2017-03-27 13:52:00

ቅዱስነታቸው በጠቅላላ አስተምህሮዋቸው "የክርስቶስን ብርሃን ተመልከቱ" ማለታቸው ተገለጸ።


በሣምንት ሁልት ጊዜ ዘወትር ረዕቡ እና እሁድ እለት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ መሪነት የጠቅላላ አስተምህሮ  እንደ ሚሰጥ ይታወቃል። ይህንንም የጠቅላላ አስተምህሮ ለመከታተል በርከት ያሉ ምዕመናን እንዲሁም የሮም ከተማን እና አከባቢዋን የሚጎበኙ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች አጋጣሚውን ተጠቅመው በዚህ ቅዱስነታቸው በሚያደርጉት የጠቅላላ አስተምህሮ ተሳታፊ ይሆናሉ።

የዚህን ዜና ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

ርዕሰ ሊቃን ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በትላንትናው እለት ማለትም በመጋቢት 17/2009 ዓ.ም. ያሰተላለፉት አስተምህሮ በእለቱ በላቲን ስርዓተ አምልኮ አቆጣጠር በ4ኛው የዓብይ ፆም ሳምንት ሰንበት ላይ በተነበበው ከዩሐንስ ወንጌል 9: 1-41 ላይ በተወሰደው ኢየሱስ ዐይነ ስውር ሆኖ የተወለደውን ሰው ማዳኑን በሚገልጽ የእግዚኣብሔር ቃል ዙሪያ ያጠነጠነ እንደ ነበረ ተገልጹዋል።

“ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን ተአምር በመፈጸሙ የዓለም ብርሃን መሆኑን አስመስክሩዋል” በማለት አስተምህሮዋቸውን የጀመሩት ቅዱስነታቸው “እያንዳንዳችን የተፈጠርነው እግዚኣብሔርን እንድናውቀው ነው፣ ነገር ግን በኃጢያታችን ምክንያት ከልጅነታችን ጀምሮ ዓይናችን ታውሩዋል፣ አዲስ የእምነት ብርሃን ያስፈልገናል፣ ይህንንም ብርሃን የሚሰጠን ኢየሱስ ነው” ብለዋል።

“ይህ በወንጌል የተጠቀሰው እና የዓይን ብርሃኑን መልሶ የተጎናጸፈው ሰው ለክርስቶስ የማዳን ሚስጢር  ራሱን ክፍት አድርጎ ነበር” ያሉት ቅዱስነታቸው እኛ “ኢየሱስ የዓለም ብርሃን” መሆኑን ለመረዳት በሚያዳግተን ወቅት ሁሉ “ይህ ዓይነ ስውር የነበረው ሰው ይህንን እውነታ እንድንረዳ ያግዘናል” ካሉ ቡኃላ “በተለይም ደግሞ በዙሪያችን የሚንጨላጨሉ ጥቃቅን ብርሃናትን እንዳንመኝ ይረዳናል” ብለዋል።

እያንዳንዳችን በጥምቀት አማካይነት የክርስቶስ ብርሃን “በርቶልናል” ያሉት ቅዱስነታቸው በዚህም ምክንያት እንደ ብርሃን ልጆች ሆነን ራሳችንን እንድንመራ ተጠርተናል ብለዋል።

“እውነተኛ የሆነ ብርሃን መያዝ እና በብርሃን መጉዋዝ ምን ማለት ነው”? በማለት ጥያቄን በማንሳት አስተምህሮዋቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ይህም ማለት አሉ ቅዱስነታቸው ልጥያቄያቸው መልስ ሲሰጡ “ይህም ማለት በቅድሚያ ሐሰት የሆኑ ብርሃናትን ማስወገድ ማለት ነው” ብለዋል። “ሌላኛው ሐሰተኛ ብርሃን የሚባለው ደግሞ ራስ ወዳድነት ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው “ ሰዎችን እና ነገሮችን ለእኛ ጥቅም፣ ደስታ እና ክብር ብቻ እንዲመች አድርገን በምንገመግምበት ወቅቶች ሁሉ ከእነዚህ ነገሮች ጋር ሐቀኛ የሆነ ግንኙነትና ሁኔታ መፍጠር አንችልም” ብለዋል።

እንደ አውሮፓዊያኑ የቀን አቆጣጠር ከ1936- 1939 ዓ.ም. በእስፔን በክርስቲያኖች ላይ ተነስቶ በነበረው ጥላቻ ምክንያት የተገደሉ 114  ካህናት እና ምዕመናን በአለፈው ቅዳሜ ማለትም በመጋቢት 16/2009 ዓ.ም. በእስፔን የብፅዕና ማዕረግ እንደ ተሰጣቸው በማስታወስ አስተምህሮዋቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “እነዚህ ካህናት፣ ገዳማዊያን እና ምዕመናን በጀግንነት የክርስቶስን፣ የወንጌል ሰላማዊነት እና የወንድማማችነት እርቅ አስፈላጊነትን መስክረው ነው ያለፉት” ካሉ ቡኃላ የእነርሱ ምስክርነት እና አማላጅነት ቤተ ክርስቲያን ፍቅር እንዲገነባ የምታደርገውን እንቅስቃሴና ተሳትፎ  ይደግፍሃል” ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በአስተምህሮዋቸው ማገባደጃ ላይ ባለፈው ቅዳሜ እለት ማለትም በመጋቢት 16/2009 ዓ.ም. የአንድ ቀን ሐዋሪያዊ ጉብኝት ለማድረግ ወደ ሚላን ከተማ መሄዳቸውን አስታውሰው የዚህ ጉብኝታቸው አስተባባሪዎችን ሁሉ እና በዝግጅቱ ላይ ተሳታፊ የሆኑትን ሰዎች ሁሉ አመስግነው በእዚያ የነበሩ አማኞች እና አማኝ ያለሆኑ ሰዎች ሁሉ ላደርጉላቸው መስተንግዶ እና አቀባበል ከፍ ያለ ምስጋናን ካቀረቡ ቡኃላ ለእለቱ ያዘጋጁትን አስተምህሮ አጠናቀዋል።

 








All the contents on this site are copyrighted ©.