2017-04-15 14:41:00

በሚያዝያ 6/2009 ዓ.ም. የተደረገው የመስቀል መንገድ


እንደ ሚታወቀው 2009 ዓ.ም. የሕማማት ሣምንት ማገባደጃ ላይ እንገኛለን። በትላንትናው እለት ማለትም በሚያዚያ 6/2009 ዓ.ም. አርብ እለት ክርስቶስ የተሰቀለበት ቀን በተለያዩ መንፈሳዊ ክንውኖች ተክብሮ እና ተዘክሮ አልፉዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ ይህንን ክርስቶስ  የተሰቀለበትን ቀን ለመታደም በሮም ከተማ ውስጥ በሚገኘው ጥናታዊው ኮሌሴውም አከባቢ በሚገኘው ሥፍራ በተገኙበት ወቅት የሮም ከተማ ከንቲባ በሆኑት ቬርጂኒያ ራጂ አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን በስፍራው ተገኝተው የመስቀል መንገድ ጸሎት ታድመዋል።

የመስቀል መንገድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ለማዳን ብሎ የተቀበለውን መከራ የሚያስታውስ ጸሎት ሲሆን በተለይም ኢየሱስ ሞት በተፈረደበት በዓርብ ስቅለት እለት መስቀሉን ተሸክሞ እስከ ሚሰቀልበት ሥፍራ ድረስ ያደረገውን 14 የስቃይ ምዕራፎች የሚያሳይ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ስፊ ቦታ የሚሰጠው ጸሎት ነው።

በትላንትናው እለት ምሽት ይህንን ጸሎት ለመታደም ከ20,000 በላይ ምዕመናን በስፍራው የተገኙ ሲሆን ቅዱስነታቸውም በስፍራው ተገኝተው የሻማ መለኮስ ሥነ-ሥረዓት ካደረጉ ቡኃላ ጸሎቱን በይፋ አስጀምሩዋል። በእየ አመቱ በስቅለተ አርብ ቀን በሚደረገው የመስቀል መንገድ ላይ የተለያዩ ተጋባዥ ምዕመናን የአስተንትኖ ጸሎት እንዲያዘጋጁ ይጋበዛሉ። በዚህም መሰረት በትላንትናው እለት በተደረገው የመስቀል መንገድ ላይ የአስተንትኖ ጸሎት ያዘጋጁት ፈረንሳዊቷ የመጻሐፍ ቅዱስ ምሁር የሆኑት በተጨማሪም የራዚንገር ፋውንደሽን ሽልማት (Ratzinger Prize) አሸናፊ የሆኑት ክብርት አን-ማሪ ፔሌቲዬር የእዚህ ዓመት የመስቀል መንገድ የአስተንትኖ ጸሎት ያዘጋጁት እርሳቸው መሆናቸው ታውቁዋል።

በወቅቱ የተካሄደውን የመስቀል መንገድ 14 ማረፊያዎችን የተለያዩ 14 ሰዎች መስቀል እንዲሸከሙ የተመረጡ ሲሆን የሮም ሰበካ ዬኔታ የሆኑት ካርዲናል ቫሊንን ጨምሮ ከሮም ከተማ የተመረጡ ቤተሰቦች፣ አካለ ስንኩላን፣ ከፖላንድ እና ከጣሊያን የተመረጡ ሁለት ተማሪዎች፣ ከሪሚን ከተማ የመጡ ሁለት ምዕመናን፣ ሁለት የሕንድ ተወላጅ የሆኑ ደናግላን፣ ከቡርኪና ፋሶ እና ከኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፖብሊክ የመጡ ሁለት ምዕመናን፣ ከግብጽ፣ ከፖርቱጋል እና ከኮሎምቢያ የመጡ ምዕመናን በተደረገው ሁደት ላይ መስቀሉን በየተራ እንዲሸከሙ ተደርገዋል።

