸዋል። በተለይም ጌታ ለሐዋሪያቱ ያስተማረውን “አባታችን ሆይ የሚለውን ጸሎት” ሁለቱንም አብያተ ክርስትያናት በሚያስማማ መልኩ የጋራ የሆነ ትርጉም እንዲኖረው እና በተጨማሪም የፋሲካ በዓል በተመሳሳይ ቀን ይከበር ዘንድ ሁኔታዎች እዲመቻቹ እና ጥናት እንዲደረግም ጥሪ አቅርበዋል። የካቶሊክ እና የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስትያናት ጋብቻ እና ቤተሰብ ቅዱስ መሆናቸውን እና ለተፈጥሮ እንክብካቤ ማድረግ የሚሉትን የሰው ልጅ እሴቶችን በመለከተ የጋራ የሆነ አቋም ያላቸው መሆኑን ጠቁመው እነዚህን የጋራ እሴቶች በጋራ መመስከር እንደ ሚጠበቅባቸውም በስምምነቱ ወቅት ተገልጹዋል። ይህ የጋራ የስምምነት ሰንድ አክሎ እንደ ሚያሳየው በግብፅ እና በመካከለኛው ምስራቅ በሚገኙ ክርስትያኖች ላይ በእምነታቸው ምክንያት ብቻ እየተፈጸመ የሚገኘውን ስደት እና ግድያ በመቃወም የተጀመረውን ጸሎት አጠናክረው መቀተል እንደ ሚኖርባቸውም ያትታል።

ይህ የጋራ የመግባቢያ ሰንድ በካቶሊክ እና በኮፕቲክ ኦርቶዶክሰ አብያተ ክርስትያናት መካከል የውጥረት ምንጭ የሆኑትን ከአንዱ ቤተ ክርስቲያን ወደ ሌላኛው እመንት የሚቀይሩ ክርስቲያኖች በድጋሚ ይጠመቁ የሚለውን ከፍተኛ ቦታ ተሰጥቶት የነበረው አወዛጋቢ የነበረ ጉዳይ መቅረፍ የቻለ ሰንድ መሆኑም ተገልጹዋል።

ክቡራን እና ክቡራት ታዳሚዎቻችን  የካቶሊክ ቤተ ክርስትያን ርዕስ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ እና የግብፅ የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የሆኑት ቴውድሮስ ዳግማዊ በሚያዝያ 20/2009 ዓ.ም. የሁለቱን አብያተ ክርስቲያናት ግንኙነት አስመልክተው የተፈራረሙትን ሰንድ ሙሉ ይዘት  እንደ ሚከተለው እናቀርብላችዋለን።

  1. < > ማለትም የሮም ጳጳስ እና የመላው የካቶሊክ ቤተ ክርስትያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ እና የመንበረ ቅዱስ ማርቆስ ፓትሪያርክ እና የእስክንድሪያ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቴውድሮስ ዳግማዊ በድጋሚ እንድንገናኝ፣ በወንድማማችነት ስሜት እንድንተቃቀፍ እና በድጋሚ የጋራ ጸሎት ለማድረግ በመገናኘታችን፣ ይህንን አስደሳች አጋጣሚ የፈጠረልንን እግዚኣብሔርን በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት እናመሰግነዋለን። በቅዱስ ጴጥሮስ እና በቅዱስ ማርቆስ መንበር መካከል ስላለው የወንድማማችነት እና የጓደኝነት ግንኙነት ሁሉን ቻይ የሆነውን እግዚሐብሔርን እናከብረዋለን። እዚህ ግብፅ በጋራ መገናኘታችን ከአመት ወደ አመት እያደገ የሚገኘውን ግንኙነት ጥንካሬን፣ መቀራረብን፣ እምነትን እና ጌታ የሆነውን የክርስቶስ ፍቅር ለማሳየት እንድል የከፈተ ግንኙነት ነው። ይህችን ተወዳጅ የሆነችውን “በውስጣችን ሕያው የሆነችውን” የግብፅ ሀገር የሰጠንን እግዚኣብሔርን እያመሰገንን፣  ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሸኖዳ 3ኛ “በእግዚኣብሔር የተባረከ ሕዝብ” (ኢሳያስ 19፡25) እንዳሉት ሁሉ ይቺህ ሀገር በጥንታዊው የፈርኦን ስልጣኔ፣ የግሪክ እና የሮም ውርስ የሆነች፣ የኮፕቲክ ባሕል ያላት እና እስልምና የሚገኝባትም ሀገር ናት። ግብፅ  ለቅዱስ ቤተሰብ መጠግያ የሆነች፣ የሰማዕታት እና የቅዱሳን ሀገር ናት።< > የሆነ የጓደኝነት እና የወንድማማችነት ግንኙነት የመነጨው በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን በነበረን ህብረት ምክንያት እና ከኒቂያ ጉባሄ አንስቶ በተለያዩ ጊዜያት ባደረግናቸው የተዋህዶ ጉባሄዎች እና ጠንካራ በነበረው “የእምነት ጠባቂ” ቅዱስ አትናቴዎስ በመሳሰሉ ታላቅ የቤተ ክርስትያን አባቶች ላይ መሰረቱን ያደረገ ነው። ሕብረታችን በጸሎታችን እና ተመሳሳይ በሆነ የስርዓተ-አምልኮ፣ እንዲሁም በጋራ ታላቅ አክብሮት በምንሰጣቸው ሰማዕታት፣ የመናንያን ሁሉ አባት በመባል በሚታወቀው የቅዱስ አንጦኒዮስን መልካም አብነት በመከተል በመናኒያን ሕይወት እንድገት እና መስፋፋት ውስጥም ይገለጻል።

