2017-04-01 12:04:00

ቤተሰብ በዓለም ውስጥ መልካም ዜና ሆኖ መኖሩን ቀጥሉዋል።


“በየደረጃው ለሕይወት ራሱን ክፍት ያደረገ፣ በአንድ ወንድ እና በአንድ ሴት ኅብረት ላይ የተመሰረተ ቤተሰብ፣ በዓለም ውስጥ መልካም ዜና ሆኖ መኖሩን ቀጥሉዋል” ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ እንደ አውሮፓዊያን የቀን አቆጣጠር ከነሐሴ 21-26 2018 ዓ.ም በደብሊን ከተማ ለሚካሄደው ዓለማቀፍ የቤተሰብ ጉባሄ ዝግጅት ይሆን ዘንድ በትላንትናው እለት ማለትም በመጋቢት 21/2009 ዓ.ም. ከአስተላለፉት መልእክት የተወሰደ ነው።

የዚህን ዜና ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

አንደ አውሮፓዊያኑ የቀን አቆጣጠር ከነሐሴ 21-26 2018 ዓ.ም በደብሊን ከተማ የሚካሄደው ዓለማቀፍ የቤተሰብ ጉባሄ “የቤተሰብ ወንጌል ለዓለም ደስታ” በሚል መርዕ ሐሳብ እንደ ሚከበረ ከወዲሁ የተገለጸ ሲሆን በመጋቢት 20/2009 ዓ.ም. በቅድስት መንበር የሕትመት ቢሮ ከተሰጠው መግለጫ ለመረዳት እንደቻልነው የቤተሰብ ሕይወት ይበልጡኑ ይጠናከር ዘንድ ቅዱስነታቸው እንደ አውሮፓዊያኑ የቀን አቆጣጠር በመጋቢት 19/2016 ዓ.ም. የጻፉት አሞሪስ ላይቲሲያ በአማሪኛው በግርድፉ ሲተረጎም “የፍቅር ሐሴት” በሚል አርእስት ያሳተሙት ቃለ ምዕዳን በቤተሰብ ውስጥ ሊኖር ስለሚገባው ፍቅር የሚተነትን ቃለ ምዕዳን በመሆኑ የቤተሰብ አባላት በዚህ ቃል ምዕዳን ውስጥ የተጠቀሱትን ቁምነገሮች በመጠቀም ሕይወታቸውን ማጠናከር እንደ ሚገባቸውም ተጠቅሱዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ እንደ አውሮፓዊያን የቀን አቆጣጠር ከነሐሴ 21-26 2018 ዓ.ም በደብሊን ከተማ ለሚካሄደው ዓለማቀፍ የቤተሰብ ጉባሄ ያስተላለፉት መልእክት በሁለት ጥያቄዎች ላይ መሰረቱን ያደረገ ነበር። በቀዳሚነት የተቀመጠው “ቅዱስ ወንጌል ለዓለም የደስታ ምንጭ ሆኖ እየቀጠለ ነው ወይ?” የሚለው ጣይቄ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን በቀጣይነትም ቅዱስነታቸው ያቀረቡት ጥያቄ  “ቤተሰብ ዛሬም ለዓለም መልካም ዜና እየሆነ ቀጥሉዋል ወይ”? የሚለውን ጥያቄ ደግሞ ቅዱስነታቸው በቀጣይነት አንስተዋል።

“እኔ እንደ ማስበው ቤተሰብ ዛሬም ቢሆን ለዓለም መልካም ዜና መሆኑ እየቀጠለ ያለ ጉዳይ ይመስለኛል” ያሉት ቅዱስነታቸው ይህም አዎንታዊ አስተሳሰብ የመነጨው ቤተሰብ መሰረቱን ያደረገው በእግዚኣብሔር ላይ በመሆኑ የተነሳ ነው ብለዋል።

የእግዚኣብሔር ፍቅርና የእርሱ “አዎንታ” የፍጥረታት ሁሉ ልብ ውስጥ ይገኛል ያሉት ቅዱስነታቸው ይህም “አዎንታ” ራሳቸውን በየደረጃው በሕያወት ለሚገጥማቸው አገልግሎት ክፍት ባደረጉ ወንድ እና ሴት ኅብረት ውስጥም ይነጸባረቃል ብለዋል።

የእግዚኣብሔር “አዎንታዊ” ምላሽ በተለይም ደግሞ በተለያዩ ነገሮች ልባቸው ለቆሰለ፣ ለተበደሉ፣ ፍቅርን ላላጣጣሙ ሰዎችን ሁሉ ለመርዳት እና ለመደገፍ ዝግጁ ነው ያሉት ቅዱስነታቸው ቤተሰብ “አዎንታዊ የእግዚኣብሔር ፍቅር” የሚገለጥበት ስፍራ ነው ብለዋል።

“ቤተሰብ በዚህ የእግዚኣብሔር ፍቅር ላይ መሰረቱን ሲያደርግ ብቻ ነው በዓለም ውስጥ የእግዚኣብሔ ፍቅር ዳግም እንዲፈጠር ማድረግ እና የእግዚኣብሔርን ፍቅር መግለጽ የሚችለው በዚሁ መንገድ ብቻ ነው፡ ያለ እግዚኣብሔር ፍቅር እንደ እግዚኣብሔር ልጅ፣ እንደ ቤተሰብ እና እንደ እህት ወንድም ሆኑ መኖር በፍጹም አይቻልም” ብለዋል።

ቅዱስነታቸው ይህንን አጋጣሚ ተጠቅመው በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ የቤተሰብ አባላት ራሳቸውንና ሕይወታቸውን እንዲፈትሹ በማሰብ የምትኖሩት ሕይወት “በእግዚኣብሔር ፍቅር ላይ መሰረቱን ያደረገ ነው ወይ? በፍቅር እና ለፍቅር ብቻ ነው የምትኖሩት? የሚለውን ጥያቄ በመጠየቅ የቤተሰብ አባላት ራሳቸውን ሊመረምሩ ይገባል ብለዋል።

“የፍቅር መገለጫ የሆኑ ተግባራትን በምናከናውናቸው እለታዊና ቀላል በሆኑ ተግባራት መግለጽ እንችላለን” ያሉት ቅዱስነታቸው ይህም በቀላሉ “እባክህን፣ አመሰግናለሁ እና ይቅርታ” የሚሉትን ቀለል ያሉ ቃላትን በመጠቀም መግለጽ እንደ ሚቻልም ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው ገልጸዋል።

“በእየለቱ በቤተሰብ ውስጥ የሚያጋጥሙትን ተግዳሮቶች፣ ድክመቶችና መታከቶችን ሁሉ ከግምት በማስገባት እኛ የቤተሰብ አባላት እና የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች የሆንን ሁላችን የቤተሰብ ሕይወት ይጠናከር ዘንድ ማስተማር እና መደገፍ ይጠበቅብናል፣ ራሳቸውን መርዳት የማይችሉትን መርዳት፣ በሕይወት ጉዞዋቸው ከእነርሱ ጋር አብሮ መጓዝ፣ በጎ ፈቃድ ያላቸውን ሰዎች ሁሉ በዚህ ተግባር በማሳተፍ የቤተሰብ ሕይወት እንዲጸና እና ሰላማዊ ይሆን ዘንድ መትጋት ያስፈልጋል” ካሉ ቡኃላ መልእክታቸውን አጠናቀዋል።

 








All the contents on this site are copyrighted ©.