በእለቱ የትደረገውን የመስቀል መንገድ እንደሚከተለው ተርጉመነዋል

ጊዜውም ደርሱዋል። ኢየሱስ በስቃይ በተጎዱ ሰውነቱ እና ልቡን ይዞ አቡዋራማ በሆነው በገሊላ እና በይሁዳ መንገድ ላይ የሚያደርገው ጎዞ፣ የእግዚኣብሔርን መንግሥት በፍጥነት ለማወጅ የሚያደርገውን ጎዞ፣ ዛሬ በጎልጎታ ፍጻሜው ላይ ደርሱዋል እዚህም ላይ ያበቃል።  ዛሬ መስቀሉ መንገዱን ዘግቶታል። ኢየሱስ ከዚህ በላይ ወደ ፊት መጉዋዝ አልቻለም።

ከዚህ በላይ ወደ ፊት መጓዝ አልቻለም!

እዚህ ላይ የእግዚአብሔር ፍቅር በምልአት ከልክ በላይ መገለጹን ያሳያል፣ ከልክም በላይ።

ዛሬ ሁሉም የሰው ልጅ በልጁ ይድን ዘንድ የሚሻው የአብ ፍቅር ጽንፉን አልፎ ቃላችንን በምናጥፍበት ጊዜያት ሁሉ፣ ራሳችንን በመኳተን ውስጥ በምናገኝበት ወቅቶች ሁሉ፣ ፍርሃታችን ሁሉ በእግዚአብሔርን አሳብ እና ዕቅዶች እንዲዋጡ ያደርጋል።

በጎልጎታ ላይ ከሁሉም ገጽታዎችን በሚቃረን መልኩ የምናገኘው ሕይወት፣ ፀጋ እና ሰለም አደጋ ላይ መወደቃቸውን ነው። እዚህ ላይ ሊተኮርበት የሚገባው እና ሁላችንም ጠንቅቀን የምናውቀው ነገር የሰይጣን መንግሥት መስፈኑን ሳይሆን ነገር ግን የእግዚኣብሔር ፍቅር አሸናፊነትን ነው።

በመስቀሉም ሥር ቢሆን ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጠው ዓለማችን በውድቀቶች እና በመከራዎች፣ በመማጸን እና በተቃውሞ ውስጥ የሚገኘው ሰዎች፣ በድኽነት እና በጦርነት ምክንያት ወደ እግዚኣብሔር የሚደረገው ለቅሶ፣ በስደተኞች ከታጨቁ ጀልባዎች ወዘተርፈ ይገኛሉ።

እንባዎች በጣም ብዙ ናቸው። ልጁ የመከራ ጽዋን ለእኛ ብሎ ጠጣ።

እንባዎች የቱንም ዓይነት ቢሆኑ፣ መከራዎቻችንም የተኛውንም ያህል ቢበዙ እነዚህ ሁሉ በጊዜ ባሕር ውስጥ ሰጥመው አልጠፉም። በአንጻሩ በፍቅር ምስጢር ውስጥ ለመገለጽና ክፉ ነገሮችን ሁሉ ለማጥፋት በእርሱ ይወሰዳሉ።

ጎልጎታ እግዚኣብሔር ለሰው ልጆች ያለውን የማይናወጥ ፍቅር ይነግረናል። ውልደትም የተፈጠረው በዛው ሥፍራ ነው። ይህም ሁሉ የወንጌል ደስታ ነው የምንልበትን ብርታት ያስፈልገናል። ለእዚህ እውነታ እውቅናን ካልሰጠን በስተቀር በስቃይ እና በሞት ወጥመድ ውስጥ ገብተን እንቀራለን። የክርስቶስ ሕማማት በሕይወታችን ውስጥ ፍሬ እንዳያፈራ እናደርገዋለን።