    ይፋዊ በሆነ መልኩ (1054) ሁለቱ አብያተ ክርስትያናት ከመለያየታቸው በፊት ለቅዱስ ቁርባን የነበረን ተመሳሳይ ልምድ ዛሬ አንድነታችንን ለማጠናከር ለምናደርገው ጥረት ከፍተኛ የሆነ አስተዋጾ አለው። የካቶሊክ እና በኮፕቲክ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስትያናት ይፋዊ በሆነ መልኩ ተለያይተን የቆየን ብንሆንም  በቀድሞ ክፍለ ዘመን የነበሩን ብዙዎቹ ግንኙነቶች  በልዩነታችንም ጊዜያት ሁሉ ቀጥለው እስከ ዛሬ ድረስ በመድረስ እነሆ ዛሬ እንደ አዲስ ማንሰራራት ጀምረዋል። በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የጋራ ጥረታችንን አፋፍመን እንድንቀጥል ከልዩነቶቻችን ባሻገር ሊታይ የሚችል ህብረት ላይ መድረስ እንድንችል መንፈስ ቅዱስ ይገፋፋናል።

    3. ከእኛ በፊት የነበሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛ እና ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሽኑዳ ሦስተኛ የዛሬ 44 ዓመት ገደማ ታሪካዊ ግንኙነት ባደረጉበት ወቅት ከብዙ መቶ አመታት በፊት በሁለቱ አብያተ ክርስትያናት መካከል በተነሳው ልዩነት ምክንያት ተከሰቶ የነበረውን ክፍተት የተነሳ የተቋረጠው የፍቅር ግንኙነት የሰላም እና የወንድማማችነት መተቃቀፍን በማሳየት በድጋሚ በማደስ መገለጻቸው ይታወሳል። እንደ የአውሮፓዊያኑ የቀን አቆጣጠር በግንቦት 30/2073 ዓ.ም. ተፈረሞ የነበረው የጋራ ሰንድ እንደ የማዕዘን ድንጋይ በመሆን ለውይይቶች መንገድ የከፈተ እና በሁለቱ አብያተ ክርስትያናት መካከል በነገረ መለኮት ዙሪያ ውይይት እንዲደረግ መነሻ ነጥብ የሆነ፣ ብዙ የሚባል ፍሬ ያፈራ እና በካቶሊክ እና በአጠቅላይም በመላው የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ ውይይቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ መንገድ የከፈተ ነበር። በዚያም ሰንድ ላይ አብያተ ክርስትያኖቻችን የሐዋሪያዊ ባሕላችንን መስመር በጠበቀ መልኩ “እግዚኣብሔር አንድም ሦስትም ነው የሚል እምነት” እና “የአንደኛውን የእግዚኣብሔር ልጅ መለኮታዊነት፣ መለኮታዊነቱን በተመለከተ ከእግዚኣብሔር ጋር ሊሰትካከል የሚችል ምንም ነቀፋ የሌለበት፣ ከሰዎች አንጻር ስንመለከት ፍጹም የሆነ ሰው መሆኑን” በጋራ እውቅና ስጥተውት ነበር። “ለእኛ የተሰጠን መለኮታዊ ሕይወት በሰባቱ ምስጢራት የሚደገፍ” መሆኑንም እውቅና ሰጥተው የነበረ ሲሆን በተጫማሪም “የእውነተኛው ብርሃን፣ የእግዚኣብሔር እናት የሆነችው እመቤታችንን ድንግል ማሪያም መለኮታዊ ክብር እንደ ሚሰጡም” ግልጸው ነበር።