እንጸልይ

ጌታ ሆይ! እይታቸው እየደከመ ነው። እንዴት ነው ይህንን መንገድ ከእናንተ ጋር ሆነን መራመድ የምንችለው? ስምህ “መሐሪ” ነው። ነገር ግን ይህ ስም የሚያሳብድ ነው።

በልባችን ውስጥ ያለውን አሮጌው አቁማዳ ይሰንጠቅ! በልጅህ መስቀል ሥር በምንሆንባቸው ጊዜያት ሁሉ እይታችንን በወንጌል መልካም ዜና ይብራ። በዚህም መልኩ እኛ የክርስቶስን ፍቅር “ጥልቀቱን፣ ስፋቱን እና ቁመቱን” በተጽናና ልብ እና በብርሃን በተጥለቀለቀ መልኩ ለማክበር እንችላለን።

አንደኛ ማረፊያ

ኢየሱስ ሞት ተፈረደበት

የሉቃስ ወንጌል 22፡66 “በነጋም ጊዜ የሕዝቡ ሽማግሌዎችና አለቆች ጻፍቶችም ተሰብስበው ወደ ሸንጎ ውሰዱት”።

የማርቆስ ወንጌል 14፡64-65

“ስድቡን ሰምታችኋል፤ ታዲያ፣ ምን ይመስላችኋል?”፤እነርሱም ሞት ይገባዋል በማለት በአንድ ቃል ፈረዱበት። በዚህ ጊዜ አንዳንዶቹ ይተፉበት ጀመር፤ ዐይኑንም ሸፍነው በጡጫ እየመቱት፣ “እስቲ ትንቢት ተናገር!” ይሉት ነበር። ሎሌዎችም በጥፊ እየመቱ ወሰዱት።

ሁለተኛ ማረፊያ

ጴጥሮስ ኢየሱስን ካደው

የሉቃስ ወንጌል 22፡59-62 “አንድ ሰዓት ያህል ቈይቶም፣ ሌላ ሰው በርግጠኝነት፣ “ይህ ሰው ገሊላዊ ስለ ሆነ ያለ ጥርጥር ከእርሱ ጋር ነበረ” አለ። ጴጥሮስ ግን፣ “አንተ ሰው፤ የምትለውን እኔ አላውቅም” አለ፤ ይህንም ተናግሮ ገና ሳይጨርስ ዶሮ ጮኸ። ጌታም መለስ ብሎ ጴጥሮስን ተመለከተው፤ ጴጥሮስም፣ “ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ብሎ ጌታ የተናገረው ቃል ትዝ አለው። 62ጴጥሮስም ወደ ውጭ ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ።

 

ሦስተኛ ማረፊያ

ኢየሱስ እና ጲላጦስ

የማርቆስ ወንጌል 15፡1,3,15 “ጠዋት በማለዳ የካህናት አለቆች ከሽማግሌዎች፣ ከጸሓፍትና ከመላው የሸንጎ አባላት ጋር ወዲያው ከተማከሩ በኋላ ኢየሱስን አስረው ወሰዱት፤ ለጲላጦስም አሳልፈው ሰጡት። የካህናት አለቆችም በብዙ ነገር ከሰሱት። ጲላጦስም፣ “ለምን መልስ አትሰጥም? እነሆ በብዙ ነገር ከሰውሃል” ሲል እንደ ገና ጠየቀው።ጲላጦስም ሕዝቡን ደስ ለማሰኘት ሲል በርባንን ፈታላቸው፤ ኢየሱስን ግን ገርፎ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠው

ተማቴዎስ ወንጌል 27፡24 “ጲላጦስ ሁኔታው ሽብር ከማስነሣት በስተቀር ምንም ፋይዳ የሌለው መሆኑን ተመልክቶ፣ “እኔ ከዚህ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ፤ ከእንግዲህ ኀላፊነቱ የራሳችሁ ነው” በማለት ውሃ አስመጥቶ በሕዝቡ ፊት እጆቹን ታጠበ።”

ትንቢተ ኢሳያስ 53፡6 “እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤ እያንዳንዳችንም በየመንገዳችን ነጐድን፤ እግዚአብሔርም፣ የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ ጫነው”።

አራተኛ ማረፊያ

ኢየሱስ የክብር ንጉሥ

የማርቆስ ወንጌል 15፡16-18 “ወታደሮቹ ፕራይቶሪዮን ወደተባለ ወደ ገዡ ግቢ ወሰዱት፤ ሰራዊቱንም ሁሉ በአንድነት ሰበሰቡ። ቀይ ልብስም አለበሱት፤ የእሾኽ አክሊል ጐንጒነው በራሱ ላይ ደፉበት። ከዚያም፣ “የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን!” እያሉ እጅ ነሡት”።

ትንቢተ ኢሳያስ 53፡2-4 “በፊቱ እንደ ቡቃያ፣ ከደረቅም መሬት እንደ ወጣ ሥር በቀለ፤የሚስብ ውበት ወይም ግርማ የለውም፤ እንድንወደውም የሚያደርግ መልክ አልነበረውም። በሰዎች የተናቀና የተጠላ፣ የሕማም ሰውና ሥቃይ ያልተለየው ነበር። ሰዎች ፊታቸውን እንደሚያዞሩበት ዐይነት፣ የተናቀ ነበር፤ እኛም አላከበርነውም። በርግጥ እርሱ ደዌያችንን ወሰደ፤ ሕመማችንንም ተሸከመ፤ እኛ ግን በእግዚአብሔር እንደ ተመታ፣ እንደ ተቀሠፈ፣ እንደ ተሠቃየም ቈጠርነው።

አምስተኛ ምስጢር

ኢየሱስ መስቀሉን ተሸከመ

ሰቆቃው 1፡12 ““እናንት መንገድ ዐላፊዎች ሁሉ፤ ይህ ለእናንተ ምንም አይደለምን? ተመልከቱ፤ እዩም፤በጽኑ ቍጣው ቀን፣ እግዚአብሔር ያመጣብኝን፣ በእኔ ላይ የደረሰውን፣ የእኔን መከራ የመሰለ መከራ አለን?”።

መጽሐፈ መዝሙር 146፡ 5,7-9 “ረዳቱ የያዕቆብ አምላክ የሆነ፣ ተስፋውንም በአምላኩ በእግዚአብሔር ላይ የጣለ ሰው ምስጉን ነው፤ ለተበደሉት የሚፈርድ፣ ለተራቡት ምግብን የሚሰጥ እርሱ ነው፤ እግዚአብሔር እስረኞችን ከእስራት ያወጣል፤ እግዚአብሔር የዕዉራንን ዐይን ያበራል፤ እግዚአብሔር የተዋረዱትን ከፍ ያደርጋል፤ እግዚአብሔር ጻድቃንን ይወዳል፤ እግዚአብሔር ስደተኞችን ይጠብቃል፤ድኻ ዐደጎችንና መበለቶችን ይደግፋል፤ የክፉዎችን መንገድ ግን ያጠፋል።”

 

ስድስተኛው ማረፊያ

ኢየሱስ ከቀሬናዊው ስምዖን ጋር ተገናኘ

የሉቃስ ወንጌል 23፡26 “ኢየሱስንም ይዘው ሲወስዱት፣ ስምዖን የተባለውን የቀሬና ሰው ከገጠር ሲመጣ አግኝተው መስቀሉን አሸክመው ኢየሱስን ተከትሎ እንዲሄድ አስገደዱት።”

የማቲዎስ ወንጌል 25፡37-39 “ጻድቃንም መልሰው እንዲህ ይሉታል፤ ‘ጌታ ሆይ፤ ተርበህ አይተን መቼ አበላንህ? ወይም ተጠምተህ አይተን መቼ አጠጣንህ? እንግዳ ሆነህ አይተን መቼ ተቀበልንህ? ወይስ ታርዘህ አይተን መቼ አለበስንህ? እንዲሁም ታመህ ወይም ታስረህ አይተን መቼ ጠየቅንህ?’”