    4. እንደ የአውሮፓዊያኑ የቀን አቆጣጠር በግንቦት 10/2013 ዓ.ም. በሮም አደረግነው በነበረው የወንድማማችነት ስብሰባ ላይ በየአመቱ ግንቦት 10 ቀን በሁለቱ አብያተ ክርስትያንት መካከል ያለውን የወንድማማችነት ግንኙነት ለማጠናከር ይውል ዘንድ መስማማታችን ይታወሳል። ይህ በአዲስ መንፈስ የጀመርነው መቀራረባችን እኛን አንድ የሚያደርጉን ነገሮችን የተቀበልነው በጥምቀታችን ወቅት በአንዱ ጌታ አማካይነት መሆኑን እንድንረዳ አድርጎናል። በጥምቀት አማካይነት ነው የክርስቶስ አንድ አካል የሆነችው የቤተ ክርስቲያን አንድ አካል መሆን የቻልነው። ይህ የጋራ የሆነ ውርሳችን ነው በፍቅር እና በእርቅ እያደግን ወደ ህብረት የምናደርገውን የጋራ መንፈሳዊ ጎዞ መሰረት የጣለልን።

    5. ምንም እንኳን የተወሰኑ ጉዳዮችን እውን ማድረግ የቻልን ቢሆንም ቅሉ ገና ብዙ መንገድ መጓዝ እንዳለብንም እናውቃለን። በተለይም ደግም እንደ አውሮፓዊያኑ የቀን አቆጣጠር በ2000 ዓ.ም. ርዕሰ ሊቃን ጳጳሳት ሽኑዳ 3ኛ እና ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዩሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ በግብፅ መገናኘታቸው እና መወያየታቸው ትልቅ አጋጣሚን የከፈተ ነበር። እነርሱ የጀመሩትን መንገድ ለመከተል መልካም እረኛ በሆነው በክርስቶስ ፍቅር ለመታገዝ አብረን ወደ ፊት ለመጓዝ እና በአንድነት እንደምናድግ ጥልቅ የሆነ እምነት አለን። የህብረት እና የፍቅር ምንጭ የሆነው እግዚኣብሔር ጥንካሬውን ይሰጠን።

    6. ይህ ፍቅራችን በጋራ በምናደርገው ጥልቅ የሆነ ጸሎት ይገለጻል። ክርስትያኖች በአንድነት በሚጸልዩበት ወቅት ከሚለያያቸው ነገሮች ባሻገር አንድ የሚያደርጋቸው ነገሮች እንደ ሚበዙ ይረዳሉ። ኅብረት ለመፍጠር ያለን ጉጉት የመነጨው “አባት ሆይ! እኔ የምለምነው ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ ነው!” (ዩሐንስ 17፡21) ብሎ ኢየሱስ ከጸለየው ጸሎት ነው። ጌታ ያስተማረንን ጸሎት አንድ የጋራ ትርጉም እንዲኖረው በማድረግ እና የፋሲካን በዓል በአንድ ቀን በማክበር በሐዋሪያት እምነት ላይ ሥር መሰረቱን ያደረገውን እምነታችንን በጸሎት እናጠናክር።