ሰባተኛ ማረፊያ

ኢየሱስ ከኢየሩስላሌም ሴቶች ጋር ተገናኘ

የሉቃስ ወንጌል 23፡27-28,31 “ብዙ ሕዝብና ደረታቸውን እየደቁ የሚያለቅሱለት ሴቶችም ከኋላው ይከተሉት ነበር። 28ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ ዘወር ብሎ እንዲህ አላቸው፤ “እናንት የኢየሩሳሌም ሴቶች፤ ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ እንጂ ለእኔ አታልቅሱ፤እንግዲህ በእርጥብ ዕንጨት እንዲህ ካደረጉ፣ በደረቁ ምን ያደርጉ ይሆን?”።

ስምንተኛ ማረፊያ

ኢየሱስ ልብሶቹን ተገፈፈ

የዩሐንስ ወንጌል 19፡23 “ወታደሮቹ ኢየሱስን ከሰቀሉ በኋላ፣ እጀ ጠባቡ ሲቀር፣ ልብሱን ወስደው ለእያንዳንዱ አንድ አንድ እንዲዳረስ ለአራት ተከፋፈሉት፤ እጀ ጠባቡም ከላይ እስከ ታች አንድ ወጥ ሆኖ ያለ ስፌት የተሠራ ነበር።

መጽሐፈ ኢዮብ 1፡21 “በዚህ ሁሉ፣ ኢዮብ አልበደለም፤ በእግዚአብሔርም ላይ ክፉ አልተናገረም።”

ዘጠነኛ ምስጢር

ኢየሱስ ተሰቀለ

የሉቃስ ወንጌል 23፡33-34 “ከእርሱ ጋር እንዲገደሉ ሌሎች ሁለት ወንጀለኞችን ወሰዷቸው። ቀራንዮየተባለ ቦታ በደረሱ ጊዜ ሰቀሉት፤ ወንጀለኞቹንም አንዱን በቀኙ፣ ሌላውን በግራው ሰቀሏቸው። ኢየሱስም፣ “አባት ሆይ፤ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” አለ። እነርሱም ልብሱን በዕጣ ተከፋፈሉት።”

ትንቢተ ኢሳያስ 53: 5 “ነገር ግን እርሱ ስለ መተላለፋችን ተወጋ፤ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ በእርሱ ላይ የወደቀው ቅጣት ለእኛ ሰላም አመጣልን፤ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን።”

 

 

 

አስረኛ ማረፊያ

ኢየሱስ በመስቀል ላይ እያለ አሾፉበት

የሉቃስ ወንጌል 23፡35-39 “ሕዝቡም ቆመው ይመለከቱ ነበር። ገዦችም፣ “ሌሎችን አዳነ፤ በእግዚአብሔር የተመረጠው ክርስቶስ እርሱ ከሆነ፣ እስቲ ራሱን ያድን” እያሉ አፌዙበት። ወታደሮችም ቀርበው ያፌዙበት ነበር፤ የሖመጠጠ የወይን ጠጅ እየሰጡትም፣ “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ከሆንህ፣ ራስህን አድን” ይሉት ነበር። ከራሱም በላይ፣ “ይህ የአይሁድ ንጉሥ ነው” የሚል ጽሑፍ ነበር። ከተሰቀሉት ወንጀለኞችም አንዱ የስድብ ናዳ እያወረደበት፣ “አንተ ክርስቶስ አይደለህምን? እስቲ፣ ራስህንም እኛንም፣ አድን” ይለው ነበር።”

የሉቃስ 4፡3,9-11 “ዲያብሎስም፣ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፣ እስቲ ይህ ድንጋይ እንጀራ እንዲሆን እዘዘው” አለው።ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም ወስዶ በቤተ መቅደስ ጒልላት ላይ አቆመውና እንዲህ አለው፤ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፣ እስቲ ራስህን ከዚህ ወደ ታች ወርውር፤ ምክንያቱም እንዲህ ተብሎ ተጽፎአል፤“ ‘ይጠብቁህ ዘንድ፣ መላእክቱን ስለ አንተ ያዛቸዋል፤ እግርህም ከድንጋይ ጋር እንዳይጋጭ፣ በእጆቻቸው ወደ ላይ አንሥተው ይይዙሃል።’ ”

አስራ አንደኛ ማረፊያ

ኢየሱስ ከእናቱ ጋር ተገናኘ

የዩሐንስ ወንጌል 19፡25-27 “በኢየሱስ መስቀል አጠገብ እናቱና የእናቱ እኅት፣ እንዲሁም የቀልዮጳ ሚስት ማርያምና መግደላዊት ማርያም ቆመው ነበር። በዚያም ኢየሱስ እናቱንና የሚወደውም ደቀ መዝሙር አጠገቧ ቆሞ ሲያያቸው እናቱን፣ “አንቺ ሴት ሆይ፤ ልጅሽ ይኸው” አላት፤ ደቀ መዝሙሩንም፣ “እናትህ ይህችው” አለው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይህ ደቀ መዝሙር ወደ ቤቱ ወሰዳት።

አስራ ሁለተኛ ማረፊያ

ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሞተ

የዩሐንስ ወንጌል 19:28-30, 33-35 “ከዚያም ኢየሱስ ሁሉ ነገር እንደ ተፈጸመ ዐውቆ፣ የመጽሐፍ ቃል እንዲፈጸም፣ “ተጠማሁ” አለ። በዚያም የሆመጠጠ ወይን የሞላበት ዕቃ ተቀምጦ ነበር፤ እነርሱም ሰፍነግ በወይን ጠጅ ነክረው፣ በሂሶጵ ዘንግ ወደ አፉ አቀረቡለት፤ ኢየሱስም ሆምጤውን ከተቀበለ በኋላ፣ “ተፈጸመ” አለ፤ ራሱን አዘንብሎ፣ መንፈሱን አሳልፎ ሰጠ። ወደ ኢየሱስ በመጡ ጊዜ ግን ሞቶ ስላገኙት ጭኖቹን አልሰበሩም፤ ነገር ግን ከወታደሮቹ አንዱ የኢየሱስን ጐን በጦር ወጋው፤ ወዲያውም ደምና ውሃ ፈሰሰ። ይህን ያየው ሰው ምስክርነቱን ሰጥቶአል፤ ምስክርነቱም እውነት ነው፤ እውነትን እንደሚናገርም ያውቃል፤ እናንተም እንድታምኑ ይመሰክራል።”

አስራ ሦስተኛ ማረፊያ

ኢየሱስን ከመስቀል ላይ አወረዱት

የሉቃስ ወንጌል 23፡53 “በተፈቀደለትም ጊዜ፣ ሥጋውን አውርዶ በበፍታ ገነዘው፤ ከድንጋይ ተፈልፍሎ በተሠራና ገና ማንም ባልተቀበረበት መቃብር ውስጥ አስቀመጠው።”

አስራ አራተኛ ማረፊያ

ኢየሱስን ከመስቀል አውርደው በመቃብር ውስጥ አኖሩት

የሉቃስ ወንጌል 23፡55-56 “ከገሊላ ጀምሮ ከኢየሱስ ጋር የመጡት ሴቶችም ተከትለው መቃብሩን አዩ፤ ሥጋውንም እንዴት እንዳስቀመጡት ተመለከቱ። ከዚያም ተመልሰው ሽቱና ቅባት አዘጋጁ፤ ሕጉ በሚያዘው መሠረት በሰንበት ቀን ዐረፉ።”

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 








All the contents on this site are copyrighted ©.