    7. በአንድነት የአንዱን ጌታ ማዕድ ወደ ምንቋደስበት የተቀደሰ እለት እየተጓዝን እንደ መሆናችን መጠን፣ በብዙ ጉዳዮች ላይ መተባበር እና አሁንም ቢሆን የምንጋራቸውን ዋና ዋና እሴቶችን ተጨባጭ በሆነ መንገድ መግለጽ ይኖርብናል። የሰው ልጆች ሕይወት ቅዱስ መሆኑን እና የሰው ልጆች መብት መከበር እንዳለበት፣ ጋብቻ ወይም ትዳር ቅዱስ መሆኑን፣ ከእግዚኣብሔር በአደራ የተሰጠንን ተፈጥሮን ማክበር የሚሉትን የሰው ልጆች መሰረታዊ የሆኑ እሴቶችን በጋራ መመስከር እንችላለን። በአሁኑ ጊዜ እየተጋፈጥናቸው የምንገኘው ዓለማዊነት እና በግዴልሽነት ስሜት እየተመራ የሚገኘውን ዓለማዊ ትስስር (golbalization) እነዚህ ጉዳዮች እያስከተሉ የሚገኙትን ተግዳሮቶች በወንጌል እሴቶች ላይ እና ቱባ በሆነ በየአንድአንዳችን ቤተ ክርስትያን ባሕል ላይ ተመስርተን የጋራ የሆነ ምላሽ እንድንሰጥ ተጠርተናል። በሐዋሪያዊ ተግባራት ውስጥ ፍሬያማ የሆነ ልውጥ ለማምጣት፣ በተለይም ደግሞ በትምህርተ ክርስቶስ፣ በገዳም እና በመንፈሳዊ መህበራት መካከል የጋራ የሆነ መንፈሳዊነትን ለማዳበር ይቻል ዘንድ የኦሪየንታል (የምስራቃዊ) እና የላቲን (ምዕራብ) አብያተ ክርስትያንትን ጥናቶች በጥልቀት ማሳተፍ ያስፈልጋል።

    8. የጋራ የክርስትና ምስክርነታችን ለግብፅ ማህበረሰብ እና ተቋማት በፀጋ የተሞላ የእርቅ እና የተስፋ፣ የፍትህን ፍሬ እንዲያፈራ የተዘራ ዘር እና የሰላም ምልክት ነው። ሁሉም የሰው ልጆች በእግዚኣብሔር አምሳል እንደ ተፈጠሩ ስለምናምን፣ ክርስትያኖች እና የሙስሊሙ ማኅበረሰብ አብረው በሰላም የመኖር ሕልውናቸው እንዲረጋገጥ፣ እግዚኣብሔር የሚመኘው ህብረት እና ስምምነት በመላው የሰው ልጆች መካከል እንዲፈጠር በማድረግ እና የእያንዳንዱ ሰው መብት እኩል መሆኑን ይረጋገጥ ዘንድ ጥረታችንን ማድረግ እንቀጥላለን። የግብፅ ደህንነት እና መጭው እድል በጋራ ያሳስበናል።  ሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች በሀገሪቷ ሕይወት ውስጥ የመሳተፍ መብት እና ግዴታ፣ ሙሉ እና አኩል የሆነ የዜግነት መብት እና ይህንን ሀገር በጋራ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የመሳተፍ መብት አላቸው። በሰዎች መብት ላይ መሰረቱን ያደረገ የሕሊና ነጻነትን ያካተተ የሐይማኖት ነጻነት፣ የመብቶች ሁሉ የማዕዘን ድንጋይ ነው። የተቀደሰ እና የማይገሰስ መብት ነው።

    9. በግብፅ እና በመላው ዓለም በተለይም ደግሞ በመካከለኛው ምስርቅ ለሚገኙ ክርስትያኖች የምናደርገውን ጸሎት አጠናክረን እንቀጥል። አሳዛኝ በሆነ ተመኩሮ ውስጥ የሚገኙ እና በስደት ደማቸው የፈሰሰ ምዕመናኖቻችን፣ ክርስትያን በመሆናቸው ብቻ ለስደት የተዳረጉ ምዕመናኖቻችን፣ የእነዚህ ሰማዕታት ውህደት ህብረት እንድንፈጥር፣ እግረ መንገዳችንም ሰላም እና እርቅ እንድንፈጥር ሁላችንንም ያስገነዝበናል። ቅዱስ ሐዋሪያው ጳውሎስ “አንድ የአካል ክፍል ሲሰቃይ ሌላውም የአካል ክፍል አብሮት ይሰቃያል” (1ቆሮንጦስ 12፡26) በማለት ጽፍልናልና።

    10. በፍቅሩ የተነሳ የሞተልን እና ከሙታን የተነሳው የኢየሱስ ምስጢር ወደ ሙሉ ውህደት በምናደርገው ጉዞ መሐል ላይ የገኛል። አሁንም ቢሆን ሰማዕታቶቻችን መንገድ አመላካቾቻችን ናቸው። በቀድሞ የቤተ ክርስትያን ዘመናት ውስጥ የሰማዕታት ደም አዳዲስ ክርስትያኖችን የሚፈጥር ዘር ነበር። አሁንም ቢሆን በእኛ ዘመን የእነዚህ የብዙሀኑ ሰማዕታት ደም የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ሁሉ ውህደት እንዲፈጥሩ የሚረዳ ዘር፣ በዓለም ውስጥ ህብረት እና ሰላም የሚፈጥር ምልክት እና መሣሪያ እንዲሆን እንመኛለን።

    11. ቤተ ክርስትያንን ለሚያነጻት፣ በዘመናት ሁሉ ለሚጠብቃት እና ወደ ሙሉ ሕብረት ለሚመራት እየሱስ፣ የቤተ ክርስትያን ህብረት ይፈጠር ዘንድ እራሳችንን ለመንፈስ ቅዱስ ተግባራት ታዛዥ በማድረግ፡-“ዛሬ እኛ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ እና ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቴወድሮስ ዳግማዊ የጌታችን የእየሱስ ክርስቶስን፣ እንዲሁም የወንድም እና እህት ምዕመናኖቻችንን ልብ ለማስደሰት፣ በአንድ ሐሳብ እና ልብ በመሆን በአንዳችን ቤተ ክርስትያን ውስጥ የተጠመቀ ሰው በማንኛው ምክንያት የሌላኛውን ቤተ ክርስቲያን አባል ለመሆን ቢፈልግ በድጋሚ ምስጢረ ጥምቅ መቀበል እንደ ሌለበት በእውነተኛ ልብ በጋር ወስነናል (አንድ በኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን ውስጥ የተጠመቀ አንድ ምዕመን በማንኛውም ምክንያት ካቶሊክ ለመሆን ቢፈልግ ወይም በተቃራኒው. . . እንደ ገና መጠመቅ አያስፈልገውም፣ ምክንያቱም አንዱ ቤተ ክርስትያን ለሌላኛው ቤተ ክርስትያን ጥምቀት እውቅና ሰቱዋል ማለት ነው)። ይህንንም የምናውጀው ለመጽሐፍ ቅዱስ ታዛዥ በመሆን እና በተጨማሪም በኒቂያ (325 ዓ.ም.)፣ በቁስጥንጥንያ (381 ዓ.ም.) እና በኤፌሶን (449 ዓ.ም.) በተደረጉት ጉባሄዎች ላይ በአለን እምነት የተነሳ ነው።

    በመንፈስ ቅዱስ አማካይነትና እርሱ በመረጠበት ጊዜ በክርስቶስ ምስጢራዊ አካል አማክይነት ወደ ሙሉ ኅብረት እድንደርስ እግዚኣብሔር አባታችን ይመራን ዘንድ እንጠይቃለን።

    12. ስለዚህም በሰላም ተሳስራችሁ ከመንፈስን ቅዱስ የሚገኘውን አንድነትን ለመጠበቅ ትጉ። በተጠራችሁ ጊዜ ለአንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ ሁሉ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ እንዲሁም አንድ ጌታ፣ አንድ እምነትና አንድ ጥምቀት አለ። ደግሞም ከሁሉም በላይ የሆነ፣ በሁሉም የሚሠራ፣ በሁሉ የሚኖር የሁሉም አባት የሆነ አንድ አምላክ አለ” (ኤፌሶን 4፡3-6) ብሎ ሐዋሪያው ጳውሎስ በጻፈልን ቃል እንመራ።

ግብፅ ካይሮ መጋቢት 20/2009 ዓ.ም.

 








All the contents on this site are copyrighted ©.